Pages

Monday, October 15, 2012

የኛ ኃይል



ዞን ዘጠኝ የተወሰደ


“ፒያሳ፤ መሐሙድጋ ጠብቂኝ” በመሐመድ ሰልማን የተጻፈ እና ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈ ኢ-ልቦለዳዊ መጣጥፎች ስብስብ ነው፡፡ የዛሬ ዓመት ገደማ ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ በተባለ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት  አማካይነትመጽሐፉን የመገምገሚያ ዝግጅት አምስት ኪሎ በሚገኘው ብሔራዊ ሙዚዬም ቀርቦ ነበር፡፡ በውይይቱ መሐል የመጽሐፉ ዝነኝነት ምንጮች ምን ምን ናቸው የሚል ውይይት የነበረ ሲሆን ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ‹‹ደራሲው የአዲስ ነገር ጋዜጣ ጸሐፊ የነበረ›› መሆኑን እና ‹‹ጽሑፎቹም በአዲስ ነገር ጋዜጣ እና ድረገጽ ላይ ወጥተው የነበሩ›› መሆናቸውን ጠቀሰ፡፡ ውይይቱ የአዲስ ነገር ጋዜጣ መታሰቢያ ይመስል፣ የትዝታ ጫወታው ተጧጧፈ እናም ከውይይቱ ተሳታፊዎች አንዱ የሚከተለውን ሲናገር ረዥም ጭብጨባ አዳራሹን አደመቀው ወጣቱ አስተያየት ሰጪ በንግግሩ መሃል የተጠቀመው እና ጢም ብሎ የሞላውን አዳራሽ በጭብጨባ ያናጋው ንግግር የሚከተለው ነበር፡፡

‹‹ይህ ትውልድ በአዲስ ነገር ጋዜጣ የሚደራደር ትውልድ አይደለም፡፡››

ጉዳዩን አስገራሚ የሚደርገው ወጣቱ ይህንን የተናገረው አዲስ ነገር ጋዜጣ መታተም ካቆመች ከሁለት ዓመታት በኋላ መሆኑ ሲሆን፣ አጋጣሚው የጋዜጣዋ መንፈስ በበርካቶች ልብ ውስጥ በትኩስነት መኖሩን የሚናገር ነበር፡፡

ዛሬ፣ ጥቅምት 5/2005 የዓለም የጡመራ የተግባር ቀን (Blog Action Day 2012) “የኛ ኃይል” በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡ የጡመራ የተግባር ቀን በየዓመቱ የሚከበር፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ ጦማሪዎች በሙሉ በአንድ ሐሳብ ዙሪያ የሚጽፉበት ቀን ነው፡፡ የተጀመረው እ.ኤ.አ. በ2007 ሲሆን በተመሳሳይ  ዓመት ‹‹አካባቢ››፣ በ2008 ‹‹ድህነት››፣ በ2009 ‹‹አየር ለውጥ››፣ በ2010 ‹‹ውሃ››፣ በ2011 ‹‹ምግብ›› በሚል ሲካሄድ ዘንድሮ ደግሞ በ2012 ‹‹የእኛ ኃይል›› በሚል እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የዘንድሮው መሪ ቃል፣ ማኅበረሰብ፣ እኩልነት፣ ፀረ-ሙስና እና ነጻነትን በተመለከተ የኛ ኃይል ምን እንደሆነ በመስበክ እንዲከበር ታስቦ የተመረጠ ነው፡፡ አከባበሩ ቀላል ነው፤ አስተባባሪዎቹ እንዳስቀመጡት ‹‹profile someone or a group who inspires you by the way they made a positive influence… (ባመጡት አዎንታዊ ተጽዕኖ ያነቃቃችሁን የሆነ ሰው ወይም ቡድን በመምረጥ ጻፉ…)›› የሚል ነው፡፡

እኛም ጮክ ብለን ስናስብበት እና በጭንቅላታችን ያቃጨለችው አዲስ ነገር ጋዜጣ ብቻ ሆነች፡፡ አዲስ ነገር ጋዜጣ ለሁለት ዓመታት (ከጥቅምት 2000 እስከ ታሕሳስ 2002) ብቻ በስርጭት የቆየች ነገር ግን መራኄ አዘጋጇ መስፍን ነጋሽ የጋዜጣዋን ሁለተኛ ዓመት አስመልክቶ እንደገለፀው ‹‹አጭር ግን ረዥም ዓመት›› የኖረች ያክል የማትረሳ ጋዜጣ ናት፡፡

Tuesday, October 9, 2012

የኃይለማርያም ፲ ተግዳሮቶች

From አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ


የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ኅልፈት ከተሰማ 50 ቀናት ሆኑት፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ቃለ መሓላ ከፈፀሙ ደግሞ 18 ቀናት፡፡ እነዚህ ከሁለት ሳምንታት እምብዛም ያልበለጡ ቀናት የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን አያያዝ ለመገምገም በቂ አይደሉም ነገር ግን ‹‹ያባት ዕዳ ለልጅ›› በሚለው ብሒል መሠረት የመለስን ፈለግ በመከተል እና ባለመከተል መካከል፣ ሊያመጧቸው በሚችሏቸው ለውጦች እና ሕዝብ/አገር ከሚጠብቅባቸው ነገሮች አንፃር የሚጠብቃቸውን ተግዳሮት ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በተለይ ከቪኦኤ የእንግሊዝኛው አገልግሎት ጋር ባደረጉት የ40 ደቂቃ ቃለምልልስ፥ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የተለየ አቋም እንደሌላቸው መታዘብ ይቻላል፡፡ ፓርቲውም ቢሆን የአቶ መለስን ውርስ ለማስቀጠል እንደሚተጋ በተደጋጋሚ ተናግሯል፡፡ በተቃራኒው መለስ የሚባልላቸውን ያህል ውጤታማ እና ፍፁም አልነበሩም፡፡ ለዚህም ምስክሩ ሳይዘጉ የተዉአቸው የሚከተሉት አጀንዳዎች ናቸው፡፡ የአቶ ኃይለማርያም ተግዳሮቶች ሁነው ይቀጥላሉ፡፡