(በፍቃዱ ኃይሉ)
ይህን መጣጥፍ ያዘጋጀሁት እያስጴድ ተስፋዬ “ምክረ-ሀሳብ ለረጋ ፖለቲካዊ ስርአት” በሚል ላቀረበው ጽሑፍ መጋቢ መልስ ይሆን ዘንድ ነው። በቅድሚያ እያስጴድ ጊዜ ወስዶ እና አሰላስሎ “የተረጋጋ ስርዓተ ማኅበር ለመፍጠር እንቅፋት ሆነዋል” ያላቸውን ነጥቦች በመዘርዘር እና የመፍትሔ ሐሳቦችን በመሰንዘር ውይይት ለማነሳሳት በመሞከሩ ከልቤ ላመሰግነው እወዳለሁ። እንዲህ ዓይነት የሰከነ ውይይት እና ቆም ብሎ ለማሰላሰል የሚረዳ መጣጥፍ ማዘጋጀት በተለይ በዚህ ሁሉ ነገር በሚጣደፍበት እና የማኅበራዊ ሚዲያ ተደራሲዎች ትኩረት ባጠረበት ጊዜ አስቸጋሪ እንደሆነ እረዳለሁ። ሆኖም፣ የውይይቱ በረከት እንዳያመልጠኝ፣ እሱ በቀደደው የውይይት አጀንዳ ላይ ተመርኩዤ የኔንም ሐሳቦች እንደሚከተለው አቀርባለሁ። (ጽሑፉን በፒዲኤፍ ለማንበብ ይህንን ሊንክ ይከተሉ።)
ይህ ጽሑፍ ሦስት ዋና ክፍሎች አሉት። የመጀመሪያው ክፍል “የእያስጴድን አንብሮ” (Eyasped’s Thesis) እኔ በተረዳሁት ልክ አሳጥሬ የማቀርብበት ነው። ሁለተኛው ክፍል አንብሮው ላይ ግምገማ የማቀርብበት ነው። ሦስተኛው ክፍል እያስጴድ ማካተት ነበረበት የምላቸውን “ተጨማሪ ሐሳቦች” የማቀርብበት ነው።
1. የእያስጴድ አንብሮ
የመጋቢ መልስ ሐሳቤን ከማቅረቤ በፊት የእያስጴድ አንብሮ (thesis) የያዛቸውን ጭብጦች፣ እኔ በተረዳሁት መልኩ ለማቅረብ እሞክራለሁ። መጣጥፉ በአራት ምዕራፎች የተቀነበበ ነው። የመጀመሪያው ምዕራፍ ኢትዮጵያውያን የተረጋጋ ስርዓት ማኖር ለምን እንደተሳነን ይተነትናል። ሁለተኛው ምዕራፍ ችግሩን የመመልከቻ መነፅር ያቀርባል። በሦስተኛው ምዕራፍ ወደ መፍትሔ የሚወስደንን ማዕቀፍ ያመላክት እና በአራተኛው እና የመጨረሻው ምዕራፍ አዲስ አገር ዐቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ በመመሥረት ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት እንደሚቻል ይደመድማል። (የእያስጴድን አንብሮ ጨምቄ በማቀርብበት እና በምገመግምበት ጽሑፍ ውስጥ አንዳንድ የቃላት አጠቃቀሞችን ለእኔ አጻጻፍ ዘዬ በተመቸ መልኩ እንደቀየርኳቸው ከወዲሁ ለማሳወቅ እወዳለሁ።)
1.1. የተረጋጋ አገረ መንግሥት ማኖር አለመቻል
እያስጴድ የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት ለማኖር አራት መሠረታዊ ነገሮች መሟላት አለባቸው ብሎ ይሟገታል። እነዚህ አራት ነጥቦች 1ኛ) ሕዝባዊ ይሁንታ ያለው መንግሥታዊ አስተዳደር፣ 2ኛ) የሕግ የበላይነት እና ተጠያቂነት፣ 3ኛ) ሰላም እና መረጋጋት፣ እንዲሁም 4ኛ) መሠረታዊ የልማት ጥያቄ ናቸው። ይሁንና ከእነዚህ አስቀድሞ በጥልቀት የሚያብራራው ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ሳይሆን አገረ መንግሥቱ (the State) ራሱ ቅቡልነት ማጣት እና የጋራ የፖለቲካ ማኅበረሰብ መገንባት አለመቻልን ነው።
የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት የቅቡልነት እጦት መንስዔዎችን ሲዘረዝር ኢትዮጵያ የአውሮፓውያን ቅኝ ተገዢ ባትሆንም፣ የግዛት ድንበሯን ራሷ ማስመር አለመቻሏን እንዲሁም አፍሪካውያን ጎረቤቶቻችን ከቅኝ ግዛት ነፃ የመውጣት ንቅናቄዎች ሲጀመሩ የኢትዮጵያውያን ብሔረሰቦች ልኂቃንም እነርሱን አርአያ በማድረግ የነፃ አውጪ ንቅናቄ መጀመራቸውን ይጠቅሳል። ይህ በእንዲህ እያለ ኢትዮጵያውያን የጋራ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ያደረጓቸው ሙከራዎች አልተሳኩም። ምክንያቱም፣ አንደኛ፣ አውሮፓውያን ይህን እንዲያደርጉ ያገዛቸው የኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ የመደበኛ ትምህርት መዳረስ፣ የመገናኛ ብዙኃን ዕድገት ሲሆኑ፣ እነዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የተሟሉ ሁኔታዎች አልነበሩም። ሁለተኛ፣ የአገረ መንግሥቱ እርሾ (the core state) የሆነው የፖለቲካ ማኅበረሰብ በአገረ መንግሥቱ ከታቀፈው ጠቅላላ ሕዝብ አንፃር ያለው ቁጥር አናሳነት (ሕዳጣንነት) የሚከተለው የማንነት አቅላጭ (assimilationist) ፖሊሲ ባርቆበት እንዋ፟ጣለን ያሉ ብሔረሰቦች የነፃ አውጪ ንቅናቄ እንዲጀምሩ አስገድዷቸዋል የሚል ነው።
1.2. የችግሩ አረዳድ
በሁለተኛው ምዕራፍ፣ እያስጴድ ብሔርተኝነት እና ብሔርተኞችን ዋነኛ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጫወታ ሕግ እና ተዋናዮች መሆናቸውን የሚያመላክት ሐተታ አቅርቧል። በተለይ አራት የብሔርተኝነት ቡድኖችን ውልደት እና ዕድገት በመዘርዘር የተፈጠረውን የፖለቲካ ትርዒት ምሥል ለመከሰት ይሞክራል።
የመጀመርያው የብሔርተኝነት ዓይነት፣ እያስጴድ የአቢሲኒያ ወይም የሐበሻ ወይም የአማራ/ትግራይ ብሔርተኝነት ብሎ የሚጠራው ሲሆን፣ እንደርሱ ይህ ብሔርተኝነት በዓለምም አንጋፋው ነው። የሐበሻ (አማራ-ተጋሩ) ብሔርተኝነት የተወለደው የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነትን፣ “የሐበሻን መልክ”፣ እና የአማርኛ/ትግርኛ ቋንቋ ችሎታን የወል መሠረት አድርጎ እንደሆነም ያትታል። ከዚያም ይህ ብሔርተኝነት በዳግማዊ ምኒልክ የደቡብ ኢትዮጵያ ዘመቻዎች ወቅት “የአማራ መደብ” ሲፈጥር፣ ሰሜን ላይ ደግሞ የተጋሩ ብሔርተኝነት በዐፄ ዮሓንስ (አጋር አልባ) አሟሟት እንዲሁም የትግርኛ ተናጋሪው ሕዝብ ለሁለት መከፈል ቁጭት ሳቢያ እንዲወለድ አድርጓል ሲል ያትታል። የትግራይ ብሔርተኝነት የወያኔ ገበሬዎች አመፅ፣ በሕወሓት የትጥቅ ትግል ተፋፍሞ ሲቀጥል፣ በቅርቡ በተደረገው የትግራይ ጦርነት ጫፍ ላይ ደርሶ የመገንጠል ስሜት አዳብሯል ይላል። በሌላ በኩል በድኀረ አብዮቱ የኦርቶዶክስ ክርስትና ከቤተ መንግሥት መውጣት፣ በ1985ቱ ሕገ መንግሥት መፅደቅ፣ እንዲሁም የ2010ሩን የፖለቲካ ለውጥ ተከትለው የተከሰቱት ግጭቶች እና የፖለቲካ ኃይሎች አሰላለፎች መቀያየር ጠንካራ (assertive) የአማራ ብሔርተኝነት ከቀደመው “ኢትዮጵያዊነት” ወይም “የሐበሻ ብሔርተኝነት” ተፈልቅቆ እንዲወጣ አድርጎታል ይላል።
የኦሮሞ ብሔርተኝነትን ሲያትት፣ በጣሊያን ወረራ ጊዜ
የወለጋ እና የጅማ ኦሮሞዎች ለመፍጠር የሞከሩት ፌዴሬሽን ብሔርተኝነቱን ጠንስሶታል በማለት፣ በፌዴሬሽኑ መመሥረት እና በ2010ሩ
ለውጥ ሒደት ውስጥ የተፈጠሩ/ያደጉ ሦስት ዋና ዋና የኦሮሞ ብሔርተኝነቶች ዓላማዎችን ይዘረዝራል። እነዚህም የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ
የቅኝ ግዛት ነው፣ የራሱን ነፃ ብሔረ መንግሥት (nation-state) መመሥረት አለበት የሚሉ
(ምሳሌ ኦነግ)፣ ጥያቄው የጭቆና ነው፣ በኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ውስጥ ራስን በራሱ የማስተዳደር ነጻነቱ ይረጋገጥለት የሚሉ (ምሳሌ
ኦፌኮ) እና ኦሮሞ ኢትዮጵያን በራሱ አምሳል መልሶ መቅረፅ አለበት የሚሉ (ኦሕዴድ) ናቸው። በሌላ በኩል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት
ወቅት የኦጋዴን እና ሀውድ አካባቢዎች ወደ ኢትዮጵያ መካ፟ለላቸው፣ የኅብረ ሶማሌ (Pan-Somali) ንቅናቄ መጧጧፍ እና የኦብነግ መመሥረት የሶማሊ ብሔርተኝነትን የቀረፁ ክስተቶች ሆነው
ተጠቅሰዋል። በዚህ ሳቢያ የሶማሊ ብሔርተኝነትም ነፃ የኦጋዴን ብሔረ መንግሥት መመሥረት የሚሹ፣ በፌዴሬሽኑ ውስጥ ራሳቸውን በራሳቸው
ማስተዳደር የሚሹ እንዲሁም የኅብረ ሶማሊ አገረ መንግሥትን መቀላቀል የሚሹ ብሔርተኞችን ያቀፈ ነው።
1.3. የመፍትሔ አማራጭ
በሦስተኛው ምዕራፍ የመፍትሔ አማራጮች ተብለው የቀረቡ ሐሳቦችን የሚተነትነው እያስጴድ፣ መጀመሪያ ላይ ያሰፈረው “አገራዊ ምክክር” (National Dialogue) ነው። ይሁንና አገራዊ ምክክር አስፈላጊ ቢሆንም፣ ከሌሎች አገራት ተሞክሮ እንደምናየው አገራዊ ምክክር ሥሙ የተሸጠለትን ያህል ውጤታማ ስላልሆነ ሁሉንም ተስፋችንን እሱ ላይ መጣል እንደሌለብን እና የኢትዮጵያም ጅምር ሙከራ ብዙ ጉድለቶች ያሉበት መሆኑን ይተርካል። በሁለተኝነት ያስቀመጠው የልኂቃን ድርድርን ጉዳይ ሲሆን፣ የልኂቃን ድርድር ከሥልጣን መጋራት ባሻገር ሕጋዊ እና ተቋማዊ አወቃቀሮችን መልሶ መገንባትንም መጨምር እንዳለበት ያትታል።
በዚህ ምዕራፍ መንግሥታዊ ስርዓቱ ላይ የሚሰጡ አስተያየቶችንም ይተቻል። ኢትዮጵያን መሰል ዘርፈ ብዙ ብዝኃነት ላለው አገር፣ በማቻቻል ሥልጣን የመጋራት ዴሞክራሲያዊነት (consociationalism power sharing democracy) ወይም አሰባሳቢ ዴሞክራሲያዊነት (centripetal democracy) ናሙናዎች እንደ አማራጭ ይቀርባሉ ይላል። ሆኖም ሁለቱም ናሙናዎች ግጭት ለመከላከል ከመበጅታቸው ባሻገር ውጤታማ መንግሥት የማቋቋምና አሰባሳቢ ማንነት የመገንባት ዕድል አይሰጡም ሲል ይተቻቸዋል። በተጨማሪም ናሙናዎቹ የአፍሪካ አገራትን ዐውድ (ብዙ ብሔረሰቦች በአንድ አገረ መንግሥት ውስጥ መኖር፣ የሲቪክ ባሕል አለመዳበር እና ብሔረሰቦች ድንበር ዘለል አሰፋፈር ያላቸው መሆኑን) ከግምት ውስጥ ያስገቡ አይደሉም ሲል ይደመድማል። በተጨማሪም ሕገ መንግሥቱ አሰባሳቢ የሲቪክ እሴቶች ያልደነገገ መሆኑ፣ በሕገ መንግሥቱ የተካተቱ አንዳንድ ሲቪል እሴቶችም በክልሎችም ሕገ መንግሥቶች ያልታቀፉ በመሆኑ እና ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት አለመኖሩን ዋና ክፍተቶች ብሎ ይጠቅሳቸዋል።
በዚህ ትንታኔ ላይ በመመሥረት፣ በ50%+1 ጠቅላላ
ድምፅ እና በክልሎች የተወሰነ የድምፅ ወለል (minimum vote) መሠረት በቀጥታ ምርጫ ያገኙት
ድምፅ ልዩነት ከ60%፡40% የጠበበ ከሆነ አሸናፊው ፕሬዚደንት፣ ተሸናፊው ምክትል የሚሆኑበት፣ አልያም ፕሬዚደንቱ የራሱን ምክትል
የሚመርጥበት ስርዓት ጠቁሟል። በተጨማሪም፣ በተመጣጣኝ ውክልና (proportional representation) ምርጫ ስርዓት የተመረጡ አባላት ያሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ እንዲሁም የሕገ
መንግሥት ፍርድ ቤት መቋቋምን እንደመፍትሔ አቅርቧል። አልፎ ተርፎም ድንበር ዘለል የብሔረሰቦችን አሰፋፈር ከግምት ውስጥ ያስገባ
የጣምራ ዜግነት መብት እንዲረጋገጥ እና የወልቃይትና አዲስ አበባ ውዝግቦችን ይፈታሉ ብሎ የገመታቸውን በርካታ አማራጮች ዘርዝሯል።
1.4. አገር ዐቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ
እያስጴድ ያቀረባቸውን የመፍትሔ ሐሳቦች ወደ መሬት ማውረድ የሚቻለው ያንን የለውጥ ማኒፌስቶ ያነገበ የፖለቲካ ተቋም መኖር እንዳለበት እና ይህም አገር ዐቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ መሆን እንዳለበት ያስረዳል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ አሁን ያለውን የኃይል አሰላለፍ ሲተነትን ብልፅግና ፓርቲ፣ ሕወሓት፣ እና በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ያሉ አማፂዎችን በቅደም ተከተላቸው የኃይል ሚዛን ባለቤት አድርጎ ያሰልፋቸዋል። ይሁን እንጂ አንዳቸውም መንገጫገጭ ከመፍጠር ይልቅ ብልፅግናን ለመጣል የሚያስችል አቅም እንደሌላቸው ይሟገታል። ስለሆነም አዲስ እና አገር ዐቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ መመ፟ሥረት አለበት በማለት ጽፏል።
በጽሑፉ የታለመው የፖለቲካ ፓርቲ መንግሥታዊ ጫናዎችን
መቋቋም እንዲችል እና ቀስ በቀስ ሕዝባዊ መሠረቱን እንዲያሰፋ በማሰብ፣ መጀመሪያ (በአጭር ጊዜ ግብ) የማንቃት፣ የበጎ አድራጎት
እና በይነ-ኅብረተሰባዊ አጋርነትን የሚያጎለብቱ ሥራዎች እንዲሠራ፣
በረዥም ጊዜ ግቡ ደግሞ ስትራቴጂካዊ ቦታዎች ላይ አቅምን አሰባስቦ በመወዳደር እና ፓርላማ በመግባት በስተመጨረሻ የመንግሥት ሥልጣን
መረከብ የሚያስችል አቅም ማኖር ነው።
2. ጥቅል የአንብሮው ግምገማ
የእያስጴድን አንብሮ በአንድ ዓረፍተ ነገር መጠቅለል ቢያስፈልግ “ኢትዮጵያ ‘የተረጋጋ መንግሥት’ ወይም ‘የተረረጋ አገረ መንግሥት’ ማኖር ይቻላት ዘንድ፥ ‘የጋራ አገራዊ የፖለቲካ ማንነት መገንባት’ አለባት” የሚለው የሚያጠቃልለው ይመስለኛል። ስለሆነም፣ የአገረ መንግሥቱን የቅቡልነት ቀውስ ሲተነትን በዋነኝነት እንደማሳያ የተጠቀመው ተገዳዳሪ የሚባሉትን ብሔርተኛ ቡድኖች እና በውስጣቸው ያለውን ክፍፍል መንስዔ እና ዕድገት በመተንተን ነው። ትንታኔው ብሔርተኛ ቡድኖቹ እንወክላቸዋለን የሚሏቸውን ብሔረሰቦች ፖለቲካዊ ማንነት፣ ስጋት እና ራዕይ አጣምሮ ለማየት ሞክሯል። ሆኖም፣ እነዚህ የተከፋፈሉ ነገር ግን ዕጣ ፈንታቸው የተሳሰሩ ቡድኖች በሚያደርጓቸው ትግሎች ውስጥ ሰላምና መረጋጋትን ማግኘት ስለሚቸግር፥ የብሔረሰብ ድንበር ተሻጋሪ የፖለቲካ ፓርቲ እንዲፈጠር እና ይህ ፓርቲ ቀስ በቀስ የጋራ የፖለቲካ ማንነት ያላቸውን የተለያዩ ቡድኖች ወደ መሐል የሚያሰባስብ የፖለቲካ ፓርቲ መመሥረትን እንደ ስልት እንዲጠቀሙ ምክረ ሐሳቡን (አንብሮውን) ያቀርባል።
2.1. ስለ አገረ መንግሥቱ አለመረጋጋት
የእያስጴድ አንብሮ እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት አለመረጋጋት ዋነኛ መንስዔ የኢትዮጵያ ድንበር የቅኝ ግዛት መሥመሮችን ተከትሎ የተሠመረ በመሆኑ እና አንዳንድ ብሔረሰቦች በድንበር ተቆራርጠው ሁለት እና ከዚያ በላይ አገራት ውስጥ (የሶማሊ ብሔረሰብ በኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፤ የተጋሩ ብሔረሰብ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ፤ ወዘተ) በመከፋፈላቸው ምክንያት፣ ከዚያም በኋላ በተለይም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት ፖሊሲዎች ብሔረሰቦችን ወደ አንድ የዘውግ ማኅበረሰብ ማቅለጥ (assimilation to an ethnolinguistic identity) በማተኮሩ የመዋ፟ጥ ስጋት የገባቸው ብሔረሰቦች ተደራጅተው የብሔረ መንግሥት ግንባታ (nation-state building) ሙከራውን በመቃወማቸው ሳቢያ የተፈጠሩ ገፊ እና ጎታች ምክንያቶች ሳቢያ ተገዳዳሪ ብሔረሰቦች ተፈጥረዋል።
ይሁንና እያስጴድ ከአገረ መንግሥት ምሥረታው እና ካልተጠናቀቀው ወይም ተቀባይነት ካጣው የብሔረ መንግሥት ግንባታ እኩል (ወይም የበለጠ) የተረጋጋ አገረ መንግሥት ማኖር እንዳይቻል ምክንያት የሆነውን አምባገነናዊነት እና ሥልጣንን መግራት አለመቻል መሆኑን ሳይዳስስ ያልፈዋል። ንጉሣዊውን አገዛዝም ይሁን ከዚያ በኋላ የመጡት ሁለት (ሶሻሊስት እና ፌዴራላዊ) ሪፐብሊኮች አንድ የሚያደርጋቸው ሥልጣን ማዕከል ላይ የተከማቸ መሆኑ እና በግለሰብ ወይም በቡድን ፈላጭ ቆራጭነት የሚመራ፣ መንግሥት በብዙኃን ይሁንታ የማይቋቋም፣ እና መሪዎች በኃይል ወይም በተፈጥሮ አደጋ ካልሆነ በቀር ከሥልጣን የማይወርዱ መሆኑ ነው።
ደጋግሜ እንደምጠቅሰው፣ ዋናው የአለመረጋጋት መንስዔ፣
ሥልጣን ላይ መውጫ እና መሰንበቻው መንገድ ነውጥ (violence)
መሆኑ ነው። እያስጴድ
ማክስ ቬበርን በመጥቀስ የነውጥ-አቅም የበላይነት (monopoly of violence) ቅቡልነት ባለው መንግሥት ዘንድ መሆን አለበት ይላል፤ ይህ
ብዙዎቻችንን የሚያስማማ ነው። ይሁን እንጂ መንግሥት ያንን የነውጥ-አቅም
የበላይነት ወንጀልን ለመከላከል፣ ፀጥታ ለማስፈን እና አገረ መንግሥቱን ከውጭ ወረራ ለመከላከል እንጂ ሥልጣን ላይ ለመውጫም ይሁን
ለመሰንበቻነት መጠቀም አይኖርበትም። ይህንን ለመከላከል፦
- መንግሥት እና ዜጎች ያላቸውን የግንኙነት ዓይነት የሚወስን ማኅበራዊ ውል (social contract /ሕገ መንግሥት/) ማኖር፣
- የመንግሥትን ሥልጣን ለመግራት የሚያስችል የሥልጣን ክፍፍል ማበጀት፣
- የሥልጣን መሠረቱ የብዙኃን ይሁንታ እንዲሆን የሚያስችል ስርዓተ መዋቅር መዘርጋት ያስፈልጋል።
በተጨማሪም የመንግሥት እና አገረ መንግሥቶች ዝግመተ ዕድገትን በአግባቡ በመተንተን የምንፈልገውን ነገር ከነባራዊው ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ንደፈ ሐሳቦችን እንድናስቀምጥ ይረዳናል ብዬ እገምታለሁ። “የአገረ መንግሥታት አመሠራረት እና ዕድገት ምን ይመስላል? የመንግሥታት ዕድገት እና ከዜጎች ጋር ያለው ግንኙነት ምን ዓይነት መልክ አለው? ሰላማዊ ስርዓተ መንግሥታት ምን ዓይነት የመንግሥት ዓይነት አላቸው? ብዝኃ ብሔረሰብ፣ ብዝኃ እምነት የሆኑ ሕዝቦች እንዴት ሰላም እና መረጋጋት ማምጣት ቻሉ? በኢትዮጵያ ያለውን የነውጠኝነት ባሕል እንዴት መግታት ይቻላል?” የሚሉትን ጥያቄዎች መልስ ማሰላሰል የነጠረ የመፍትሔ ሐሳብ ለማፍለቅ ያስችላል ብዬ እገምታለሁ።
2.2. የችግሩ አረዳድ
የኢትዮጵያን ችግር በቅጡ ለመረዳት በተገዳዳሪ ብሔርተኞች መነፅር መመልከት ጠቃሚ መሆኑን ያመላከተው እያስጴድ በተለይ የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የትግራይ እና ሶማሊ ብሔርተኝነቶችን ተንትኗል። ትንታኔው እያንዳንዱን ብሔርተኝነት በተናጠል ማየት ላይ ያተኮረ ነው። ይሁንና፣ ብሔርተኝነቶቹ እና የሚከተሉት ትርክት እርስ በርስ የተሳሰሩ መሆኑን በትንታኔው በጥልቀት አልተመለከታቸውም። በተለይም እያስጴድ “የጋራ ፖለቲካዊ ማንነት መገንባት” በሚል ላስቀመጠው መፍትሔ ወሳኝነት ስላላቸው የሚያስተሳስሯቸው እና የሚያለያይዋቸው ነገሮች ምን እንደሆኑ መተንተን ጠቃሚ ይመስለኛል። በእያስጴድ መጣጥፍ የጎደለ የሚመስለኝን ይህንን ትንታኔ እንደሚከተለው በመጋቢነት በማስቀመጥ ከተገዳዳሪ ብሔርተኝነት ጋር የተያያዘውን ችግር የበለጠ ለማስረዳት እና ለመረዳት ይቻላል ብዬ የምገምተውን አቀራረብ እከተላለሁ።
- ሁለቱ ትርክቶች
የኢትዮጵያ ዘመናዊ አገረ መንግሥት በሰሜን ደገኞች ተቆርቁሮ ደቡባዊ ቆላዎችን ማካተቱን ብዙዎቻችን የምንስማማበት ይመስለኛል። በዚህም የአማርኛ ቋንቋ፣ የኦሮቶዶክስ ክርስትና እምነት፣ እና የሰሜን ደገኞች ባሕል የኢትዮጵያ (መንግሥት እና አገረ መንግሥት) ማንነት መገለጫ ሆኖ ለረዥም ጊዜ ኖሯል። ይህም “የብሔረሰቦች ጥያቄ” በሚል የቀረበውን ጥያቄ አጭሯል። በዚህ መሐል የተፈጠሩትን ትርክቶች የታሪክ ምሁራን በሁለት ዘርፍ ያስቀምጡታል። አንደኛው ታላቁ ትውፊት (the great tradition) የሚሉት ሲሆን፣ ይህ ትርክት ኢትዮጵያን በሰለሞናውያን ትርክት ከንግሥተ ሳባ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ የዘለቀ የታሪክ ባለቤት የሚያደርግ ሲሆን፣ በተቃራኒው ሞጋች-ታሪኮች (counter-histories) በሚል የሚታወቁት ትርክቶች ተፈጥረዋል። ሞጋች-ታሪኮች የዛሬይቱን ኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ምሥረታ ከዳግማዊ ምኒልክ ወዲህ የሚያደርጉት ሲሆን፣ ከታሪካዊቷ ኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ቀጥተኛ ያልሆነ እና የላላ ነው ይላሉ። አልፎ ተርፎም፣ ኢትዮጵያውያን ወጥ ታሪክ የላቸውም፣ ይልቁንም ብሔረሰቦች የየራሳቸው ታሪክ፣ ባሕል፣ እና አስተዳደር የነበራቸው ኅብረተሰቦች በአንድ ኃይል የተሰበሰቡበት የፖለቲካ ሥሪት ነው የሚል ነው። የታላቁ ትውፊት ትርክት ቢያንስ እስክ 1983 ድረስ ገዢ ትርክት የነበረ ቢሆንም፣ ከ1983 በኋላ ግን ሞጋች-ታሪኮች በምትኩ ገዢ ሆነዋል። ገዢ ትርክት የምለው መንግሥታዊ ዕውቅና የተሰጠው መሆኑ ላይ ነው።
- ሦስቱ ኃይሎች
ሁለቱ የታሪክ ትርክት አንጓዎች ሦስት ዓይነት ኃይሎችን
ፈጥረዋል። እነዚህን ኃይሎች እያስጴድ በጽሑፉ ውስጥ የብሔርተኝነት ዓይነቶች (variants/spectrum) ሲል ይገልጻቸዋል። እነዚህን ኃይሎች የሚወክሉ ብሔርተኞችን እኔ ትውፊታዊው ኢትዮጵያዊነት
(Traditional Ethiopianist)፣ የዘውግ ፌዴራላዊነት (Ethno-federalist)፣ እና የተገንጣይነት (Secessionist) ኃይሎች ብዬ እጠራቸዋለሁ።
- የትውፊታዊው ኢትዮጵያዊነት ኃይሎች (Traditional Ethiopianists)፤ እነዚህ ኃይሎች የኢትዮጵያን ታሪክ አዎንታዊ ጎኖች የሚያጎሉ፣ በብሔረሰቦች መካከል የነበሩና
ያሉ ቅራኔዎችን አሳንሰው የሚመለከቱ፣ ማዕከላዊ መንግሥቱ ጠንካራ እንዲሆን እና ነባር/ትውፊታዊ እሴቶቹን እንዳይለቅ የሚታገሉ ናቸው።
የእነዚህ ኃይሎች ሕዝባዊ መሠረት ባብዛኛው ከተሜዎች እና ከቅይጥ ብሔረሰብ አባሎች የተወለዱ ዜጎች ሲሆኑ፣ በተለይ የአማራ፣ ጉራጌ
ብሔረሰብ ተወላጆች ያሉበት ስብስብ ነው። እነዚህ ኃይሎች ከዘውግ ፌዴራላውያን ዘውግን መሠረት ያደረገ (ethnolinguistic) የፌዴራል ስርዓትን ቢቃወሙም፣ አሰፋፈርን መሠረት ያደረገ ፌዳራላዊ
ስርዓት በመርሕ ደረጃ ይደግፋሉ።
- የዘውግ ፌዴራላዊነት ኃይሎች (Ethno-Federalists)፤ እነዚህ ኃይሎች የኢትዮጵያን አገረ መንግሥት ብሔረሰቦችን በመጨቆን የተመሠረተ አድርገው የሚያዩ
ከመሆናቸውም ባሻገር የዘውግ ፌዴራሊዝሙ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከተተገበረ ለታሪካዊ ችግሮቹ መድኅን ይሆናል ብለው የሚያምኑ ናቸው።
የዘውግ ፌዴራላውያን ከፌዴራል መንግሥቱ ይልቅ የክልል መንግሥታት የበለጠ የሥልጣን ምንጭ እንዲሆኑ ይሠራሉ። ብዙዎቹ የኦሮሞ እና
የትግራይ (ከጦርነቱ በፊት) ብሔርተኞች እዚህ ይመደባሉ፤ ደቡባዊው የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ የሚኖሩ ብዙዎቹ ብሔረሰቦችም እዚህ ምድብ
ውስጥ ያርፋሉ። የዘውግ ፌዴራላውያን ከዘውግ ብሔርተኞች (Ethnonationalists)
ጋር አንድ ዓይነት
አይደሉም፤ ለምሳሌ የአማራ ብሔርተኞች የዘውግ ብሔርተኞች ቢሆኑም በትርክት ግን ከነባሩ ኢትዮጵያዊነት ኃይሎች ጋር አንድነት አላቸው።
- የተገንጣይነት ኃይሎች (Secessionist)፤ እነዚህ ኃይሎች የኢትዮጵያን አገረ መንግሥት እንደ ቅኝ ገዢ የሚመለከቱ እና እንደ መፍትሔውንም መገንጠል አድርገው የሚያቀርቡ ኃይሎች ናቸው። የተገንጣይነት ኃይሎች የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የተፈጠረችው የአውሮፓውያንን መሣሪያ በታጠቁ እና የአውሮፓውያንን ምሣሌ በተከተሉ ሰሜናዊ ቅኝ ገዢዎች ነው ብለው ያምናሉ። ኤርትራ ከመገንጠሏ በፊት የኤርትራ ብሔርተኞች ይህንን ትርክት ያራምዱ ነበር። እንደ ኦብነግ እና ኦነግ ያሉ ኃይሎችም በዋነኝነት ይህንን ትርክት ያራምዱ ነበር።
ስለሆነም የኢትዮጵያ ተገዳዳሪ ብሔርተኛ ኃይሎች ከነልዩነታቸው በነዚህ ሦስት ኃይሎች ውስጥ የተወሰኑ ናቸው። ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሁለት ዋልታ የሚሽከረከር ሆኖ እናገኘዋለን። ትውፊታዊው ኢትዮጵያዊነት ቀስ በቀስ ወደ ሒሳዊ ኢትዮጵያዊነት እየተሸጋገረ እና ከዘውግ ፌዴራላዊነት ጥያቄዎች ውስጥ ከፊሉን እያነገበ እያደገ ነው ብዬ አምናለሁ። ይህም፣ ወደ የዜግነት ኢትዮጵያዊነት (civic Ethiopianism/nationalism) የሚያመራ ከሆነ፣ የዜጎች መብቶችን ማዕከል ያደረገ እና ማዕከላዊው መንግሥት ከክልላዊ መንግሥታቶች ይልቅ ጠንካራ እና ላዕላይ እንዲሆን ይታገላል የሚል ግምት አለኝ። በተቃራኒው የዘውግ ፌዲራላዊነት የቡድን መብቶችን ማዕከል በማድረግ የሚያድግ ሲሆን፣ የፌዴራሉ ሥልጣን ከክልሎች እንዲፈልቅ ይታገላል። ይህም ምናልባት ወደ ሁለት ፓርቲ ስርዓት ያመራ ይሆናል። አገር ዐቀፍ ፓርቲ የመመሥረት ሐሳብ ሲነሳም የማሰባሰቢያ መሥፈርቱ በነዚህ ዙሪያ የሚያጠነጥን ሊሆን ይችላል።
- ከብሔርተኝነት ባሻገር
በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሁሉንም ነገር በብሔርተኝነት መነፅር
የመመልከት አባዜ ሌላው ችግሮቹንም፣ የመፍትሔ አማራጮቹንም እያወሳሰበ ያለ ችግር ነው። እያስጴድ በትንታኔው ያላነሳው ነገር የብሔረሰብ
ጥያቄም ይሁን ሌሎች ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች በሙሉ 1ኛ) በብሔርተኝነት ብቻ መልስ እንደማያገኙ፣ 2ኛ) በብሔርተኝነት
መልስ ለማግኘት መሞ፟ከሩ ተገዳዳሪ ኃይሎችን በመፍጠር የጋራ የፖለቲካ ማንነት የመገንባቱን ሕልም እንዳቀጨጨው እና ሰላምና መረጋጋት
እንዳይመጣ ተጨማሪ ተግዳሮት መሆኑን፣ 3ኛ) ብሔርተኝነት የብሔረሰብ ጭቆናን ከአገር ዐቀፍነት ወደ ክልላዊነት እንዳሸጋገረው፣ 4ኛ)
በብሔርተኝነት ሌሎች ማንነቶች (ለምሳሌ ፆታ፣ እምነት፣ አካባቢያዊነት፣ ወዘተ።) እና ማንነትን (መደብን፣ ፆታን፣ ወዘተ።) መሠረት
ያደረጉ ጭቆናዎች ትኩረት አለማግኘታቸውን ነው። ስለሆነም፣ ተገዳዳሪ ብሔርተኝነትን በመረዳት፣ የብሔርተኝነቶችን መንስዔዎች መልስ
ከማበጀት ጎን ለጎን ሁለገብ የሆነ የዜጎች ጥያቄ ማዕቀፍ ማቅረብ ያስፈልጋል። ጥያቄዎቹን በአግባቡ መለየት መልሶቹንም በአግባቡ
ለመለየት ያግዛል። ለዚህ ሁነኛው መንገድ ሲቪክ የፖለቲካ እሴቶችን፣ ማለትም የዜግነት መብቶች እና ግዴታዎች ከትውልድ ቦታ እና
ሐረግ የበለጠ ገዢ እንዲሆን ማድረግ፣ ልዩነትን መቀበልና መቻቻል፣ ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውን መቀበል፣ ሕጎች ሁሉ
ፍትሐዊ እንዲሆኑ መትጋት፣ እና ለሕዳጣን ጥበቃ ማድረግ፣ ወዘተ መገንባት ነው።
2.3. የመፍትሔ ሐሳቡ
ፓርቲው አሁን ፓርላመንታዊ የሆነውን የመንግሥት ቅርፅ “የእያስጴድ ናሙና” ብዬ የምጠራውን የመንግሥት ዓይነት ይጠቁማል። ናሙናውን (ሞዴሉን) የእያስጴድ ብዬ የጠራሁበት ምክንያት ናሙናው ሌላ ቦታ ስለመጠቀሱ ወይም ስለመተግበሩ መረጃ ማግኘት ስላልቻልኩ ነው። ምንም እንኳን የፕሬዚደንታዊ እና ፓርላመንታዊ ስርዓት ቅይጥ ቢመስልም፣ ተጠሪነቱ ለፓርላማው የሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ስለሌለው ናሙናው (ሞዴሉ) ቅይጥ ስርዓት ምድብ ውስጥ አይወድቅም።
የእያስጴድ ናሙና (እኔ እንደተረዳሁት) በፕሬዚደንታዊ ውድድር፣ አሸናፊው እና ተሸናፊው ዕጩዎች (በተቀራራቢ ድምፅ ሲሸናነፉ) ዋና እና ምክትል ሆነው ለመተባበር የሚገደዱበት እና የሚኒስትሮች ካቢኔ ሲቋቋም ሁለቱም በተለያየ መጠን ተወካይ የሚሰይሙበትን ዕድል ይሰጣል። ሞዴሉ ሁለቱን ተቀናቃኞች ሥልጣን እንዲጋሩ በማድረግ አሸናፊው ሁሉንም ጠቅልሎ የሚወስድበትን አሠራር በማስወገድ ግጭትን ለመከላከል፣ ብሎም ትብብርን ለማበረታታት ያልማል። በተጨማሪም፣ የሕዝብ ድምፅ ብክነትን (በሁለት መንገድ፡ ተመጣጣኝ ውክልናን የምርጫ ስርዓትን ጨምሮ) በመከላከል ብዙዎቹ መራጮች በመንግሥት የሚወከሉበትን ዕድል በማስፋት ቅቡልነት ያለው መንግሥት ለማኖር መፍትሔ ይሆናል ብሎ ይገምታል። የእያስጴድን ናሙና በሰፊው ታዋቂ ከሆኑ የመንግሥት ዓይነቶች አንፃር በሚከተለው ሰንጠረዥ እንመልከተው።
የመንግሥቱ ዓይነት |
ፓርላመንታዊ ስርዓት |
ፕሬዚዳንታዊ ስርዓት |
ቅይጥ ስርዓት |
የእያስጴድ ናሙና |
ርዕሰ መንግሥት |
ጠቅላይ ሚኒስትር(ፓርላማው ውስጥ የአሸናፊው ፓርቲ ወይም ጥምረት መሪ) |
በቀጥታ የተመረጠው ፕሬዚዳንት |
ፕሬዚዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ይከፋፈላሉ |
የምርጫው አሸናፊ ፕሬዚዳንት፣ ተሸናፊው ምክትል ይሆናሉ። ልዩነታቸው ከሰፋ ፕሬዚዳንቱ
ምክትሉን ይሾማል። |
ርዕሰ አገረ መንግሥት |
ፕሬዚደንት ወይም ንጉሥ/ንግሥት (ትዕምርታዊ ወይም
ትዕይንታዊ ሥልጣን) |
በቀጥታ የተመረጠው ፕሬዚዳንት |
በቀጥታ የተመረጠ ፕሬዚዳንት |
በቀጥታ የተመረጠ ፕሬዚደንት |
የሥራ አስፈፃሚው አመራረጥ |
በፓርላማው የሚሾምና የሚሻረው ጠቅላይ ሚኒስትር ሚኒስትሮቹን ይሠይማል። |
የሥልጣን ዘመኑ የተገደበው ፕሬዚደንት ካቢኔውን ይሾማል |
ፕሬዚዳንቱ በቀጥታ ይመረጣል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፕሬዚዳንቱ አቅራቢነት በፓርላማው
ይሾማል። |
ፕሬዚዳንቱ እና ምክትሉ በ70፡30 ምጥጥን የሚኒስትሮች ካቢኔን ይሠይማሉ። |
ሕግ አውጪው |
(በየትኛውም ዘዴ የተምረጠ) ፓርላማ (በኢትዮጵያ አሸናፊው ሁሉንም የሚወስድበት
/first
past the post/ ይመረጣል) |
ከፕሬዚዳንቱ በተለየ ምርጫ የተመረጥ ፓርላማ |
ከፕሬዚዳንቱ በተለየ ምርጫ የተመረጠ ፓርላማ |
በተመጣጣኝ ውክልና የተመረጠ ፓርላማ |
ሕግ ተርጓሚው |
ነፃ እና ገለልተኛ ፍርድ ቤት (አንዳንዶች ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት አላቸው።
በኢትዮጵያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ሥራ ነው) |
ብዙዎቹ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት እና ፍርድ ቤቶች |
ብዙዎቹ ፍርድ ቤቶች እና የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት |
ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት |
ጥንካሬው |
§
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪነቱ ለፓርላማ ነው §
በቀላሉ ከሥልጣን ሊነሳ ይችላል §
ትብብርን ያበረታታል |
§
የሥልጣን ክፍፍሉ ግልጽ ከሆነ ጥሩ ሚዛን ይኖራል §
ፕሬዚዳንቱ ቀጥታ የሕዝብ ውክልና ስለሚኖረው
ጠንካራ አመራር ሊፈጥር ይችላል |
§ የሁለቱን ስርዓቶች ጥንካሬ ያጣምራል § የመንግሥትን ወካይነት ያሰፋል |
§ የመንግሥቱ ቅቡልነት ይጨምራል § የሕግ የበላይነት እና ተጠያቂነትን ያበረታታል (???) § ግጭት ይከላከላል
§
የመራጮች ድምፅ ብክነት ይቀንሳል |
ድክመቱ |
§ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ እየተቀየረ የተረጋጋ መንግሥት ማቆም ሊቸግር ይችላል § የማይስማሙ ፓርቲዎች ጥምረት ሊያስከትል ይችላል |
§ ፕሬዚዳንቱ እና የፓርላማው ማጆሪቲ ከተለያዩ ፓርቲዎች ከሆኑ ውሳኔዎች ቅርቃር ውስጥ ሊገቡ
ይችላሉ። § ፓርላማው ፕሬዚዳንቱን ተጠያቂ የማድረግ አቅም ያጣል። |
§
የፕሬዚዳንቱ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን
ድርሻ እና ክፍፍል ግራ አጋቢነት §
የሁለቱንም ስርዓቶች ደካማ ጎን አጣምሮ ሊወስድ
ይችላል። |
§ የጋራ የፖለቲካ ማንነት ለመፍጠር ይቸግራል § ውጤታማ መንግሥት ማቋቋምን ያስቸግራል § የሁለት ፓርቲ ስርዓት ውስጥ ካልሆነ አይሠራም |
ምሳሌ አገራት |
እንግሊዝ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ጀርመን፣ ኢትዮጵያ |
አሜሪካ፣ ብራዚል፣ አርጀንቲና |
ፈረንሳይ፣ ራሺያ |
የለም |
የእያስጴድ ናሙና ያቀረበው የመንግሥት ዓይነት (form of government) “የመንግሥትን ቅቡልነት ሊጨምር ይችላል” የሚለው ሐሳብ ያስማማኛል። በተጨማሪም ተፎካካሪ አካላት የሥራ አስፈፃሚውን በጋራ ለመምራት በመገደዳቸው የተለየ ዓይነት የቁጥጥር እና ሚዛን ዕድል በመፍጠር ለሕግ የበላይነት እና ለተጠያቂነት መንገድ ሊከፍት ይችላል። ይሁንና በተፎካካሪዎቹ የሚመሠረተው መንግሥት የታለመለትን ዓይነት የጋራ የፖለቲካ ማንነት ያለው ኅብረተሰብ የመገንባት፣ ውጤታማ መንግሥት የማቋቋም፣ እና በስተመጨረሻም የአገረ መንግሥቱን ቅቡልነት በማሳደግ፣ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን መቻሉ ያጠራጥረኛል። እንደሚገመተው 1ኛ) ተፎካካሪዎቹ ተፃራሪ ፖሊሲዎችን ለማስፈፀም ለመራጮቻቸው ቃል በመግባት የሚወዳደሩ በመሆኑ፣ 2ኛ) ዕጩዎቹ የተለያየ ርዕዮተ ዓለም ወይም የፖለቲካ መሥመር የሚከተሉ ፓርቲዎችን የሚወክሉ ሊሆን ስለሚችል፣ 3ኛ) ተመራጩቹ በቀጣዩ ምርጫም ዳግም ለፉክክር ሊቀርቡ ስለሚችሉ ተጣጥመው ለመሥራት ይቸገራሉ። በዚህም እያስጴድ “ውጤታማ መንግሥት ማቋቋም” ያለውን ዓላማ እንዳይሳካ ሊያደርገው የሚችል የመንግሥት ዓይነት ይሆናል። ውጤታማ መንግሥት ደግሞ በተለይ በመልማት ላይ ላሉ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው።
የእያስጴድ ናሙና ሁለት አበይት ፓርቲዎች ይኖራሉ የሚል
እና የመራጮች ድምፅ አይከፋፈልም የሚል ቅድመ እሳቤም (presupposition) የያዘ ይመስለኛል። ይሁንና፣
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከተነሳን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ቢካሔድ ከሁለት በላይ ዕጩዎቹ ሊወዳደሩ የመቻል ዕድላቸው በጣም ከፍተኛ
ነው። በአንፃራዊነት ዴሞክራሲያዊ ነው የተባለው የ1997ቱ ምርጫም ቢሆን፣ ብዙው የመራጮች ድምፅ የተከፋፈለው፣ በሦስት ጥምረቶች፣
በኢሕአዴግ፣ ቅንጅት እና ኅብረት መካከል ነው። ማለትም ፕሬዚዳንቱን ከ50% በላይ ድምፅ እንዲያገኙ የሚያስገድደው የእያስጴድ ናሙና
ይህንን የበርካታ ዕጩዎች መኖር የሚያስከትለውን የድምፅ ብክነት ከግምት ውስጥ ያስገባ አልመሰለኝም። በመሆኑም፣ የትኛም እጩ ከ50
በመቶ በላይ የመራጮች ድምፅ ካላገኘ ችግሩ እንዴት ነው የሚፈታው? ወይም ደግሞ አሸናፊው ዕጩ ከ25 በመቶ በታች የመራጮች ድምፅ
ቢያገኝስ? ሌላው እያስጴድ ያልመለሰው ጥያቄ፣ ሕዝባዊ መሠረት ያለው ፓርቲ መገንባት ተአማኒነት
እና ተቀባይነት ያለው ምርጫ እንዲካሔድ ዋስትና የማይሰጥ መሆኑን ነው።
2.4. አገር ዐቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ እንደ መንገድ
እያስጴድ በአሁኒቷ ኢትዮጵያ ያለው ብቸኛው አቅም ያለው ፓርቲ ብልፅግና ብቻ መሆኑን ይገልጻል። ብልፅግና ከኢሕአዴግ የወረሰውን መዋቅር እና ሀብት የሚያንቀሳቅስ ከመሆኑም በላይ ከትግራይ በስተቀር ክልሎችንም ፌዴራል መንግሥቱንም ስለሚያስተዳድር፣ እንዲሁም ፓርቲው ከመንግሥት ቢሮክራሲ ጋር ስለተዋሐደ ብቸኛው አቅም ያለው ፓርቲ መሆኑ አያከራክርም። ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተቃራኒው በሐሳብም፣ በተግባርም እጅግ የተከፋፈሉ እና የተዳከሙ ከመሆኑም ባሻገር ባለፈው ምርጫ ሊፎካከሩ ይችላሉ ተብለው ከተጠበቁት ውስጥ ጥቂቶቹ በብልፅግና የሥልጣን ማጋራት ሰበብ የፓርቲያቸው ውስጣዊ አንድነት ተዳክሟል፣ ሌሎቹ ደግሞ በምኅዳሩ መጥበብ ከበፊቱ የበለጠ ተዳክመዋል። ስለሆነም ብልፅግናን መፎካከር የሚችል ፓርቲ የለም። እያስጴድ ግን ያንን ፓርቲ መፍጠር ይቻላል ብሎ በምክረ ሐሳቡ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ አጋርቷል። እኔ በእያስጴድ ሐሳብ አልስማማም፤ ምክንያቶቼን እንደሚከተለው አቀርባለሁ።
- ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለምን ለውጥ አያመጡም?
ኢትዮጵያ በሕገ መንግሥትዋ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን የምትቀበል ቢሆንም፣ በተግባር፣ በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ የአንድ ፓርቲ ስርዓትን የምትተገብር አገር ነች። ይሁንና ለይስሙላ እንዲንቀሳቀሱ የተተዉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ። እነዚህ ፓርቲዎች በውስጣዊ እና ውጪያዊ ተግዳሮቶች ሳቢያ በጣም የተከፋፈሉ፣ ደቃቃ፣ እና እንኳን በፌዴራል ደረጃ፣ የክልል እና የዞን ምክር ቤቶችን ማሸነፍ የሚቸግራቸው ናቸው። ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ደካማ መሆን ከሚጠቀሱት ምክንያቶች ውስጥ የፖለቲካ ምኅዳሩ መጥበብ፣ የፓርቲዎቹ ንቁ እና ባለ ራዕይ አባላት ማፍራት አለመቻል፣ ቋሚ የሀብት ምንጭ አለመኖር፣ እና የአካታችነት ችግር ናቸው። የእያስጴድ ምክረ ሐሳብ እነዚህን ተግዳሮቶች በምን እና እንዴት ተሻግሮ ከዚህ በፊት ያልተሳካውን አማራጭ መሆን የሚችል አገር ዐቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ መመሥረት እንደሚችል ግልጽ አይደለም።
- የፖለቲካ ምኅዳሩ መጥበብ፤ የችግሩ ዋነኛ መንስዔ የፖለቲካ ምኅዳሩ ሲሆን፣ ይህም ገዢው ፓርቲ ሥልጣኑን ተገን በማድረግ የመንግሥት መዋቅርን እና ሀብትን በመጠቀም የመሰብሰብ፣ ደጋፊዎቻቸውን የማንቀሳቀስ፣ ሀብት የመሰብሰብ፣ እና የማደራጀት አቅም እንዳይኖራቸው አድርጓል። ይህም ጠንካራ ፓርቲ አድጎ እንዳይወጣ እና ተገዳዳሪ (ወይም አማራጭ) እንዳይሆን፣ መንግሥትም በሕዝብ ይሁንታ ሥልጣን ላይ እንዳይወጣ እና እንዳይወርድ እንቅፋት ሆኗል። የፖለቲካ ምኅዳሩ አማራጭ ፖለቲካ ማብቀል ያልቻለበት ዋነኛው ምክንያት መንግሥት እና ፓርቲው አንድ በመሆናቸው ምክንያት ነው። ኢትዮጵያ በገቢር የአንድ ፓርቲ ስርዓት ነች ስንል ገዢው ፓርቲ የማይቀየር ነው ማለቴ (ብቻ) አይደለም። ይልቁንም፣ እያንዳንዱ የቢሮክራሲው ቁልፍ ቦታ በሙሉ በፓርቲ ሹመኞች የተያዘ እና ውሳኔዎችም በፓርቲ ደረጃ የሚወሰኑ በመሆናቸው ነው። ገዢው ፓርቲ የፈለገውን ሕግ ያወጣል፣ ሕጉን በፈለገው ጊዜ ይተገብራል። ሕግ ቢጥስም የሚጠይቀው የለም። ተቃዋሚዎች የሚወዳደሩት ከዚህ ሲያሻው የመንግሥትን ሀብትና መዋቅር፣ ሲያሻው ደግሞ የገዢ ፓርቲነት ፕሪቪሌጁን ተጠቅሞ ብዙ ደጋፊ መግዛት ከሚችል ፓርቲ ጋር ነው።
- ንቁ እና ራዕይ ያለው አባል ማፍራት አለመቻል፤ ተቃዋሚዎች ፓርቲ ለማቋቋም እና ለመምራት አባሎቻቸው የግል ሕይወታቸው ላይ የሚመጣ ፈተና (ባብዛኛው የእስር) ለመቀበል መዘጋጀት አለባቸው፤ ይህንን እያወቁ አባል መሰብሰብ እጅግ አስቸጋሪ ነው። ራሳቸውን ከመንግሥት የስለላ መዋቅር እና ሰርጎ ገብነት መከላከልም እንዲሁ ተጨማሪ ሸክማቸው ነው፤ ይህም አባላት እርስበርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩ እና ውስጣዊ የሐሳብ ልዩነትን እንዳይታገሱ ያደርጋቸዋል። በእነዚህ ሁሉ ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው የሚወጡት የፓርቲ መሪዎች በተደጋጋሚ እንደሚባለው “አኩራፊ ወጣቶች” እና “ጊዜ ያላቸው ጡረተኞች” ብቻ ይሆናሉ። እንደዚህ ዓይነት ፓርቲዎች የብዙዎችን ቀልብ መሳብ አይችሉም። ባለፉት ሁሉም ምርጫዎች ውስጥ ተቃዋሚዎች የቱንም ያህል ጩኸት ቢያሰሙ ለፌዴራል እና ክልል ምክር ቤቶች የሚያቀርቧቸውን ዕጩዎች አጥተው ሲቸገሩ ያልተስተዋለበት ጊዜ የለም።
- አማራጭ ፖሊሲ የላቸውም፣ ቢኖርም አይታወቅም፤ ብዙዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚታወቁት በሚመሯቸው ታዋቂ ግለሰቦች እና በገዢው ፓርቲ እርምጃዎች ላይ በሚያወጧቸው የተቃውሞ መግለጫዎች ነው። ከዚህ ውጪ ይህንኛው የፖለቲካ ፓርቲ ከዚያኛው የሚለ፟የው በዚህ ነው ለማለት የሚያስችል ፖሊሲ የላቸውም፤ ቢኖራቸውም አይታወቅም። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የሚሰበስቧቸው አባላትም ገዢው ፓርቲ ላይ ባላቸው ተቃውሞ ላይ የተመሠረተ ስለሚሆን የፖሊሲ አንድነት የላቸውም።
- ቋሚ የሀብት ምንጭ አለመኖሩ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ዋነኛ የገቢ ምንጭ ከአውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ተወላጆች የሚሰበሰብ ገንዝብ ነው። የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ይህንን የሀብት ምንጭነቱን ተመክቶ ፓርቲዎቹን በፈለገው አቅጣጫ ሲዘውራቸው፣ አልያም ተፈላጊነታቸውን ሲያኮሰምነው በተደጋጋሚ ተመልክተናል። ይህ የገቢ ምንጭ ጥገኝነት ለፓርቲዎቹ መከፋፈል እና አንድ መሆን አለመቻልም እንዲሁ አስተዋፅዖ አድርጓል። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ከዚህ ውጪ ያላቸው የመንቀሳቀሻ ሀብት ምርጫ ቦርድ የሚሰጣቸው ገንዘብ ነው። በዚህም ምክንያት እያስጴድ በጽሑፉ የሚጠቅሰውን ዓይነት የልማት ሥራዎች ለመሥራት እና ሁለት የምርጫ ዘመን (terms) አባላት እያደራጁ እና እያነቁ ማቆየት ቀርቶ የፓርቲውን የቢሮ ኪራይ እና መሠረታዊ የጽሕፈት እና ጥበቃ የመሳሰሉ ሥራዎችን ወጪ የሚሸፍንበት ቋሚ የገቢ ምንጭ ይቸግረዋል። ፓርቲው ተደራሽነቱን ለማስፋት በርካታ ቅርንጫፎችን የሚከፍት ከሆነ ደግሞ ችግሩ የተባባሰ ይሆናል።
- የአካታችነት ችግር፤ ሌላውና ትልቁ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ችግር አካታችነት ነው። ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአካባቢ ዕድር ይመስላሉ፤ ብዙዎቹ አመራሮቻቸው እና አባሎቻቸው ከአንድ ሰፈር የተሰባሰቡ ናቸው። አገር ዐቀፍ ወይም ክልላዊ ተብለው የተሰባሰቡት ፓርቲዎች በመሪው ስብዕና ተማርከው ይመስላል። ብዙዎቹ “የኢትዮጵያ...” ተብለው የተመሠረቱ አገር ዐቀፍ ፓርቲዎች ኦሮሚያ፣ ሶማሊ፣ ወይም ትግራይ ክልሎች ውስጥ ተቀባይነትም ሕዝባዊ መሠረትም የላቸውም። በተመሳሳይ የብሔረሰብ ፓርቲዎችም የጎጥ አባላት የሚበዙባቸው ናቸው። በብሔረሰብ እና በአካባቢ ጎጥ ከመከፋፈልም በተጨማሪ ፓርቲዎቹ የተለያዩ እምነት ተከታዮችን በአንድ ጣሪያ ሥር የማስተናገድም ችግር አለባቸው። ሴቶችን ማካተት ደግሞ ጭራሹኑ የማይታወሳቸው ነገር ይመስላል። የአካታችነት ችግር የከፋ የሚሆነው፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ችግሩን የሚገባውን ያህል ትኩረት ሰጥተውት እና ስትራቴጂ ቀርፀው ሊቀርፉት ሲንቀሳቀሱ ስለማይታይ ነው።
- ውስጣዊ ዴሞክራሲ አለመኖር፤ ብዙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከገዢው ፓርቲ የሚለዩት በሥልጣን ላይ ባለመሆናቸው ብቻ ይመስላል። ፓርቲዎቹ መሪዎቻቸውን ለመለወጥ ይቸገራሉ፤ ለመለወጥ ሙከራ ሲደረግም ፓርቲው ይከፋፈላል። የውስጥ አሠራራቸው በአብዛኛው በአንድ ግለሰብ ላይ የተመሠረተና አምባገነናዊ ነው። ከመሪው ቀጥሎ በፓርቲው ውስጥ የሚታወቅና ተቀባይነት ያለው ሁለተኛ አመራር ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ነው።
እነዚህን ችግሮች ተጋፍጦ ጠንካራ አገር ዐቀፍ ፓርቲ ለመመሥረት፣ በመጀመሪያ የፖለቲካ ምኅዳሩ መቀየር ይኖርበታል። የፖለቲካ ምኅዳሩ መቀየር ተቃዋሚዎች እና ገዢው ፓርቲ በእኩል ሜዳ እንዲጫወቱ ያስችላቸዋል። በዚህም ተቃዋሚዎች አባላትን ያለስጋት እና ብዙ ፈተና መመልመል፣ ከተለያዩ የአገር ውስጥ ምንጮች ሀብት ማሰባሰብ፣ ከተለያዩ ኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመነጋገር አማራጭ ፖሊሲ መቅረፅ እና ሌሎችም ውስጣዊ (የአካታችነት እና ዴሞክራሲያዊነት) ችግሮቻቸውን በመቅረፍ በጊዜ ሒደት ነጥሮ የሚወጣ አማራጭ ፓርቲ እንዲኖር ማድረግ ይችላሉ።
ቅድሚያ የልኂቃን ድርድር፤ ለምኅዳሩ መስፋት ደግሞ፣ እያስጴድ በመፍትሔ አማራጩ የሚያነሳው (ነገር ግን እምብዛም ገፍቶ ያልተከራከረበት) “የልኂቃን ድርድር” ወሳኝ ሚና ይጫወታል። የልኂቃን ድርድሩ በጥንቃቄ እና በገለልተኛ አካላት የተመረጡ ቁልፍና ሕዝባዊ መሠረት ያላቸው የፖለቲካ ልኂቃን የሚሳተፉበት መድረክ (“የሽግግር መድረክ”) የሚከናወን ሊሆን ይችላል። መድረኩ የመንግሥት የዴሞክራሲ ተቋማትን (ምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ እምባ ጠባቂ፣ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር፣ የሚዲያ እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ተቋማት) መሪዎችን በጋራ ዕጩ አድርገው የሚሾሙበት፤ አስፈላጊ ከሆነም፣ የፌዴራል እና የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮችንም መድረኩ ገለልተኝነታቸውን በተስማማባቸው ሙያተኞች እንዲሰይም ማድረግ ይቻላል። በተጨማሪም፣ መድረኩ ምርጫና ምርጫ ነክ የሆኑ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ሕግጋት (እና የተቋማት አወቃቀር) ክለሳ ጉዳይ ላይ በጋራ የሚደራደሩበት እና የሚወስኑበት፣ ውሳኔያቸውንም በበላይነት የሚያስፈፅሙበት ሥልጣን እንዲኖረው በማድረግ በቀጣይ ፍትሐዊ ምርጫ እንዲዘጋጅ እና ገዢው ፓርቲ ሥልጣኑን ለማስጠበቅ፣ ተቃዋሚዎቹ ሥልጣን ለመቀማት የሚደረጉ ነውጥ አዘል ንቅናቄዎችን በሙሉ ለማስቆም የሚስማሙበት መድረክ ሆኖ መዘጋጀት ይኖርበታል።
መድረኩ በሕግ የተደነገገ ጊዜያዊ (ምናልባት ለሦስት ዓመታት የሚዘልቅ) ሥልጣን ኖሮት አገራዊ መረጋጋት ሳይናጋ ሰላማዊ የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ይችላል። ይህ የሚደረገው ሌሎች የመንግሥት አገልግሎት ዘርፉ ላይ ተቀማጩ መንግሥት እና ቢሮክራሲው በገልለተኝነት ሥራውን እንዲመራ የሚያስችለው ሥልጣን ብቻ ተሰጥቶት ይሆናል። ነገር ግን ይህንን ተቀማጩ መንግሥት በቀላሉ አይቀበለውም። እንዲቀበለው ለማድረግ ሥልጣኑን እና የፓርቲ ኅልውናውን ስጋት ውስጥ የሚከት ሰላማዊ ሕዝባዊ ንቅናቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
- ሕዝባዊ ንቅናቄዎች ለልኂቃን ድርድር
ኢትዮጵያ ውስጥ በምርጫ መንግሥት የሚቀየርበት መንገድ የለም። በምርጫ መንግሥት ካልተቀየረ ደግሞ መንግሥቱ ሕዝባዊ ይሁንታም ይሁን ቅቡልነት አይኖረውም። በዚህ የተማረሩ ዜጎች ደግሞ ወደ ትጥቅ ሊገቡ ይችላሉ። የትጥቅ ትግልም ቢሆን ሕዝብን ደም ያስለቅሳል እንጂ የብዙኃን ይሁንታ ያለው ስርዓት አያዋልድም።
- ምን ዓይነት የለውጥ ዓይነት?
V-Dem Project በመባል የሚታውቅ የስዊድኑ ጎተንበርግ ዩንቨርሲቲ የሚሰበስበው ዓለም ዐቀፍ የፖለቲካ ሒደት ዳታ አለ። ይህንን ዳታ በመጠቀም እ.አ.አ ከ2000 እስከ 2020 አምባገነናዊ አገራት ውስጥ የተከሰቱ የፖለቲካ ለውጦችን ለመተንተን በናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዴሞክራሲ የተሠራ (ያልታተመ) ጥናት አለ። ጥናቱ የለውጥ ዕድሎች ብሎ የዘረዘራቸው አምባገነኑ ያልተጠበቀ የምርጫ ሽንፈት ሲገጥመው፣ ሕዝባዊ ተቃውሞ ሲገለብጠው፣ የምርጫ ውዝግብ ሲነሳበት፣ በትጥቅ ትግል ሲሸነፍ፣ በመፈንቅለ መንግሥት ሲወርድ፣ ወይም በድንገት ሲሞት የተከሰተውን ለውጥ የሚተነትን ነው።
በጥናቱ መሠረት አምባገነኑ ወይም የመረጠው ተተኪ (ብዙ ጊዜ በፕሬዚዳንታዊ ስርዓት) በድንገት ከተሸነፈባቸው 22 አጋጣሚዎች ውስጥ 11ዱ በአምስት ዓመት ውስጥ ዴሞክራሲያዊ እመርታ አሳይተዋል። በሕዝባዊ ተቃውሞ ደግሞ ከተከሰቱ 11 አጋጣሚዎች ውስጥ አምስቱ በአምስት ዓመት ውስጥ ዴሞክራሲያዊ እመርታ አሳይተዋል። በምርጫ ውዝግብ (ከ9 አጋጣሚዎች አምስቱ)፣ በትጥቅ ትግል (ከ9 አጋጣሚዎች ሦስቱ)፣ በመፈንቅለ መንግሥት (ከ4 አጋጣሚዎች ዜሮ)፣ በድንገተኛ ሞት ወይም ጤና ማጣት (ከ23 አጋጣሚዎች ውስጥ አንዱ) በአምስት ዓመታት ውስጥ የምርጫ ዴሞከራሲያዊ እመርታ አሳይተዋል።
ከፓርላመንታዊ ስርዓቶች ይልቅ፣ ፕሬዚዳንታዊ ስርዓቶች ለአምባገነንነት ተጋላጭ ናቸው። ነገር ግን ፕሬዚዳንታዊ ስርዓቶች ላልተጠበቀ የምርጫ ሽንፈትም ያላቸው ተጋላጭነት ከፓርላመንታዊ ስርዓቶች የሰፋ ነው። አምባገነን ፕሬዚደንቶች በምርጫ ከተሸነፉ በኋላ ወይም ውዝግብ ከተነሳ ዴሞክራሲ የመወለድ ዕድሉ አንፃራዊ ሰፊ ነው (ከ31 አጋጣሚዎች 16ቱ)። የሕዝባዊ ንቅናቄዎችም ይህንን ዕድል ያሰፉታል። በዚህ መሠረት “የእያስጴድን ናሙና” ለማዋለድ፣ ቅድሚያ መንግሥትን ለለውጥ (ወይም ለልኂቃን ድርድር) የሚጋብዙ (ወይም የሚያስገድዱ) ሕዝባዊ ንቅናቄዎች ያስፈልጉናል።
- ፍኖተ ካርታ፦ ለውጡ እንዳይሰረቅ
ከምርጫ 97 መክሸፍ በኋላ ነፃ እና ገለልተኛ ብዙኃን መገናኛዎች እና ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ታፍነው፣ ሐሳብን የመግለጽ፣ የመሰብሰብ እና የመደራጀት መብቶች ተገድበው፣ ፓርቲዎች በተዳከሙበት ጊዜ ለውጥ ማምጣት የቻሉት ቅርፅ አልባ ንቅናቄዎች ናቸው። የኦሮሚያ እና የአማራ ተቃውሞዎች ይሄ ነው የተባለ ተቋም አልነበራቸውም። መንግሥት ሊያስቆማቸው ወይም ሊያፍናቸው የሚችልበት መንገድ አልነበረውም። ስለዚህ ጠንካራ ይመስል የነበረው ፓርቲ ተፍረከረከ። ነገር ግን ለውጡ በፓርቲው ሌሎች አባላት በመጠለፉ የተጠበቀው ለውጥ ሳይመጣ ቀረ። በተመሳሳይ፣ ከሃምሳ ዓመት በፊት አብዮቱ የተወለደው ባለቤት እና ቅርፅ በሌለው ንቅናቄ ነበር። ያም ለውጥ በደርግ መኮንኖች ተጠልፎ ሙሉ ድል ሳያስገኝ ቀረ። (እዚህ ጋር አማራጭ ፓርቲዎች አያስፈልጉም እያልኩ እንዳልሆነ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እፈልጋለሁ። ነገር ግን ለውጥ ለማምጣት ለሚረዳው ንቅናቄ ግብዓት ይሰጣሉ እንጂ በዚህ ዐውድ ለውጥ ማምጣት አይችሉም እያልኩ ነው።)
የለውጥ ዕድሎች ሲከስቱ ብዙ ጊዜ ድል እንደመጣ ይቆጠራል። እውነተኛው ትግል ግን የሚጀምረው የለውጥ መስኮቱ ሲከፈት ነው። በዚህ ጊዜ የተፈጠረውን የሥልጣን ክፍተት (power vacuum) ሥልጣን ለመቆናጠጥ አድፍጠው የሚጠብቁ አካላት ይጠልፉታል። ጥያቄው፣ ከፓርቲ ይልቅ ለመንግሥት የአፈና ስርዓት ያልተመቸ ንቅናቄ ነው የሚያስፈልገው የሚለው አይደለም። ንቅናቄዎቹ ለውጥ ካመጡ በኋላ እንዴት ለውጡ እንዳይሰረቅ መጠበቅ ይቻላል የሚለው ነው።
“የልኂቃን ድርድሩ” ቁልፍ ሚና የሚጫወተው ለዚህ ነው። ንቅናቄዎቹ ከዚህ በፊት እንደነበረው ከመንግሥት ጉያ የሚወጡ አዲስ ጨቋኝ አፈ ቀላጤዎችን አምኖ እንዳይቆም፣ ይልቁንም የልኂቃን የድርድር መድረክ እንዲመሠረትና ውጤት እንዲያመጣ ያለማቋረጥ ግፊት ማድረግ አለበት። በዚህም፣ 1ኛ) በሽግግር ወቅት የሚፈጠረው ቀውስ (collapse of order) እንዳይከሰት፣ 2ኛ) የለውጥ አጀንዳዎች በግለሰብ ወይም በአንድ ቡድን ብቻ እንዳይወከሉ፣ 3ኛ) ለውጥ በአንድ ጀንበር ስለማይመጣ የለውጥ መዋቅር (framework) በመድረኩ እንዲቀየስ ማድረግ ይቻላል። ይሁንና፣ እነዚህ ግቦች እንዲሳኩ ንቅናቄው ስሜቱ ሳይበርድ እንዲሔድ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ንቅናቄውን በተወሰነ መልኩ መቆጣጠር ያስፈልጋል። ይህንን ለማድረግ ፍኖተ ካርታ ያስፈልጋል።
አሁን ባለው ሁኔታ መንግሥት የለውጥ ንቅናቄዎችን በሙሉ በሽብርተኝነት ሥም የሚያፍንበት ዕድል ሰፊ ነው። ነገር ግን ለውጥ አይቀሬ ነገር ነው። አምባገነናዊ አስተዳደሮች ደግሞ ያለምንም ጥርጥር ይለወጣሉ። በምትካቸው የሚመጣው ግን እንደነርሱው አምባገነን መንግሥት ስላለመሆኑ ግን ለውጥ ብቻውን ዋስትና አይሰጥም። ስለሆነም የለውጥ እንቅስቃሴዎች (ሕዝባዊ ንቅናቄዎች) በወል የሚመሩበት ፍኖተ ካርታ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት እንዲሁም በተለያዩ ጊዜ እየመጡ የሚሔዱ መንግሥታት ችግር ምን፣ ምን ናቸው? የተለያዩ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ክፍሎች ስለ ኢትዮጵያ ያላቸው ራዕይ ምን ይመስላል? የሚስማሙበት እና የሚቃረኑት በምንድን ነው? ተቃርኗቸውን የሚያስታርቀው መዋቅራዊ ለውጥ እንዴት ያለ ነው? በተጨማሪም፣ የረዥም ጊዜ ውዝግብ የሆኑ ጉዳዮች፣ (እንደ ምሳሌም፣ የፌዴራሊዝሙ አወቃቀርና አስተዳደር ወሰን ጉዳይ፣ የመንግሥት ቅርፅ ጉዳይ፣ የበይነመንግሥታዊ ግንኙነት ጉዳይ፣ የቋንቋ ጉዳይ፣ የመንገንጠል መብት ጉዳይ፣ የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ፣ የኢኮኖሚ ሞዴል ጉዳይ) የመሳሰሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ምሁራን፣ አክቲቪስቶች፣ የፖለቲካ ተዋንያን፣ እና ሌሎችም ተሰባስበው የሚነድፉበት እና ይህንንም የሚያኸዝቡብት (popularize) የሚያደርጉበት መድረክ መፍጠር አለባቸው። ይህንን በተለይ ደኅነነቱ በተጠበቀ ሥፍራ (በአውሮፓ እና አሜሪካ አሕጉሮች) ማድረግ ይቻላል።
የሽግግር ፍኖተ ካርታውን የሚያዘጋጁት እና የሚያኸዝቡት
ሰዎች በሕዝባዊ ንቅናቄው ሊሳተፉም ላይሳተፉም ይችላሉ። ነገር ግን ፍኖተ ካርታው በተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የፖለቲካ
ድርጀቶች፣ የፖለቲካ ልኂቃን፣ አክቲቪስቶች፣ መንግሥትም ጭምር ተቀባይነት እንዲያገኝ ሊወተውቱ ይችላሉ። በርካታ ተዋናዮች ዘንድ
ተቀባይነት ማግኘት ከቻለ፣ የለውጥ ኃይል ሲከሰት ያንን ከመተግበር ውጪ አማራጭ አይኖረውም። በአብዮቱ ጊዜ “መሬት ላራሹ” የሚለው
ጥያቄ ገናና በመሆኑ፣ ደርግ ያንን ሕዝባዊ ቅቡልነት ለማግኘት እንደተጠቀመበት ሁሉ፣ ፍኖተ ካርታውን መተግበር የመጪዎቹ ኃይሎች
የውዴታ ግዴታ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል።
3. ተጨማሪ ሐሳቦች
የእያስጴድ አንብሮ በርካታ ወሳኝ ቁም ነገሮችን ሲዳስስ በተለይ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ መዋቅራዊ ችግሮች የሆኑ አንዳንድ ሊዘነጉ የማይገቡ ነገሮችን ሳያነሳ አልያም በጨረፍታ በመዳሰስ ብቻ አልፏቸዋል። ስለዚህ፣ በዚህ ርዕስ ሥር የማነሳቸው ተጨማሪ ሐሳቦች፣ የተረጋጋ አገረ መንግሥት ማኖር አለመቻላችን መሠረታዊ መንስዔዎች ሆነው በእያስጴድ አንብሮ ያልተዳሰሱ ብዬ የማምናቸውን ነው።
የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የችግሮች ሁሉ የበላይ ችግር፣ ከችግሮቹ መንስዔ
ይልቅ ምልክቱን ማከም (treating the symptoms) ነው ብዬ አምናለሁ። ከግማሽ ምዕተ ዓመት
በፊት የኢትዮጵያ ልኂቃን የኢትዮጵያውያንን ጥያቄ በመደብ እና ብሔረሰብ መነፅር፣ አልፎ አልፎም ድርብርብ ጥያቄዎችን በማንሳት መልሶችን
አፈላልገዋል። የመሬት ላራሹ አዋጅ እና የኢትዮጵያ ብሔርን መሠረት ያደረገ ፌዴራሊዝም ምሥረታዎች ያኔ የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ
የተደረጉ ሙከራዎች ናቸው። የመፍትሔ እርምጃዎቹ የኢትዮጵያውያንን ሕመም ለተወሰነ ጊዜያት (ወይም የተወሰነውን ሕመም ብቻ) ካስታገሱ በኋላ ሕመሙ መልሶ ሲያገረሽ ወይም የጎንዮሽ ጉዳቱ
ተባብሶ ሲወጣ እየተስተዋለ ነው። ስለዚህ መልስ ከመስጠታችን በፊት “የችግሩን መንስዔ አውቀነዋል ወይ? ለመሆኑ ጥያቄው ምንድን ነው?” ብለን መጠየቅ
ያለብን ይመስለኛል።
3.1. ማንነትን ነፃ ማውጣት
የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም፣ ደጋፊም ተቃዋሚም አለው። ትሩፋቶቹን እያመሰገኑ፣ ጉዳቶቹን የሚያወግዙ ጠርዝ ያልመረጡ ተመልካቾችም አሉት። ነገር ግን ከሦስት ዐሥርት ዓመታት ተሞክሮ በኋላ የፌዴራል ስርዓቱ መዋቅራዊ ችግሮች በግልጽ እየታዩ ስለሆነ ትሩፋቱን ተቀብሎ፣ ጉዳቶቹን ለማረም “ተሐድሶ” የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነን። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መዋቅር ያልተማከል አስተዳደርን አስተዋውቋል። ዜጎች ባሕላቸውን እንዲያስድጉ እና በኩራት እንዲያስተዋውቁ ዕድል ሰጥቷል። በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመማር፣ የመሥራት፣ እና የመዳኘት ዕድሎችንም ሰጥቷል። ነገር ግን ክልሎች በብሔር መስመር በመፈጠራቸው ሳቢያ፣ ብሔርተኝነት እንዲጦዝ እና “አንድ አገራዊ የፖለቲካ ማንነት” በመፍጠር ፈንታ፣ “ተገዳዳሪ የፖለቲካ ማንነቶች” ተፈጥረዋል። ተገዳዳሪ የፖለቲካ ማንነቶች መፈጠራቸው ደግሞ ድሮ፣ ድሮ በግጦሽ መሬት እና በመጠጥ ውሃ በመንደር ውስጥ ተወስነው ይቆዩ የነበሩ ግጭቶች ክልላዊ (ብሔር ተኮር) ሆነው አድርገዋል። ግጭቶች ከፌዴራሊዝሙ መተዋወቅ በኋላ ያለውን የግጭት ትሬንድ በሚከተለው ግራፍ መመልከት እንችላለን።
የግራፉ ምንጭ፤ The Moving Average Trend for the frequency of ethnic conflicts in Ethiopia 1991-2016 (Zerihun & Samuel, 2019).
ይህ መዋቅራዊ ችግር ያስከተለው የግጭቶች ደረጃ መጨመር “የተረጋጋ አገረ መንግሥት ለማኖር” ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል። በተጨማሪም፣ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም “ቀዳማይ ኩነኔ” (original sin) የሚባለው የዘውግ/ብሔር ማንነትን ብቸኛው እና ዋነኛው ማንነት አድርጎ ማቅረቡ ነው። በ30 ዓመታት ውስጥ የዘውግ ማንነት (ethnic identity) ወደ ሥልጣን ለመቅረብም ይሁን ሀብት ለማካበት ዋነኛ ምንጭ ሆኗል። ነገር ግን 1ኛ) ዜጎች የሚኖራቸው ማንነት የዘውግ ብቻ አይደለም፤ የዘውግ ማንነታቸውም ከሌሎችም ማንነቶቻቸው (ምሳሌ፣ ፆታ፣ እምነት፣ የኢኮኖሚ መደብ፣ የትውልድ ሥፍራ፣ ወዘተ) የበለጠ አስፈላጊ መሆን የለበትም። ነገር ግን የኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ናሙና (model) የዘውግ ማንነትን ነፃ ለማውጣት ሲል ሊሎች ማንነቶችን ደፍቋል። ከዚያም በላይ፣ የዘውግ ማንነት ብያኔው የዜጎችን ነፃ ፈቃድ ማዕከል ያደረገ ስላልሆነ ጠባብና አግላይ ነው።
- የመንግሥትና ሕዝብ ማኅበራዊ ውል፤ ሕገ መንግሥት የመንግሥት ኃይሎች ከዜጎች የሕዝብ ኃይሎች ጋር በመብቶች እና ግዴታዎቻቸው ዙሪያ የሚገቡት ቃል ኪዳን ሰነድ ነው። የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ከብዙ በሲቪክ እሴቶች ከተጻፉ ሕገ መንግሥቶች በመለየት “እኛ ኢትዮጵያውያን...” ብሎ በመጀመር ፈንታ “እኛ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች፣ እና ሕዝቦች…” ብሎ ነው የሚጀምረው። ይህ ከላይ ከላይ ሲመለከቱት አደገኛ አይመስልም። ነገር ግን የቃል ኪዳን ሰነዱ በመንግሥት እና በብሔረሰቦች መካከል የተገባ ቃል ኪዳን እንዲሆን ያደርገዋል። ሕገ መንግሥቱ ምንም እንኳን የግል ነጻነትን የሚደነግጉ አንቀፆች ቢኖሩትም፣ ዜጎቹን በብሔረሰብ ማንነታቸው እንጂ እንደ ባለ ብዙ ማንነት ነጠላ ዜጋ ሊያውቃቸው አይፈልግም፤ የኢትዮጵያ ዜጋ ለመሆን መጀመሪያ ግለሰብ ሳይሆን፣ የብሔረሰብ አባል መሆን ይጠይቃል። ይባስ ብሎ ብሔረሰባዊ ማንነት ደግሞ የሚበየነው በተባዕታዊ የዘር ሐረግ መሆኑ የበለጠ የዜግነት መንገዱን ጠባብ ያደርገዋል። እንደ ስዊዘርላንድ ያሉ ባለብዝኃ ቋንቋ አገራት፣ ሕገ መንግሥታቸው “እኛ ስዊሳውያን እና ካንቶኖች…” ብሎ ይጀምራል። “እኛ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች (ክልሎች)...” ብሎ እንደመጀመር ነው። ዜግነትን ከማንነት ነፃ ማውጣት እና ዜጎች ማንነታቸውን የመበየን ነጻነት በማጎናፀፍ ከአንድ በላይ ማንነት እንደሚኖራቸው ከግምት ውስጥ ማስገባት እና በማናቸውም ሁኔታ ዜጎች የሚያስቀድሙት ማንነት ሊኖራቸው እንደሚችል እና ይህም ቋሚ እንደማይሆን ከግምት ውስጥ ያስገባ ማኅበራዊ ውል ያስፈልጋል።
- የቋንቋ ፖሊሲ፤ ኢትዮጵያ ብሔረሰባዊ ቋንቋን መሠረት ያደረገ ፌዴራሊዝም እየተከተለች ለረዥም ጊዜ የቋንቋ ፖሊሲ አልነበራትም። አሁንም ባደባባይ ከሚታወቀው ይልቅ በጓዳ የሚተገበረው የቋንቋ ፖሊሲ ይበዛል። ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት፣ በቋንቋ መማር እና መሥራት ዋነኛ የፌዴራሊዝሙ ትሩፋት ተብሎ ይጠቀሳል። ይሁን እንጂ የቋንቋ ፖሊሲውን ለመተግበር የግድ በብሔረሰብ መሥመር የተሠመረ ድንበር አያስፈልግም። ስዊዘርላንድን በምሳሌ ከወሰድን በአራት የቋንቋ ቀጠናዎች ውስጥ ያሉ 26 ካንቶኖች (እኛ ክልል የምንላቸው ዓይነት ራስ ገዝ /autonomous/ ግዛቶች) አሏት። ብዙ ካንቶኖች ተመሳሳይ ቋንቋ ይናገራሉ። ጀርመንኛ፣ ፈረንሳይና ጣልያንኛ የፌዴራል መንግሥቱ እኩል ደረጃ ያላቸው ብሔራዊ ቋንቋዎች ናቸው፤ ሆኖም፣ የሮማንሽ ቋንቋ ተናጋሪዎችም የፌዴራሉን መንግሥት አገልግሎት በቋንቋቸው ማግኘት ይችላሉ። ካንቶኖቹም የየራሳቸውን ቋንቋ የመምረጥ ነፃነት አላቸው። ብዙዎቹ አንድ የሥራ ቋንቋ አላቸው። ከፊሎቹ ደግሞ ሁለት የሥራ ቋንቋ አላቸው። ለምሳሌ፣ ጀርመንኛ ቋንቋ የ17 ካንቶኖች ብቸኛ የሥራ ቋንቋ ሲሆን፣ በሦስት ካንቶኖች ደግሞ ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ ነው። ግራውቡንደን (Graubünden) የተሰኘ ደግሞ ሦስት ቋንቋዎች አሉት። የስዊዘርላንድን የቋንቋ ብዝኃነት አስተዳደር ለኢትዮጵያ ሁለት ምሳሌ ይሰጣል፤ አንደኛ፤ ተመሳሳይ ቋንቋ መናገር የግድ በአንድ የአስተዳደር ወሰን መከለልን አይጠይቅም፣ ሁለተኛ፤ ፌዴራሉም ይሁን ክልሎቹ በጥናት ተመሥርተው አንድ፣ ሁለት ወይም ሦስት ቋንቋዎችን የሥራ ቋንቋቸው ማድረግ ይችላሉ።
- የራስ ገዝነት ደረጃዎች እንደየሁኔታው፤ የኢትዮጵያ ብሔርን መሠረት ያደረገ ፌዴራሊዝም ሕዳጣንን የበለጠ ሕዳጣን፣ የዳር አገርን የበለጠ የዳር አገር አድርጓልም ይባላል። የቀድሞውን የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልልን ያየን እንደሆን 54 ያህል ብሔረሰቦች ያሉት ሲሆን፣ ሁሉንም ብሔረሰቦች ራስገዝነት ለመስጠት ልዩ ዞን፣ ልዩ ወረዳ እየተባለ ተሸንሽኖ ነበር። ይህ አስተዳደራዊ ፋይዳውም (relevance) ይሁን ውጤታማነቱ (effectiveness) እጅግ አከራካሪ ነው። በዚህም ምክንያት ሁሉም ክልሎች አንድ ዓይነት የራስገዝነት (autonomy) ደረጃ እና አስተዳደር ሊኖራቸው የግድ አይሆንም። ክልሎቹ እንደየፍላጎታቸው እና እንደሚያስፈልጋቸው ዓይነት ጥበቃ የተለያየ ራስገዝነት ደረጃ ሊኖራቸው ይችላል። በካናዳ ፌዴሬሽን ከዐሥሩ ክልሎች ኪዩቤክ የተለየ የራስገዝነት ደረጃ አላት፤ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሕዝቧ “የተለየ የማኅበረሰብ” ክፍል ተድርጎ ይቆጠራል። ሌላው ቀርቶ ከብሔራዊ የጡረታ ዕቅድ የተለየ የጡረታ ቋት ያላት ኪዩቤክ ብቻ ነች። ተመሳሳይ አሠራሮች፣ ቤልጂየም እና ሕንድ ውስጥም አሉ።
- የቋንቋ አጠቃቀም፤ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም አንዱና ዋነኛው የቀውስ መንስዔው የቋንቋ አጠቃቀሙም ጭምር ነው። “ክልል” የሚለው ቃል ጀምሮ፣ የብሔረሰብ መጠሪያዎች ለክልሎች መሰጠታቸው የብሔረሰቡን ተወላጆች ከዚያ ግዛት ጋር ያቆራኝ ይመስላል (አማራ ክልል፣ ሶማሊ ክልል፣ ወዘተ።)። የቋንቋ አጠቃቀሙ ወደ ወረዳ እና ዞኖችም ይወርዳል። አልፎ ተርፎም የክልል ሕገ መንግሥቶች “ነባር” እና “መሥራች” የመሳሰሉ ቃላቶችን ይጠቀማሉ። ይህም ለአግላይነት አሠራር መንገድ ይከፍታል። የስዊዘርላንድ ካንቶንን ያየን እንደሆነ ትርጉሙ “ንዑስ ክፍል” ሆኖ እናገኘዋለን። የቋንቋ አጠቃቀም ለብሔረሰብ ብያኔ፣ ለክልል፣ ዞን እና ወረዳዎች፣ ለሌሎችም የሉዓላዊነት ጥያቄ እና ብያኔ መከለስ ይኖርባቸዋል። ይቻላልም።
የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ያልታሰበ ጦስ ብሔርተኝነትን
ተቋማዊ ማድረጉ ነው። በዚህ ሳቢያ የተፈጠሩ ወይም የተባባሱ ግጭቶች እና የጋራ የፖለቲካ ማንነት መገንባት አለመቻል ሊቀረፉ የሚችለው
የፌዴራሊዝሙ ችግሮችን በመለየት መዋቅራዊ ለውጦች ማምጣት ሲቻል ነው። ይህን ለማድረግ ቋንቋ የፖለቲካ መሣሪያ እንዳይሆን የሚያስችል
ፖሊሲ ማበጀት (de-politicization of states) እና አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦችን
ለአስተዳድር አመቼ ባልሆነ ድንበር ጠቅልሎ አለማሰር (de-ethnicization
of regional states) ከመፍትሔዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው።
3.2. የመንግሥትን ሥልጣን መለጎም
የሰው ልጆች ሁሉ የመጨረሻ ግብ ነፃነት እና ክብር (liberty and dignity) ነው ብዬ አምናልሁ። የምናወራው ሁሉ ለነጠላ ዜጎችም ይሁን ለቡድኖች እና ብሔረሰቦች፣ ነፃነትን እና ክብርን የማያጎናፅፍ ከሆነ ፈተና ውስጥ መውደቁ አይቀርም። ዘመናዊ አገረ መንግሥታት መፈጠር ከጀምሩ ሦስት መቶ ዓመት እንኳን አልሞላቸውም። ከዚያ በፊት፣ የዓለም ሕዝቦች በብዙ ትውፊታዊ የአስተዳደር ዓይነቶች ውስጥ ሲያልፉ ነበር። ሁሉም አስተዳድሮች በገዢዎች እና ተገዢዎች መካከል የማያቋርጥ ድርድር ይደረግባቸዋል። እነዚህ ድርድሮች በዘመን ሐዲድ ተገዢዎችን ዜጎች (ባለብዙ መብት) እያደረጉ እና ገዢዎችን ደግሞ የሕዝብ አገልጋይ እያደረጓቸው መጥተዋል። ይሁንና በተፈጥሮው መንግሥት አዳ፟ኝ (predator) ሲሆን ዜጎች ደግሞ (prey) ናቸው ማለት ይቻላል። ነገር ግን ሁለቱም ይፈላለጋሉ።
ዳሮን አሴሞግሉ እና ጄምስ ሮቢንሰን የሕዝብ እና መንግሥትን ግንኙነት በማጥናት እና በሕዝባዊ መጽሐፎች በማቅረብ ረገድ የዘመናችን ማርክስ እና ኤንግልስ ናቸው። አምና ባሳተሙት “The Narrow Corridor” (ጠባቡ ኮሪደር) በተሰኘው መጽሐፋቸው መንግሥት እና ሕዝብ ለራሳቸው ሲሉ ይተጋገላሉም፣ ይተባበራሉም (do not just compete, they also cooperate) ይሉናል። ጠባቡ ኮሪደር የሚሉት “አረመኔ መንግሥታት የሚያደርሱት ጭቆና እና መንግሥታት ባይኖሩ ደግሞ ሊከሰት የሚችለው ነውጥና አልቦ-ሕግ መሆንን በመፍራት መካከል ያለውን የነፃነት ኮሪደር ነው።”
እነአሴሞግሉ፣ ያንን ጠባብ ኮሪደር ማግኘት የምንችለው የአረመኔውን መንግሥት እግሩን በረዥም ሰንሰለት አስረን (shackle the Leviathan) ነው ይላሉ። የመንግሥት ሥልጣንን መገደብ የሠለጠነ አገረ መንግሥት ለማኖር ሀሁ ነው። ሥልጣንን የመገደብ ነገር ሲነሳ ሁሌም የምጠቅሰው ከአሜሪካ መሥራች አባቶች አንዱ፣ ጀምስ ማዲሰን የጻፈውን ነው። “ሰዎች መልዓክ ቢሆኑ ኖሮ፥ መንግሥታት አያስፈልጉም ነበር። ሰዎችን የሚገዟቸው መላዕክት ቢሆኑም ኖሮ፥ መንግሥታት ላይ ቁጥጥር መጣል አያስፈልግም ነበር። ሰዎችን ሰዎች በሚያስተዳድሩበት ሁኔታ መንግሥትን መቅረፅ፥ ከባድ ፈተና አለበት። መጀመሪያ ገዢው ተገዢዎቹን መቆጣጠር መቻል አለበት፤ ከዚያ ገዢው ራሱን እንዲገዛ ማስገደድ ያስፈልጋል።”
ስለሆነም ጥያቄው የኢትዮጵያ ጠባብ ኮሪደር የት ነው? እንዴት ይስፋ? መንግሥት ሕዝብን በአግባቡ ለመግዛት መጀመሪያ እንዴት ራሱን ይግዛ የሚለው ነው?
የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀውሶች መንስዔዎች መካከል ዋና
ዋናዎቹ አምባገነናዊነት ግንባር ቀደሙ ነው። ምናልባትም ነውጠኝነት፣
አግላይነት (ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ያካተተ መንግሥት እና ቢሮክራሲ ማቋቋም አለመቻል) እና ድኅነት የአምባገነንነት ተረፍ
ምርቶች ሳይሆኑ አይቀርም። አምባገነንነት የመንግሥት ሥልጣን ካለመገደቡ የሚመነጭ ሲሆን፣ ይህንን ለማድረግ የተሻለ ሆነው የሚገኙት
ሦስቱን የመንግሥት ቅርንጫፎች (ሥራ አስፈፃሚው፣ ሕግ አውጪው፣ እና ሕግ ተርጓሚው) እርስ በርስ ተቆጣጣሪ እንዲሆኑ እና ሚዛን
እንዲጠብቁ ማስቻል ነው። ለዚህም የሚከተሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ አለብን፦
- የሦስቱ የመንግሥት ቅርንጫፎች የሥልጣን
ምንጭ (መውጫ እና መሰንበቻ /origin and survival/) ምንድን ነው?
- የመንግሥት ቅርንጫፎቹ የሥልጣን ገደብ
በግልጽ ይታወቃል?
- የመንግሥት ቅርንጫፎቹ እርስበርስ ይጠባበቃሉ?
እነዚህን የመንግሥት ዓይነቶች በድጋሚ ለሥልጣን በሚያበጁት
ገደብ በሚቀጥለው ሰንጠረዥ እንመልከታቸው።
የመንግሥቱ ዓይነት |
ገለጻ |
ፕሬዚዳንታዊ ስርዓት |
ፕሬዚዳንቱ በቀጥታ ይመረጣል፤ ፓርላማው ሊያነሳው የሚችልበት ዕድል ጠባብ ነው። |
ፓርላመንታዊ ስርዓት |
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማው ይመረጣል፤ በሁለቱ ቅርንጫፎች መካከል ላይጠባበቁ
ይችላሉ። |
ጣምራ ሥራ አስፈፃሚ (ከፊል ፕሬዚዳንታዊ ስርዓት) |
የሥራ አስፈፃሚው ሥልጣን በቀጥታ በተመረጠ ፕሬዚዳንት እና ተጠሪነቱ ለፓርላማ
በሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ይመራል፤ የሥልጣን ክፍፍል ይኖራል። |
ጣምራ ምክር ቤት (ከፊል ፓርላመንታዊ ስርዓት) |
ሁለት ምክር ቤቶች ያሉት ሲሆን፣ ሥራ አስፈፃሚው (ጠቅላይ ሚኒስትሩ) ለአንደኛው
ምክር ቤት ተጠሪ ነው። |
የእያስጴድ ናሙና |
የሥራ አስፈፃሚ ሥልጣን በፕሬዚዳንቱ እና በምክትሉ መካክል ይከፋፈላል። ነገር
ግን ለፓርላማው ተጠሪ የሆነ አስፈፃሚ አካል የለም። |
በኢትዮጵያ ትልቁ ተግዳሮት የሥራ አስፈፃሚውን ሥልጣን መግራት ነው። አሁን ኢትዮጵያ የምትከተለው ፓርላመንታዊ ስርዓት ደግሞ ሁለቱ (ሥራ አስፈፃሚው እና ፓርላማው) መካከል የእርስበርስ ቁጥጥርን ያላላል (ቡድናዊ አምባገነንነትን ያበረታታል)። ፕሬዚዳንቱም ሥልጣኑ የትዕምርት ብቻ ነው፤ የሥልጣን ምንጩም በቀጥታ ምርጫ የሚገኝ አይደለም። በሦስቱም የመንግሥት ስርዓቶች (ንጉሣዊው እና ሁለቱ ሪፐብሊኮች) ኢትዮጵያ የሥራ አስፈፃሚው ጡንቻ ከሌሎቹ ቅርንጫፎች የፈረጠመ ነው። አንዱ ምክንያት በዋነኝነት የፀጥታ ኃይሉ ሁሉም ቅርንጫፎች ተጠሪነታቸው ለሥራ አስፈፃሚው መሆኑ ሲሆን፣ ሁለተኛው የሲቪል ሰርቪሱ ቢሮክራሲ ከፓርቲ ጋር መጋባቱ ነው። የሥራ አስፈፃሚውን ሥልጣን መገደብ እና የኃይሉ ምንጭ የሆኑትን የፀጥታ አካላት ተጠሪነታቸውን በአፈ ጉባዔ ለሚመራው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ወይም ለፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ማከፋፈል የተሻለ ሚዛን በመጠበቅ አንዱን የሥራ አስፈፃሚ ክንድ በረጅሙ ለማሰር (shackling) ይረዳል። ቢሮክራሲው፣ ገዢው ፓርቲ የተመረጠባቸውን ፖሊሲዎች ለማስፈፀም ከሚያስፈልጉት ቁልፍ ቦታዎች ውጪ ቢሮክራሲው ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች እንዲመራ እና ተጠሪነቱም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሆን በማድረግ ሌላኛውን እጁን በረዥሙ ማሰር ይቻላል።
- ሚዲያ እና ሲቪል ማኅበረሰብ
እንደ አባባሉ ሚዲያ እና ሲቪል ማኅበረሰብ አራተኛ የመንግሥት ቅርንጫፎች ናቸው። ሁለቱም የመንግሥት ሥልጣንን ለመግራት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ (በቀጥታ) የሌሉ ነገር ግን ከሦስቱ የመንግሥት ቅርንጫፎች የበለጠ የኅብረተሰብ ኃይል (societal force) ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ከመንግሥት ጋር ባላቸው ግንኙነት መሠረት፣ በግርድፉ ሦስት ዓይነት ሚዲያዎች አሉ። በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩ፣ በፖለቲካ ኃይል የሚዘወሩ፣ እና ለትርፍ የተቋቋሙ። ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚፈጥሩት በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩት እና በፖለቲካ ኃይል የሚዘወሩት ናቸው፤ ሁለቱም ላይ የመንግሥት (ገዢው ፓርቲ) ተፅዕኖ እጅግ የሰፋ ነው። ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችንም በተመለከተ የሥራ አስፈፃሚው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው። ይህንን ለመመከት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች (ተቆጣጣሪ) ባለሥልጣንም ይሁን የሚዲያ ባለሥልጣን ተጠሪነታቸው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሆን በማድረግ የሥራ አስፈፃሚውን ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት መቀነስ ይቻላል።
በተጨማሪም፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመደራጀት (የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ፖለቲካ ፓርቲዎች) እና ሐሳብን ከመግለጽ ነፃነት ጋር በተያያዘ የሚያወጣቸው ገደቦች ላይ የገደብ ሕግ ማውጣት። ከተቻለ ደግሞ በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩ የሚዲያ ተቋማትን በሙሉ በሕዝብ ኢንዶውመንት የሚተዳደሩ በማድረግ ከሥራ አስፈፃሚው ተፅዕኖ ማላቀቅ አራተኛው ቅርንጫፍ በመሆን የሚጫወቱትን ሚና ሊያሳድግ ይችላል።
- የሕግ የበላይነት
የሕግ የበላይነት ለሰላም፣ የብዙኃን ይሁንታ፣ ለቅቡልነት መጀመሪያም መጨረሻም ነው። ነገር ግን የሕግ የበላይነትም በሥራ አስፈፃሚው ጡንቻ የሚሸረሸር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ምክር ቤቱ ባላፀደቀው በጀት የምሠራቸውን ሥራዎች በተመለከተ ሪፖርት ሊጠይቀኝ አይገባም” ሲሉም ይሁን ኦዲተሩ “በገንዘብ ሚኒስትር በኩል ፈሰስ ያልተደረጉ የፕሮጀክት ወጪዎች ኦዲት የማድረግ ሥልጣን የለኝም” ሲል፣ ወይም ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች ከሥራቸው ጋር በተያያዘ ለእስር ሲዳረጉ፣ ወይም በልማት ሳቢያ ንብረታቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች መንግሥትን ፍርድ ቤት አቁመው መሞገት ሳይችሉ ሲቀር፣ ሁሉም የሕግ የበላይነት አለመኖር ምልክቶች ናቸው። የሕግ የበላይነት በሌለበት ዐውድ የተረጋጋ መንግሥት ማኖር አይቻልም።
የሕግ የበላይነት ስንል ማንኛውም ሰው (ግለሰብ፣ ተቋማት፣
እና መንግሥት) ከሕግ በላይ አለመሆኑን እና ሁሉም ሰዎች (ባለሥልጣናትን ጨምሮ) በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውን ነው። ግልጽና ወጥ
በሆነ አተገባበሩ ሊደረግና ሊታቀድ የሚችለውን በመተንበይ አገራዊ መረጋጋትን ያረጋግጣል። በተጨማሪም የሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን፣
የግጭት አፈታት ዘዴዎችን በማስፋት፣ ፍትሃዊነትና ገለልተኝነትን በማረጋገጥ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። የመንግሥትን ሥልጣን በሕግ በመገደብ፣
ግለሰቦችንና ተቋማትን ተጠያቂ በማድረግ፣ እንዲሁም ግልጽነትን በማረጋገጥ ተጠያቂነት ያለው ሥርዓት ይገነባል፤ በመጨረሻም መሠረታዊ
ሰብዓዊ መብቶችን በመጠበቅ፣ በዜጎችና ተቋማት መካከል እምነትን በማዳበር ዘላቂና አስተማማኝ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት እንዲረጋገጥ
መሰረት ይጥላል።
እያስጴድ እነዚህን አስተያየቶች እና ሌልችም ግብዓቶችን
ከግምት ውስጥ በማስገባት አንብሮውን ቢከልሰው፣ ሰንዱ ለዘለቄታው የመፍትሔ ሐሳብ ያዋልዳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
ጥሬ እይታ እና ውይይት ጋባዥ ሃሳቦች አንስተዋል እናመስግናለን
ReplyDelete