Skip to main content

መጽሐፍ የሚወጣው፣ የተዋነይ ዘ ጎንጅ 5 መሥመር ቅኔ

ጎንጅ ቅኔ ያጠናበት ደብር ሥም ነው። ደብረ ጥበብ ጎንጅ ቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም። ተዋነይ የባለቅኔው ሥም ነው። (የግዕዝ ትርጉሙ "ዋናተኛ" ማለት ነው።) ሊቁ ተዋነይ የልኅቀቱን ያክል እምብዛም አይወራለትም፤ ነገር ግን በዘመኑ ወደር የሌለው ልኂቅ ስለመሆኑ ሥራው ይናገራል። የሕይወት ተፈራ "Mine to Win" የተሰኘ ድርሰት መቼቱን በዐፄ ዮሓንስ ንግሥና ዘመን፣ በጎጃም/ጎንደር የቅኔ መማሪያ ደብሮች ያደረገ ልብወለድ ነው። ልቦለዱ የቅኔ ትምህርት ስርዓትን ያስተዋውቀናል፤ በበኩሌ የቅኔ ትምህርትን እና የቅኔ ሊቃውንት ታላቅነት ቀድሞ ከነበረኝ ግንዛቤ የበለጠ እንዲሆን አድርጎኛል። በተለይ የተዋነይ ዘ ጎንጅ (በውኑ ዓለም የነበረ ባለቅኔ) ተከታይዋ አምስት መሥመር ቅኔ መጽሐፍ የሚወጣት እንደሆነች ልቦለዱ አሳሰበኝ። ወይም በአጭሩ ብዙ ምዕራባውያን ስንት መጽሐፍ የጻፉለት ፍልስፍናን በአምስት መሥመር ይዟል። የቅኔው ትርጓሜ የመጽሐፍ ቅዱስን እና የመጽሐፍ ቅዱሱን ፈጣሪ ኅልውና ይሞግታል።
“የአምን ወይገኒ
ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ
ብዙኃን እንዘ ይገንዩ ይስግዱ ቅድሜሁ
ለነጽሮ ዝኒ ነገር እሥራኤል ከመይፍርሑ
ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ
ወ ፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ።”
(ተዋነይ ዘ ጎንጅ። ምንጭ፣ሕይወት ታደሰ ወደአማርኛ የተረጎመችው የሕይወት ተፈራ መጽሐፍ)
ትርጉሙን በኋላ እመለስበታለሁ። ስለተዋነይ መጀመሪያ የሰማሁት የበውቀቱ መጽሐፍ ላይ ነበር። እሱም በጨረፍታ - “የሌሊት ዜማዎች” የሚለው ግጥሙ ውስጥ። በውቀቱ ተዋነይን በግጥሙ ግርጌ ማስታወሻው አስተዋውቆን ያልፋል፣ “ተዋነይ በቅኔ ቤት አፈ ታሪክ ሞትን በግዝት ለሰባት ዓመታት ያቆመ ጀግና ነው"። ከዚያ በኋላ፣ አዲስ አድማስ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ተዋነይ የተላከበትን መልአከ ሞት ደጃፉ ላይ በምትሐት 7 ዓመት አቁሞት በማርያም አማላጅነት ነው ገብቶ ነፍሱን እንዲወስድ የፈቀደለት የሚል አፈ ታሪክ አለ ይለናል። በሌላ በኩል ዕፀ ሕይወት አግኝቶ ነገር ግን በአጠቃቀም ስህተት ግማሽ ሰውነቱ ሞቶ ግማሹ ሲኖር፣ ፈጣሪውን ለምኖ ነው ሙሉ ለሙሉ የወሰደው የሚል ሌላ አፈ ታሪክም አለ። የኋላ ኋላ ቴዲ አፍሮም አንድ ዘፈኑ ላይ ሥሙን ጠቅሶት ያልፋል።

በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን የተጻፈው የአለቃ ተክለየሱስ ዋቅጅራ "የኢትዮጵያ ታሪክ" (በሚል በሥርግው ገላው የተሰናዳው መጽሐፍ) ላይም ሥሙን እንዲሁ በአጭሩ ተጠቅሶ አገኘሁት። እንዲህ ይላል፣ “ዐፄ በካፋ በዘመኑ ከክፉ ሥራ በቀር ፩ ቀን በጎነት ሥራ አልሠራም። ያን ግዜ ተዋነይ የሚባል የጎንጅ ደብተራ ጠንቋይ ነበረው። ሙያው ከርሱ ጋራ ነበረ። በካፋም ፱ ዓመት ነግሦ [በ1723] በክፉ ሞት ሞተ።" ተዋነይን የቀድሞ ታሪክ የሚያስታውሰው እንዲህ ነው ማለት ነው? በርግጥም ይህን መሰል ቅኔ እየጻፈ መልካም ሥም ቢኖረው ነበር የሚገርመኝ። የፍቅር እስከመቃብሩ "ጉዱ ካሣ" የእውነተኛ ባለታሪክ ቢሆን ኖሮ (የእውነተኛ ሰው መነሻ ተደርጎ ነው የተጻፈው የሚሉ አሉ) በታሪክ የሚታወሰው እንደቀውስ ነበር። ከዚህ አንፃር የተዋነይ ዘ ጎንጅ እንደ ጠንቋይ መታወስ ላይገርም ይችላል። በነገራችን ላይ፣ ተዋነይ የዐፄ በካፋ አማካሪ ከመሆኑ በፊት የንጉሡን ምግብ ዕፀ መሰውር ለብሶ (እንዳይታይ ሆኖ) ይበላባቸው ነበር የሚባል አፈ ታሪክም አለ።
ከዚያ በኋላ ደግሞ ገጣሚው ኤፍሬም ሥዩም “ተዋነይ" በሚል ርዕስ “ብሉይ የግዕዝ ቅኔያት ፍልስፍና” ትርጉም የያዘ መጽሐፍ አሳትሟል። "ቅድመ መግቢያ"ውን የጻፉለት ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን የተዋነይን ሁለት ቅኔዎች መርቀውልን ያልፋሉ። ከሁለቱ አንዱ የታችኛው ነው።
“ፀሐየ ሰማይ ያውዒ ሀገረ መርቄ ርኁቅ፣
እንዘ ቅርብቶ ደደከ ኢያመውቅ።"
ትርጉሙ እንዲህ ነው፦
አንቺ ፀሐይ - አፍንጫሽ ሥር ያለው - ደጋ ምንም ሳይሞቅ፣
እንደምን ተቻለሽ - ቆላውን ከሩቁ - እንደዚህ ማወበቅ።
[ሳይንስ ለዚህ የተዋነይ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ የአየር ጥቅጥቅነት (ዴንሲቲ) ከፍታ ቦታ ላይ የሚቀንስ መሆኑን ነው። ሙቀት ደግሞ በባዶ ቦታ (ቫኪዩም) ላይ አይቆምም። ዞሮ፣ ዞሮ ሳይንስ የሚመልሰው ጥያቄው ቀድሞ የተገኘ እንደሆነ ነው።] ተዋነይ የነበረው ጭንቅላት እንዲህ ዓይነት ጠያቂ ነበር፤ አጠያየቁ ደግሞ በቅኔ።

ስለተዋነይ ሕይወት ይሄ ነው የሚባል መረጃ አላገኘሁም። ነገር ግን የዛሬ ሰዎች ለተዋነይ ቅኔ ያስተማረው መንፈስ ቅዱስ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ሰምቻለሁ። በመጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ በውኃ ላይ እንደተራመደ ሁሉ፣ ተዋነይም በጣና ውኃ ላይ የሚራመድ ምትሐተኛ ነበር የሚሉትም አሉ። በደመና ተጭኖ ዓለምን ጎብኝቷል እስከማለትም ይደርሳሉ።
"ተዋነይ በጣና፣
ይመስላል ደመና" ይባላል። 
ኤፍሬም "የቅኔ ፈጣሪዋ" ይባላል ይለናል - ተዋነይን። ነገር ግን በትርጉሙ ላይ በመግቢያዬ የጠቀስኳትን፣ ይሄን ሁሉ ለመዘብዘብ ያበቃችኝን ቅኔውን፣ ከሌሎች ተርጓሚዎች በተለየ ነው የተረጎማት። ሲጀመር፣ የመጨረሻዎቹን ሁለት ስንኞች ብቻ ነው የሚተረጉማቸው። ሲቀጥል፣ የአማርኛ ትርጉሙ ላይ አምስቱንም መሥመሮች ነው የሚተረጉማቸው። "የሚያነቡት አማርኛውን ብቻ ነው" ብሎ ነው ብለን እንዳንገምት ደግሞ መግቢያው ላይ "ምጣኔነቷ ሁለት መሥመር ነው" ይለናል። ትርጉሙን እነሆ፣
“የሕግ ባለሟል
የፍት’ አባት ሙሴ
ከሕግ አንቀፅ በፊት ሊያመልከው ‘ሚሻውን
ፈጣሪን ፈጠረው።
ፍትሕ ‘ሚባል እግዜር
ሕግ የሚባል እግዜር
ሙሴ እርሱን ለመውደድ ሲጨነቅ አይና
ፈጣሪ ወደደው ሙሴን ፈጠረና።”
ይህ የኤፍሬም ትርጉም፣ በኔ እምነት፣ የተዋነይን ፍልስፍና ግልጽ አያደርገውም። የመጨረሻዎቹን ሁለት ስንኝ ትርጉሞች ያየን እንደሆነ፣ ‘ፈጠረ’ የሚለውን ቃል ለሙሴ ሲሆን ‘ወደደ’፣ ለፈጣሪ ሲሆን ደግሞ ‘ፈጠረ’ እያለ ተርጉሞታል። ይህ “ሙሴ ፈጣሪውን ፈጠረ” ብሎ አንድ ክርስቲያን ሊጽፍ አይችልም ከሚል አዕምሮ የፈለቀ ትርጉም ይመስላል። ይህንን ይዤ አንዲት በፒኤችዲ ደረጃ የግዕዝ ተማሪ ወዳጄ የሆነችው ሔዋን ስምኦን ጋር ሔድኩኝ። እሷም [‘አዋቂዎች ጠይቃ’] ‘ፈጠረ’ የሚለው የግዕዝ ቃል ሊኖሩት ከሚችሉት ትርጉሞች መካከል ሁለቱ “ወደደ” እና “ፈጠረ” የሚሉት መሆናቸውን ነገረችኝ። (የሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን ግዕዝ - አማርኛ መዝገበ ቃላት ግን ‘ፈጠረ’ ለሚለው እና ለ11 ብዜቶቹ አንድም ‘ወደደ’ የሚል ወይም ተቀራራቢ ትርጉም አይሰጥም።) የሆነ ሆኖ፣ በእርሷ የስድ ንባብ ትርጓሜ፣ የሙሉ ቅኔው እያንዳንዱ ስንኝ እንዲህ ሊተረጎም ይችላል።
“ያምናል ይገ:ዛል
ዓለም ሁሉ ራሱ ለፈጠረው
ብዙዎች አምነው በፊቱ ሲሰግዱ
ይሄንንም ነገር ለማስተዋል እሥራኤል ይፈሩ ዘንድ
ሙሴ ፈጣሪውን ወደደው
ፈጣሪውም እሱን ወደደው”
ይሁን እንጂ በእሷ ትርጉም ውስጥ ያሉት የመጨረሻዎቹ ሁለት ስንኞች፣ ከላይኞቹ ስንኞች ጋር በዐውድ አይገጥሙም። ትርጉማቸው እንዲያ ከሆነ ቅኔውን ተራ ያደርጉታል። ይህ ትርጉም የሚስማማቸው ሊቃውንት፣ ‘ተዋነይ የተቸው ከእሱ በፊት የነበረውን የጣኦት አምልኮ ነው’ ብለው ያምናሉ ብላኛለች። ነገር ግን እንደብሉይ ኪዳን ከሆነ ሙሴም ቢሆን መሰዊያ አስቀርፆ ነው እንዲያምኑ የሰበካቸው - መጽሐፉም የሚነግረን እንደዛ ነው። በዚህ የቅኔው ትርጉም ሔዋን እንዳለችኝ፣ "ብዙ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የተስማሙበት ነው"። እኔ ግን ስምምነቱን አሳምኖኝ አልተቀበልኩትም። የቤተ ክርስትያን ሊቃውንት ሥራ አማኞችን መጨመር እንደሆነ አውቃለሁ። ስለዚህ የሕይወት ተፈራ መጽሐፍ (የአማርኛው ትርጉም) ላይ ያለውን የቅኔውን ትርጉም አማኝ ሊቃውንቱ የሚወዱትም የሚቀበሉትም አይመስለኝም። ሆኖም፣ ይህ የሕይወት ትርጉም፣ የመጨረሻዎቹን አወዛጋቢ ስንኞች ከላይኞቹ ጋር በዐውድ ስምም እንዲሆኑ ያደርግልናል። ከኤፍሬም ሥዩም ትርጉም የተሻለ የሚያሰኘውም ዐውዱ ነው።
“የሰው ልጅ በገዛ’ጁ፥ ላስቀመጠው ፈጥሮ
ይገ:ዛል ባንክሮ
ሰው ፈርቶ እንዲገ:ዛ፥ እንዲሰላ ኑሮ
ለዚኽም ማስረጃው የሙሴ ነገር ነው አምላኩን መፍጠሩ
አምላኩም ፈጠረው በአምሳሉ በግብሩ።”
(ሕይወት ታደሰ/ሕይወት ተፈራ/ኀሠሣ)

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዘፍጥረት” የሚባለው የመጀመሪያው መጽሐፍ የተጻፈው በሙሴ ነው። (የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዝ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ 5 መጽሐፍት በሙሴ እንደተጻፉ ብዙ ጥናቶች ይናገራሉ፤ ራሱ መጽሐፉ ይህንን ይጠቅሳል። ለምሳሌ ዘፀአት 24፥4 "ሙሴም የእግዚአብሔርን ቃሎች ጻፈ" ይላል፣ ሌሎችም ይህንኑ ያረጋግጣሉ።) የተዋነይ ፍልስፍና እዚህ ላይ ነው የሚገለጠው። ሙሴ እንዲህ ጻፈ፣ “እግዚአብሔርም አለ። ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ” (ዘፍጥረት 1፥26)። ተዋነይ ሲያነበው፣ የሙሴ ጽሑፍ ውስጥ የሰው ምኞት የታየው ይመስለኛል። የፈጣሪን በራሱ በሰው አምሳል የመሳል ነገር (ቀናተኝነት፣ ቁጡነት፣ መመለክ/መከበር መፈለግን፣ ወዘተ…)፣ የሰው ልጅ የሌሎች ፍጥረታት ገዢ የመሆን ምኞትም እዚሁ የዘፍጥረት ጥቅስ ላይ ተጽፏል። ስለዚህ መጀመሪያ ሰው ሳይሆን ፈጣሪ ነው በሰው አምሳል የተፈጠረው (“ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ”)፣ ከዚያ በሙሴ ቃል ውስጥ ነው፣ ፈጣሪ ሰውን የፈጠረው ( "ወ ፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ")።

ተዋነይ ዘ ጎንጅ የሙሴን ድርጊት እንደፍትሓዊ እርምጃ የቆጠረው ይመስላል። እስራኤላውያን ፈርተው የሚታዘዙለት አንድ ሕግ አውጪ መኖር ነበረበት። ለዚያም ነው በአምሳሉ መልሶ የሚፈጥረውን ፈጣሪ ሙሴ ቀድሞ በአምሳሉ የፈጠረው እያለን ይመስላል።

Comments

  1. ሚስተር ቤንጃሚን የኢሜል ዝርዝሮችን እነሆ ፣ Lfdsloans@outlook.com ፡፡ / ወይም ደግሞ ንግዴን ለመጀመር በ 90,000.00 ዩሮ ብድር የረዳኝ WhatsApp + 1-989-394-3740 እና እኔ በጣም አመስጋኝ ነኝ ፣ እዚህ አንድ ነጠላ እናት ነገሮች እንዳላደረጉ መንገድ ለመፍጠር እየሞከርኩ ነው ፡፡ ከእኔ ጋር ቀላል ይሁኑ ግን ንግዴ እየጠነከረ ሲመጣ እና እያሰፋ ሲሄድ እያየሁ በሚስተር ሚስተር እርዳታ ፊቴ ላይ ፈገግታ አሳየኝ ፡፡ የገንዘብ ድጋፍን መፈለግ ወይም በዚያ ንግድ ውስጥ መከራን ማለፍ ወይም የመነሻ የንግድ ሥራ ፕሮጀክት መጀመር መፈለግ ይህንን ማየት እና ከችግራቸው ለመውጣት ተስፋ ሊኖረው ይችላል ... እናመሰግናለን ፡፡

    ReplyDelete

Post a Comment

Popular posts from this blog

The "Corridor Development" is a Façade of the Prosperity Party

Befekadu Hailu I have seen a news report claiming that 40% of central Addis Ababa will be demolished for the corridor development; I am not able to confirm the validity of the news but it sounds real to me given the size of massive operations in the demolition of old neighborhoods and construction of bike lanes, green areas, and glittering street lights. I like to see some beauty added to my city but cannot help mourning the slow death of it too. Addis Ababa was already in a huge crisis of housing and the demolition of houses is exacerbating it. Apparently, Prime Minister Abiy Ahmed is eager to showcase his vision of prosperity by demonstrating how fast his administration can do magic by beautifying the front sides of the streets with lights, new pavements, and painted fences ("to fake it until he makes it" in my friend's words). Therefore, he and his party do not care about the miserable human stories behind the scenes and they will harass you if you tell it (Azeb Woku...

የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ

በፍቃዱ ዘ . ኃይሉ “የአዲስ አበባ ብሔርተኝነት” ቢኖር ኖሮ መሪው ልጅ ሚካኤል ይሆን ነበር። አሁን አሁን እሱ ስለ አዲስ አበባ የዘፈናቸውን ዘፈኖች ቁጥር ራሱ በትክክል መቁጠር ይቸግረኛል። ለአዲስ አበባ ከተዘፈኑ ዘፈኖቹ ውጪም በየዘፈኑ ውስጥ የሚጨማምራቸው መልዕክቶች በራሳቸው መወድሰ አዲስ አበባ ናቸው። ለምሳሌ፣ በቅርቡ በለቀቀው ‘አዲስ አራዳ’ በተሰኘው አልበሙ ውስጥ ‘የድሬ ልጅ’ የሚል ዘፈን አለው። ዘፈኑ የተዘጋጀው ያው የአዲስ አበባ እህት ተደርጋ የምትቆጠረውን ድሬ ዳዋን ለማወደስ ነበር። ልጅ ሚካኤል ግን የአዲስ አበባ ፍቅሩ ያመልጠውና የሚከተለውን ያቀነቅናል፦ “መጣልሽ በሏት፣ ድሬ ድረስ፣  ከአዱ ገነት፣ ከሸገር፣ ከአዲስ ደረሰ፣... የሸገር ልጅ አራዳ ነው፣ ሰው አክባሪ፣ ሰው ወዳዱ፣ ቀላጅና ተረበኛ፣ ፍቅር ይዞ የሚተኛ፣ ‘አለው’ የለ፣ ‘የለው’ የለ፣ ከሁሉ ጋ፣ ግባ ጀባ...፤” ፤ ልጅ ሚካኤል በዚህ አልበሙ ብቻ አዲስ አበባን የሚያውድሰባቸው ሌሎችም ዘፈኖች አሉ፤ ‘ አዲስ አራዳ ’ የሚለው የአልበሙ መጠሪያ እና ‘ሸገር’ የሚሉት ዘፈኖቹ ዋነኞቹ ናቸው። ታዲያ እንዲህ በአዲስ አበባ ፍቅር የሚቃጠለው ልጅ ሚካኤል "ሊነግረን የሚፈልገው ምንድን ነው?" የሚለው ጥያቄ ደጋግሞ ይመጣብኛል። ይህ የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ ምንነትን ለመረዳት የሚጥር ፖለቲካዊ መጣጥፍ ነው። ‘አዲሱ አራዳ’ ማነው? በዚህ ዘፈኑ በብዙዎቻችን ዕድሜ የትዝታ ማኅደር ውስጥ የሚገኙ ነገር ግን በአዲስ አበባ ልማት ሥም የፈረሱ እና እየተረሱ ያሉ ሰፈሮችን ሥም ያነሳሳል። ዘፈኑ በግጥሙም በዜማውም፣ የሐዘን እንጉርጉሮ ያለበት ነው። ምሳሌ እንውሰድ፦ “ጨርሰሽ ስትወጪ ከቡፌ ዳ’ላጋ፣ ጠብቂኝ እንዳልል፣ ቆመሽ መሐሙድ’ጋ፣ አገር ...