(በፍቃዱ ኃይሉ)
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዐቢይ አሕመድ እርካብና መንበር በአባዱላ ገመዳ የተቀየሰ ይመስለኝ ጀምሯል። ምክንያት አለኝ። አባዱላ በተቀናቃኞቹ ጃዋር መሐመድም፣ ዐቢይ አሕመድም አድናቆት የተቸራቸው ሰው ናቸው።
ጃዋር መሐመድ፣ 'አልፀፀትም' በሚለው መጽሐፉ በጣም ጥቂት ሰዎችን ነው በአዎንታዊ ያነሳው። ከነዚህ ሰዎች መካከል አባዱላ ገመዳ አንዱ ናቸው። በዚህ መጽሐፉ ላይ ጃዋር እንደሚለው፣ አባ ዱላ "ኦሮሚያን ከጫፍ እስከ ጫፍ ስለሚያውቃት ስለመጣችሁበት ወረዳ ጉዳይ ቦታዎችን እና ሰዎችን በስም እየጠራ ያዋራችኋል። ይህ ሁኔታው ለሰውዬው ፖለቲካ ያላችሁን ጥላቻ ለጊዜውም ቢሆን ረስታችሁ እንድታዳምጡት ይጋብዛል። አሜሪካ ሳለሁ የሰላማዊ ትግል ስልቶችን ለመቀየሰ የአገዛዙን የውስጥ አሠራር እና አመለካከት ለመረዳት ከፍተኛ ጉጉት ስለነበረኝ ከአባዱላ እና ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር ያዳበርኩት ግንኙነት ጠቅሞኛል" ብሏል። ጃዋር ከመንግሥት ለውጡ አስቀድሞ ክፍተቱን ለመሙላት የሚችል ፓርቲ እንዲያቋቁም አባ ዱላ ምክር ለግሰውት እንደነበርም ጽፏል። እሱም በበኩሉ ከኦሕዴድ መኮንኖች ጋር ሲነጋገር "ለውጡን ቢመሩ" ብሎ ከጠቆማቸው ሰዎች አንዱ አባዱላ ገመዳ ነበሩ። እርሳቸው ላይ የነበረው ብቸኛው ቅሬታ ፖለቲካው ውስጥ የቆዩ በመሆናቸው እንደ ለውጥ መሪ አይወሰዱም የሚለው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም የአባዱላን ሥም 'የመደመር መንገድ' በሚለው መጽሐፋቸው በአዎንታዊ መልኩ አንስተውታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ መጽሐፍ ለውጡ እንዴት እንደመጣ ያትታሉ። ሆኖም እኛ የምናውቀውን "ቲም ለማ" ጭራሹኑ አይጠቅሱትም። ይልቁንስ "መጋቢታውያን" እያሉ በሚጠሯቸው፣ በእርሳቸው እና ደመቀ መኮንን ተጠንስሶ ስለተከናወነው ለውጥ ይተርካሉ። እዚህ መጽሐፍ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአባዱላ ገመዳ “የተለየ ቅርበትና ወዳጅነት” እንደነበራቸው ጽፈዋል። ሌላው ቀርቶ ጄነራል ከማል ገልቹ እና ኮሎኔል አበበ ገረሱ ሠራዊቱን ከድተው የኤርትራ አማፂያንን ሊቀላቀሉ ሲሄዱ እንዳነጋገሯቸውና፣ አባዱላና እሳቸው በችግሩ ቢግባቡም የትግል ስልቱ ከውስጥ መሆን አለበት ብለው እንደወሰኑ በመጥቀስ ፈረንጆቹ እንደሚሉት “partners in crime” (ለወንጀል የሚተማመኑ ወዳጆች) እንደነበሩ ፍንጭ ይሰጡናል።
ዛሬ የብልፅግና ቁንጮ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች ወይ ኦሮሞ አልያም ፕሮቴስታንት ናቸው። ስለዚህ ሁኔታ ከአንድ እጅግ ተፅዕኖ ፈጣሪ የኦሮሞ ፖለቲከኛ ጋር ስናወራ የነገረኝም ነገር በዚህም የአባዱላን ተፅዕኖ ሊኖር እንደሚችል ይጠቁማል። 'አባዱላ፣ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ከኢስላሚስት ንቅናቄ ጋር እየተጋባ ሲቸግራቸው፥ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ከኦርቶዶክስ ክርስትና ጋር ተኳርፏል፣ ከኢስላሚስቶች ጋር መወዳጀቱ ደግሞ ዓለም ዐቀፍ ቅቡልነት ይነሳዋል፣ ስለዚህ ፕሮቴስታንት ኦሮሞዎች ቢመሩት ይሻላል ብለው በማሰብ እነ ዐቢይ አሕመድን ወደ ፊት አመጧቸው' ብሎኛል።
ተርዬ ኧስተበ (Terje Østebø) ባለፈው ግንቦት ባሳተመው ጥናታዊ ጽሑፉ ላይ ይህንን የሚያጠናክር ሐተታ "አባዱላ... ብዙ ክርስቲያኖችን ወደፊት በማምጣት በምዕራባውያን ዘንድ የኦሮሞ ፖለቲካ ልኂቃኖች የሙስሊሞች የበላይነት አለበት የሚለውን ገጽታ ለማስተካከል ሞክረዋል" በማለት ጽፏል። አባዱላ ወደ ፊት ካመጧቸው ፕሮቴስታንቶች ውስጥ ለማ መገርሳ፣ ሽመልስ አብዲሳ፣ አዳነች አቤቤንና ራሳቸው ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ብዙዎቹ ፕሮቴስታንቶች ነበሩ ይላሉ ተመራማሪው። አባዱላም እኤአ በ2009 ከኦርቶዶክስ ወደ ፕሮቴስታንት መቀየራቸውን ጥናቱ ይጠቅሳል።
ፋክት መጽሔት ላይ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከለውጡ ዓመታት በፊት ዐቢይ አሕመድ የማዕከላዊ ኮሚቴን ተቀላቅለው የአባዱላን ውለታ ለመመለስ እየሠሩ ነው በሚል በጨረፍታ ይጠቅሳቸዋል። በወቅቱ የጋዜጠኛው ግምት አባዱላ በኢሕአዴግ የውስጥ ለውስጥ ሽኩቻ ዐቢይን እየተጠቀሙበት እንደሆነ ነበር። ሆኖም፣ እርሳቸው ዐቢይን ወደ ፊት እያመጡ፣ ወይም ዐቢይ ለራሳቸው መንገድ እየጠረጉ፣ ወይም እርስ በርስ እየተናበቡ እየሠሩ ይሁን አይሁን ለማረጋገጥ ይከብደናል። ነገር ግን በውጤቱ ስንመዝነው፣ በአንድም በሌላም መልኩ አባዱላ ለዐቢይ አሕመድ እርካቡ ነበሩ ማለት የምንችል ይመስለኛል።
ቶም ጋርድነር፣ 'The Abiy Project' በሚል ባሳተመው መጽሐፉ "Were it not for Abadula’s blessing, Abiy may well have found it impossible to overcome his lack of both academic and formal military qualifications in his quest for power" ሲል ጽፏል፤ "በአባዱላ ቡራኬ ባይሆን ኖሮ፣ ዐቢይ የትምህርትና ወታደራዊ ልምድ ስለሚያንሳቸው ወደ ሥልጣን የሚያደርጉት ጉዞ ፈፅሞ አይሳካም ነበር" እንደማለት። እንደ ጋርድነር ከሆነ፣ በአንድ ወቅት አባዱላ እና ዐቢይ የአባትና ልጅ ያህል ቅርርብ ነበራቸው፤ አባዱላ የትም ቢሔዱ ዐቢይ አብረዋቸው ይሔዱ ነበር።
ለመሆኑ አባዱላ ገመዳ ማን ናቸው?
አባዱላ ገመዳ ከሰላሌ ወደ አርሲ የሔዱ፣ ከኦርቶዶክስ ኦሮሞ ቤተሰቦች የተወለዱ ሰው ናቸው። ወደ ፖለቲካ የገቡት በልጅነታቸው ነው። በደርግ መንግሥት የኢትዮጵያ ሠራዊት አባልነት፣ ሻዕቢያን ለመውጋት ወደ ኤርትራ ከዘመቱ አንድ ዓመት በኋላ ተማርከው በሻዕቢያ እስር ቤት አምስት ዓመት አሳልፈዋል። ሻዕቢያ ምርጫ እየሰጠ የምርኮ እስረኞቹን ሲፈታ የእርሳቸው ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን) ሆነ፤ ይህኔ ገና 26 ዓመታቸው ነው። ከ1976 እስከ 1982 ከኢሕዴን ጋር ደርግን ሲዋጉ ከርመው፣ ከሕወሓት ጋር በተደረገ ምክክር ከሌሎች ጓዶቻቸው ጋር ኦሕዴድን መሥርተዋል። ኦሕዴድ የኢሕአዴግ አባል ሆኖ በሽግግር መንግሥቱ እና በኦሮሚያ ምሥረታ እና አስተዳደር ለሁለት ዐሥርት ዓመታት ዘልቋል። ("60 ዓመታት" በአባዱላ ገመዳ)
አባዱላ አብዛኛውን የትግል ጊዜያቸውን ያሳለፉት በጎንደር እና ትግራይ ነው። ኦሕዴድም የተመሠረተው ትግራይ ነው። በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የቅቡልነት ችግር የነበረበት ፓርቲ ነበር። በኢሕአዴግ ውስጥ የነበረውም ሚና ኦነግን መቀናቀን ስለነበር፣ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ የገጽታ ችግር ነበረበት። በተጨማሪም ኦሕዴድ በኢሕአዴግ ውስጥ ከሕወሓት እና ብአዴን ያነሰ ጉልበተኛ ነበር፤ መከላከያ ውስጥ የሚበዙት የሕወሓት እና ብአዴን የቀድሞ ተዋጊዎች ነበሩ። ኦሕዴድን በግንባሩ ውስጥ ወደ ላይ በማምጣት ረገድ የአባዱላ ተጋድሎ ቀላል አይመስልም።
አባዱላ ከኦሕዴድ አባልነት፣ ወደ መከላከያ፣ ከዚያም ወደ ሲቪል ኦሕዴድነት ሲገላበጡ ነው የከረሙት። ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት መልስ፣ ሕወሓት ሲከፋፈል እሳቸው ወደ ሲቪል ኃላፊነት ተመልሰው የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል። ራሳቸው በመጽሐፋቸው እንደተረኩት የመከላከያ ሚኒስትርነት ሹመታቸውን ያወቁት ቃለ መሐላ የፈፀሙ ዕለት ጠዋት ነው። ከዚያ በኋላም በምርጫ 97 ተወዳድረው በተቃዋሚዎች ተሸንፈዋል። ያ ሁሉ አልፎ የኦሮሚያ ፕሬዚደንት ሆነው በመሾም አገልግለዋል። የአባዱላ ፕሬዚደንትነት በኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ ጨዋታ ቀያሪ (game changer) ነበር ማለት ይቻላል።
ፕሬዚደንት አባዱላ
ጃዋር መሐመድ በመጽሐፉ "አባዱላ የኦሮሚያ ፕሬዝዳንት በነበረበት ወቅት የሕወሓት ጣልቃ ገብነትን በመቀነስ፣ ድሮ ጠባብ እየተባሉ ሲገለሉ የነበሩ ወጣቶችን ወደ መንግሥት በማስገባት፣ የክልሉን አስተዳደራዊ ሥራ በማሳለጥ ልማቱን ማፋጠን ችሎ ነበር" ብሎ ጽፏል።
በርግጥም በፕሬዚደንትነት ዘመናቸው ኦሮሚያን ከሕወሓት የበላይነት ለማላቀቅ እንዲሁም የኦሮሞ ባለሀብቶችን ለመፍጠር ብዙ ጥረዋል። አንዱ ምሳሌ የኦሮሚያ ቴሌቪዥንን በተመለከተ እንዲዘጋ ሲጠየቁ ሰጠሁት ያሉት ምላሽ ነው። በዚህ ምላሻቸው “ተልዕኮዬ የኦሮሞን ሕዝብ ከተገዥነት አስተሳሰብ አላቆ እሱን መግዛት እና ማስተዳደር የሚችል የአገር ባለቤት መሆኑን እንዲገነዘብ የሚረዳ የሚዲያ ተቋም መገንባት” ነው የሚል ነበር። በዚህ ጥረታቸው ታዲያ “የኦሮሚያ ቴሌቪዥንን ለማቋቋም ከፍተኛ ሙያዊ” ድጋፍና ጥረት ያደረጉት ዐቢይ አሕመድና ሽመልስ ክንዴ የተባሉ ሰው ናቸው ይሉናል፤ መጽሐፋቸው ላይ ከምስጋና ጋር።
የአባዱላ ክኅሎት ከሰው ጋር መግባባት ነው። ሰፊ ቤተሰብ ያላቸው እና ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች (ከኦሮሚያ ውጪ ጭምር) የተለያዩ ልጆችን አምጥተው አሳድገው ለቁም ነገር አብቅተዋል። ‘ዳውን ሲንድረም’ ያለባትን ልጃቸው ዲቦራን ታሪክ መጽሐፍ ጽፈውበት ማስተማሪያ አድርገውታል። በጡረታ ዘመናቸው ዲቦራ ፋውንዴሽን የሚባል አቋቁመውም ግንዛቤ ለማስጨበጥ እየሠሩ ነው። በወጣትነታቸው አፍቅረዋት ከአረገዘች በኋላ የተጠፋፉትን ሴት ጉዳይ በመጽሐፋቸው ይጠቅሳሉ። በኋላ ደረጄ ኃይሌ በሠራው ፕሮግራም፣ ከልጃቸው ጋር መገናኘታቸውንና ወለም ዘለም ሳይሉ መቀበላቸውን አይተናል። የአመራር ዘዴያቸውም ከዚህ የቤተሰብ ሰውነታቸው የተቀዳ ይመስላል። በፕሬዚደንትነት ዘመናቸው በኦሮሚያ እየዞሩ ከኅብረተሰብ በመነጋገር የነዋሪዎችን ፍላጎት ይጠይቁ እንደነበር ጽፈዋል። እንዲያውም፣ “አንዳንድ አመራሮች ምን ያዞረዋል? መቼ ቁጭ ብሎ ሥራ ይሠራል? እያሉ በትዝብት ያዩኝ ነበር” ብለዋል።
የአባዱላ ሥም በተነሳ ቁጥር የሚነሳው ጉድፍ የሙስና ጉዳይ ነው። ኤርምያስ ለገሰ “ባለቤት አልባ ከተማ” በሚል ርዕስ በ2006 ባሳተመው መጽሐፉ አባዱላ ገመዳን በሙሰኝነት ደጋግሞ ከሷቸዋል። እሱ እንደሚለው፣ ሙሰኝነት በፓርቲያቸው ሳይቀር የተወቀሱበት ነው። እንዲያውም አምስት ሚሊዮን ብር አውጥተው የገነቡትን የቅንጦት ቤት በግምገማ ለኦሕዴድ በስጦታ እንዲያበረክቱ ተገድደዋል ይላል። እርሳቸው ግን በቀጥታ ይህንን ባይጠቅሱም፣ በፕሬዚደንትነት ዘመናቸው አራት ዓይነት ጦርነት ኦሕዴድ ላይ ተከፍቶ ነበር ይላሉ። “ሁለተኛው [ጦርነት] የድርጅቱና የክልሉ አመራር ተረጋግቶ ሥራውን እንዳይሠራ በየእለቱ የሚፈበረክና በውሸት በተዘጋጀ ዶክሜንት ጭምር አመራሩ ይህንን ያህል ገንዘብ ተቀብሏል ከሚል አንስቶ በክልሉ አድሎ ይካሔዳል የሚል ከየትኛውም ጊዜ በላይ የኢሕአዴግ የሥራ አስፈፃሚ የግምገማ አጀንዳ ሆኖ የቀጠለበት ነበር” ብለዋል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ በኦሮሚያ ሲንቀሳቀሱ ሕዝቡ ባሕላዊ ልብሶች፣ ፈረስና በቅሎ፣ ሀብል እንደሚሸልማቸው ገልጸው፣ “ፈረስና በቅሎ እዚያው ይቀራሉ። ብዙ ጊዜ ባሕላዊ ልብሶችና ሀብልና ቀለበትንም አካባቢዬ ላሉት እሰጣለሁ። በመጨረሻ ግን እንድትመልስ የሚል መመሪያ ደረሰኝ። በእጄ የቀረውን ሰብስቤ አስረከብኩ” ብለው ጽፈዋል። የኤርምያስ ለገሠ ተረክና ይኼ ይገናኝ አይገናኝ ግን እንጃ።
አባዱላ የኦሮሞ ባለሀብቶችን መሬት በማደል ለማበልፀግ መሞከራቸውም ተደጋግሞ ይነገራል። መነሻቸው የኦሮሞ ሕዝብ በገዛ ክልሉ የሀብት ባለቤት አይደለም እና መሆን ይገባዋል የሚል ነበር። የመሬት ነገር ሲነሳ፣ አባዱላ በኦሮሚያ ፕሬዚደንትነታቸው ዘመን፣ ቢሯቸው ደብዳቤ ሲገባ ‘መሬቱ ይሰጠው’ ብለው ፈርመዋል እየተባለ ይቀለድ እንደነበር የቀድሞው የኦሕዴድ አባል ኤርምያስ ለገሠ አውስቷል።
የሆነው ሆኖ፣ የኦሮሚያ ቢሮክራሲ በኢሕአዴግ ጊዜ፣ በተለይም በርሳቸው የአስተዳደር ዘመን ከፍተኛ ሙሰኝነት ተንሰራፍቶበት እንደነበር የአደባባይ ምሥጢር ነው።
የአባዱላ ተፅዕኖ በዐቢይ አሕመድ
ይህንን ጽሑፍ እንድጽፍ የቀሰቀሰኝ ሰሞኑን የሶፍ ዑመር ዋሻን የማስዋብ እና ተደራሽ የማድረግ ሥራ ተሠርቶ ሲመረቅ ከተገኙ እንግዶች መካከል ጡረተኛው አባዱላ አንዱ ነበሩ። አባዱላ የሕይወት ታሪካቸውን በጻፉበት መጽሐፍ ላይ እንደባሌ ትልቅ ሽፋን የሰጡት አካባቢ የለም። ከአካባቢው ሕዝብ ጋር ያላቸው ስሜታዊ ቁርኝት ሥር የሰደደ ይመስላል። የሚገርመው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ልክ አባዱላ በመጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ ስለ ባሌ ሕዝብ ታላቅነት እና ስለመሠረተ ልማት ጥማቱ ጥቅምት 18 ፓርላማ ቀርበው ጥያቄ ሲመልሱ ጊዜ ወስደው ተንትነዋል። አባዱላ መጽሐፋቸው ላይ የጻፉት ሐተታ እና ዐቢይ በፓርላማ የተናገሩት በጣም ተመሳሰሉብኝ።
ሌላም ልጥቀስ። “[የሚገርመው] ከአየር ማረፊያ ተነስቶ ዋና ከተማዋን ከዳር እስከ ዳር የሚያቋርጠው መንገድ ያለቀበት ፍጥነት ሲሆን፥ ሌላ ቦታ የበቀሉ ትላልቅ ዋርካ የሚያካክሉ ዛፎች ተነቅለውና ተጭነው መጥተው በክሬን ወርደው ሲተከሉ መንገዱን ከዓመታት በፊት የተሠራ በማስመሰል ተጨማሪ ውበት የሚሰጡበት ሁኔታ በርግጥም አስደናቂ ነበር” የሚል ጽሑፍ ብታነቡ ማን ስለማን የሚያወራ ይመስላችኋል? አባዱላ በ2011 ባሳተሙት መጽሐፋቸው ላይ፣ የቻይና የመጀመሪያ ጉዟቸው ላይ ስላዩት ለውጥ የጻፉት ቃል በቃል ተገልብጦ ነው። ነገርዬው ዛሬ ዐቢይ አሕመድ “ይመሩታል” በሚባለው የኮሪደር ልማት፣ ትላልቅ ዛፎች ከሌላ ቦታ ተነቅለው መጥተው የሚተከሉበትን ሁኔታ ያስታውሳል። እናም ይኼን ነገር አባዱላ ሹክ ብለዋቸው ይሆን አስብሎኛል?
የመንግሥት ለውጡ ዋዜማ ላይ አባዱላ ነገሩን አቀላጥፈዋል ይባላል። ከአንጋፋ አመራሮች መካከል ለአፍታም ቢሆን ያፈነገጡት እርሳቸው ብቻ ነበሩ። በወቅቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ነበሩ። ከዚያ አስቀድሞ ግን በሚያዝያ ወር 2006 የመጀመሪያው የቄሮ ተቃውሞ ሲጀመር መሠረቱ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ነበር። የተቃውሞው መሪዎችም የቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞ አባላት ነበሩ። ያኔ ተቃውሞው ሕዝቡ ዘንድ ዘልቆ አልገባም ነበር። ቄሮ የሚለው ቃልም ኦሮሞ ባልሆኑ ሰዎች ዘንድ ከናካቴው አይታወቅም ማለት ይቻላል። ታዲያ መንግሥት አደራጆቹን ለቃቅሞ ሲያሥር (ሐሮማያ ቦንብ አፈንድተዋል ከተባሉት ውጪ) ወጣቶቹን ያለምንም ክስ ከማዕከላዊ እንዲሰናበቱ ያደረጓቸው አባዱላ ነበሩ።
አባዱላ ይህንን መጽሐፋቸው ላይ አይጠቅሱትም፤ ነገር ግን ኦሕዴድ የመጪው ትውልድ ብሎ የመለመላቸውና ያስተማራቸው ወጣቶች ጎርፍ ሆነው መጡ ብለው ጽፈዋል። እርሳቸው እንደሚሉት ከ984/85 ጀምሮ ኦሕዴድ ራሱን ያዘጋጀው “የመጪው ትውልድ ፓርቲ” እሆናለሁ በሚል ነበር። “በ2006 እንቅስቃሴው ሲጀመር፣ ጥቂቶች ተመልሰው መጥተው ጎርፉ ይሄ ነው ወይ?” ብለው ተሳልቀዋል ብለው ጽፈዋል። ሆኖም፣ “በወቅቱ ከተለያየ አካባቢ የሚፈሱ ወንዞችን ወደ አንድ እያሰባሰብን ታላቅ ጎርፍ እየፈጠርን መሆኑ በግልጽ መታየት ጀመረ” በማለት የኦሮሚያ ተቃውሞን ኦሕዴድ እንደደገፈው ፍንጭ ሰጥተዋል።
በመንግሥት ለውጡ ዋዜማ የኦሮሞ ሕዝብ ተናቀ ብለው ከአፈጉባዔነታቸው መልቀቂያ አስገብተው ነበር። ተቃዋሚዎች እርምጃውን አወድሰው ሳይጨርሱ ግን ወደ ሥራቸው ተመልሰዋል። አባዱላ ጡረታ የወጡት በዐቢይ አሕመድ ዘመን ነው። ጡረታ እንደወጡ ለጥቂት ጊዜ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ ነበሩ። አሁንም በኢመደበኛነት የማማከር ሥራ ይሠራሉ ይባላል።
በርግጥም አባዱላ የዐቢይ - መጀመሪያ ወደ ሥልጣን መወጣጫ እርካብ፣ በኋላም ሥልጣን ላይ ተደላድሎ መሰንበቻ መንበር - ጠራጊ ናቸው።
አባዱላ ገመዳ የሕይወት ገድላቸውን የጻፉበት “60 ዓመታት” የተሰኘው ከላይ የጠቃቀስነው መጽሐፍ የመጨረሻ ምዕራፍ “በነፃነት የምኖርበት አገር ይኑረኝ” ይላል። እንደተመኙትም፣ ዛሬ ዛሬ በቦሌ መንገድ ያለ አጃቢ ወክ ሲያደርጉ፣ ከቤተሰባቸው ጋር ሲዝናኑ ይታያሉ። የተመኙት (የሠሩለት ሰምሮ) ኦሕዴድ ኢሕአዴግን አቅልጦ፣ እርሳቸው ወደፊት ባመጧቸው የኦሕዴድ ሰዎች የሚዘወር ብልፅግና ፓርቲን ሠርቷል። ኦሕዴድን ስለሚወዱት መፍረሱ ላያስደስታቸው ይችላል። ነገር ግን የብልፅግና መንግሥት የእርሳቸውን ሕልም ከግብ ያደረሰ ይመስለኛል።
እርሳቸው እንደተመኙት “ኦሮሞ አገር እየመራ ነው።” ይህንን የኦሮሞ ተቃዋሚዎችም የማይክዱት ሐቅ ነው። ጃዋር መሐመድ “ቀጣዩ ትግል” በሚል በጻፈው ረዥም የኦሮምኛ መጣጥፉ ኦሮሞ ሥልጣን መቆናጠጡን አምኖ፣ ችግሩ እንደቀድሞዎቹ መሪዎች አምባገነን በሆነ መንገድ ነው እየመራ ያለው እና ቀጣዩ ትግላችን ለዴሞክራሲ መሆን አለበት ብሏል። በርግጥም ብልፅግና የለየለት አምባገነን ሆኗል። ብዙ የአገሪቱ አካባቢዎችም በብልፅግና ዘመን የማያባራ ለሚመስል ግጭት ተዳርገዋል። አባዱላ “በነፃነት የምኖርበት አገር ይኑረኝ” ያሉት ምኞታቸው ለዘለቄታው እንዲሰምር ያሳደጓቸውን የዛሬይቱ ኢትዮጵያ መሪዎች መምከር ያለባቸው ይመስለኛል። ሁላችንም ነፃ ካልወጣን፣ ማንኛችንም ነፃ አንወጣምና።

 
 
 
ወንድም በፍቃድ እንዲህ ባለው ፁሁፍ ነው እንድትከሰት የምሻው አባድላ የጠቅላዩ የጡት አባት ነው
ReplyDeleteI mean, he is a kingmaker. He recruited Tekale Uma and Addisu Arega, too.
ReplyDeleteአባ ዱጋ ለደም ውሃ ቅርብ ነው በሚለው ብሂላቸው ይታወቃሉ። ኢትዮጵያውያን የተናቀ ያስረግዛል በሚለውም ብሂል ይታወቃሉ በተግባር ግን ብዙ ሰው ለዚህ ትምህርት ተገዢ አይመስለኝም። ስንቱ ጋሻ መሬት ወስዶ ሲፎልልበት አባዱጋን 175 ካሬ ላይ ለአረፈች ጥማድ መሬት በሀሜት ስሙን ሊያጠፊት ሞከሩ። እንከን የለበትም የሚል የለም ግን ደሞ በሚዛን ሲሆን ውሃ ያነሳል። እረጅም እድሜ ለዲቦራ አባት 🙌🙌🙌
ReplyDeleteሁላችንም ነፃ ካልወጣን፣ ማንኛችንም ነፃ አንወጣም።
ReplyDeleteበፍቄ:ጥሩ ትንተና ነው። ግን ግን "አብይ" የእርካብ አባቱ ደፍረው የሰላም አምጣ ምክር ይለግሱት ይሆን? አብይስ የእርካብ አባቱን በእርግጥ ይሰማ ይሆን? በእርግጥ ከዚህ ምስቅልቅል የመውጫ መንገድ አባዱላ የሚጠቁሙት ይመስለኛል። ልብ ከገዛና ከደፈር ሊሰማቸው ይገባል። Thanks for the analysis!
ReplyDeleteእንዲህ ስትጽፍ ነው ደስ የሚለው።
ReplyDelete