Pages

Sunday, March 25, 2012

እውትም ‘ሰሚ ያጡ ድምፆች!’

From አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

መጀመሪያ እንዲህ ነበር፤
“የኛ ሙሽራ ኩሪ ኩሪ፣
አገባሽ አስተማሪ፡፡”

ከዚያ በኋላ፤
(በጓደኛዬ እርዳታ ርዕሱን ያስታወስኩት የዶ/ር በፍቃዱ ‹ሰሚ ያጡ ድምፆች› ላይ እንደሰፈረው)
መምህራን በየክፍለሃገራቱ ተሰማርተው የነበረ ቢሆንም ደሞዛቸው 202 ብር (ቱኦቱ) ብቻ ነበር፡፡ መምህራኑ ይቺን ‹ቱኦቱ› ምን ከምን እንደምን እንደሚያደርጓት ይቸግራቸው ነበር፡፡ ስለዚህ እንደመፍትሔ ሌላ መምህርት በማግባት ወጪን በመጋራት ገቢን 404 ብር (ፎር-ኦ-ፎር) ለማደረስ ይጥሩ ነበር፡፡ (ትዳር ትርጉሙ ገቢን ማሳደግ ወይም ወጪን መጋራት እንጂ ፍቅር አልነበረም ማለት ነው፡፡) ይሄ ነገር እየተለመደ ሲመጣ የመምህር ሚስት መምህርት (ወይም የመምህርት ሚስት መምህር) ‹ፎሮፎር› የሚል ቅፅል ተሰጣቸው፡፡ “ፎሮፎሬን ተዋወቃት” ማለት ልክ “ባለቤቴን ተዋወቃት” እንደማለት ሆነ፡፡

ትንሽ ከረምረም ሲል ደግሞ፤

ባል ሳታገባ ዕድሜዋ እያመለጣት የመጣች ሴት ስትገኝ መንደሬው “ምነው ቆንጂት ምንስ ባል ቢጠፋ መምህር አጣሽ?” ይባል እንደጀመር ዶ/ሩ በዚያው መጽሃፋቸው ላይ መግለፃቸው ይታወሰኛል፡፡

ሰሞኑን፤
መምህራኑ ክብራችንን የሚነካ ነው ያሉትን - ለዲፕሎማ ምሩቅ የ31 ብር እና ለዲግሪ ምሩቅ የ73 ብር የደሞዝ ጭማሪ ያደረገው መንግስት “ጭማሪው የመምህርነትን ሙያ ክብር የሚያስጠብቅ ነው” እያለ ነው፡፡

እንዴት ነው ነገሩ?
መምህራን ሀገር መሪ ናቸው፡፡ እነርሱ የሚፈጥሩት ትውልድ ነው ሃገርን የሚረከበው (የሚመራው)፣ መምህራን ቤተሰብ መረን የለቀቀውን ልጅ ነው አር’ቀው (አቅንተው/አርቅቀው) የሚያሳድጉት፣ መምህራን የእያንዳንዱን ዜጋ ሕይወት መስመር የማስያዝ ሥራ ነው የሚሰሩት፡፡ የመምህርነትን ያህል ኃላፊነቱ የከበደ ትውልድን የመቅረጽ ሚና የመጫወት ዕድል የሚሰጥ የሥራ ዓይነት አስቤ አይመጣልኝም፡፡

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ከላይ መግቢያችን ላይ ባየነው መልኩ ‹የመምህራንን ማሕበራዊ ዋጋ እንዲያሽቆለቁል ያደረገው ማን ነው?› ብለን የጠየቅን እንደሁ÷ መልሱ ደሞዛቸው መሆኑን እናስታውሳለን፡፡  

የመምህራን ደሞዝ አነስተኛነት የሥራ ዘርፉ ብቃታቸው ከፍ ያሉ ባለሙያዎች ወደዘርፉ እንዳይገቡና ብቁ ዜጎችን እንዳያፈሩ እየተከላከለ ነው፡፡ ውስጡ ያሉትም ሸሽተው እንዲወጡ፣ ባይወጡም ኃላፊነታቸውን በትጋት እንዳይወጡ ለሞራል ልሽቀት ዳርጓቸዋል፡፡ በዚህ አካሔድ የተሽመደመደው የትምህርት ጥራታችን ባለህበት እርገጥ ማለቱን አያቆምም፡፡ ያውም ባለበት መቆም ከቻለ፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ አገራችን በድህነት እና በኋላ ቀርነት ውራነቷን አስጠብቃ ትኖራለች ማለት ነው፡፡

ሰሞኑን የተደረገው የደሞዝ ጭማሪ በጣም አሸማቃቂ ነው፤ ምናልባትም መምህራኑ ይሄ ከሚጨመርላቸው ‹ቆይ ጠብቁ› ቢባሉ የሚሻላቸው ይመስለኛል፡፡ ኢሕአዴግ የቀድሞዎቹን የመምህራን ማሕበር አመራሮች ከምርጫ 97 በኋላ አሽቀንጥሮ ቢጥላቸውም በእጅ አዙር አዳዲስ አመራሮችን ሾሟል፡፡ አመራሮቹም እውነትም ለሹያሚያቸው ታማኝነታቸውን ለማረጋገጥ ይመስላል የደሞዝ ጭማሪው ተገቢና በቂ እንደሆነ እየደሰኮሩ ነው፡፡ ደግነቱ መምህራኑ ማሕበሩ አይወክለንም ማለት ጀምረዋል - ለእነርሱ የማይሟገት ማሕበር እንዴትስ ይወክላቸዋል?

የኢትዮጵያ መንግስት በአምስት ዓመቱ መጨረሻ፣ በብሔራዊ ባንክ  የአንድ ትሪሊዮን ብር ተቀማጭ ለማድረግ ሕልም አለው፡፡ መልካም ሕልም ነው፡፡ ቢሆንም የሰው ስጋ እየበላ የሚያስቀምጠው ብር ለማን እንደሚሆን ግልፅ ማድረግ አለበት፡፡ የመምህራኑ የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ የመኖር ጥያቄ እንጂ የቅንጦት ጥያቄ አይደለም፡፡ መምህራኑ ብር እና ክብር ያስፈልጋቸዋል፡፡

አለበለዚያ ግን፤ መንግስት መዘንጋት የማይኖርበት አንድ ነገር አለ፡፡ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መውደቅ ጀርባ፣ ከመንግስቱ ኃይለማርያም መውደቅ ጀርባ እና አሁንም በቅርቡ ከምርጫ 97 ወንበር ነቅናቂ የምርጫ ሒደት ጀርባ መምህራን ጉልህ ሚና ነበራቸው፡፡ አሁንም ቢሆን አምስት ለአንድ የተቦደኑትን ተማሪዎች የሚያስተምሩት፣ ኢሕአዴግ መልምሎ የሾማቸው ዳይሬክተሮች ሳይሆኑ፣ ብሶተኞቹ መምህራኖች መሆናቸውን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡

ያቺ ደጋግመን የሰማናት ቀልድ በጆሮዬ እያቃጨለች አስቸገረችኝ፡፡ ትምህርት በሬዲዮ ላይ ነው፡፡ የሬዲዮዋ መምህር ስለብር ኖቶች እያስተማረች እያለች÷ “እባክዎ መምህር፣ ለተማሪዎቹ የመቶ ብር ኖት አውጥተው ያሳዩዋቸው፤” ትላለች፡፡ መምህሩ ግን ጭጭ - መቶ ብር ከየት ይመጣል?

መምህራን ክብራቸውን ለማስጠበቅ በአቋማቸው መፅናት አለባቸው፡፡ አሁን የአንዳንድ ትምህርት ቤት መምህራን አድማ ቢመቱም፣ ፀጥ ለጥ ብለው ሥራቸውን የቀጠሉ መምህራን መኖር ትግሉን ሕብረት ያሳጣውና ያኮላሸዋል፡፡ ስለዚህ መምህራን የገዛ ክብራቸውን በገዛ አቋማቸው የሚወስኑበት ገደል አፋፍ ላይ ቆመዋል፡፡ ክብራቸውን ገደል ይከቱት ይሆን ወይስ?

ጉዳዩ የአገር ጉዳይ መሆኑን ተማምነናል፡፡ እኛም ከመምህራን ጎን በመቆም ለአገር ጉዳይ ተቆርቋሪነታችንን እናስመስክር፡፡

No comments:

Post a Comment