Pages

Sunday, April 1, 2012

መራመድና ባሉበት መሽከርከር፤ ሁለት የኑሮ ፈሊጦች

From አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

ወ/ሮ ሙሉ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ማሕበራትና ሴክቶራል አሶሲየሽን ፕሬዚዳንት - ልምዳቸውን እያጋሩ ነው፡፡ “ጣጣ” በማያውቀው አማርኛቸው የተራመዱበትን የሕይወት መንገድ (ልበለው ስኬት) ያወራሉ፣ ያወራሉ፤ እኔም አዳምጣለሁ፣ አዳምጣለሁ፡፡ በመሃል ‘ከራስ ጋር መወዳደር’ ስለሚባል ነገር አነሱና ተናገሩ፡፡ “መወዳደር ያለብን ከሰዎች ጋር ሳይሆን ከራሳችን ጋር ነው፣ እከሌ እንዲህ ስለሆነ እኔም መሆን አለብኝ ማለት የለብንም” አሉ፡፡ ተቀየምኳቸውና እርሳቸው ጨርሰው ታዳሚው ጥያቄ እንዲጠይቅ ዕድል ሲሰጠው እጄን ዘለግ አድርጌ አወጣሁ፡፡

“አነጋገርሽን ወድጄልሻለሁ፤” ብዬ ጀመርኩ፡፡ በነገራችን ላይ ወይዘሮዋ፣ የአራት ልጆች እናት ቢሆኑም፣ የ33 ዓመት የሥራ ልምድ ቢኖራቸውም ዕድሜያቸውን 24 እያሉ ነው የሚናገሩት (energetic መሆናቸውን ለመግለፅ ይመስለኛል፤) እንዲያውም የ24 ዓመት ሰው እንዴት 33 ዓመት የሥራ ልምድ ይኖረዋል ሲባሉ÷ ቀሪው ‘over time’ የሰራሁት ነው ብለው መመለሳቸውን ነግረውናል፡፡ ለዚያ ነው እኔም አዳራሹ ውስጥ አንቺ ማለቴ፡፡ ስቀጥል፤

“ነገር ግን ከራስ ጋር ስለመወዳደር የተናገርሽውን ልስማማበት አልችልም፤ ምክንያቱም አንድ ሰው እየተራመደ እስከሆነ ድረስ ራሱን መቅደም ያቅተዋል ብዬ አልገምትም፡፡ ችግሩ ሰውዬው የሚራመደው በራሱ ፍጥነት መሆኑ ላይ ነው፡፡ በጥንችል ዘመን እኔ በኤሊ ፍጥነት ብጓዝ ምን ዋጋ አለው? ስለዚህ ከሰዎች ጋር መወዳደርን እንደ ጠላትነትነት ሳይሆን እንደኑሮ ፈሊጥ ልናየው ይገባል፤ ማደግ የምንችለው በትክክለኛው የውድድር pace መጓዝ ስንችል ብቻ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ ይህንን ብታብራሪልኝ፡፡” ብዬ ደሰኮርኩ፡፡

ወ/ሮ ሙሉ ብዙም አልተቃወሙኝም፡፡ ከራስ ጋር መወዳደር ሲባል ተወዳዳሪ ዓለም እንዳለ መዘንጋት እንዳልሆነ አብራርተው፤ ስንወዳደር ግን በራሳችን መክሊት ልንወዳደራቸው ከሚገቡን ሰዎች ጋር መሆኑን አበክረው መከሩን፡፡ አለበለዚያ ዛሬ እኔ ተነስቼ ከኃይሌ ገ/ሥላሴ ጋር ካልሮጥኩ እና ካላሸነፍኩ ብል ዋጋ የለውም ማለታቸው እንደሆነ ነገሩን፡፡

ተስማማን፡፡ ይሄንን ጽሁፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ሐሳብ ግን የፈለቀው ይህንን ምልልስ በረዘዝኩበት (በገረብኩበት) በልምድ ማጋራቱ ዕለት ማግስት ነው፡፡ የራሴን ሐሳብ ራሴ ውድቅ አደረግኩት፡፡ ከሌሎች ጋር መወዳደር የሚለውን ወዲያ እናቆየውና እውን ብዙዎቻችን ከገዛ ራሳችን ጋር እየተወዳደርን ነውን?

ከራስ ጋር መወዳደር፤ ዘበት!
ጠዋት እነሳለሁ፣ እወጣለሁ፣ ሥራ እገባለሁ፣ ለምሳ እወጣለሁ፣ እመለሳለሁ፣ ከሥራ እወጣለሁ፣ ሰዎች አገኛለሁ፣ ወደቤት እመለሳለሁ፣ እተኛለሁ፡፡ ከዚያ የዚህ አንቀጽ መጀመሪያ ላይ ወዳለው መመለስ ነው፡፡ ብዙዎቻችን መንግሥት ወይም መስሪያ ቤታችን በየዓመቱ የሚጨምረውን ደሞዝ፣ ወይም አዲስ ሥራ ስንቀጠር የምናገኘውን ዕድገት ብቻ እየቆጠርን ካምናው ይሻላል፣ ከራሴ አንፃር ብዙ ተጉዣለሁ እንላለን፡፡ ግን ውሸት ነው፡፡ ከራሳችን ጋርም ሆነ ከሌሎች ጋር አልተወዳደርንም፡፡

ሁላችንም ፍራቻ አለብን፤ አዲስ ነገር የመፍራት፣ አዲስ ነገር የለመድኩትን ዋስትና ቢያሳጣኝስ እያሉ የመስጋት ‹ፎቢያ› አለብን፡፡ ስለዚህ ከለመድነው ትራክ አንወጣም፡፡ በዚያው ላይ ደጋግመን፣ ደጋግመን እንመላለስበታለን፡፡ ሕይወታችን ልክ በስታዲዬም ትራክ ላይ እንደሚደረግ ውድድር ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹን አራትመቶ ሜትሮች ብቻ አዲስ ትራክ እየረገጥን እንሮጣለን፤ ከዚያ በኋላ ግን እየደግምነው፣ እየደግመነው እንሽከረከራለን፡፡ ስንጀምረው የነበረን ሞራል እና ጥንካሬ ደግሞ እየከዳን፣ እየከዳን ይመጣል፡፡ መጨረሻ ላይ አብረውን አንድ ትራክ ላይ ሲሮጡ ከነበሩ ሰዎች አንፃር ተመዝነን አሸናፊ እንባላለን፡፡

ባለፉበት መንገድ ደጋግሞ መመላለስ የብዙሐኑ ዕጣ ፈንታ ነው፡፡ ብዙሐኑ ሁሌም ቢሆን ቲፎዞ ነው፡፡ በሕይወት ዓለም ጥቂት ተጫዋቾች አሉ፡፡ ከተጫዋቾቹ ውስጥ የሚያሸንፉት ደግሞ የጥቂት ጥቂቶች ናቸው፡፡ ብዙሐኑ የሚደግፈው ቡድን ቢሸነፍም ባይሸነፍም በለመደው መንገድ እየቶፈዘ የሚያልፍ እዚህ ግባ የማይባል ነገር ግን ብዙ የሚል ቅጥያ ያለው ተመልካች ነው፡፡

የሚራመዱ ሰዎች በሕይወታቸው አዲስ ነገር መሞከር የማይፈሩ፤ እየሞከሩ፣ እየወደቁና እየተነሱ፣ እየቀየሩና እየተቀየሩ ባለፉበት መንገድ እንደታቦት ሳይመለሱ የሚጓዙ ናቸው፡፡

ዕድሜ በየዓመቱ በአንድ ይጨምራል፤ ደሞዝም እንደዚያው ሊጨምር ይችላል፡፡ በሕይወታችን የምናበረክተው ከገንዘብ በላይ ትርጉም ወይም መልክ ያለው ነገርስ በየዓመቱ ስንት ይጨምራል? በአምና ትራክ ላይ እየተሽከረከርን፣ አንድም እሴት ለማንጨምር ለኛ - ከአምናው ላልተሸልን ሰዎች - ወዮልን!!!

No comments:

Post a Comment