Pages

Saturday, June 20, 2020

What's Next for TPLF?


TPLF's decision to hold an election in time came a little too late. No one expects that the National Election Board of Ethiopia (NEBE), whose accountability is to the House of People's Representative (HPR), will help them run the election.  House of People's Federation (HoF) has already decided it is the HoPR that will blow the last whistle to decide when the next general and regional election should run (well, after the health institutions announced that COVID is no more a threat.) 

Can Tigray Run its Own Election in Time?
If TPLF is really committed to doing the election, the first thing to do is to establish an independent electoral commission. This needs a fair time. A law establishes the commission must be drafted and approved by the regional council, the institution needs to have space, people, and structure in due time. Then, it should register political parties that function in the region. Then, introduce the election schedule - which includes voters’ registration, competitors' campaign, voting day, etc.

Thursday, June 18, 2020

የብሔር ጥያቄ እና የብሔር ሽቀላ


በኢትዮጵያ ውስጥ መልስ የሚሹ በርካታ የማንነት ጥያቄዎች አሉ፤ ከጥያቄዎቹ መካከል ግን ነጥሮ የወጣው ወይም እንዲወጣ የተደረገው “የብሔር ጥያቄ” ብቻ ነው። ይህ መሆኑ በነባሮቹ ታሪካዊና ማኅበራዊ ጥያቄዎች ላይ ተጨማሪ ጥያቄዎች፣ ቁርሾዎች እና ቅራኔዎች እንዲደራረቡና ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሮች እየተባባሱ እንዲሔዱ አድርጓል። የብሔር ጥያቄ አቀንቃኞች ብሔርተኝነትን እንደ ብቸኛ መፍትሔ ያቀርባሉ። ይህ ዓይነቱ አቀራረብ ችግርን በችግር የመፍታት ዘዴ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉት ዘለግ ያለ ዕድሜ ያላቸው የማንነት ጥያቄዎች መልሱ ብሔርተኝነት ሳይሆን ፍትሕ ነው። በዚህ መከራከሪያ ላይ በቅጡ ለመግባባት የኢትዮጵያ የማንነት ጥያቄዎችን መሠረት፣ የብሔር ጥያቄ በማንነት ጥያቄዎች ውስጥ ያለውን ቦታ፣ እንዲሁም ችግሮቹን ከዚህ በፊት ለመፍታት የተሔደባቸው ዘዴዎች ለብልጣ ብልጦች የፈጠሩትን የማይገባቸው እርከን ላይ የመንጠላጠል ዕድል አፍታትቶ መነጋገር ያስፈልጋል።

የማንነት ጥያቄ ነባራዊነት

ረዥሙ የዐፄ ስርዓት በአንድ በኩል በአንድ ድንበር የታጠረ የፖለቲካ ማኅበረሰብ አበርክቶ ሲያልፍ፣ በሌላ በኩል ብዙ መልስ የሚያሻቸው ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን ለተከታታይ ትውልዶች ጥሎ አልፏል። የደርግ ወታደራዊ ጭቆና እና የትሕነግ (TPLF) የዘውግ ምደባ ዐፄያዊው ስርዓት ጥሎት በሔደው ሸክም ላይ ሲደመሩበት ጥያቄውን ከወትሮው የበለጠ ውስብስብ አድርገውታል።

የኢትዮጵያ ዐፄዎች አገር ንብረቱን በሙሉ የግላቸው አድርገው ነበር የሚቆጥሩት። ይህ ግዙፍ የመደብ ልዩነት ፈጥሯል። የመደብ ልዩነቱ በገዢዎች እና ተገዢዎች ዘንድ ሰፊ የሀብት እና የማኅበራዊ ማዕረግ ክፍተት ጥሎ አልፏል። የመደብ ልዩነቱን ለማስፋት መሬት ትልቁን ሚና ተጫውቷል። የመሬት ባለቤትነት ለባላባቱ የተተወ ሲሆን፣ አርሶ ባላባቱን የሚያበላው ብዙኀኑ ገባሪ ዘንድም ቢሆን የገባሪነት ማዕረጉ ለየቅል ነበር። ሰሜኑ ባብዛኛው ቋሚ ገባሪ ሲሆን፣ ደቡቡ ደግሞ በጥቅሉ ተነቃይ ገባሪ ነበር። ይህንን የመደብ ጥያቄ በመ.ኢ.ሶ.ን. ምክር ደርግ መሬት ላራሹን ሲያውጅ ከሞላ ጎደል የተቀረፈ ቢሆንም ቅሉ፣ የማኅበራዊ ማዕረግ (Social Status) ልዩነቱ ግን እየተራባ ቀጥሏል።

Friday, June 12, 2020

የትግራይ ክልል ምርጫ፤ ስለ ዴሞክራሲ ወይስ አልሞት ባይ ተጋዳይነት?


የትግራይ ክልል ብሔራዊ ምክር ቤት ምርጫውን ከጳጉሜ በፊት ለማካሔድ ዛሬ ሰኔ 5፣ 2012 ወሰነ። የዚህ ውሳኔ አዝማሚያ ወዴት ነው?

ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ከብልፅግና ጋር ያለው ፀብ የትግራይ ክልል ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ፀብ ተደርጎ መቆጠር ከተጀመረ ውሎ አድሯል። በሕወሓት ደጋፊነታቸው የሚታወቁ አክቲቪስቶች ኢትዮጵያን “ጎረቤት አገር” እያሉ የሚጠሩበት ጊዜ አለ። ሕወሓትም ክልሉን እንደ ነጻ አገር በመቁጠር የሚያደርጋቸው ብዙ ነገሮች አሉ። በክልሉ መንግሥት እና በፌዴራሉ መንግሥት መካከል የነበረው ኩርፊያ ወደለየለት ፀብ የተሸጋገረው ብልፅግና ከተመሠረተ በኋላ ቢሆንም ቅሉ፥ ፀቡ እየተባባሰ መታየት የጀመረው ደግሞ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳው ከተሰረዘ በኋላ ነው። ሕወሓት በክልሌ ምርጫ በጊዜው አካሔዳለሁ ማለቱ ውዝግቡን እስካሁን ያልደረሰበት ቁንጮ ላይ ያደርሰዋል። በተለይም ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ሁሉንም ክልሎች የሚመለከት ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ ይህ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ውሳኔ መምጣቱ፣ ጉዳዩን ከድጡ ወደ ማጡ ይሰደዋል። ትግራይ በሌላ አነጋገር ራሷን እንደ ሉዓላዊ አገር እየተመለከት ያስመስላታል።

ሕወሓት፤ የገዛ ‘ትሩፋቱ’ ሰለባ

ሕወሓት በአሁኒቷ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መዋቅር ዝርጋታ ላይ ዐቢይ ተዋናይ ነው። ሕገ መንግሥቱ፣ የፌዴሬሽኑ አወቃቀር፣ የምክር ቤቶቹ አደረጃጀት እና ሥልጣን በዋነኝነት የተወጠኑት በሕወሓት ነው። ሕወሓትም እንከን አልባ መንግሥታዊ መዋቅር እንደሆነ ይናገር ነበር፤ ነገር ግን ድንገት ከፌዴራሉ መንግሥት ገዢ ፓርቲነት ተገልሎ የክልል ገዢ መንግሥት እና የፌዴራሉ መንግሥት ተቃዋሚ ሲሆን፥ በፊት እንከን አልባ መስለው ይታዩት የነበሩት ስርዓቶች እና አሠራሮች በሙሉ ተቃዋሚ ሆኗል። ይህ ነው ሕወሓትን የገዛ ትሩፋቱ (ሌጋሲው) ሰለባ የሚያሰኘው።

የመጀመሪያው ሰለባነቱ ከመሐል አገርነት ወደ ዳር አገርነት መገፋቱ ነው። የፌዴራል አወቃቀሩ በሕዝብ ብዛት ሦስት ትልልቅ ክልሎችን (ኦሮሚያ፣ አማራ እና ደቡብ) በመፍጠሩ ምክንያት ሌሎቹ ክልሎች በሙሉ ከአጋርነት በስተቀር ዋጋ የሌላቸው አድርጓቸዋል። በክልሎች መሐል ያለው የሥልጣን ልዩነት (በሕዝብ ተወካዮች እና ፌዴሬሽን ምክር ቤት ባላቸው መቀመጫ መሠረት) እጅግ የተበላለጠ ሆኗል። ሕወሓት የፌዴራል ገዢ ፓርቲነት ሥልጣኑን ካጣ በኋላ፥ ኢሕአዴግ ውስጥ ሆኖ አጋር ፓርቲ ይላቸው የነበሩ “ትራፊ ይጣልላቸው” የነበሩ ክልላዊ መንግሥታት ዕጣ ደርሶታል።

ሁለተኛው ሰለባነቱ ሰሞኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ የሕገ መንግሥት ተርጓሚ ሆኖ በሕገ መንግሥት ከመሰየሙ የሚነጭ ነው። እንደሚታወቀው የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ መዋቅር አብላጫ መቀመጫ በገዢው ፓርቲ ይወሰዳል፤ እነዚህም ቁጥራቸው የሚወሰነው በብሔሩ ሕዝብ ቁጥር ነው። ይህም ሁለት ችግሮች ይፈጥራል። ብዙ ተወካዮች የሚኖረው/ራቸው ብሔር/ሮች ውሳኔ ሁሉም ላይ እንዲጫን ያደርገዋል። በሌላ አነጋገር እንደ ትግራይ አናሳ ቁጥር ያላቸውን ብሔሮች አናሳ ዕድል ይሰጣቸዋል። ሁለተኛቸው ችግር የምክር ቤቱ አባላት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች እንደመሆናቸው፥ የሚወስኑት ውሳኔ በምንም መልኩ የፓርቲያቸውን ጥቅም የሚነካ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም። ስለዚህ ብዙኀን ተወካዮች ያሉት ብልፅግና የሚፈልገው ውሳኔ ሲወሰንለት፣ ሕወሓት ግን “የበይ ተመልካች” ብቻ ሆኗል። ለዚህም ነው አፈ ጉባዔዋ በፓርቲያቸው ግፊት ከኃላፊነታቸው “በገዛ ፈቃዳቸው” እንዲነሱ የተደረጉት።
ሕወሓት መልሶ ራሱን ጠልፎ የሚጥል፣ የክልሉንም ተጠቃሚነት የሚጎዳ ውሳኔዎችን በኀይለኝነት እና አፍላ ዘመኑ ለምን አደረገ ለሚለው ትክክለኛ ምላሽ ማግኘት ይከብዳል። ምናልባት በየዋሕነት፣ ምናልባት ትክክለኛው መፍትሔ ይህ ነው በሚል ቅንነት፣ አልያም ደግሞ ሥልጣን አላጣም ወይም ከሥልጣን አልወርድም በፈለግኩት መንገድ ሕጉን አስፈፅማለሁ በሚል ከንቱ ምኞት ሊሆን ይችላል።

ምርጫ ማሰናዳት

ሕወሓት በክልሌ ምርጫ አካሒዳለሁ በማለት ተደጋጋሚ መግለጫ ያውጣ እንጂ በሕግ አግባብ በሦስት ወር ዕድሜ ብቻ ለቀረው የምርጫ ጊዜ መርሐ ግብር አላወጣም። የምርጫ ዝግጅት ገለልተኛ ተቋም የሚፈልግ ሲሆን፣ አሁን ያለው ተቋም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብቻ ነው። ሕወሓት በመግለጫው እንዳመላከተው ምርጫ ቦርድ ምርጫ ያዘጋጅልኝ ብሎ ጥያቄ ቢያቀርብ እንኳን፣ ቢያንስ የስድስት ወር ጊዜ እና በግምት ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ያስፈልገዋል። ይህ እንግዲህ በኮቪድ ምክንያት የሚስፈልገው ተጨማሪ ወጪ ከግምት ውስጥ ሳይገባ ነው። ይህ በአንድ በኩል አፈፃፀሙ ከሚፈልገው ግዜ አንፃር ምርጫው ወቅቱ ካለፈ በኋላ እንዲካሔድ የሚያስገድደው ስለሆነ የተነሳውን የጊዜ ጥያቄ መልስ እንዳያገኝ ያደርገዋል። በሌላ በኩል ይህንን የሚያክል በጀት ክልሉ ለምርጫ ማውጣት ይችላል ተብሎ አይታሰብም። የፌዴራሉ መንግሥት ደግሞ ይህንን ለመስጠት ፈቃደኛ ይሆናል ብሎ ማሰብ የዋሕነት ነው፤ ምክንያቱም የፌዴራሉ መንግሥት ምርጫ የሚካሔድበትን ጊዜ በፌዴሬሽን ምክር ቤቱ እንዲራዘም አስወስኗል። ያንንም ለሁሉም ክልሎች ተፈፃሚ እንዲሆን ነው የሚፈልገው። ይሄም ሁሉ ደግሞ የትግራይ ክልል ምርጫ ይዘጋጅልኝ ብሎ ቦርዱን የሚጠይቅበት የሕግ አግባብ ካገኘ ነው። ስለዚህ የምርጫ መሰናዶው ጉዳይ በትግራይ ክልል ብቻ ይሳካል ብሎ ማሰብ፣ ‘ላም አለኝ በሰማይ፣ ወተቷንም አላይ’ በሚል ያስተርታል። ይልቁንም መፍራት ሌላ ሌላውን ነው።

የምርጫው ጉዳይ እውን የማይሆነው በአፈፃፀም የጊዜ ፍላጎት፣ በጀት እጥረት እንዲሁም የሕግ አግባብ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ሕወሓት ራሱ ሌሎች ክልሎች ውስጥ ምርጫ በማይካሔድበት ጊዜ በክልሉ ለብቻው ምርጫ ማካሔድ አይፈልግም። ምክንያቱም ምርጫው ሕወሓት የማይፈልገውን ዓይነት ትኩረት ይስብበታል። በዚያ ላይ የክልሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና አገር ዐቀፍ ተብለው የተመሠረቱት ፓርቲዎች፣ ብልፅግና፣ ኢዜማ፣ ኦነግና አብንን ጨምሮ ተወዳዳሪ ማቅረብ የሚችሉት በሙሉ ተሳትፎ ያደርጋሉ። ወልቃይትና ራያ እንዲሁም ተቃውሞ እየተነሳባቸው ያሉ የትግራይ አካባቢዎች በሙሉ የጦፈ ክርክር እና ፉክክር ሊታይባቸው ይችላል። ሕወሓት የመሐል አገርን በጠላትነት በመፈረጅ የፈጠረውን ጊዜያዊ የተጋሩዎች አንድነት የሚሸረሽር እና ትግሉን ውስጣዊ ገጽታ የሚያሰጠውን ፉክክር ለማስተናገድ ዝግጁነት የለውም። ስለዚህ በትግራይ ክልል ውስጥ ከፌዴራል መንግሥቱ ምርጫ በተለየ የጊዜ ሰሌዳ የሚካሔድ ምርጫ አለ ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው። 

የዘፈኑ ዳርዳርታ

ሕወሓቶች ምርጫውን በጊዜው ለማካሔድ የፈለጉት ለሕዝብ ድምፅ ዋጋ የሚሰጡ ሆነው እንዳልሆነ ለማወቅ መመራመር አያስፈልግም። ጉዳዩ በአንድ በኩል የውስጥ የቤት ሥራቸውን ለማዳፈኛ የውጭ ጠላት መፈለጊያ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የፉክክር ነው። የሕወሓት አመራሮች በፊት ይንቋቸው በነበሩ የኢሕአዴግ አባላት በካልቾ ተመትተው ወደ ዳር መገፋታቸውን አምነው መቀበል አልፈለጉም ወይም አልቻሉም። ለዚህም የማዕከላዊ መንግሥቱን የሚቃረን ነገር በሙሉ ያደርጋሉ። በዚህ መንገድ ውጥረት ውስጥ የሚገባውን ማዕከላዊ መንግሥት ማሳጣት ወይም ማሸነፍ ይፈልጋሉ። ይህ ካልሆነላቸው ግን ተያይዞ መጥፋትም ቢሆን ይሞክራሉ። ትግራይን እንገነጥላለን የሚለው ጥያቄ የትግራይን ሕዝብ መደራደሪያ በማድረግ እንደሚመጣ መጠበቂያው ጊዜ አሁን ነው። በርግጥም ሕወሓቶች አሁን የፖለቲካ ካርዶቻቸውን በሙሉ ጨርሰዋል፤ አንቀፅ 39 የመጨረሻዋ ካርድ ልትሆን ትችላለች። በሕወሓቶች የኩራት፣ እንዲሁም የአልሞት ባይ ተጋዳይነት ፖለቲካ ምክንያት የአገር እና ሕዝቦች ደኅንነት አደጋ ጫፍ ላይ ቆሟል።  የሕወሓት የአጥፍቶ መጥፋት የመጨረሻው መጀመሪያ እነሆ የዚህ የምርጫ እናካሔዳለን መፈክር ነው። ምርጫ ማካሔድም ይሁን እንገንጠል ማለት ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ናቸው። የሕወሓት እርምጃ ግን ከሥልጣን እና ጥቅማጥቅም ጋር አብረው የቆረቡ ባለሥልጣኖች የትግራይን ሕዝብ ለመስዋዕትነት የሚዳርግ እርምጃ እንጂ የዴሞክራሲ ዒላማ የለውም።