Pages

Monday, April 23, 2012

የኢትዮጵያ መንግስት መጠላቱን የሚያሳብቁ ምልክቶች

From አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

እንደግለሰብ የምንጠላቸውን እንጂ የሚጠሉንን የማወቅ ዕድላችን ጠባብ ነው፡፡ እንደመንግስት ግን ጠባብ አይደለም፤ ሆኖም መንግስታቱ አምባገነን ከሆኑ በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ጥላቻቸውን የሚገልጹበት ድፍረት አያገኙም ስለዚህ እንደተጠሉ ላያውቁ ይችላሉ የሚል የግል ስጋት አለኝ፡፡ ፊደል ካስትሮ በስልጣናቸው ዘመን፣ በሕይወት ታሪካቸው ላይ የተሰራውን ፊልም ሕዝቡ በምን ዓይነት የፍቅር ስሜት እንደሚመለከተው ለማየት ራሳቸውን ቀይረው ሲኒማ ቤት ገቡ አሉ፡፡ እናም ገና ፊልሙ እንደጀመረ የፊደል ካስትሮ ፊት መታየት ሲጀምር ተመልካቹ በሙሉ ቆሞ አጨበጨበ፡፡ እርሳቸው በደስታ እየፈነደቁ ፀጥ አሉ፡፡ ታዲያ ከጎናቸው ተቀምጦ የነበረው፣ ‹‹አንተ፤ እየተነሳህ አጨብጭብ እንጂ! ካድሬዎቹ ያዩሃል’ኮ›› አላቸው ይባላል፡፡ ስለዚህ የኛዎቹም ይህ ዓይነት ቅዠት ውስጥ ሊሆኑ ስለሚችሉ÷ ሕዝብ እንደጠላቸው የሚያሳብቁ አንዳንድ ነገሮችን እናስታውሳቸው፡፡

1. የጋዜጦች አቋምና የስርጭት ብዛታቸው ጉዳይ
አገራችን በሕገመንግስቷ ‹ሐሳብን በነፃ የመግለፅ› መብት እንዳስቀመጠች ቢነገርላትም ‹‹ነፃ›› የሚለው እስከምን ድረስ እንደሆነ አጠራጣሪ እውነታዎች እየተከሰቱ ነው፡፡ መንግስትን የሚነቅፉ ጋዜጦች እና ጋዜጠኞች ወይ ይታሰራሉ አሊያም በስደት አሳራቸውን ያያሉ፡፡ በዚህ ሁሉ መሃል ግን ‹የሚነቀፈውን ለመንቀፍ› በሚል የተቋቋሙት ጋዜጦች ቀርቶ ለወትሮው በውበት፣ ፋሽን፣ ፍቅር እና ጤና ጉዳዮች ላይ ብቻ ያጠነጥኑ የነበሩ መጽሄቶች ሳይቀሩ ፖለቲካ እንደቅመም ይዘው መውጣት ጀምረዋል፡፡

አንድ ሰሞን ቴዲ አፍሮን የሽፋን ገጽ ላይ ይዞ መውጣት የመጽሄቶች ሕልውና እንደነበር ይታወሳል፡፡ አሁን ደግሞ መንግስትን የሚነቅፍ ጽሁፍ ይዞ መውጣት ለተነባቢነት ሁነኛ መፍትሄ ሆኗል፡፡ የፍትሕ ጋዜጣ ኮፒ መመንደግ ከዚሁ ከመንግስት መጠላት እና የፍትሕ ጋዜጠኞችም መንግስትን የመንቀፍ ድፍረት ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት አለው፡፡

2. ፌስቡክ እና ጦማሮች
አግኝተውት የማያውቁትን ወዳጅ ፍለጋ ፌስቡክ ውስጥ ከሚገቡ ኢትዮጵያውያን ይልቅ ስለወቅታዊ ጉዳዮች ‹ማን ምን አለ?› የሚለውን ፍለጋ የሚገቡት ብዙ ናቸው፡፡ በተለይም ከዓረቡ ዓለም የፌስቡክ አብዮት ወዲህ የአገር ልጆች ፌስቡክም በአብዮት ናፍቆት እየተናጠ ነው፡፡ ፌስቡክ ውስጥ መሪዎቻችንን መሳቂያ፣ መሳለቂያ የሚያደርጉ ምስሎችን ማየት፣ እያንዳንዷን የመንግስት እርምጃ የሚተቹ ጽሁፎችን ማንበብ የተለመደ ነው፡፡

በተጨማሪም በርካታ ጦማሪዎች የግል ጦማር (blog) እየከፈቱ የግል አስተያየታቸውን መሰንዘር ጀምረዋል፡፡ በዙዎቹ ጦማሪዎች በአገራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ሲሆኑ÷ መንግስትን በአለንጋ ትችቶቻቸው ከመሽንቆጥ የማይመለሱ ናቸው፤ ለማወደስ የተቋቋሙ ጥቂት ጦማሮች ቢኖሩም ባብዛኛው በአንባቢ ድርቅ የሚሰቃዩ ናቸው፡፡

3. የቴዲ አፍሮ ክብረወሰን
በኢትዮጵያ ሕዝብ ልቦና ውስጥ ቴዎድሮስ ካሣሁን ያለው ቦታ የዘፋኝነት ብቻ ሳይሆን የአርበኝትም ጭምር ነው፡፡ ቴዲ አፍሮ በአጋጣሚ የሚናገራትም ሆነ በግጥሙ ውስጥ የሚያስቀምጣት ሐረግ ፖለቲካዊ ፍቺ ይሰጣታል፡፡ የዘንድሮው አልበም ገበያም የደራው እና 10 ሚሊዮን ብር በመሸጥ የሃገር ውስጥ ክብረወሰን ለመስበር የበቃው÷ ሕዝብና አጋጣሚ በቸረው የመንግስት ተፃራሪ አቋሙ ነው፡፡

የቴዲ አፍሮ ‹ጥቁር ሰው› የተሰኘ አልበም ጥሩ እንደሆነ ሊያስረዱኝ ይሞክሩ ከነበሩ ሰዎች መካከል ይጠቅሱልኝ የነበረው ‹ጥቁር ሰው› እና ‹ስለ ፍቅር› የተባሉትን ዘፈኖች ነው፡፡ ስለፊተኛው ‹‹ምኒልክ መወደሳቸው የኅወሓት ሰዎችን አንጀት ያሳርራል›› በሚል፣ ስለኋለኛው ደግሞ፡-
‹‹… አፈር ይዞ ውስጡ አረንጓዴ
     ለምን ይሆን የራበው ሆዴ?....›› የሚለውን ግጥም ይጠቅሱልኛል፡፡

እንግዲህ የቴዲ አፍሮ ተወዳጅነትም የሚያረጋግጠው የመንግስትን መጠላት እንደሆነ መፍረድ ቀላል ነው ማለት ነው፡፡

4. የጀማሪ አባሎች ስጋት
ኢሕአዴግ ሰባት ሚሊዮን አባላት እንዳሉት ይናገራል፡፡ በርግጥ የአባላት ብዛት የተደጋፊነትን ብዛት እንደማያረጋግጥ (በምርጫ 97) ያረጋገጠው ብቸኛ የዓለማችን ፓርቲ ኢሕአዴግ ራሱ ይመስለኛል፡፡ ሆኖም በአባሎቹ ቁጥር ብዛት ሲቪውንና ደረቱን ለማሳበጥ ከመሞከር አልተቆጠበም፡፡ ይህ በእንዲህ እናዳለ ምናልባት ሥራ ከተገኘ፣ ምናልባት ሹመት ከተገኘ፣ ምናልባት ነፃነት ከተገኝ፣ ምናልባት ምናምን ከተገኘ ብለው በየወሩ የአባልነት መዋጯቸውን በምናልባት የሚገፈግፉ አባላት÷ አባልነታቸውን በምስጢር መያዝ ይወዳሉ፡፡ መረጃ አፈትልኮ የታወቀባቸው ዕለት እንኳን የሚዘባርቁት ምክንያት የገዢው ፓርቲ አባልነት ማሕበራዊ ነውር የሆነ ያስመስለዋል፡፡

ይሄ ሁሉ የሆነው የሆድ ነገር አባል ያደረጋቸው ዜጎች ከተጠላው መንግስት ተርታ ተሰልፈው ከወገናቸው ወዲያ እንዳይመደቡ በመስጋታቸው ነው፡፡

5. ኢቴቪዮጵያ
የኢሕአዴግ መንግስት ሁሉንም የመንግስት ሚዲያዎች የፓርቲ ልሳን ቢያደርጋቸውም እንደኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ግን በየቤቱ እያንኳኳ የሚገባ ደፋር የለም፡፡ ምን አስቦ እንደሆነ ባይታወቅም (በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ) ከነጋዴው፣ ከመምህሩ፣ ከክርስቲያኑ፣ ከሙስሊሙ… ከተገኘው ሁሉ ጋር በመቀያየም ላይ አትኩሮ እየተንቀሳቀሰ ያለው ኢሕአዴግ በኢቴቪ የሚያቀርባቸው የፕሮፓጋንዳ ዶኩመንተሪዎች የታለመላቸውን ያህል ውጤት በማስመዝገብ ፈንታ ለቴሌቪዥኑ ቅጽል ስሞችን አፍርተውለታል፡፡

በኢቴቪ በኩል መንግስት ‹እንዲህ አደረግኩላች› ሲል÷ ‹እንዲህ አደረግኳችሁ› እንደማለት፣ ‹እንዲህ አደረጓችሁ› ሲል ደግሞ ‹እንዲህ አደረጉላችሁ› ያለ ይመስል በተቃኒው ይተረጎምበታል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ ነገርን ጠምዝዞ የመተርጎም ልምድ ያፈራው ከኢሕአዴግ ቴሌቪዥን (ኢቴቪ) ወዲህ ነው፡፡ የዚህ ሁሉ አንድምታ ከጠሉት መንግስት እውነት የራስ ውሸት ይሻላል የሚል ነው፡፡

መደምደሚያ፡- የኢትዮጵያ መንግስት ተጠልቷል፡፡ በርግጥ ይህንን መንግስት እያወቀ ችላ የሚልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ነው፣ ምናልባትም ደግሞ መንግስትም የኢትዮጵያን ሕዝብ ስለሚጠላው የተለየ ነገር አይጠብቅ ይሆናል፣ ምናልባትም ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጥሩ ነገር ተሳክቶልኝ ሰርቼ እክሳቸዋለሁ ብሎ አስቦ ይሆናል፡፡ የመንግስት ፍላጎት ምንም ቢሆን ምን የሕዝቡ ጥላቻ ግን የሚያመለክተው ለውጥ እየፈለገ እንዳጣ ብቻ ነው፡፡

1 comment:

  1. እንደ ከተሜነቴ ሳየው፤ የኢትዬጵያ መንግስት መጠላት አይገርመኝም፡፡ የብሔር ፖለቲካው፤ ኮሚኒስታዊ ፕሮፓጋንዳው እና እስካሁን በኔጌቲቭ ኢነርጂ ማስተዳደሩ ከመጠላትም በላይ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ግን ግን..እዚህ አሜሪካ ያለው፤ ተወዳጅ የሚመስለው መንግስት፤ የሚወርድበትን ስድብ እና የሚደረግበትን የጥላቻ ቅስቀሳ ሳይ፤ የተቃዋሚዎችን ምርር ያለ ስም ማጥፋት እና ሁሉን ነገር የመቃወም ስሜት ሳይ፤ በዓለም ላይ የማይጠላ መንግስት ያለ አልመስል ይለኛል፡፡ መንግስት በባሕርይው እንዲጠላ የተፈጠረ ነገር ሳይሆን አይቀርም፡፡

    ReplyDelete