Pages

Sunday, November 5, 2017

ተቃዋሚዎች ከራሳቸው ይልቅ ኢሕአዴግን ያምኑ ይሆን?

ከዓመታት በፊት አንድነት ፓርቲ በሕይወት ሳለ፣ የቀድሞዎቹ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት አቶ ስዬ ኣብርሓ እና ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ፓርቲውን ሊቀላቀሉ ሲሉ ትልቅ ፌሽታ ሆኖ ነበር። እንዲያውም ‘መርሕ ይከበር’ በሚል የተገነጠለው ቡድን፣ እነርሱን ለመቀበል የተዘጋጀውን ድግስ በአመፅ እስከማደናቀፍ ደርሷል(?)። ቅራኔው “እነርሱ የተለየ አቀባበል የሚደረግላቸው የገዢው ፓርቲ የቀድሞ አባል ስለሆኑ ነወይ?" የሚል ነበር። ተቃዋሚው የቀድሞ የኢሕአዴግ አባል ለቅቆ ሲወጣ ማግነን ያውቅበታል። በአንድ በኩል ሳስበው፣ መቃወማቸው ትክክል መሆኑን የገዢው አባላት መልቀቅ ለተቃዋሚዎቹ ስለሚያረጋግጥላቸው ይመስለኛል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ከጥቅም ባሕር ውስጥ መውጣት ስለሚከብድ ያንን እያሰቡ ይመስለኛል። የኋለኛውን እንዳላምን እንደ ዶ/ር ነጋሶ፣ ከጥቂቶቹ በቀር ብዙዎቹ ተገፍተው ነው ከገዢው የሚወጡት።

የሆነ ሆኖ፣ አናንያ ሶሪ በስላቅ እንደተናገረው፣ ‘ብለን ብለን ኦሕዴድ እና ብአዴን ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ ዛሚ እና ENN ነጻ ሚድያዎች የሆኑበት ዘመን ላይ ደርሰናል’። ለማንኛውም በምናገባኝ ነገሩን ከመታዘብ ይልቅ የኦሕዴድ (እንዲሁም የብአዴን) የሰሞኑ እምቢተኝነት እውነት ወይስ የሕወሓት ሴራ? ተቃዋሚው (በፓርቲ የታቀፈውም ያልታቀፈውም) ጉዳዩን እንዴት ነው ማስተናገድ ያለበት? የሚሉትን ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት እንሞክር።

የጠላቴ ጠላት ለኔ ምኔ?

በተቃዋሚዎች ዘንድ "የሕወሓት የበላይነት" መኖሩ እምብዛም አጠራጣሪ አይደለም። ማኅበራዊ ሚድያ አሁን (ከተዳራሽነቱ በላይ) በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሐሳብ አቅጣጫ አስማሪ እንደመሆኑ ይህንን እምነት የበለጠ በማስረፅም ሆነ በመታገል ረገድ የጉዞ ካርታ (road map) አስቀማጭ ነው። ይህንን ብዙዎች መረዳታቸው ሽሚያ ፈጥሯል። መጀመሪያ ታሪክን፣ ከዚያ ድልን፣ አሁን ደግሞ ሟችና ገዳይን መሻማት ደረጃ ላይ ተደርሷል። በዚህ መሐል የሕወሓት ደጋፊ/ካድሬዎችም የራሳቸውን ትርክት ይፈጥራሉ። ተቃዋሚው ደግሞ እነርሱ የወደዱትን መጥላት፣ እነርሱ የጠሉትን መውደድን እንደ ምላሽ ይገብራል። አንዳንዴ ሳስበው የሕወሓት ካድሬዎች ተቃዋሚው የሚፈልጉትን እንዲያደርግላቸው ከፈለጉ፣ ያንን ነገር እንዳያደርገው መቀስቀስ ብቻ የሚበቃቸው ይመስለኛል። "ገዱን የምወደው ሕወሓት ስለምትጠላው ነው” የሚል መፈክር ሰምቻለሁ። አቶ ገዱ በሕወሓት ካድሬዎች ፌስቡክ ላይ ከመተቸታቸው በቀር ፓርቲያቸው (ብአዴን) በሕወሓት እልቅና የሚተዳደረው ኢሕአዴግ አባል ነው። የኦሕዴድ የሰሞኑ ነገርም ያው ነው። ይህ ዓይነቱ ምክንያት ለብአዴንም ይሁን ለኦሕዴድ የድጋፍ መሠረት ሊሆኑ አይችሉም።

ኦሕዴድ እና ብአዴን እውን ሕወሓት ላይ አምፀዋል?

ከአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በፊት ፌዴራል ፖሊስ የኦሮምያ ከተሞችን መናኻሪያው ሲያደርገው፣ በአማራ ከተሞች ግን (ቢያንስ ተቃውሞዎችን ለመበተን) አልገባም ነበር። የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በታወጀበት ወቅት የሚበዙት እስረኞች የታፈሱት ከኦሮሚያ አካባቢ ነበር። ሌላው ደግሞ እነ ኮሎኔል ደመቀን ለፌዴራል መንግሥቱ አሳልፎ ባለመስጠቱ፣ በዚያ ላይ ብአዴን በላዕላይ ደረጃ ሹም ሽረት ባለማድረጉ፣ በተወሰነ ደረጃ ብአዴን የክልሉን ነጻነት (autonomy) እያስከበረ ነው ማለት ነው በሚል ወስጄው ነበር። ይሁን እንጂ የኋላ ኋላ በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ወቅት የክልሉን ነዋሪዎች ትጥቅ የማስፈታቱ ሥራ በፌዴራሉ የፀጥታ ኃይሎች በዝምታ እንደተሠራ ሰማሁ። እንዲሁም ከክልሉ ታፍሰው መቐለ፣ ባዶ ሽድሽት ታስረው የተፈቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አባሎች አግኝቼ የክልሉ ነጻነት (ወይም የአቶ ገዱ እና ፓርቲያቸው እምቢተኝነት) ላይ ያለኝ የማመን ዝንባሌ ቀስ በቀስ ተገፈፈ። በርግጥም አሁን፣ የሕወሓት ካድሬዎች ስሞታቸውን ከብአዴን ላይ አንስተው ወደ ኦሕዴድ አዙረዋል። ኦሕዴድም በተራው ደጋፊ እየጎረፈለት ነው።

ኦሕዴድ በተቃዋሚዎች ዘንድ ሳይቀር ተአማኒነት እንዲያገኝ ያደረገው በኦሮሚያ ሶማሊ ክልሎች ድንበር ነዋሪዎች ዘንድ በተደረገው ግጭት ላይ፣ የክልሉ መንግሥት ባሳየው ለክልሉ ነዋሪዎች ያደላ ተቆርቋሪነት ነው። በዚህ ላይ የሶማሊ ክልል መንግሥት ያንፀባረቀው ብስለት የጎደለው ምላሽ ግጭቱን በማባባስ፣ የኦሕዴድን ተቀባይነት ጨምሮታል። የሶማሊ ክልል ገዢ ፓርቲ (መንግሥት) የ2008ቱን ሕዝባዊ አመፅ ከመቃወም ጀምሮ፣ ያሳየው ዝንባሌ በሕወሓት ወዳጅነት አስፈርጆታል።
ስለዚህ ከሶማሊ መንግሥት ጋር የኦሮሚያ መንግሥት መጋጨቱ፣ ኦሕዴድ ሕወሓትን እንደደፈረ ተደርጎ ተተርጉሟል። በተለይ እኔ ራሴ ቢሾፍቱ ተገኝቼ ባየሁት የኢሬቻ በዓል ላይ እና ከዚያ በኋላ በተካሔዱ ተቃውሞዎች ላይ የክልሉ ፖሊስ አንድም እርምጃ አለመውሰዱ፣ ቀድሞም እነጃዋር “ገዳያችን አግኣዚ ነው” የሚሉትን ተአማኒ አድርጎታል። ለኦሕዴድም ግርማ አላብሶታል።

የኢሕአዴግ አባሎች እንቢታ ምን ፋይዳ አለው?

"የሕወሓት የበላይነት" በፌዴራል መንግሥቱ ብቻ ሳይሆን በኢሕአዴግ ውስጥም አለ። ይህ የሚጀምረው ከአመሠራረታቸው ነው። የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች፣ በሕወሓት ፍላጎትና ርዕዮተዓለም ተጠርበው፣ ለሕወሓት በኦሮሚያ፣ አማራ እና ደቡብ ክልሎች ቅቡልነት ለማስገኘት የተፈጠሩ ቡድኖች ናቸው። ‘እነዚህ የግንባሩ አባላት የሚያደርጉት ‘መፈንቅለ ሕወሓት’ ተረኛ ጨቋኝ ከማምጣት ውጪ ምን ያመጣሉ?’ የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም።

Thursday, November 2, 2017

ማነው አሳሪ? ማነው ፈቺ?

አግባብ ያልሆኑ እስሮች፣ ያልተጠበቁ ፍቺዎች እና የማይታመኑ የፍቺ ክልከላዎች ደጋግመው ቢከሰቱም ሁሌ እንደ አዲስ የሚያወያዩን አጀንዳዎች ናቸው። ኦቦ በቀለ ገርባ የታሰሩት የኦሮሞ ሕዝብን ጥያቄ ያለ ፍርሐት ስላስተጋቡ ብቻ ነው። ይህን የምለው ለይስሙላ አይደለም፤ የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ያቀረበባቸውን ማስረጃ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ አራተኛ ወንጀል ችሎት ተገኝቼ አድምጬያለሁ። ችሎቱ ክሳቸውን ከሽብር ወደ 'በንግግር አመፅ ማነሳሳት' (የወንጀል ሕጉ አንቀፅ 257/ሀ) ዝቅ ሲያደርገው ዋስትና እንደሚያሰጣቸው ግልጽ ነበር። ችሎቱ በዋስትና ጉዳይ ውሳኔ ለመስጠት ከአንድ ቀጠሮ በላይ ሲወስድ አይቼ አላውቅም። እርሳቸውን ግን ደጋግሞ ቀጠሮ ሲሰጣቸው፣ ዳኞች ዋስትናውን መከልከልም ሆነ መፍቀድ የፈሩ ይመስል ነበር። በመጨረሻ የሞት ሞታቸውን ከለከሏቸው እና አረፉ። ይግባኝ ተባለ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ30 ሺሕ ብር የስር ፍርድ ቤት የከለከለውን ፈቀደ። ቂሊንጦ እስረኛ ማቆያ ቤት እስረኛውን በመፍታት ፈንታ ደብዳቤው ላይ የተጻፈው ቁጥር አደናገረኝ በሚል ሰበብ ሁለት ቀን አሳደራቸው። በመሐል ፋና ሬዲዮ የኦቦ በቀለ ፍቺ በዐቃቤ ሕግ ይግባኝ ባይነት፣ በሰበር ሰሚ ችሎት ታገደ የሚል ዜና ይዞ ወጣ። Déjà vu. 

ሐምሌ ወር 2007፣ በእነዘላለም ወርቅአገኘሁ መዝገብ ሀብታሙ አያሌው፣ አብርሃ ደስታ፣ የሺዋስ አሰፋ፣ ዳንኤል ሺበሺ እና አብርሃም ሰለሞን ነጻ ከተባሉ በኋላ የተከሰተው ይሄንኑ ይመስል ነበር። ቤተሰቦቻቸው ሲፈቱ ለመቀበል ቂሊንጦ በር ላይ ሲመላለሱ፣ ማረሚያ ቤቱ ሰበብ ሲፈጥር አቆያቸው፤ በመሐል፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍቺያቸውን እንዳገደው ተሰማ። ከዚያ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ በዞን ዘጠኝ ጉዳይ ከታሰሩት አምስቱ ድንገት ስማቸው ተጠርቶ ከቂሊንጦ እስረኛ ማቆያ ቤት ተጠርተው ውጡ ተብለው ነበር። ለቀሪዎቹም ሆነ ለወጪዎቹ በጣም አስደንጋጭ ገጠመኝ ነበር። ዐቃቤ ሕግ የነዚህን አምስቱን ክስ አንስቷል ተባለ። ከሁለት ሳምንት በኋላ ቀሪዎቻችን ፍርድ ቤት ቀረብን፣ ያኔ "ተከላከሉ ወይም በነጻ ተሰናበቱ" መባል ነበረብን። ቀጠሮ ተሰጠን፣ ተደገምን፣ 5 ጊዜ። ጥቅምት የሞት ሞታቸውን ቀሪዎቻችን ፈቱን። የነ ሀብታሙ ጉዳይ በጠበቃቸው ይግባኝ ባይነት ዓመት ያክል ተንዘላዝሎ፣ እነርሱም ተፈቱ። 

ማነው አሳሪ?

ለዚህ ጥያቄ እርግጠኛ መልስ ማግኘት ይከብዳል። ከልምድ ግን መገመት ይቻላል። እኔና ጓደኞቼ ማዕከላዊ በነበርንበት ጊዜ ማዕከላዊ የነበሩት (በቁጥጥር ሥር ያዋሉን) መርማሪ ፖሊሶች ስለኛ የሚያውቁት ጥቂት ነገር ነበር። ወረቀታቸውን እያገላበጡ ሲጠይቁን፣ የሆነ ከጀርባቸው ያለ ሰው እነዚህን ጥያቄዎች ጠይቋቸው ብሎ እንደላካቸው ያስታውቅባቸው ነበር። በሰጠናቸው መልሶች የረኩ መስለው ከሔዱ በኋላ፣ እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው ይመለሳሉ። መልሳችን የላኳቸውን ሰዎች አላረካም ማለት ነው። ይሔ ነገር ለኔ ያመላከተኝ ቢኖር ከኋላቸው አለቆቻቸው መኖራቸውን ሳይሆን፣ የአለቆቻቸውም አለቆች መኖራቸውን ነው። በኔ ግምት 'የመረጃ እና ደኅንነት ቢሮ' (ደኅንነቶች) ከሁሉም የሽብር ነክ እስሮች ጀርባ ናቸው። 

ጠበቆች አዲስ ክሶች በተመሠረቱ ቁጥር 'የሕግ ባለሙያ እንዴት እንዲህ ዓይነት ክስ ያዘጋጃል?' እያሉ ይገረማሉ። ዐቃቤ ሕጎች፣ ለችሎት 'ክሱን አላየሁትም አሁን ነው የደረሰኝ' ሲሉ ሰምቼ አውቃለሁ። የሚሰጡት ሰበብ 'ዐቃቤ ሕግ ተቋም ነው፤ አንዱ ያዘጋጀውን ክስ ሌላው ያስቀጥለዋል' የሚል ቢሆንም አያሳምነኝም። የሽብር ክሶቹን የሚጽፋቸው ረዥም እጅ ያለ ይመስለኛል - ይኸውም ሊሆን የሚችለው የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ብቻ ነው። 

የዳኞች መለማመድ

የሽብር ችሎትን መዳኘት ሕሊና ላለው የሚያሰቃይ ነገር ነው። አብዛኞቹ ተከሳሾች የአሰቃቂ ጥቃት ሰለባ ናቸው። ያንንም ሰሚ ባገኝ በሚል ተስፋ በችሎት ይተነፍሱታል። ክሱ ዝርክርክ ነው። ማስረጃዎቹ አይረቡም። ተከሳሾቹ በችሎቱ ነጻነት አያምኑም። ዳኞቹ በተለያዩ ጊዜዎች የተለያዩ ስሜቶችን ሲያስተናግዱ ይቆዩና ወደኋላ ላይ የተከሳሾቹን ሕመም መረዳት፣ ማባበል፣ ለውሳኔያቸው ረዥም ማብራሪያ መስጠት እና ፈራ ተባ እያሉ አንዳንድ እስረኞችን መፍታት ይጀምራሉ። ወዲያው ግን ይቀየራሉ።  የሽብር ችሎቶች ዳኞች በጣም ቶሎ፣ ቶሎ ከመቀያየራቸው የተነሳ አንዱ የጀመረውን ጉዳይ ሌላ የመጨረሱ ዕድል ሰፊ ነው። 

በገዢዎቻችን እና በዳኞች መካከል ያለውን ግንኙነት ከውጭ ምልከታ ለመመዘን ሞክሬያለሁ። በቀጥታ 'እከሌን ይሄን ያክል ፍረድበት፣ እከሌን ፍታው' የሚባሉ አይመስለኝም። ነገር ግን ዳኞቹ ሲሾሙ መጀመሪያ ለስርዓቱ ያላቸው ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ መግባት የለበትም። አንዳንዶቹ ለገዢው ቡድን ጥብቅና ይሰማቸዋል። በዚያ ላይ ሹመቶች አሉ። በታማኝነታቸው ልክ ነው ቀደምቶቹ የተሾሙት።  በሌላ በኩል፣ በተለይ በሽብር ጉዳይ፣ ተከሳሾች የሚመሠረትባቸው የክስ አንቀፅ በራሱ መልዕክት ነው። አሳሪው ተከሳሹን ምን ያህል ማሰር እንደሚፈልግ በክሱ ያመለክታል። በዚያ ላይ የግል ፍርሐታቸው አለ፤ 'መንግሥት በዚህ የጠረጠረውን እኔ እንዴት ማስረጃ የለም ብዬ እፈታዋለሁ?' ከዚያም ውጪ ምናልባት በውስጥ ስብሰባቸው ላይ 'ጉዳዩ ሲሪዬስ ነው' ይባሉ ይሆናል። ለዚህም ይመስለኛል፣ ዳኞች ከእስረኞቹ ጋር ሲለማመዱ፣ ሐዘኔታ ሲሰማቸው፣ መተዋወቅ ጥርጣሬያቸውን እያጠፋ የመፍታት ድፍረታቸው ሲጨምር አስተዳደሩ የሚፐውዛቸው። አሁን ለምሳሌ የአራተኛው ወንጀል ችሎት ሦስቱም ዳኞቹ ከዚህ ወር ጀምሮ ተቀይረዋል። የ19ኛው ችሎት ዳኞችም በቅርቡ ተቀያይረዋል።

ከዚያ ውጪ ያለው ጫወታ በዐቃቤ ሕግ ሥም ነው። ሲያሻቸው ክሱን ያከብዱታል፤ ሲያሻቸው ያቀሉታል። ሲያሻቸው ክሱን ያቋርጡታል። ሲያሻቸው ምስክሮችን በማፈላለግ ሥም የችሎቱን መደመጥ (እስኞቹ ወኅኒ ተጥለው) ያራዝሙታል (ለዚህ ተባባሪያቸው ምስክሮቹን ማቅረብ ያለበት ፖሊስ ነው)። ሲያሻቸው ፍቺውን በይግባኝ ያሳግዱታል (ለዚህ ደግሞ ተባባሪዎቻቸው የማረሚያ ቤት አስተዳደሮች ናቸው)። 

ማረሚያ ቤቶች ውስጥ የፍቺ ወረቀት መጥቶለት እንዲቆይ የሚፈልጉት ሰው ላይ ሰበብ ይፈጥራሉ። ማረሚያ ቤቶች ውስጥ "ደኅንነት" የሚባሉ ሠራተኞች አሉ። የሥራ ድርሻቸው ምን እንደሆነ አይታወቅም፤ ግን ፈላጭ ቆራጭ ናቸው። እንደሚመስለኝ፣ ዐቃቤ ሕጎች ይግባኝ እንዲሉ (ደኅንነት መሥሪያ ቤቱ) ሲወስን፣ በቀጥታ ለማረሚያ ቤቶቹ የደኅንነት ሠራተኞች፣ እስረኞቹ በሰበብ እንዲቆዩ ትዕዛዝ ይሰጧቸዋል። በዚህ ግዜ ከላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩ ይፈፀማል። ዐቃቤ ሕጎች ይህንን በራሳቸው አይፈፅሙትም ብዬ የምገምተው በምክንያት ነው። አብዛኛዎቹ ወጣቶች ናቸው። ካልታዘዙ በቀር በሥራው ላይ እስከ ይግባኝ ለመሔድ የተዘጋጀ ምንም የሥራ መነቃቃት አይታይባቸውም። እንዲሁ ሥራ አጥተው የገቡ ስልቹዎች ናቸው። ብዙውን ክስ አያውቁትም፤ እንዲያውም ችሎት ውስጥ ሲነበብ ከታዳሚው ጋር እየሰሙ የትየባ ስህተት ገጥሞ እንዲያርሙት ሲጠየቁ ግራ ይጋባሉ።

ታዲያ ማነው ፈቺ?

ድንገት ክሳቸው ተቋርጦ የተፈቱ ሰዎች፤ የሞት ፍርድ፣ የ22 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸው በ6 ወይም በ3 ዓመታቸው የተፈቱ ሰዎች አሉ። ይቅርታ ጠይቀው ያልተፈቱ አሉ፤ ይቅርታ ጠይቀው የተፈቱ አሉ። ይቅርታ ሳይጠይቁ የተፈቱ አሉ። መታሰራቸውም አግባብ ስላልነበር፣ መፈታታቸው ብዙዎቻችንን ያስደስተናል። ግን ማነው የሚፈታቸው? በምን መመዘኛ?  የማረሚያ ቤቱ ሥልጣን፣ ከፍርድ ቤቱ ይለያል። ነገር ግን ፍርድ ቤት "የእስረኞችን መብት አትጣስ" ሲባል ጆሮ ዳባ ልበስ የሚለው እና ባለፈው ዓመት የአራተኛው ወንጀል ችሎት ዳኞች "እኛን አትሰሙንም" ብለው ያማረሩት ማረሚያ ቤት ሥልጣን አለው እንዳይባል፤ የለውም። በቀድሞ ታጋዮች የሚመራው ማረሚያ ቤት ለሽብር እስረኞች ከፍተኛ ጥላቻ አለው። ሥልጣን ቢኖረው ስንቶቹ የሙስና እስረኞች (ከቀድሞ ታጋዮችም አሉበት) ለአስተዳደሮቹ በሚሰጡት መደለያ ብዛት ቀዳሚው ተፈቺ ይሆኑ ነበር። ስለዚህ ፈቺ አሁንም የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ነው። መፈታትም የነጻነት፣ ወይም የእስር ዘመንን ማረጋገጫ ሳይሆን የፖለቲካ ጫወታ ነው። አንዳንዴ እየከፋፈሉ እያሰሩ፣ እየከፋፈሉ መፍታት። ሌላ ግዜ ስጋት የሆነውን አቆይቶ፣ ስጋት ያልሆነውን  በመፍታት መደለል። ሌላም፣ ሌላም…

ከዚህ ውጪ ያለው ግምት ብዙም አይስማማኝም። ምክንያቱም፣ አሳሪም የደኅንነቱ ቢሮ፣ ፈቺውም የደኅንነት ቢሮ።

Tuesday, October 24, 2017

የምርጫ ስርዓቱ መሻሻል ጉዳይ

ብዙ ሰው ችላ ብሎታል። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ግን "መደራደራቸውን" ቀጥለዋል። ከኢሕአዴግ ጋር እየተደራደሩ ያሉት ፓርቲዎች ምንም ሕዝባዊ ቅቡልነት/ውክልና የላቸውም ማለት ይቻላል። ለዚያ ነው "ድርድሩ" ጆሮ ያጣው። ዞሮ ዞሮ ኢሕአዴግ "ድርድሩን" ሲጠራ በተነሳበት ዓላማ ሊጠናቀቅ ተዳርሷል። የምርጫ ስርዓቱን ማሻሻል። ኢሕአዴግ ውጤቱን "በድርድር" የተገኘ ለማስመሰል ስለፈለገ እንጂ ቀድሞውንም ስርዓቱን ለማሻሻል ወስኗል። ለምን እና እንዴት?

፩) ቀዳሚ አሳላፊ (First Past The Post /FPTP) የተባለው የአሁኑ ስርዓት ድምፅ አባካኝ ነው። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት የምርጫ 2002 የአዲስ አበባ ውጤትን እናመጣለን። በወቅቱ ከመረጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ውስጥ 54% ኢሕአዴግን መረጡ፣ 37% መድረክን መረጡ፣ 9% ሌሎች ተቃዋሚዎችን መረጡ። ነገር ግን ከአንድ ተቃዋሚ በስተቀር ፓርላማ ባለመግባቱ በጥቅሉ የ46% የአዲስ አበባ መራጮች ድምፅ ባክኖ ቀርቷል።

፪) ብዙ መራጭ ባላቸው የምርጫ ክልሎች ብዙ ድምፅ ያገኙ ተወዳዳሪዎች ሲወድቁ፣ ትንሽ መራጭ ባለባቸው የምርጫ ክልሎች ያሉ ተወዳዳሪዎች ባነሰ ድምፅ አልፈዋል። ለምሳሌ በዚያው የ2002 ምርጫ ወቅት በአንድ የምርጫ ክልል 42,555 ድምፅ ያገኙት የመድረክ ተወዳዳሪ አቶ ዑርጌሳ ዋኬኔ ፓርላማ አልገቡም፤ ነገር ግን በሌላ ምርጫ ክልል 12,753 ድምፅ ያገኙት የኢሕአዴግ ተወዳዳሪ ዶ/ር እልፍነሽ ኃይሌ ፓርላማ ገብተው ነበር።

፫) የምርጫ ስርዓቱ ተመጣጣኝ ውክልና (proportional representation /PR/) ቢሆን ኖሮ ለአዲስ አበባ ከተተዉት 23 የምክር ቤት ወንበሮች ውስጥ 12ቱ በኢሕአዴግ፣ 9ኙ በመድረክ እና ቀሪዎቹ ሁለቱ ለሌሎች ተቃዋሚዎች ይሔዱ ነበር። (በዚያው በ2002ቱ ምርጫ)

ይሔ ቅሬታ ሲነሳ ሰንብቶ ነበር። ኢሕአዴግ ግን ባለፉት ሁለት ምርጫዎች ወቅት ባገኘው ድምፅ መሠረት ስርዓቱ ተመጣጣኝ ውክልና ቢሆንም ኖሮ ማለፉ አይቀርም ነበር። ምክንያቱም፣

ሀ) ከምርጫ 97 ወዲህ መራጩ ሕዝብ በምርጫው ስርዓት ዴሞክራሲያዊነት ተስፋ ቆርጧል። ለመምረጥ የሚሔዱትም ወይ የቀበሌ ባለሥልጣናትን የሚፈሩ ተቃዋሚዎች፣ ወይም የኢሕአዴግ ደጋፊዎች፣ ወይም ጥቂት በምርጫ ፖለቲካ መቁረጥ ያቃታቸው መራጮች ብቻ ናቸው።

ለ) ኢሕአዴግ ምርጫው አንድ ዓመት ሲቀረው ገለልተኛ ሚዲያዎችን ከበፊቱ የበለጠ በማፈን ወይም በማገድ፣ ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞችን በማሰር፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በመሰንጠቅ እና የመንግሥት ሚድያዎችን እና የመንግሥት ተቋማትን ለቅስቀሳ በመጠቀም ራሱን ብቸኛ ተወዳዳሪ አድርጎ ያቀርባል።

ሐ) ኢሕአዴግ ለታይታ ያክል ተቃዋሚ የፓርላማ አባል እንዲኖረው ቢፈልግም፣ በየምርጫ ክልሎች የሚያሠማራቸው ካድሬዎች በሙሉ በኋላ ላይ ላለመገምገም ሲሉ በራሳቸውን የምርጫ ክልል ኢሕአዴግን አሸናፊ ለማድረግ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ዘዴ ተጠቅመው ያሸንፋሉ። 100% ውጤት የተገኘው በነዚህ ተንኮሎች እና ዘዴዎች ነው።

ስለዚህ (ሐ) ላይ የተጠቀሰው ችግር ሳይፈጠር (ካድሬዎቹ አሉታዊ ግምገማ ሳይቀርብባቸው) ተቃዋሚ ፓርላማ የማስገቢያው መንገድ የ"ተመጣጣኝ ውክልና" በመጠቀም መሆኑን ኢሕአዴግ ተረድቷል። ነገር ግን ደግሞ ድንገት የምርጫ 97 ዓይነት ነገር ተከስቶ በቀላል የተቃዋሚዎች ዳግማዊ መነቃቃት በተመጣጣኝ ውክልና የሚገኘው ውጤት የተቃዋሚዎቹን ድምፅ ድምር ከኢሕአዴግ ሊያስበልጠው እንደሚችል ያውቃል። ለዚህ ነው "ቅይጥ ትይዩ" (Mixed-Parallel) የሚባል የስርዓት ማሻሻያ ይዞ የመጣው።

በጣም የሚያሳዝነው ተቃዋሚዎች "ቅይጥ ትይዩ" የተባለው የምርጫ ስርዓት ምን ዓይነት እንደሆነ አለማወቃቸው ብቻ ሳይሆን፣ ኢሕአዴግ እንዲያስረዳቸው መጠየቃቸውም ጭምር ነው።

በተመጣጣኝ ውክልና ስርዓት ከግል ተወዳዳሪዎች ውጪ ፓርቲዎችን ወክለው የሚቀርቡ ግለሰቦች አይኖሩም። ፓርቲዎቹ ባገኙት ውጤት ልክ ነው ለወንበሮቹ ሰው የሚመድቡት። ቅይጥ ትይዩ የተባለው ስርዓት የተወሰኑ ወንበሮች በቅድሚያ አላፊ ስርዓት፣ የተወሰኑ ወንበሮች ደግሞ በተመጣጣኝ ውክልና የሚገኝበት እና ሁለቱንም የምርጫ ስርዓቶች ጎን ለጎን ማስኬድ የሚቻልበት ስርዓት ነው። ይህ የምርጫ ስርዓት አንድ ፓርቲ ለረዥም ዓመታት የገዛባቸው አገሮች የተከተሉት ስርዓት ነው። በተለይ የምርጫ ክልሎቹን በደጋፊዎቹ አሰፋፈር ማወቀር (gerrymandering) የቻለ ፓርቲ ዘላለም አሸናፊ  የሚሆንበት ስርዓት ነው።

ተቃዋሚዎቹ ስለተጠቆመው የምርጫ ስርዓት ኢሕአዴግ ካብራራላቸው በኋላ ነው "መደራደራቸውን" የቀጠሉት። አሁን 11 ፓርቲዎችን ያቀፈው ቡድን 60:40 (ማለትም 60% ቀዳሚ የሚያልፍበት፣ 40% ተመጣጣኝ ውክልና) እንዲሆን "የመደራደሪያ" ምጥጥን በማቅረብ "ቅይጥ ትይዩ" ስርዓትን ተቀብለዋል።

በበኩሌ፣ ትክክለኛው "ሕዝባዊ ስርዓት" የሚለካው በምርጫው ውጤት ሳይሆን በምርጫዎች መካከል ባለው ሕዝባዊ ተሳትፎ ነው ብዬ ነው የማምነው። ይህ ደግሞ ያለ ሲቪል ማኅበራት፣ ያለ ገለልተኛ ብዙኃን መገናኛና ለሕዝብ ወገንተኛ የሆኑ ተቋማት በሌሉበት ይሳካል ብዬ አላምንም። ሆኖም፣ የምርጫ ስርዓቱም ቀላል ቁም ነገር ነው ብዬ አላስብም። ስለዚህ፣ ለእንደኛ ዓይነቱ አገር ድምፅ አባካኙ ቀድሞ አላፊ ስርዓት አዋጭ ነው ብዬ አላምንም። የተሻለው ተመጣጣኝ ውክልና ነበር። ይህ ግን ቀድሞም የይስሙላ በተባለው ድርድር፣ በፓርቲዎች አላዋቂነት ሳቢያ የማይሆን ሆኗል። ኢሕአዴግ በራሱ ፍላጎት የጀመረውን ድርድር እንደፍላጎቱ እየጨረሰው ነው።

Sunday, October 15, 2017

የባንዲራ ማኒፌስቶ!

ልጅ እያለን፣ ታላላቆቻችን እኛን እርስበርስ እያደባደቡ ሲዝናኑብን እንዲህ ያደርጉ ነበር። ምራቃቸውን መሬት ላይ ሁለት ቦታ ላይ እንትፍ እንትፍ ይሉና፣ "ይቺኛዋ ያንተ እናት፣ ያቺኛዋ ደግሞ ያንተ እናት ናት" ይሉናል። ከዚያም "ማነው የማንን እናት የሚረግጠው?" ሲሉ፣ አንዱ ቀድሞ የሌላኛውን "እናት" (በትፋት የራሰውን አፈር) ከረገጠ ድብድቡ ይጀመራል። የተተፋበትን አፈር የረገጠውን ልጅ ዝም ማለት፣ እናትን አስረግጦ ዝም እንደማለት ነበር የሚቆጠረው። የውርደት፣ የሽንፈት ስሜት አለው። በልጅነት ዐሳባችን የእናታችንን ትዕምርታዊ መገለጫ ማስደፈር እናታችንን ከማስደፈር ዕኩል ስለሚሰማን ወትሮ ከማንደፍረው ሰው ጋር ሳይቀር እንጋጫለን።

የባንዲራ ትዕምርትም እንደዚሁ ነው። ሰንደቅ ዓላማ የአገርና የአገራዊ ፖለቲካ አስተሳሰብ ትዕምርት (‘ሲምቦል’) ነው። ሁለት አገራት ወደጠብ ሲገቡ በሕዝባዊ ተቃውሞ ሰልፎች ላይ ባንዲራ ማቃጠል፣ በፊት በፊት ፋሽን ነበር። አሁንም ድረስ ባንዲራ የማቃጠል ተቃውሞ አለ።

የባንዲራ ትዕምርታዊነት ሰፊ በመሆኑ ቬክሲሎሎጂ የሚል የጥናት ዘርፍ ተቋቁሞለታል። በባንዲራ መከባበርም፣ መናናቅም ይገለጻል። ሕዝባዊ ሐዘን ይገለጽበታል። ደስታ ይበሰርበታል። የአገር ፍቅር ልክ ይመዘንበታል።

“ከብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን” ባሻገር!

አቶ መለስ "ባንዲራ ጨርቅ ነው” ብለው ሲናገሩ የሳቱት ጉዳይ ይህንን ትዕምርታዊ ውክልናውን ነው። በርግጥ ይህንን አሉ በተባለበት ወቅት አገሪቱ ከአንድ ይፋዊ ሰንደቅ ዓላማ ወደ በርካታ ባንዲራዎች እየተሸጋገረች ስለነበር፣ "ባንዲራ ጨርቅ" ብቻ ከሆነ ያንን ሁሉ ለውጥ ለምን ማድረግ እንዳስፈለጋቸው መጠየቅ ነበረባቸው። አቶ መለስ ይህንን ብዙ ሕዝብ የሚያስከፋ ‘የአፍ ወለምታ’ የባንዲራ ቀን እንዲከበር በማድረግ ነው ለማረም የሞከሩት። የመጀመሪያውን ክብረ በዓልም ራሳቸው ባንዲራ እየሰቀሉ ነው ያስጀመሩት። ነገር ግን ንግግራቸው እስከዛሬም በአሉታዊ ሚና ይጠቀስባቸዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ - ባንዲራ በኢትዮጵያ፣ በፊት በፊት የአንድነት መገለጫ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ማንፀባረቂያ (ማኒፌስቶ) ሆኗል። በኢትዮጵያውያን የሚውለበለቡት የባንዲራዎች ብዛት የፖለቲካ አመለካከታችንን ያክላል። ልሙጡ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ እንዲሁም ባለኮከቡ። አልፎ አልፎ ባለ ‘ሞኣ አንበሳውም’ አለ። የገዳው ጥቁር፣ ቀይና ነጭ፣ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልሉ ጥቁር፣ ነጭና እና ቀይ (መሐሉ ላይ ዛፍ)። የኦነጉም ባንዲራ አለ። እነዚህ አነታራኪዎቹ ናቸው።

በኢትዮጵያ በ2003 የተሻሻለው የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ከወጣ ወዲህ (ሌሎቹ ባይጠቀሱም) ቢያንስ ‘ኮከብ የሌለውን’ ባንዲራ ማውለብለብ ተከልክሏል (ለብሶ መታየትን ግን የሚከለክል ሕግ አላየሁም። ቢሆንም አገር ውስጥ ከላይ የጠቀስኳቸውን ባንዲራዎች ይዞ ወይም ለብሶ መገኘት ለቅጣት ወይም እንግልት ይዳርጋል።) ነገር ግን በዳያስፖራ  የተቃውሞ ሰልፎች ላይ እንደየሰልፉ ዓይነት - በተለይ ሁለቱ (‘የኦነግ’ የሚባለውና ልሙጡ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ) ባንዲራዎች የማይቀሩ ናቸው። አሁን አሁን፣ በተለይ የኦሮሚያና የአማራ ክልል መንግሥታት ከሕወሓት ጋር ትከሻ መለካካት ጀምረዋል ከተባለ በኋላ ሕዝባዊ ሠልፎች ላይ ሕጋዊ ዕውቅና የሌላቸውን ባንዲራዎችን ማውለብለብ እዚህም ተለምዷል።

እንደምን በአንድ ባንዲራ እንኳ መስማማት ተሳነን?

Friday, October 6, 2017

የአማራ ብሔርተኝነት እንቆቅልሽ (የመቋጫ መጣጥፍ)

"የአማራ ሥነ ልቦና" በሚል ርዕስ ቀደም ሲል የጻፍከት አጭር የእንግሊዝኛ መጣጥፍ ብዙ ጥያቄዎችን አጭሯል። የጽሑፉ ዋነኛ ዓላማ ስለአማርኛ ቋንቋ ዕድሜ፣ ወይም ስለአማራ ሕዝብ ኅልውና ባይሆንም፣ ብዙዎቹ አንባቢዎች ግን የተረዱት በዚያ መንገድ ነበር። ወሳኙ ቁም ነገር እኔ የጻፍኩበት ዓላማ ሳይሆን አንባቢ ጋር ሲደርስ የሰጠው ስሜት ስለሆነ ይህንን ጽሑፍ አስከትያለሁ።

በመሠረቱ፣ ከዚህ በፊት በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደገለጽኩት፣ እኔ የምፈልገው ዘውግ-ዘለል የዜግነት ብሔርተኝነት (civic nationalism) ነው፡፡ ይህን ስል ግን የዘውግ ብሔርተኝነትን እና በዘውግ መደራጀትን እቃወማለሁ ማለቴ አይደለም፤ በዘውግ ላይ የተመሠረቱ ጥያቄዎች እስካሉ ድረስ ያንን በመከልከል ማስቆም ይቻላል ብዬ አላምንም፡፡ ነገር ግን የተለያዩ የዘውግ ቡድኖችን እና ፍላጎቶቻቸውን አቻችሎ በአንድ ለማኖር የዜግነት ብሔርተኝነት ማበበ አለበት ባይ ነኝ፡፡ ይሁን እንጂ ብዙዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች በዘውግ ስለተዋቀሩ እና የመንግሥታዊ አደረጃጀቱም ይህንን (ለዜግነት መብቶች በርዕዮተዓለም መደራጀት) ምቹ ሁኔታ ስላልፈጠረለት አገሪቷ የፉክክር ቤት ሆናለች። ስለሆነም፣ ይሔ እና መሰል ጽሑፎች፣ በአገራችን የተንሰራፋው በአሁኑ ወቅት የበለጠ ተቀባይነት ያለው የዘውግ ብሔርተኝነቱ አካሔድ ቢያንስ ወደፊት ወደ ዜግነት ብሔርተኝነትን እንዲያድርግ የማደርገው ጥረት አካል እንደሆነ ይታወቅልኝ።

አሁንም ከዚህ በፊት "የተጣመመ የብሔርተኝነት ቅርንጫፍ" በሚል የኦሮሞ ብሔርተኝነት አራማጆች ላይ አስተዋልኩት ብዬ የጠቃቀስኩት የጠራ ዘር እና የዘር ሐረግ በመቁጠር ላይ የተመሠረተ ብሔርተኝነት አዝማሚያ “ገና አፍላ ነው” በሚባለው የአማራ ብሔርተኝነት ላይም በጉልህ ያስተዋልኩ መሆኑ የጽሑፌ ዋና መነሻ ነው፡፡ የጠራ ዘር ፍለጋ እና የዘር ቆጠራ ፍልስፍና፣ ዘውግ ወይም ብሔርተኝነት ማኅበራዊ ሥሪት መሆኑን ክዶ በደም የሚወረስ ከማስመሰሉም በተጨማሪ፣ መሠረታዊ መብቶችን ለመጣስ ሰበብ ሆኖ ሊመጣ ይችላል።

ዶ/ር አድማሱ ከበደ ‹የአማራ ብሔርተኝነት ከተለመደው የብሔርተኝነት ንቅናቄ የተለየ መንስዔ ይዞ ነው የተነሳው› በማለት ሲተነትኑ፣ ‹ከአማራ ብሔራዊ መነቃቃት አስቀድመው ብሔራዊ መነቃቃት ያገኙት ሌሎች የኢትዮጵያ የዘውግ ቡድኖች እንደሌላ ስለቆጠሩት (othering) የተፈጠረ ብሔርተኝነት ነው› ብለው ጽፈዋል::

በዚህ ግንዛቤ በታሪክ አማራ ማነው? አማርኛስ የማነው? እና የአማርኛ የዝግታ ዕድገት ዛሬ አማራ ስለምንለው ሕዝብ ‹ሌላነት› የሚነግረን ነገር አለ? የሚሉትን እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በማንሳትና መልስ በመፈለግ የአማራ ብሔራዊ (የዘውግ ማንነት) መሠረቶች ምንነት ላይ መላምት አሳልፋለሁ። ይህም የአማራ ብሔርተኝነት ከዜግነት ብሔርተኝነት ጋር በመርሕ የማይጋጭ እንዲሆን በሚደረገው ጥረት ውስጥ የውይይት ዕድል በመስጠት አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት እምነት አለኝ።

Sunday, September 17, 2017

የአራማጅነት ሀሁ…

‘አክቲቪዝም’ በአማርኛ ቁርጥ ትርጉም አልተገኘለትም። እንዲሁ በየዐውዱ "የለውጥ አራማጅነት"፣ "የመብቶች አቀንቃኝነት"፣ ወዘተ… ነው የሚባለው። የእንግሊዝኛ ቃሉን ግርድፍ ትርጉም ከወሰድን "ንቁ ተሳታፊ" ከሚለው የሰፋ ትርጉም የለውም። በኢትዮጵያ ቃሉ በተደጋጋሚ መደመጥ የጀመረውና ራሳቸውን ‘አክቲቪስት’ ብለው የሚጠሩ ሰዎች የተከሰቱት ከማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ማደግ ጋር ተያይዞ ነው። በተለምዶ፣ ቃሉ በጥቅሉ ፖለቲካዊ ተሳትፎ የሚያደርጉ እና የሚወክሉት ድርጅት የሌላቸውን ግለሰቦች በሙሉ ለመግለጽ እየዋለ ነው። እዚህ ጽሑፍ ላይ የምጠቀምበት ገላጭ ሆኖ ያገኘሁትን "አራማጅነት" የሚለውን ቃል ነው።

አራማጅነት ምንድን ነው? 

አራማጅነት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና/ወይም አካባቢያዊ ለውጦችን ለማምጣት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው። አራማጅነት የአጭር ግዜ ፕሮጀክት ወይም ዘላቂ ንቅናቄ ሊሆን ይችላል። አንድ ጉዳይ ላይ ብቻ ያተኮረ ወይም ብዙ ጉዳዮችን ያቀፈም ሊሆን ይችላል። አራማጅነት በብዙኃኑ ተቀባይነት ያለውን አንድ ጉዳይ በመንግሥት ተቀባይነት እንዲያገኝ፤ ወይም በመንግሥት ዕውቅና ያለውን ጉዳይ በብዙኃኑም ተቀባይነት እንዲያገኝ፤ ወይም በብዙኃኑም፣ በመንግሥትም ተቀባይነት እና ዕውቅና የሌለውን ጉዳይ በሁለቱም ተቀባይነት እና ዕውቅና እንዲያገኝ ለማድረግ ሊሆን ይችላል። አራማጅነት በብዛት ከተገለሉ ሕዳጣን ወይም ከተጨቆኑ ብዙኃን መሐል በወጡ አራማጆች የሚደረግ የመብት/የጥበቃ ንቅናቄ ነው።

የአራማጅነት ስኬት እንደመነሻው ነው የሚለካው። አንዳንዴ የተነሳውን ሐሳብ የተደራጁ ሲቪል ማኅበረሰቦች ወይም የፖለቲካ ማኅበሮች አጀንዳዬ ብለው ሲይዙት ከአራማጆች እጅ ሊወጣ ይችላል። ሌላ ግዜ ደግሞ የተጠየቀውን መብት/ጥበቃ የሚያጎናፅፍ አዋጅ ሲወጣ ሊቆም ይችላል። አንዳንዴ ደግሞ የወጣው አዋጅ እና መመሪያ አፈፃፀምን እየተከታተለ፣ የተፈለገው ማኅበራዊ የግንዛቤ ለውጥ እስኪመጣ ሊቀጥል ይችላል። እንዲሁም ቀድሞ የወጣ አዋጅ ወይም የተዘረጋ ስርዓት እስኪሻር ወይም በሌላ እስኪተካ የሚደረግ አራማጅነትም አለ። በተግባር ደረጃ የማድረግ ወይም ያለማድረግ (ሌሎችንም እንዲያደርግ ወይም እንፋያደርጉ የማግባበት) ንቅናቄ ነው።

አራማጅነት የዓለማችን ዘመናዊ ባሕል ሆኗል ማለት ይቻላል። ቃሉ በዚህ ፖለቲካዊ ይዘቱ ከተመዘገበ የመቶ ዓመት ያክል ዕድሜ ይሆነዋል። ከጊዜ ግዜ እያደገ መጥቶ ዛሬ የበይነመረብ (ኢንተርኔት) ዘመን ላይ የእያንዳንዱን ጓዳ የሚያንኳኳበት ዕድል አግኝቷል።

አራማጆች ለጋዜጦች በመጻፍ፣ በራሪ ወረቀቶችን በመበተን፣ ፊርማዎችን በማሰባሰብ፣ የአዳራሽ ስብሰባዎችን እና ንግግሮችን በማካሔድ፣ በኪነ (ሥነ) ጥበብ ሥራዎች በመግለጽ፣ ብዙኃንን ያሳተፈ የእግር መንገድ ዘመቻ በማድረግ፣ ለቀናት ያክል ድንኳን በመደኮን፣ በሰላማዊ ሰልፎች፣ በአድማዎች፣ በማዕቀቦች፣ ያልተፈለገውን ተግባር (ወይም ሌላ አትኩሮትን የሚስብ) የለት ተለት ተግባርን በማስተጓጎል፣ ወዘተ… የሚዲያ፣ የኢኮኖሚ፣ የባሕል፣ የፖለቲካ፣ የአካባቢያዊ እና ሌሎችም ተፅዕኖዎችን በመፍጠር ጉዳዩ መጀመሪያ ትኩረት እንዲስብ፣ ቀጥሎ ወደ ተግባራዊ ለውጥ ጉዞ እንዲጀመር የሚያስገድዱ ንቅናቄዎችን ይፈጥራሉ።

የኢትዮጵያውያን አራማጆች የተለመዱ ስህተቶች

በአገራችን አራማጅነት ከሆነው ይልቅ ያልሆነው ነው እንደአራማጅነት የሚቆጠረው ማለት ይቻላል። ለዚህ ምክንያት ሊሆን የሚችሉት የዳበረ የፖለቲካ ባሕል አለመኖሩ፣ የሲቪል ማኅበራት ቁጥር እና ተዳራሽነት ውሱን መሆኑ፣ የሐሳብ ነጻነት አለመከበሩ እና የመሳሰሉት ናቸው። የሚከተሉት ነጥቦች ዋና ዋናዎቹን ችግሮች ነቅሰው ያወጣሉ ብዬ እገምታለሁ።