Pages

Sunday, March 25, 2012

እውትም ‘ሰሚ ያጡ ድምፆች!’

From አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

መጀመሪያ እንዲህ ነበር፤
“የኛ ሙሽራ ኩሪ ኩሪ፣
አገባሽ አስተማሪ፡፡”

ከዚያ በኋላ፤
(በጓደኛዬ እርዳታ ርዕሱን ያስታወስኩት የዶ/ር በፍቃዱ ‹ሰሚ ያጡ ድምፆች› ላይ እንደሰፈረው)
መምህራን በየክፍለሃገራቱ ተሰማርተው የነበረ ቢሆንም ደሞዛቸው 202 ብር (ቱኦቱ) ብቻ ነበር፡፡ መምህራኑ ይቺን ‹ቱኦቱ› ምን ከምን እንደምን እንደሚያደርጓት ይቸግራቸው ነበር፡፡ ስለዚህ እንደመፍትሔ ሌላ መምህርት በማግባት ወጪን በመጋራት ገቢን 404 ብር (ፎር-ኦ-ፎር) ለማደረስ ይጥሩ ነበር፡፡ (ትዳር ትርጉሙ ገቢን ማሳደግ ወይም ወጪን መጋራት እንጂ ፍቅር አልነበረም ማለት ነው፡፡) ይሄ ነገር እየተለመደ ሲመጣ የመምህር ሚስት መምህርት (ወይም የመምህርት ሚስት መምህር) ‹ፎሮፎር› የሚል ቅፅል ተሰጣቸው፡፡ “ፎሮፎሬን ተዋወቃት” ማለት ልክ “ባለቤቴን ተዋወቃት” እንደማለት ሆነ፡፡

ትንሽ ከረምረም ሲል ደግሞ፤

Tuesday, March 20, 2012

ሕዝቦች ግለሰብን ይጨቁናሉ!

From አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

ሕዝባዊ እሳቤ (popular imagination?) ስለሚባል ነገር ልናወራ ነው፡፡ የሰው ልጅ ሐሳብ ልክ በኖረበትና ባለፈበት ሕዝብ የአስተሳሰብ አድማስ የተቀነበበ ነው፡፡ ቢሆንም ግለሰቦች የረቀቁ የሕዝብ ቅንጣቶች ናቸው፤ ከሕዝባዊ አስተሳሰብ ሊያመልጡ ይችላሉ፡፡ በዘመነ ሉላዊነት (globalization) ደግሞ የግለሰቦች ለመረጃ ተዳራሽነት ከሕዝቦች ይቀድማል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በሐሳብ ሲያፈነግጡ ግን ሐሳባቸው በሕዝቦች ሐሳብ ይጨቆናል፡፡

ሕዝብ ባሕል እና እሴት የሚባሉ ያልተጻፉ ባሕረመዝገቦች አሉት፡፡ እነዚህ ባሕረመዝገቦች ትክክል፣ ተገቢና ነውር የሆኑና ያልሆኑ ነገሮች በዘልማድ ይደነግጋሉ፡፡ የሕዝቡ አባል የሆኑ ግለሰቦች ሁለት ፈተናዎች አሉባቸው፡፡ አንደኛ፤ በዚህ የአስተሳሰብ ቅርጫት ታቅፈው፣ ከቅርጫቱ አሻግረው ማሰብ የሚችሉበት ዕድላቸው ጠባብ ነው፡፡ እነዚህኞቹ ፈተና ውስጥ ቢሆኑም ፈተና ውስጥ መሆናቸውን ሳያውቁ፣ እዚያው የተፈጠሩበት እንቁላል ውስጥ (ቅርፊቱን ሰብረው ውጪውን ዓለም ለማየት ሳይታደሉ) ያልፋሉ፡፡ ሁለተኛ፤ የእንቁላሉን ቅርፊት ሰብረው ለመውጣት አጋጣሚ ያደላቸውም ቢሆኑ እንቁላሉ ውስጥ ካሉ ሰዎች’ጋ አብረው የመኖር ዕድላቸው የዚያን ጊዜ ያከትማል፤ አንድም ሐሳባቸውን በመናገራቸው ከሕዝባቸው ይነጠላሉ፣ አሊያም ሐሳባቸውን አፍነው በልብ ሳይሆን በአካል ብቻ ከሕዝቦቻቸው’ጋ ይኖራሉ፡፡

Tuesday, March 13, 2012

እንደ እርሳቸው ያለ ፊትም አልነበረ፤ አሁንም የለ፤ ምናልባት፣ ምናልባት ወደፊት ሊኖር ይችላል!

From አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ “…ዘመናዊት ኢትዮጵያን የፈጠሩ ሰው ናቸው፡፡…ሲል የመሰከረላቸው ሰው ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ናቸው፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ ባቡር፣ መኪና፣ ኤሌክትሪክ፣ ስልክ፣ ሬዲዮ፣ ጋዜጣ፣ ሲኒማ… ብቻ አይደለም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቁት፡፡ የምንወዳትን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ባንዲራችንን ለመጀመሪያ ጊዜ ያውለበለቡትም እርሳቸው ናቸው፣ ከልማዳዊ አስተዳደር ተላቅቀው ሚኒስትሮችን መሾም የጀመሩትም እሳቸው ናቸው፣ የመጀመሪያውን ዘመናዊ ትምህርት ቤትና ሆስፒታል የከፈቱትም እሳቸው ናቸው፡፡

አውሮጳውያን አፍሪቃን ሲቆራመቱ ኢትዮጵያን ግን የነርሱ ቅርጫ ከመሆን ያተረፏት እርሳቸው፣ ራሳቸውና ብልሕ አመራራቸው ነው፡፡ በርግጥ ምኒልክ ዘመን አውሮጳውያን በስልጣኔ ጎዳና ላይ ብዙ እጥፍ ተጉዘው ነበር፡፡ ምኒልክ ግን የተረከቧትን ኢትዮጵያ ከነድንቁርናዋ ለተከተዮቹ አላስረከቡም፡፡ አቅማቸው የሚፈቅደውን ያህል ለኢትዮጵያ ብርሃን አሳይተው፣ ከዚያ በፊትና በኋላ ለኢትዮጵያውያን መሪዎች ያልተፈቀደ የሚመስለውን ታምሞ የመሞት ዕድል አግኝተዋል፡፡

የአፄ ምኒልክ ደግነት፣ ዘመናዊነትና መልካም አስተዳደር ዘመን የሚዘክረው ቢሆንም÷ አፄው ለኢትዮጵያ ካበረከቱት ትሩፋት ይልቅ ጨቋኝነታቸው ይገንናል የሚሉ ወገኖችም አልጠፉም፡፡ በዘመናቸው የነበረው ሕዝብ ግን ‹እምዬ ምኒልክ› እያለ ነበር የሚጠራቸው፡፡

እውን ምኒልክ ‘እምዬ’ ነበሩ?

Sunday, March 4, 2012

እቴጌ ጣይቱ ብጡል እና እቴጌ አዜብ መስፍን

From አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

ይህንን ጽሁፍ ማንበብ ለሚፈልጉ፡- ማስጠንቀቂያ ቁጥር አንድ፤ ጽሁፉን በከፊልም ሆነ በሙሉ ለቀዳማይት እመቤቲቱ ማስነበብ አይፈቀድም፡፡ ማስገንዘቢያ ቁጥር ሁለት፤ እቴጌ አዜብን አንቺ እቴጌ ጣይቱን አንቱ እያልኩ የጻፍኩት፤ እቴጌ አዜብ ወጣት ስለሆነች (ወይም እንደወጣት ስለሚያደርጋት) ሳይሆን ከኢቲቪ በቀር አንቱ ብሎ የሚጠራት ሰው ሰምቼ ስለማላውቅ÷ እንደአርቲስት ‹አንቱ› አትባል ይሆናል ብዬ ነው፡፡

የዛሬን አያርገውና የሃገራችንን እቴጌዎች ጀብዱ መዘንጋት አይቻልም ነበር፡፡ እቴጌ ተዋበች ካሣን ‹‹እኔ ጀግና ወንድ እወዳለሁ›› እያሉ በጠላት ላይ የማያወላዳ አቋምና እርምጃ እንዲወስዱ ያደርጓቸው ነበር፡፡ እቴጌ ጣይቱ ብጡልንም የምናውቃቸውና የምናስታውሳቸው በዚሁ መሰል ጀግንነታቸው ነው፡፡ እቴጌ ጣይቱ ባይኖሩ ኖሮ የአድዋ ጦርነት ላይካሄድ፣ ኢትዮጵያም የውጫሌ ውል አንቀጽ 17ን ተቀብላ ልትቀጥል የምትችልባቸው ዕድሎች እንደነበሩ የሚገምቱ የታሪክ ባለሙያዎች አሉ፡፡ 

እቴጌ ጣይቱ ባይኖሩ ኖሮ ይሄ ዛሬ የምንመካበት ጥቁር ሕዝቦች ነጮችን ለመጀመሪያ ጊዜ ድል የነሱበት፣ ያልታጠቁ ሕዝቦች የታጠቀና የሰለጠነ ሰራዊትን መደምሰስ እንደሚችል ያሳየንበት የአድዋ ድል አይፀነስም ነበር፡፡ ከዚያም በላይ እቴጌ ጣይቱ ባይኖሩ ኖሮ የአድዋ ጦርነትን አናሸንፍም ነበር (ወይም እናሸንፋለን ለማለት ይከብድም ነበር) ምክንያቱም የጦርነቱ መደምደሚያ ከሆነው የአድዋ ጦርነት በፊት መቀሌ ላይ - ጣሊያኖቹ የሰሩት ምሽግ፣ ጫማ የሌላቸውን ኢትዮጵያውያን የማያስደርስ፣ በባለእሾህ የሽቦ አጥር የታጠረ፣ በጠርሙስ ስብርባሪ መሬቱ የተነጠፈ ነበር፡፡ ያንን ምሽግ ሰብረው መግባት የሞከሩት ኢትዮጵያውያን የሳት እራት ሆነው ቀርተዋል፡፡