Pages

Monday, May 27, 2013

#Ethiopia: ከቃሊቲ ወደ ዝዋይ፤ ለምን?


ልክ የዛሬ 22 ዓመት (ማክሰኞ ዕለት)፣ በግንቦት 20 ኢሕአዴግ ቤተ መንግሥቱን ተቆጣጠረ፡፡ በዕለቱ በኢትዮጵያ ሬድዮ እየተደጋገመ ይተላለፍ የነበረው ‹‹ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን… ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም ሲባል… ተቆጣጥሮታል›› የሚሉት ቃላት ያሉበት እወጃ ነበር፡፡ ከ22 ዓመት በኋላ ‹ደርግ ሲጠቀምበት የነበረው፣ ኢሕአዴግ እየተጠቀመበት ነው› ማለት ብቻ ይቻላል፡፡ የ‹‹ሰፊው ሕዝብ›› ጥቅምና ተሳትፎ ተመናምኖ፣ ተመናምኖ አሁን የደረሰበትን ትክክለኛ ቦታ መገመት ያስቸግራል፡፡ ስለሆነም የኢሕአዴግ መንግሥት ‹‹እየተጠቀመበት›› ያለውን ነገር እያስጠበቀ ያለው በአፈና ነው፡፡ በምርጫ አፈና፣ በሚዲያ አፈና፣ በፖለቲከኞች አፈና… ወዘተ፡፡

የዛሬ አራት ዓመት ገደማ በሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይ በመንግሥት ባለሥልጣናት ‹‹የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ›› ተብሎ የነበረውና በኋላ ደግሞ በፍርድ ቤት ‹‹ሕገ መንግሥቱን በኃይል የመናድ ሙከራ›› ተብሎ በቀረበው ክስ 23 ሰዎች በቁጥጥር ስር ሲውሉ፣ አንዱ የሞት ፍርድ እና ቀሪዎቹ ደግሞ የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ተበይኖባቸዋል፡፡

ስለነዚህ እስረኞች መዘንጋት እና የቤተሰቦቻቸው ሁኔታ ከአንድ ወር በፊት ዞን ዘጠኝ ላይ የወ/ሮ እማዋይሽን ልጅ በማነጋገር የተጻፈውን ማንበባችን ይታወሳል፡፡ አሁን ደግሞ ከነዚህ እስረኞች መካከል በእነብ/ጄኔራል ተፈራ ማሞ መዝገብ ከተከሰሱት 23 ‹‹ታራሚዎች›› መካከል ከ4ቱ በስተቀር (19ኙ) ወደዝዋይ በቅርቡ ተዛውረዋል፡፡ ዝውውሩ እነርሱን ብቻ የተመለከተ ባይሆንም፣ ድንገተኛነቱ እና ምክንያት ያልተሰጠበት መሆኑ ጥያቄዎችን እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡

ወደዝዋይ ከተዘዋወሩት መካከል ቃሊቲ እንዲቀሩ የተደረጉት አቶ መላኩ ተፈራ ጥላሁን (የሞት ፍርድ)፣ ወ/ሮ እማዋይሽ ዓለሙ (ዕድሜ ልክ)፣ ሌትናንት ኮ/ጌታቸው ብርሌ (ዕድሜ ልክ) እና ኮነሬል ፋንታሁን ሙሃባ (ዕድሜ ልክ) ናቸው፡፡ እነዚህ እስረኞች ከሌሎቹ ተለይተው ለምን እንደቀሩ (ወይም የተዛወሩት ለምን ተለይተው እንደተዛወሩ) ያነጋገርኳቸው ቤተሰቦች ምንም የሚያውቁት እንደሌለ ዘርዝረው ነግረውኛል፡፡ የቃሊቲው ማረሚያ ቤት የመጣበብ ችግር ገጥሞት ይሁን/አይሁን፣ ሌሎች ታራሚዎች ሊመጡበት ታስቦ ይሁን/አይሁን የሚታወቅ ሌላ መረጃ የለም፡፡

የታራሚዎቹ ወደቃሊቲ መዛወር በተለይም ቀድሞ ነዋሪነታቸው አዲስ አበባ የነበሩ በመሆናቸው እና ቤተሰቦቻቸውም በአዲስ አበባ የሚኖሩ በመሆናቸው ትልቅ ፈተናን በጠያቂዎቻቸው ላይ እና በታራሚዎቹም በራሳቸው ላይ ያሳድራል፡፡ ወትሮም ቃሊቲ ድረስ (በየቀኑ ቀርቶ) በየሳምንቱ እንኳን ለመመላለስ የኢኮኖሚም ይሁን የሌላ አቅም ችግር ላለባቸው ቤተሰቦች የታራሚዎቹ ወደዝዋይ መዘዋወር በረዥም ጊዜ አንዴ ብቻ እንዲጠያየቁ የሚያስገድድ ብያኔ ነው፡፡ ታራሚዎች በሚኖሩበት ክልል የመታሰር መብት አላቸው ወይም የላቸውም የሚለውን ጥያቄ ለሕግ ሰዎች ብንተወው እንኳን መንግሥት እንደሞራል አባትነቱ የታራሚዎቹን እና ቤተሰባቸውን እንግልት ለመቀነስ የሚጠበቅበትን ሞራላዊ ግዴታ እየተወጣ እንዳልሆነ መታዘብ ይቻላል፡፡
ከዚህም በላይ፣ በቅርቡ ወደዝዋይ የተዘዋወረውን ጋዜጠኛ ውብሸት እዚያው ዝዋይ ነዋሪ ሁነው ሊጠይቁት የሄዱ ሰዎችን ‹‹ከዝዋይ መጠየቅ አይቻልም›› በሚል የዝዋዩ ማረሚያ ቤት እንደመለሳቸው ሰምተናል፡፡ ይህም ሌላው ሕገ ወጥ እና ኢሞራላዊ ድርጊት ነው፤ ለታዛቢም ‹ታራሚዎቹ ወደ ዝዋይ የሚዛወሩት በብቸኝነት እንዲቀጡ ነው ወይ?› ብሎ እንዲጠይቅ ያስገድዳል፡፡

የ‹‹ታራሚ››ዎቹ አያያዝ

የታራሚዎች አያያዝ ከእስረኛ እስረኛ የተለያየ እንደሆነ ከተለያዩ ምንጮች መስማት የተለመደ ነው፡፡ ከፖለቲካ ጋር በተነካካ ጉዳይ የታሰሩ ታራሚዎች በ‹‹ሌላ›› ወንጀል ድርጊት ከታሰሩ ሰዎች ያነሰ መብት ያላቸው የሚመስልበት አሠራር አለ፡፡ የቃሊቲው ማረሚያ ቤት እነዚህን የ‹‹ፖለቲካ እስረኞች›› አይደሉም የሚላቸውን የፖለቲካ እስረኞች የመጠ’የቂያ ሰዓታቸውን በልዩነት አስቀምጦታል፡፡ ሌሎቹ ታራሚዎች ቅዳሜና እሁድ ጠዋቱን ሙሉ የሚጠየቁ ቢሆንም፣ የፖለቲካ እስረኞች ግን ከ6፡00 ሰዓት እስከ 6፡30 ለግማሽ ሰዓት ብቻ እንዲጠየቁ ይደረጋሉ፡፡ ታራሚዎቹ ሲጠየቁ ከወዳጅ ቤተሰቦቻቸው ጋር የሚወያዩትን ለማድመጥ እንዲችሉ ጠባቂዎቻቸው ከአጠገባቸው ይቆማሉ፡፡ መጽሐፍቶች ተመርምረው እና ታይተው ብቻ ነው የሚገቡላቸው፡፡ አንዳንዴ ፖለቲካ ያልሆኑ ፖለቲካ የሚመስሉ መጽሐፍቶች ሳይቀሩ እንዳይገቡ ይታገዳሉ፤ ለምሳሌ ‹የሎጥ ሚስት› የሚለው ልቦለድ ለጋዜጠኛ ውብሸት እንዳይገባ ታግዶበታል፡፡

አቶ ስዬ አብርሃ እና አቶ ታምራት ላይኔ በእስር ላይ በነበሩበት ጊዜ በእስር በነበሩባቸው ጊዜ ምግብ አሙቀው ለመብላት የሚያስችላቸው ቁሳቁስ ገብቶላቸው የነበረ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በተጨማሪም፣ የማረሚያ ክፍሎቹ የጋራ መፀዳጃ ቤት እና ሻወር ቢኖራቸውም ንፅሕናቸው የተጠበቀ ባለመሆኑ ሁለቱም ታራሚዎች ማታ፣ ማታ ወጣ ብለው እስከ አራት ሰዓት አምሽተው እንዲመለሱ ተፈቅዶላቸው ራታቸውን ሁሉ ሳይቀር ውጪ በልተው ይመለሱ እንደነበር - ስለእስረኞች አያያዝ ለማጣራት ሙከራ ሳደርግ ሰምቻለሁ፡፡

እነዚህ ሁሉ ለነአቶ ስዬ ሲደረጉ የነበሩ እንክብካቤዎች ግን ለሌሎቹ የፖለቲካ እስረኞች የሚሞከሩ አይደሉም፡፡ እንዲያውም የማረሚያ ቤቱን እራት እስከ 10 ሰዓት ድረስ መብላት እና እስከ 12 ሰዓት ድረስ ተፀዳድቶ መግባት በተለይ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት (የፖለቲካ እስረኞቹ) አያያዝ ‹‹ደንብ›› ነው፡፡

አቶ መላኩ ተፈራ ‹‹ሕገ መንግሥቱን ለመናድ መሞከር›› በተባለው ክስ የሞት ቅጣት የተበየነባቸው ፍርደኛ ናቸው፡፡ አቶ መላኩ ተፈራ ‹‹የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ መሥራች፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የሰሜን ኢትዮጵያ ዋና አደራጅ - የሙሉ ቀን ፖለቲከኛ›› እንደነበሩ ነግረውኛል፡፡ በዕድሜያቸው ገፋ ያሉ እና አልፎ አልፎ ከውጭ አገር እየመጡ ከሚጠይቋቸው ልጆቻቸው በቀር በቋሚነት የሚጠይቋቸው ባለቤታቸው ብቻ ናቸው፡፡ ሁለቱም በዕድሜ ከፍ ያሉ በመሆናቸው ለሳምንታዊዋ 30 ደቂቃም ቢሆን አረፍ ብለው መነጋገር የሚችሉበት ሁኔታ እንዲመቻች ቢጠይቁም ማረሚያ ቤቱ ምላሽ ሳይሰጣቸው ጆሮ ዳባ ልበስ እንዳለ አጫወተውኛል፡፡

እርሳቸው የደም ግፊት እና የነርቭ በሽታ እንዳለባቸው ቢናገሩም፣ በወር አንዴ የደም ግፊቱን መድኃኒት ይዘው ከሚመጡት የጤና ባለሙያዎች ጋር ከመገናኘት በላይ ክትትል አይደረግላቸውም፡፡ በቅርቡ እንደሰማነው ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙም በገጠማት የጤና ችግር አፋጣኝ እና ጥሩ ሕክምና እንድታደርግ መፍቀድ ቀርቶ በረዥም (ያውም ለታካሚዋ ቀኑ በማይነገር) የሕክምና ቀጠሮ በማመላለስ የጤንነቷ ሁኔታን ስጋት ውስጥ ሊገባ የሚችልበትን ዕድል ማረሚያ ቤቱ በቸልተኝነት ፈቅዷል፡፡ በጥቅሉ የማረሚያ ቤቱ አያያዝ በተለይም የፖለቲካ እስረኞች ላይ የሁለትዮሽ (የማግለል) አቋም ያራምዳል ማለት ይቻላል፡፡

በእነብ/ጄኔራል ተፈራ ማሞ መዝገብ የተከሰሱት ታራሚዎች ይቅርታ ከጠየቁ የከረሙ ቢሆንም አሁንም መንግሥት /ማረሚያ ቤቱ/ ሊፈታቸው ፈቃደኛ ሳይሆን፣ ጭራሽ ወደዝዋይ ማረሚያ ቤት እያዛወራቸው ይገኛል፡፡ ወደዝዋይ ማረሚያ ቤት ማዛወሩ ቋሚ ቦታ እየተፈለገላቸው ከሆነ ይቅርታቸው ‹‹ተሰርዟል ወይም ተቀባይነት አላገኘም›› ማለት ስለሚሆን ይኸው ተገልጾ ሊነገራቸው በተገባ ነበር፤ ካልሆነም ደግሞ የቤተሰባቸውንም የፍርደኞቹንም ሕይወት በሚያመሳቅል ሁኔታ እያንገላቱ ጊዜ ከማባከ ቶሎ ፈትቶ ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓትን ማስጠበቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ አሁንም ቤተሰቦች ይጠይቃሉ፤ የዝውውሩ ምስጢር ምንድን ነው? ይቅርታ የጠየቁትስ የማይፈቱት ለምንድን ነው?