Pages

Sunday, January 29, 2012

አፍንጫ ሲመታ ዓይን አያለቅስም ወይ?

From Addis Ababa, Ethiopia

አንድ የቆየ ቀልድ አስታውሳለሁ፡፡ ኒው ዮርክ ውስጥ አንዲትን ሕፃን ልጅ ውሻ ሲያባርራት ያየ አንድ ሰው ውሻዋን በያዘው አጠገቡ ባገኘው ዱላ መትቶ ይገድልና ልጅቷን ያድናታል፡፡ ይህንን ይመለከት የነበረ አንድ ጋዜጠኛ ወደሰውየው ይቀርብና ‹‹እሺ፤ ጀግናው አሜሪካዊ - እስኪ የልጅቷን ሕይወት እንዴት እንዳተረፍክ ንገረኝ?›› ሰውየው ‹‹ኧረ እኔ አሜሪካዊ አይደለሁም›› አለ፡፡ ‹‹እሺ፤ ጀግናው የኒው ዮርክ ሰው..›› ብሎ ጋዜጠኛው ሊቀጥል ሲል÷ ሰውየው ‹‹ኧረ የኒው ዮርክም ሰው አይደለሁ፤ ለጉብኝት ነው የመጣሁት›› ይለዋል፡፡ ጋዜጠኛው ፈገግ ብሎ ‹‹ታዲያ የምን አገር ሰው ነህ?›› ሲል ይጠይቃል፡፡ ሰውዬው ‹‹የሳውዲ አረቢያ›› ሲል ይመልሳል፡፡ በማግስቱ የኒው ዮርክ ጋዜጦች ‹‹አንድ አክራሪ ኢስላሚስት በኒውዮርክ ከተማ ውስጥ ውሻ ቀጥቅጦ ገደለ›› የሚል ዜና ይዘው ወጡ፡፡

ጆርጅ ቡሽ በዘመናቸው ከሰሯቸው ስህተቶች በሙሉ የከፋ ሊባል የሚችለው በሽብርተኞች ላይ ባወጁት ዘመቻ ‹‹ሽብርተኛ›› ማለት ‹‹ሙስሊም›› ማለት እንዲመስል ማድረጋቸው ነው፡፡ ይህንን ለማስተባበል መንግስታቸው ቢደክምም ተሳክቷል ማለት አይቻልም፡፡ ብዙዎች የተወናበደ አመለካከት አፍርተው ቀርተዋል፡፡ በዚህ ብስጭት ሃይማኖታዊ ሕልውናቸውን ለማዳን የፈለጉ የሚመስሉ ምስኪኖች አልቃይዳን ለመደገፍ ተገድደዋል፡፡

አሜሪካ የምታደርገው ማናቸውም ነገር በሌላው ዓለም ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡ ሉላዊነት (globalization) ባመዛኙ አሜሪካዊነት (americanization) መሆኑን ብዙዎች የሚስማሙበት ሐቅ ነው፡፡ የአሜሪካ ተጽዕኖ ለሁሉም የዓለም አገራት ይዳረሳል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ይሄ ተጽዕኖ ይንፀባረቅ ይሆናል የሚለው ስጋት ለብዙዎቻችን ልብ የሚያርድ ጉዳይ ነው፡፡

Friday, January 27, 2012

የኢትዮ ቴሌኮም ቁልቁለት

ፎቶ፤ www.stockphotopro.com

ሐሙስ ዕለት አመሻሹ ላይ ስልኬ ካርዱን ጨርሶ የጀመርኩትን ወሬ አቋረጠኝ፡፡ ወዲያው ካርድ ገዛሁና ሞልቼ ወሬዬን ለመቀጠል ተጣደፍኩ፡፡ ምን ዋጋ አለው? አዲሱ *805* የካርድ መሙያም ሆነ የቀድሞው 904 ገንዘቤን ሊቀበሉኝ አልቻሉም፡፡ ብስጭቴ እየተጋጋለ ደጋግሜ ስሞክር አመሸሁ፤ አልተሳካም፡፡ በማግስቱ ካርዱን ለወሬው የማድረስ ሕልሜ አልቆ፣ ገንዘቤን ከኪሳራ ለማዳን ማለዳ ጀምሬ መቀጥቀጤን ቀጠልኩ÷ በቀላሉ የሚሆን አልነበረም፡፡ በመጨረሻ እኩለ ቀን ሲቃረብ 805 – “Sorry, the operation failed. Bye” የሚለውን የተለመደ ጽሁፍ ካስነበበኝ በኋላ÷ ካርዴ እንደተሞላ የሚነግር አጭር የጽሁፍ መልዕክት ደረሰኝ፡፡ ደስ አለኝ ልበል?! ደስ ሊለኝ ግን አይገባም፤ ምክንያቱም ፍዳዬን ሳይ አድሬ ያረፈድኩት በኔ ጥፋት ሳይሆን በቴሌኮሙ የቴክኒክ ድክመት ነው፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ከየት ወዴት?
የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን የስንት ዓመት ስሙን በጥላ ቢሱ ኢትዮ ቴሌኮም የቀየረው የለውጥ ርምጃ የሚጀምረው በስም ለውጥ ነው ከሚል መርኅ ይመስላል፡፡ የራሱን የሚመስል ስም ያጎናፀፈው ፍራንስ ቴሌኮም ቴሌን ማስተዳደር ሲጀምር÷ የተጣለበት ተስፋ (ትርፍ መጨመር ቢሆንም) የተዘበራረቀውንና ዘመናዊነት የጎደለውን አሠራር እንዲያፀዳ በማሰብም ጭምር መሆኑም ይታወቃል፡፡ ግን እየሆነ ያለው የተባለው ነገር ነውን?

ፈረንሳዊው አስተዳደር ሥራውን አሀዱ ያለው የሞቱና ድርጅቱን የለቀቁ ሠራተኞን በኃላፊነት ቦታዎች በመመደብ ነበር፡፡ በርግጥ ያንኛው ለዚህንኛው ሲያስረክብ የተፈጠረ ስህተት ነው ተብለን አምነን ነበር፤ እየቆየን እየተመለከትን ያለነው ግን የዛኔውን እምነታችንን ዛሬ ላይ ቆመን እንድንጠራጠረው የሚያስገድድ ነገር ነው፡፡

Tuesday, January 17, 2012

የፈረንጅ አምልኮ በኢትዮጵያ

From Addis Ababa, Ethiopia
ፈረንጅ የሚለው ቃል÷foreign ከሚለው እንግሊዝኛ ቃል የመጣ ይመስለኛል፡፡ ምናልባትም አባቶቻችን foreign የሚለውን እንግሊዝኛ ፈረንጅ ብለው ሳያነቡት አይቀርም፡፡ በዚህ ዓይነት ፈረንጅ ማለት ኢትዮጵያዊ ያልሆነን ሰው ይወክላል ማለት ነው፡፡ እኔ ግን በርዕሴ ፈረንጅ ብዬ የጠቀስኩት ነጮችን መሆኑን ተገንዘቡልኝ፡፡

የፈረንጅ አምልኮ በኢትዮጵያ መኖሩን ሳናውቅ ስር ሰዶ ከርሟል፡፡ ምንም እንኳን ጉዳዩ ቅርጫፉን የዘረጋው አሁን ቢሆንም÷ ከጥንት የተጀመረ አምልኮ ስለመሆኑ የታሪክ ድርሳናትን በመመርመር መረዳት ይቻላል፡፡

የፈረንጅ አምልኮ ድሮ
የፈረንጅ አምልኮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጣባን ክርስትና እና እስልምና ወደኢትዮጵያ በገቡበት ዘመን እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ይሄ ብዙዎችን የሚያናድድ አስተሳሰብ ቢሆንም÷ እኔን ግን ከማሳመን አላለፈም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን ሀገር በቀል እምነቶችንና ስልጣኔዎችን ደምስሰው ባዕዳን ሃይማኖቶችንና ስልጣኔዎችን የተቀበሉት በነዚያ ጊዜያት ነው፡፡

Friday, January 13, 2012

ሰማንያ ሚሊዮን እስከምንደርስ እንታገላለን


አንድነታችንን የሚፈሩ ሰዎች ብቻ ናቸው የተለያየን እንደሆንን እና የተለያየ ፍላጎት እንዳለን የሚነግሩን፡፡ በፊት ኢትዮጵያውያን ነበርን አሁን ትግሬ፣ አፋር፣ አማራ፣ ኦሮሞ…… አድርገውናል፡፡ አሁን ክርስቲያን፣ እስላም… አድርገውናል፡፡ አሁን አባል፣ ደጋፊ ወይም አሸባሪ ብለውናል፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ እኛ ኢትዮጵያውያን ከሰሜንም፣ ከደቡብም፣ ከምስራቅም፣ ከምዕራብም፣ ከመሃል አገርም ብንመጣ አንድነታችን በምቾታችን ብቻ ሳይሆን በችግራችንም ሳይቀር ይገለፃል፡፡ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ድሮም ሆነ ዛሬ ችግራችን እጦት ነው - የምግብ እጦት፣ የመረጃ ወይም የእውቀት እጦት፣ የነፃነት እጦት ነው፡፡

አንድነታችን እውነት ቢሆንም እኛን የመበታተኑ ትግል ግን አልተሳካም ማለት አይቻልም፡፡ ከአንድነታችን ይልቅ ልዩነታችን እንደጌጥ አንጠልጥለነው እንድንዞር እያደረገን ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ምንም እንኳን በየጓዳችን ሁላችንም በመንግስታችን ሥራ ስንብሰከሰክ ብንቆይም ከጎናችን የተቀመጠውን ሰው ማንነት በርግጠኝነት መናገር እየፈራን፣ እሱ/እሷም እንደኛ በውስጧ የተማረረች መሆኗን ከማሰብ ይልቅ ልዩነታችንን በመጠርጠር ብቻ በዝምታ ታፍነን እና በስጋት ተበታትነን፤ ኢሕአዴግ በጣት በሚቆጠሩ ታማኝ ደጋፊዎቹ ብቻ እየታገዘ አገሪቷን እና ዜጎቿን እንደልብ እንዲያሾራቸው ረድተነዋል፡፡

በምርጫ 97 ወቅት፣ የኢሕአዴግ ከፋፍለህ ግዛ ውጤትን ማስተዋል የታደለ አንድ ወዳጄ የቋጠራት ስንኝ ሁኔታውን ፍንትው አድርጋ ታሳያለች፡፡

Monday, January 9, 2012

ገመና 2፣ ሰው ለሰው፣ ጀግንነትና ኢትዮጵያ


የገመና 2፣ እና የሰው ለሰው ድራማዎች (ሶጵ ኦጴራዎች?) ሁለቱም ተወዳጅ ጀግና ከመፍጠሩ ይልቅ፣ የሚጠላ ጀግና የመፍጠሩ ሙከራ የተሳካላቸው ይመስላል፡፡ ዘመነኞቹ የሶጵ ኦጴራ ደራሲዎች መጥፎ እና ጥሩ ሰዎችን እየፈጠሩ ከማባላት የድሮ የታሪክ አወቃቀር ስልት እየወጡ፣ ከሕይወት ውጣ ውረድ ጋር ታግለው የሚያሸንፉ ጀግኖችን በመፍጠር ላይ አተኩረዋል፡፡ የኛዎቹ ደራሲዎች የሚፈጥሯቸው ጀግኖች ግን የሚፈተኑት ለእኩይ ተግባር የተፈጠሩ በሚመስሉ ሰዎች ነውና በዚያው አካሔድ እያነሳን እንጥላቸዋለን፡፡

Monday, January 2, 2012

እስኪ ስለዋጋ - ቆም ብለን እናውጋ!

From Addis Ababa, Ethiopia
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሃገራችን ቆሞ የማይጠብቀን ነገር ቢኖር ዋጋ ነው፡፡ የሌላው፣ የሌላው ነገር ቀርቶ የአንበሳ አውቶቡስ ዋጋ እንኳን በተሳፈርንበት ዋጋ መመለስ እስከማንችል ድረስ በፍጥነት ነው የሚለዋወጠው፡፡ (“ማርያምን” አላጋነንኩትም!) ከፈረንሳይ ለጋሲዮን ወጥቼ መሃል አዲሳባ መዋል ከጀመርኩ ወዲህ በዋጋ ጉዳይ እንደሳሙና እያደር እያለቅኩ፣ አሁን የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሻለሁ፡፡

በሃገራችን ዋጋ የሚጨምሩባቸው በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋነኞቹ ግን የታክስ እና የትርፍ ጭማሪ ፍላጎት ናቸው፡፡ በጥቅሉ በሽታው መንግስት አመጣሽ ወይም ነጋዴ አመጣሽ ተብሎ ሊከፈል ይችላል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን፣ ዛሬ፣ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የትርፍ ጭማሪ ፍላጎት ላይ ብስጭቱን እንደሚከተለው ያቀርባል፡፡