Pages

Friday, April 20, 2012

ደጉ ኢትዮጵያዊ፤ ከልብ ካለቀሱ እምባ እንደማይገድ ያስመሰከረ ስብስብ


የዓለም ደቻሳ ልጆች፣ ባለቤት (መሃል) እና ወንድም (በስተቀኝ)
“አለቀለት ሲባል ፍቅር ተሙዋጠጠ
የፌስ ቡክ ዝምድና ነገርን ለወጠ::” ~ Bizu Hiwot
 
“ፌስን ቡክ አድርገው የተቀጣጠሩ
በልብ መነጽር ገጹን ያነበቡ
ሸበሌ ከትመው ታሪክ አስከተቡ፡፡” ~ Desu Aragaw
 
እነዚህ ግጥሞች የተገጠሙት ‹ደጉ ኢትዮጵያዊ› ላዘጋጀው የዓለም ደቻሳ ቤተሰብ ገቢ ማሰባሰቢያ የስነጽሁፍ ምሽት ለተገኘው የመጀመሪያ ስኬት፣ በፌስቡክ ላይ ነው፡፡ ወደስኬቱ በኋላ ላይ የምንመለስበት ቢሆንም መጀመሪያ ‹ደጉ ኢትዮጵያዊ› ምንድን ነው፣ ማነው፣ ከየት ነው፣ ወዴት ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች በአጭሩ እንመልስ፡፡
 
‹ደጉ ኢትዮጵያዊ› ከዚህ በፊት በአካል የማይተዋወቁ 16 የፌስቡክ ጓደኛሞች የፈጠሩት የፌስቡክ ቡድን ነው፡፡ የደጉ ሳምራዊን ታሪክ መነሻ አድርጎ÷ በሊባኖስ መንገድ ላይ እየተጎተተች መኪና ውስጥ እንደትገባ ከተደረገች በኋላ በማግስቱ ራሷን አጥፍታለች የተባለችውን ዓለም ደቻሳ ቤተሰቦች የእዝን ለመስጠት እና እግረ መንገዱንም ስለጉዳዩ አሳሳቢነት አነስተኛ ግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም ለማዘጋጀት የተመሰረተው ‹ደጉ ኢትዮጵያዊ› ምንም እንኳን ሕጋዊ ሰውነት የሌለው ቡድን ቢሆንም በበጎ ፈቃደኝነት መስራት የሚፈልጉትን መስራቾቹን እና በፌስቡክ በተከፈተው የቡድኑ ገጽ ውስጥ በገቡ ከ4,000 በላይ አባላቶቹ ድጋፍ የሚከተሉትን ዓላማዎች ግብ አድርጎ ለመንቀሳቀስ ሕልም አለው፡፡
  • የ‹ደጉ ኢትዮጵያ› ቡድን አባላትን ስለቤት ሰራተኞች መብት፣ ጥቃት እና ሌሎችም ነባራዊ ሁኔታዎች መሰረታዊ ግንዛቤ ማስጨበጥ፡፡
  • ከፍተኛ ጥቃት የሚፈፀምባቸውን የቤት ሰራተኛ ተቀባይ ሃገራትን/መዳረሻዎችን ለይቶ ማወቅ እና ማሳወቅ፡፡
  • ትኩረት ወደሚደረግባቸው መዳረሻ ሃገራት በርካታ የቤት ሰራተኞችን ከሚልኩ ወኪሎች (ኤጀንቶች) ጋር ዘላቂ ግንኙነት መፍጠር፡፡
  • ከየትኛው የኢትዮጵያ ክልል በርካታ ሴቶች ለቤት ሰራተኝነት እንደሚሰደዱ ለይቶ በማወቅ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መስራት፡፡
  • ‹የኢትዮጵያ ማሕበረሰብ› የተባለ የግንኙነት መረብ የቤት ሰራተኛ ተቀባይ በሆኑ መዳረሻ ሃገራት ውስጥ መመስረት እና መሰረታዊ መረጃ እና ድጋፍ መለዋወጥ፡፡
 
‹ደጉ ኢትዮጵያዊ› ትላንት ምን ሠራ?
ደጉ ኢትዮጵያዊ፣ ትላንት ሚያዝያ 11፤ 2004 በዋቢ ሸበሌ ሆቴል አዳራሽ የስነጽሁፍ ምሽት ያዘጋጀ ሲሆን በዝግጅቱ ላይ ወደ 400 የሚጠጉ ሰዎች መገኘታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ገቢው ሙሉ ለሙሉ ለዓለም ደቻሳ ቤተሰቦች በባለቤቷ እና በወንድሟ ስም በተከፈተ አካውንት ገቢ የሚደረግ የመግቢያ ትኬት የተሸጠ ሲሆን፣ ታዳሚዎች እንደየፍላጎታቸው ባለ 25፣ 50 ወይም 100 ብር ትኬት እየገዙ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ዋቢሸበሌ ሆቴልን ጨምሮ በርካታ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ድጋፋቸውን ያደረጉ በመሆኑ ዝግጅቱን ለማካሄድ ምንም ወጪ አላስፈለገም ማለት ይቻላል፡፡
 
ፕሮግራሙ መጀመሪያ ላይ የሳውንድ ሲስተም መንገራገጭ ከመጋፈጡ በቀር በስኬት ተካሂዷል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ በርካታ አንጋፋ እና አማተር ገጣሚያን ግጥሞቻቸውን ያነበቡ ሲሆን፣ የ10 ደቂቃ ዶኩመንተሪ፣ የደጉ ኢትዮጵያ ቡድን ማስተዋወቂያና አጭር ምክር በአቶ በኃይሉ ገ/መድህን ተደርጓል፡፡ አንዱአለም ተስፋዬም የዳንኤል ክብረትን ጽሁፍ ያነበበ ሲሆን መድረኩን ሜሮን ጌትነት መርታዋለች፡፡ ሙኒት እና ዮርግ ታዳሚውን ለማዝናናት የተገኙ የነበረ ቢሆንም በሳውንድ ሲስተሙ ላይ በተከሰተው ችግር ምክንያት፣ ዮርግ ጊታሩን ባይጫወትም ሙኒት ‹‹አስታውሳለሁ፣ መች እረሳለሁ›› የሚለውን ዜማ በታዳሚው ታጅባ ተጫውታለች፡፡ ከሌሎችም በርካታ የተጋበዙ እንግዶች መካከል የዓለም ደቻሳ ባለቤት፣ ወንድሟ እና ሁለት ልጆቿም እንዲገኙ ተደርጓል፡፡
 
በዕለቱ በር ላይ ከተሸጡት ትኬቶች ብቻ ከ16ሺኅ ብር በላይ የተገኘ ሲሆን÷ ዘግየት ብሎ እንደሰማሁት ደግሞ በፋራናይት ላውንጅ እና ሌሎችም ቦታዎች ተቀምጦ ከነበረ ትኬት የተገኘው ገቢ ሲደማመር ወደ 20,000 ብር ተጠግቷል፡፡ በተጨማሪም አንድ ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ ግለሰብ የልጆቹን ሙሉ የትምህርት ወጪ÷ ትምህርታቸውን እስኪጨርሱ ድረስ ለመሸፈን ቃል ገብተዋል፡፡ ሌሎችም ግለሰቦች የተከፈተውን ባንክ አካውንት ቁጥር የወሰዱ ሲሆን የ‹ደጉ ኢትዮጵያ› ትልቅ ስኬት እንደሆነ የተነገረው ግን በሃገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በፌስቡክ በተመሰረተ ቡድን አማካይነት ማሕበራዊ ፋይዳ ያለው ሥራ መስራቱና በዚሁ መቀጠል የሚችልበትን ዕድል ለሁሉም ክፍት አድርጎ ማስተዋወቁ ላይ ነው፡፡
------
ከደጉ ኢትዮጵያ ጋር አብሮ ለመሥራት የሚፈልጉ ሰዎች በፌስቡክ ወይም በኢሜይል thegoodethiopian@gmail.com መጻፍ እንደሚችሉ አባላቱ ተናግረዋል፡፡

2 comments:

  1. Goodn article..and make the correction of the name Andualem Arage....instead Andualem Tesfaye....

    ReplyDelete
  2. ይሄ ቅዱስ እና የተቀደሰ ሃሳብ ነው!! በርቱ ተበራቱ የሚያስብል ነው!!

    ReplyDelete