Pages

Sunday, April 15, 2012

የቴዲ አፍሮን አልበም ያልገዛሁባቸው 5 ምክንያቶች

From አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

ባለፈው ሳምንት የቴዲ አፍሮን አልበም እንድንገዛ የሚያስገድዱንን 5 ምክንያቶች አንብቤ ነበር፤ አላሳመኑኝም እንጂ! ስለዚህ አልገዛሁም፡፡ ባልገዛም አዳምጬዋለሁ፡፡ በርግጥ ሳይወጣ በፊት ላለመግዛት መወሰኔ በራሱ፣ ከወጣ በኋላ ለምን አልገዛሁትም ብዬ የምናገረው ነገር ሰሚን ላይማርክ ይችላል ግን ምንአገባኝ፡፡ ግን ምናልባት ‹ገንዘብ ቸግሮት የቴዲን አልበም አልገዛም› ብለው የሚያሙኝን ሰዎች ዝም ለማሰኘት ምክንያቴን እደረድራለሁ፡፡ (በነገራችን ላይ ትላንት ከኢትዮፒካሊንክ እንደሰማሁት÷ ያቺ እንኳን የፕሬዚደንት ግርማ ወልደጊዮርገስን የሕይወት ታሪክ በዶኩመንተሪ እሰራለሁ ስትል የነበረችው አምለሰት ሙጪ ስንት ሳዱላዎች የተጋደሉለትን ቴዲን በእጇ አደረገችው ማለት ነው በቃ?)
5. የአማርኛ አልበም መሆኑን አላወቅኩም ነበር
አልበሙ የአማርኛ መሆኑን ያወቅኩት ከሰማሁት በኋላ ነው፡፡ ምክንያቱም በየቦታው የተለጣጠፉት ግባብዲያ ማስታወቂያዎች በሙሉ ‹Tikur Sew, Get ready, A feast for soul, Teddy Afro ምናምን ይሉና፤ ለሳቅ ለጫወታ ማን እንደ ሜታ!› ይላሉ፡፡ እኔ የመሰለኝ ታዲያ ‹ትኩር ሰው› የሚባል የእንግሊዝኛን አልበም በኢትዮጵያዊ ቢራ አጣጥሙ የተባለ ነበር፤ እንግሊዝኛ እውቀቴ ውሱን ስለሆነ ያገሬን ዘለሰኛ ብሰማ ይሻለኛል ብዬ ነበር፡፡ እሺ! ቀልዴን ነው፡፡ የእንግሊዝኛ አልመሰለኝም፤ ነገር ግን ራሱን እንደኢትዮጵያዊ አርአያነት የሚቆጥረው ቴዲ አልበም ማስታወቂያ በእንግሊዝኛ ብቻ ሲሰራ ማኔጀሩ እና ፕሮሞተሩ አገሩ ኢትዮጵያ እንደሆነ ቢጠፋቸው እንኳን እሱን አላማከሩትም ነበር? አላምንም!

4. የነጠላ ዜማዎቹ ግጥምና ዜማ originality ስላነሳቸው
የቴዲ አፍሮ ዘፈኖች በግጥምም፣ በዜማም ስሜት ይኮረኩሩ እንደነበር የታወቀ ነው፡፡ ሆኖም ባሁኑ ሲለቃቸው የነበሩት ዜማዎች አንዴ ከኤርትራ፣ አንዴ ከሩቅ ምናምን የተቀነጫጨቡ መሆናቸውን ስንሰማ ታዝበናል፡፡ አንድ ግጥሙም ከማኅልዬ ማኅልዬ ዘ ሰለሞን ቃላቶች የተገጣጠሙ መሆናቸው አደናግሮኝ ነበር፡፡ እንዲያውም አንድ ጓደኛዬ ‹‹በቃ ቴዲ የሚችለው ግጥም ነው፤ ዜማ ከየትም፣ ከየትም ትንሽ እየቀባባ…›› ያለውን ለማመን ተቃርቤያለሁ፡፡ የሚያሳዝነው ግን አልበሙን ካደመጥኩ በኋላ ‹ያ አስደናቂው፣ አወዛጋቢው፣ አዲስ ምልከታ አጫሪው የቴዲ አፍሮ የግጥም ችሎታ የት ገባ?› አሰኝቶኛል፡፡

3. አልበሙ ስለወረደብኝ!
እዚህችጋ የቴዲ አድናቂ ብቻ ለመሆን የተፈጠሩ የሚመስሉት አድናቂዎቹ÷ የቴዲ ዘፈኖች አድማጭ ያስፈልገዋል ሊሉኝ ይችላሉ፡፡ ዘፈኖቹን ሦስት፣ አራቴ ሰማሁዋቸው፡፡ ተመልሶ ችክ ባሉ ችክችካዎች ሊያተክረን መሆኑን ሳስበው አሳዘነኝ፡፡ አልበሙን አውሶ ያስቀዳኝ ጓደኛዬም ቴዲን ከጠበቅኩበት በታች ሳገኘው ‹‹ሆዴ ባባ፣ ተናነቀኝ እምባ›› እንጂ አላነደደኝም አለኝ፡፡ ምናልባት ኃይል የሚለው ዘፈን ላይ ያለው ከኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን የተወሰደ ዜማ በሬጌ ስልት ሲሰማ የሚሰጠው ጣዕም ወጣ ያለና የሚያረካ ሊባል ይችል ይሆናል፡፡ ከዚያ በተረፈ እነ ጃ ያስተሰርያልን፣ እነ ካብ ዳኅላክን፣ እነ ሼመንደፈርን በሰማሁበት ጆሮዬ እና እሱም በዘፈነበት አፉ አሁን የዘፈናቸው ለኛም ከሚገባን በታች፣ ለእርሱም ከሚችለው በላይ ሳይሆን አይቀርም፤ ትንሽ ይደብራል፡፡

2. ውድ ነው፤ (ዋጋው!)
30 ብር ለአንድ አልበም?! በዚህ ዘመን ቴክኖሎጂ፣ በአምስት መቶ ሺኅ ቅጂዎች የሚዘጋጅ አንድ ሲዲ ከነሽፋን ማሸጊያው ጭምር የሚፈጀው ዋጋ 5 ብር አይሞላም፡፡ ታዲያ የእርሱ አልበም ምን ስለሆነ ነው 30 ብር የሚሸጠው? በየትኛውም ቴክኖሎጂ ቢሰራ ኮፒ ማድረግ እንደሚቻል ስለማውቅ፣ ኮፒ አድርጌ ተጠቅሜያለሁ፡፡ በበኩሌ አልበሙ 11 ዘፈኖች ስላሉት፣ በ11 ብር ቢሸጥ ኖሮ የመጀመሪያውን (original) ቅጂ እገዛ ነበር፡፡ ይህችኛዋ አመፃ በቴዲ ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም አርቲስቶች ላይ ነው - አዎ! ኦሪጅናል የሚባለውን አልገዛም፡፡ ምክንያቱም ተመሳሳይ ጥራት ያለውን ቅጂ፣ በነፃ ወይም ግፋ ቢል በ5 ብር አገኛለሁ፡፡ አሥር ብር የምትሸጡ ከሆነ ‹‹ለጥበቡ እድገት›› ስል እተባበራችኋለሁ፡፡

1. ይህንን መንግስት እና ይህንን ኑሮ አላማረረም (I don’t want art for the sake of art)
‹እንዴ ቴዲ እኮ ዘፋኝ ነው?› ካላችሁ፣ እንዴ እስክንድርም እኮ ጋዜጠኛ ነው እላችኋለሁ፤ ‹እንዴ ቴዲን እኮ እያሰሩት ነው?› ካላችሁ፣ እንዴ እስክንድርንም እኮ ከሰባቴ በላይ አስረውታል እላችኋለሁ፡፡ ‹የፈለገውን አቋም መያዝ፣ ማራመድ ወይም አለማራመድ አይችልም እንዴ?› ካላችሁ ግን እስማማለሁ ግን ባያስጀምረን ነበር፡፡ የምርጫ 97 ሰሞን ጥዑም ፖለቲካ ዘፍኖ ከዘፋኝነት ወደነፃ አውጪነት ካሸጋገርነው በኋላ ማፈግፈጉ ያኔ የሕዝቡን ትኩሳት ተንተርሶ ሊጠቀምብን ነበር ማለት ነው? ያኔ ተቃዋሚዎች ተስፋ አላቸው ከነርሱ ልወዳጅ ብሎ ነበር ማለት ነው? ዛሬ ድንገት ተነስቶ ‹የለም! ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ነገር አላየሁም፣ አልሰማሁም› ቢል እኔም አልሰማውም፡፡  

5 comments:

  1. we love it we have it take your garbage coment to weyane tv that the only placeu shit.

    ReplyDelete
  2. አረ Anonymous ምን ዓይነት አስተያየት ነው፡፡ የቴዲ አድናቂ ለመሆን፤ ባለጌ መሆን የሚያስፈልግ አስመሰልከ/ሺ/ው እኮ፡፡ ቴዲ ስለ ግብረገብ አልዘፈነም እንዴ!

    ReplyDelete
  3. እኚህ አስተያየቶች ለቴዲ ያለንን ፍቅር ከሙያ አንጻር የሚገመግም ስለሆነ ወድጄዋለሁ!! በሙያ አንጻር እና በገበያ አንጻር ከታየ እውነትም 30 ብር ለአንድ አልበም ውድ ነው!! እንግዲህ ቴዲ እሰከዛሬ የሰራቸውን አልበሞች እናውቃቸዋለን!! ሁሌም ቢደመጡ ቶሎ የሚሰለቹ አይደሉም ከዚህኛው ስራው ጋር ሲነጻጸር!!ሌላው ደሞ ከገበያ አንጻር በዚህ የኑሮ ውድነት የትም በየካፌው እና በየታክሲው የሚደመጥ ስለሆነ 30 ብር ማውጣት ምክንያት ላይሆን ይችላል!! ነገር ግን ለቴዲ ያለውን ፍቅር ብናየው አብዛኛው የኢትዮጰያ ህዝብ ኤርትራውያንንም ጨምሮ ልዩ ፍቅር አለን!! ሁሉንም ላያካትት ይችላል ግን አብዛኛው ብል ማጋነን አይሆንም ስለሚወደድ ብቻ ምንም ይዝፈን ምንም አ ብሎ ማዳመጥ ትንሽ ይከብዳል!! አስተያየት ቢሰጥበት ደሞ ቀጣይ አልበሙ በደምብ እንዲወደድ ስለሚፈልግ የጠነከረ ፍትጊያ እንደሚጠብቀው ቢያውቅ የተሻለ ስራ ይዞ እንዲመጣ ያበረታታዋል ስለዚህ ጥሩ አስተያየት ነው ወድጄዋለሁ!!!

    ReplyDelete
  4. Tedy's songs are amazing; the more I listen the more I like them. Amazing singer. We love you Tedy!

    ReplyDelete
  5. ዕይታህን በጣም አድንቄልሃለው።

    ReplyDelete