Pages

Wednesday, May 30, 2012

10ሩ የድህረ-ግንቦት 20 ኪሳራዎች


አቶ መለስና ጓደኞቻቸው አምባገነን ስርአትን ለመቀየር ነፍጥ አንስተው፣ በጭቆና ላለመኖር ሲሉ በህይወታቸው ተወራርደዋል፤ አላማቸውን ለማሳካት ገድለዋል ሞተዋል፡፡ ድል ቀንቷቸው የዛሬ 21 አመት አምባገነኑን የደርግ ስርአት አስወግደው ምኒሊክ ቤተመንግስት ሲገቡ ኢትዮጵያን በለውጥ ጎዳና ሊመሩ፣ ዴሞክራሲን በማስፈን በሀገሪቱ አዲስ ታሪክ እንዲያኖሩ የሚያስችል ዕድል ነበራቸው ፡፡ አምባገነኑን የኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያምን ደርግ ካስወገዱ በኋላ ግን አምባገነኑን የአቶ መለስ ዜናዊን ስርአት ከማስቀመጥ ባለፈ በግንቦት 20 ድል ታሪክ ሊሰሩ አልቻሉም፡፡ 

ያ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለበት፣ በተለያዩ ጎራዎች የተሰለፉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት ዶጋ አመድ አድርጎ ግንቦት 20, 1983 ዓ.ም የተቋጨው ጦርነት አንድን ወታደራዊ አምባገነን መሪ በኃይል በማስወገድ የይምሰል ዴሞክራሲያዊ ስርአትን(pseudo democracy) የገነባ ሲቪል አምባገነን መተካት የተወሰነ ቡድንን ወይም ግለሰቦችን ፖለቲካዊ የበላይነት(hegemony) ለማረጋገጥ ያለመ እንዳልነበር በትጥቅ ትግሉ ተሳታፊ የነበሩ ግለሰቦች ያረጋግጣሉ፡፡ የህወሓት ነባር ታጋይና የቀድሞው የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገብሩ አስራት ሰኔ 19,2002 ለወጣችው አዲስ ፕሬስ ጋዜጣ አሞራው ስለተባለ የህወሓት ጀግና ታጋይ ሲያስረዱ ‹‹አሞራው ቀና ብሎ እየተደረገና እየሆነ ያለውን ነገር ቢያይ ይገርመው ነበር›› ካሉ በኋላ የአቶ መለስ መንግስት በአሞራውና በሌሎች ታጋይ ሰማእታት መስዋዕትነት ስልጣን እየነገደ መሆኑን አብራርተዋል፡፡  

ህወሓት/ኢህአዴግ ስልጣን የያዘበት ተመሳሳይ ወቅት አምባገነናዊ ኮሚኒስት ስርአቶችን በማስወገድ ዴሞክራሲያዊ ግንባታ የጀመሩት የምስራቅ አውሮፓ ሀገራት በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ ለውጥ ማምጣታቸውን Carleton UniversityInstitute of European and Russian Studies  አጥኚ የሆኑት ድራጎስ ፖፓ (DRAGOS POPA) ሮሜኒያንና ቡልጋሪያን ነቅሰው ያመላክታሉ፡፡ የባልካን ሀገራትም ሁለት አስርት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ እምርታ ማምጣታቸውን  The democratic transformation of the Balkans በሚል ርዕስ የቀረበው የሮዛ ባልፈር እና ኮሪና ስትራቱላት (Rosa Balfour and Corina Stratulat) ጥናት ያመላክታል፡፡  ጥናቱ የባልካን ሀገራት በአጭር ጊዜያት ውስጥ ሶስት መሰረታዊ ለውጦችን ማስመዝገባቸውን ያስረዳል‹‹ከጦርነት ወደ ሰላም፣ ከኮሚኒዝም የእዝ ኢኮኖሚ ወደ ነፃ ገበያ እንዲሁም ከአንድ ፓርቲ አገዛዝ ወደ መድብለ ዴሞክራሲ ተለውጠዋል›› ይላል፡፡ በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ባለፉት 21 አመታት የታየውና አሁንም ያለው ነባራዊ ሁኔታ ለግንቦት 20 ድል የወጣውን  የህይወት ግብር እና በድሉ ማግስት የተገኘውን የግንቦት 20 ፍሬ ስናወራርድ ውጤቱ ኪሳራን የሚያመላክት ነው፡፡
ይህ ጽሁፍ በህወሓት በስተመጨረሻም በህወሓት/ኢህአዴግ መሪነት ለ17 አመታት በተደረገው ፅኑ ትግል የተገኘው የግንቦት 20 ድል ሊያመጣ ያልቻላቸውን አስር አንኳር ነጥቦች ይፈትሻል፡፡   

Tuesday, May 29, 2012

ከ21 ዓመት በኋላ (ዴሞክራሲ ሲሰላ)

From አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

ኢሕአዴግ ከ21 ዓመታት በኋላ በዴሞክራሲ ጎዳና ወደኋለ መመለሱን ለማረጋገጥ ጥናት አያስፈልገውም፡፡ ታሪክን ባጭሩ ‹‹መገረብ›› በቂ ነው፡፡ ሆኖም ከሰሞኑ የተሰራች ትንሽዬ ቅኝትም የምንገርበውን የታሪኩን ወቅታዊ ደረጃ ውጤት ታረዳናለች፡፡

ኢሕአዴግ በትጥቅ ትግል አምባገነኑን ደርግ ከገረሠሠ በኋላ የሽግግር መንግስት አቋቋመ፡፡ የሽግግር መንግስቱ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ በነፃ ሐሳብ የመግለፅ መብትን እና ወዘተ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚደነግገውን ሕገ መንግስት ቀረፀ፡፡

በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሳተፉበት ምርጫም (ከነእንከኑ) ተካሄደ፣ ተደገመ፡፡ በርካታ የግል ጋዜጦች ተከፈቱ፣ ብዙ ሰዎችም ትንፋሽ ታፍኖ ከሚኖርበት የደርግ የኑሮ ዘዬ በከፊል በመላቀቅ ለመብታቸው ጥብቅና መቆም እና ሐሳባቸውን መግለፅ ጀመሩ፡፡ በዚህ መሃል ሦስተኛው ብሔራዊ ምርጫ (97) መጣ፡፡ ያ ወቅት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ከፍተኛ ጫፍ (maximum peak) ላይ የደረሰበት ወቅት ነበር፡፡

ምርጫ 97 መጨረሻው ብጥብጥ ሆነ፡፡ ከዚያ በኋላ እያቆጠቆጠ የነበረው ሕዝባዊ ነፃነት እና ዴሞክራሲ ወደአፎቱ ተመለሰ፡፡ ኢሕአዴግም በኢትዮጵያ ታሪክ በምርጫ ስልጣን በመልቀቅ አዲስ ምዕራፍ የመክፈት ዕድሉን በገዛ ፈቃዱ ገደለው፡፡ በርካታ አዋጆች የዴሞክራሲያችንን አቅም፣ የሕዝቡን ነፃነት እና እምነት አሽመደመዱት፡፡

ዛሬ መንግስት ዴሞክራሲን እያሳደገ እንደሆነ ቢናገርም፡፡ እስካሁን ድረስ በሕገመንግስቱ የተቀመጡት መብቶች ባይፋቁም ተግባራዊነታቸው ግን ወደ 1983 ተመልሶ ‹በ› ጉብጠት (n-curve) ሰርቷል፡፡

Monday, May 21, 2012

የመፈረጅ ፍራቻ እና የመፈረጅ አደጋ


አንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ባሳለፍነው እሁድ (ግንቦት 12፤ 2004) ‹‹የስነጥበብ ሚና በማሕበረሰብ ውስጥ›› የሚል የውይይት መድረክ በብሔራዊ ቴያትር አዳራሽ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ውይይቱን የመሩት ፀሃፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ፣ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማሕበሩ አበረ አዳሙ፣ ቀራፂ በቀለ እና ሰአሊ እሸቱ ጥሩነህ ነበሩ፡፡

እነዚህ የበቁ ባለሙያዎች ጥበብ ለማሕበረሰቡ፣ ማሕበረሰቡም ለጥበብ ማበርከት ይችላሉ ያሏቸውን ጠቁመዋል፡፡ ውይይቱ የተሟሟቀው ግን ዝግጅቱ ከመጠናቀቁ አንድ ሰዓት በፊት ታዳሚዎች ጥያቄዎችን ማንሳት ከጀመሩ በኋላ ነው፡፡

በውይይቱ ውስጥ አከራካሪ የነበረው ነጥብ የኪነጥበብ ሰዎች ሐሳባቸውን ለመግለፅ የመፍራት ጉዳይ ነበር፡፡ እኔም ይህን ጽሁፍ እንድጽፍ መንስኤ የሆነኝ ይኸው የፍራቻ ጉዳይ ነው፡፡

ፀሃፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ በሙያቸው የተካኑ መሆናቸው አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይሁንና በውይይቱ መክፈቻ ላይ የያዙትን ጽሁፍ ማቅረብ ከመጀመራቸው በፊት ግልፅ ማድረግ የሚፈልጉት ነገር እንዳለ ተናገሩ፡፡ ‹‹እኔ የማንም ወገንተኛ አለመሆኔን ግልፅ ማድረግ እፈልጋለሁ፤›› አሉ፡፡ በንግግራቸው መሃልም ኪነጥበብ የማሕበረሰብ ሃያሲ ነች ካሉ በኋላ ‹‹ፖለቲካ ውስጥ አታስገቡኝ እንጂ ፖለቲካም ሃያሲ አለው›› አሉ፡፡

Friday, May 18, 2012

ዴሞክራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ወይስ የለም? (እርስዎ ምን ይላሉ?)

From አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

ዴሞክራሲ ትልቅ ፅንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ከዚያም ባሻገር ሆኖም ልክ እንደአብዛኛዎቹ የዓለማችን እውነታዎች ፍፁም ሊሟላ አይችልም፡፡ ነገር ግን ምሁራን ዴሞክራሲን መለኪያ ቅንጣቶችን ያስቀምጡለታል፡፡ በነዚህ ቅንጣቶች እየለኩም ነው ሃገራትን ዴሞክራሲያዊ፣ ከፊል ዴሞክራሲያዊ፣ ፀረ ዴሞክራሲያዊ… እያሉ ሲፈርጁ የምንመለከተው፡፡ እኛስ፣ ኢትዮጵያውያን ራሳችን ዴሞክራሲያችንን መመዘን ብንችል ብላችሁ ተመኝታችሁ አታውቁም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቂት የማሰቢያ ቋቶች (think tanks) አሁን አሁን ብቅ ብቅ ማለት ቢጀምሩም ብዙዎቹ ደፍረው ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን እያነሱ ጥናት አያደርጉም፡፡  በየዓመቱም እየገመገሙ ‹‹አድገናል፣ ወድቀናል›› አይሉንም፡፡ አገራችን ‹‹በማደግ ላይ ያለች›› በመሆኗ እና ምናልባትም እጅግ ዴሞክራሲያዊ የሆኑ መንግስታት ስታገኝ እንዲህ ዓይነት ተቋማት ወደፊት እየተበራከቱ እንደሚመጡ ተስፋ ማድረግ ብንችልም እስከዚያው ግን እኛ የበኩላችንን ጥረት ብናደርግስ?

ብዙ ጊዜ የሚሞግተኝ ጥያቄ አለ፡፡ (በተለይ ይህንን ጦማር ለማንበብ የታደልነው) ብዙዎቻችን ከተሜዎች ወይም ከተማ ቀመስ ነን፡፡ 80 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን የገጠር ነዋሪዎች ናቸው፤ በይነመረብ (Internet) ለነርሱ ቅንጦት ነው፡፡ ለብርሃን ያህል የኤሌክትሪክ ኃይል እንኳን ለማግኘት አልታደሉምና ማለቴ ነው፡፡ ታዲያ ስለኢትዮጵያ ስናወራ ከራሳችን ስሜት እና ልምድ ተነስተን እንደመሆኑ የብዙሐኑን ስሜት እና እውነት ማንፀባረቃችንን እርግጠኛ መሆን ይቸግረኛል፡፡ እርግጥ ነው፤ ገጠሬው ኢትዮጵያዊ የሚባልለትን ያህል እንዳልበለፀገ እግር ጥሎን ስንሄድ፣ ዘመድ አዝማዶቻችን ሲመጡ እና በሌሎችም አቋራጮች እንገነዘባለን፡፡

ችግሩ

Saturday, May 12, 2012

የጋንዲ፣ ኪንግ እና ማንዴላ መንፈስ

From Addis Ababa, Ethiopia

ማሕተመ ጋንዲን፣ ማርቲን ሉተር ኪንግን እና ኔልሰን ማንዴላን ስታስታውሱ መጀመሪያ ወደአዕምሯችሁ የሚመጣው ነፃነት ነው፤ በትግል የተገኘ ነፃነት፡፡ ሦስቱም ስለነፃነት የኖሩ፣ ዘመን የሞገታቸው ነገር ግን የታገሉለትን ነፃነት እየኖረ ያለው እነርሱን ተከትሎ የመጣው ትውልድ በልቡ ሃውልት ያቆመላቸው የ20ኛው ክፍለዘመን ድንቅ ፍሬዎች ናቸው፡፡ ሦስቱም የተወሰደባቸውን ነፃነት ለማስመለስ ብረት ማነገብ ያላስፈለጋቸው፣ ሰላማዊ የነፃነት እና የእኩልነት ታጋዮች ነበሩ፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያኖችስ ከነእዚህ የዓለም ሃብቶች አንፃር ራሳችንን አይተነው እናውቅ ይሆን?

ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር እና ኔልሰን ማንዴላ የማሕተመ ጋንዲ የመንፈስ ፍሬዎች ናቸው፡፡ ሁለቱም በማሕተመ ጋንዲ የትግል መርሕ የተቀረጹ ናቸው፡፡ የማሕተመ ጋንዲ መርሕ ‹ሰላማዊ ተቃውሞ› ነው፡፡

ማሕተመ ጋንዲ በእንግሊዞች የበላይነት የምትመራውን ሃገራቸውን - ሕንድ ነፃ ለማውጣት ይጠቀሙበት የነበረው ዘዴ - ብረት አልባ ጦርነት ነበር፡፡ ሰላማዊ እምቢተኝነት እና አለመተባበር የተባሉ መሳሪያዎች፡፡ ማሕተመ ጋንዲ በሕንድ ለሕንዳውያን እኩልነት መታገል ከመጀመራቸው በፊት በደቡብ አፍሪካ ያሉ ሕንዳውያን የሚደርስባቸውን ጭቆና በመታገል ነው የጀመሩት፡፡ ጋንዲ በደቡብ አፍሪካ ቆይታቸው አንደኛ መደብ ዜጋ ለሚባሉት (ነጮች) ብቻ በተፈቀደ ባቡር ውስጥ በገዛ ፈቃዳቸው (በእምቢተኝት) በመሳፈራቸው በጥበቃ ኃይሎች ተወርውረው ከባቡሩ እንዲወጡ ተደርገው ነበር፡፡ ጋንዲን ይሄ ‹‹አርፈው እንዲቀመጡ›› አላደረጋቸውም፤ እንዲያውም በእምቢተኝነታቸው በመቀጠላቸው በማግስቱ በአንደኛ መደብ የባቡር ክፍል ውስጥ መሳፈር እንዲችሉ ተፈቅዶላቸዋል፡፡

Thursday, May 3, 2012

አብዮት ወረት ነው!

From አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

ከአብዮት ስሜት ቀመሱ (‹‹የተቀለበሰው አብዮት›› ብንለውም ችግር የለውም) ምርጫ 97 ወዲህ በርካታ ኩነቶች ተከስተዋል፡፡ መንግሰት ሁለተኛ ያንን ዓይነት ገጠመኝ እንዳይከሰት ቀዳዳዎችን ሁሉ በመድፈን ሥራ ተጠምዷል፤ ተቃዋሚዎችም በበኩላቸው ያንን ዓይነት ገጠመኝ ድጋሚ ለመፍጠር የቻሉትን ያህል ደክመዋል፡፡ እስካሁን ባለው ሒደት የመንግስት ሙከራ የተሳካ ይመስላል፡፡

የብዙዎች ጥያቄ፡-
‹‹ሕዝቡ ምን ነካው? ጭቆና ተስማምቶት ነው? ፈርቶ ነው? በተቃዋሚዎች እምነት አጥቆ ነው? ወይስ...?››

በርግጥ ለነዚህ ጥያቄዎች የሚሆን አጥጋቢ መልስ ለማቅረብ ሰማንያ ሚሊዮን ሕዝብን ያካተተ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ጥናት ሳያደርጉ (በኔ የማስተዋል ደረጃ) የግልን ግምገማ ብቻ በማስቀደም ሊደረስበት የሚችለውን ድምዳሜ ነው እዚህ የማስነብባችሁ፡፡

አብዮት ምንድን ነው?