Pages

Monday, May 21, 2012

የመፈረጅ ፍራቻ እና የመፈረጅ አደጋ


አንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ባሳለፍነው እሁድ (ግንቦት 12፤ 2004) ‹‹የስነጥበብ ሚና በማሕበረሰብ ውስጥ›› የሚል የውይይት መድረክ በብሔራዊ ቴያትር አዳራሽ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ውይይቱን የመሩት ፀሃፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ፣ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማሕበሩ አበረ አዳሙ፣ ቀራፂ በቀለ እና ሰአሊ እሸቱ ጥሩነህ ነበሩ፡፡

እነዚህ የበቁ ባለሙያዎች ጥበብ ለማሕበረሰቡ፣ ማሕበረሰቡም ለጥበብ ማበርከት ይችላሉ ያሏቸውን ጠቁመዋል፡፡ ውይይቱ የተሟሟቀው ግን ዝግጅቱ ከመጠናቀቁ አንድ ሰዓት በፊት ታዳሚዎች ጥያቄዎችን ማንሳት ከጀመሩ በኋላ ነው፡፡

በውይይቱ ውስጥ አከራካሪ የነበረው ነጥብ የኪነጥበብ ሰዎች ሐሳባቸውን ለመግለፅ የመፍራት ጉዳይ ነበር፡፡ እኔም ይህን ጽሁፍ እንድጽፍ መንስኤ የሆነኝ ይኸው የፍራቻ ጉዳይ ነው፡፡

ፀሃፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ በሙያቸው የተካኑ መሆናቸው አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይሁንና በውይይቱ መክፈቻ ላይ የያዙትን ጽሁፍ ማቅረብ ከመጀመራቸው በፊት ግልፅ ማድረግ የሚፈልጉት ነገር እንዳለ ተናገሩ፡፡ ‹‹እኔ የማንም ወገንተኛ አለመሆኔን ግልፅ ማድረግ እፈልጋለሁ፤›› አሉ፡፡ በንግግራቸው መሃልም ኪነጥበብ የማሕበረሰብ ሃያሲ ነች ካሉ በኋላ ‹‹ፖለቲካ ውስጥ አታስገቡኝ እንጂ ፖለቲካም ሃያሲ አለው›› አሉ፡፡

አያልነህ ሙላቱ አርአያ ሊባሉ የሚችሉ የጥበብ ሰው ቢሆኑም በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ ፖለቲካውን ጥበብ መተቸት የምትችልበትን መንገድ ለመናገር አልደፈሩም፡፡ እኔም ይህንን ዓይነቱን ፍራቻ - የአያልነህ ሙላቱ ፍራቻ - በሚል ርዕስ ልጽፈው ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ርዕሱን ያስቀየሩኝ ምክንያቶች እኒህ ናቸው፤ (1) አያልነህ ሙላቱ ከአድማጮች ለተነሱ ጥያቄዎች ሲመልሱ ኪነጥበብ የአንድ ድርጅት ንብረት አትሆንም ማለቴ እንጂ ለእውነት ወግና ከመንግስት ጋርም ቢሆን ትጣላለች፤ ‹‹አለበለዚያ ግን ገደል ትግባ!›› ብለው በማስተባበላቸው፣ (2) ሰአሊ እሸቱ ጥሩነህ ‹‹እናንተ መስማት የምትፈልጉትን መስማት ስለምትፈልጉ እንጂ ገለልተኝነት ፍራቻም ጥላቻም አይደለም›› ብለው መናገራቸው ስላሳመነኝ እና (3) ግለሰብ ላይ ብቻ ማፍጠጡ ተገቢ ስላልሆነ ነው፡፡

ይሁን እንጂ የአያልነህ ሙላቱን ስጋት መተቸቴን አቆማለሁ ማለቴም አይደለም፡፡ እርሳቸው ምናልባት የጋበዛቸው ኢሕአዴግ ቢሆን ኖሮ ‹‹ለነገሩ የማንም ወገንተኛ አይደለሁም፤›› ይላሉ ብዬ አልጠብቅም፡፡ ምክንያቱም ጋባዡ ራሱ የሚፈራው አካል ነውና የፍራቻ መፈክሩ ቦታ የለውም፡፡

የአዲስ አበባ መስተዳድር ቴሌቪዥን ከንቲባው በሊዝ ጉዳይ ጥቂት ሰዎችን ሲያነጋግሩ አንድ አስተያየት ሰጪ ወጣት የተናገረው - የአያልነህ ሙላቱን ፍራቻ ያስታውሰናል፡፡ ወጣቱ ንግግሩን የጀመረው እንዲህ ብሎ ነው፤ ‹‹ይሄ መቃወም አይለም፤ እኔ እንደውም የኢሕአዴግ ደጋፊ ነኝ፡፡ ልማት አለ፡፡ ግን ለምንድን ነው መንግስት…›› ጥያቄውን ጠየቀ፡፡ በሚያስታውቅ ሁኔታ ወጣቱ በኢሕአዴ ተማርሯል፡፡ ነገር ግን የተማረረበትን መናገር ወይም መቃወም ሕይወቱን የሚያስከፍለው ነገር እንደሆነ ተሰምቶታል፡፡ መቃወሙ ከእነእከሌ ጋር እንዳያስፈርጀው ሰግቷል… ስለዚህ የኢሕአዴግ ደጋፊ መባልን መረጠ፡፡

እርግጥ ነው ይህ ዓይነቱ ስጋት ተቃዋሚዎች ዘንድም እየተከሰተ እንደሆነ አስተውያለሁ፡፡ ተቃዋሚዎችን ለመተቸት መሞከርም ወደ ወዲያኛው ወገን የሚያስፈርጅ ወንጀል እየሆነ የላይኛውን ቤት ባሕል ታችቤቶች ሲርመጠመጡበት ማየት የማይገባ ድርጊት ነው፡፡

ወደ ውይይቱ ስንመለስ፤ አቶ አበረ በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ደራሲዎች ችግር የሚጽፉትን የሚያነብላቸው ሰዎች ችግር እንጂ ፍራቻ እንዳልሆነ ተከራክረዋል፡፡ እንዲያውም የደራሲዎቻችንን ጽሁፍ አንብቡ እና ፍራቻ ካለበት፣ ስለወቅታዊ ቀውሶች ካልጻፉ ታዘቡን ዓይነት ውርርድ ከታዳሚው ጋር ተወራርደዋል፡፡ ‹‹ደራሲው ተበድሮና ሕይወቱን ለአደጋ አጋልጦ የሚፅፈው መጽሃፍ በአንባቢ ድርቅ ተመትቷል፡፡››

ኢሕአዴግ ሕዝቡን እንዲፈራው የሚያደርገው ባልተጻፈ አዋጅ እንደሆነ አቶ አበረ የገባቸው አልመሰለኝም፡፡ ምክንያቱም የማይፈራ ሕዝብ ካለ ጠያቂም ሕዝብ ይኖራል፡፡ እስካሁን (ከብርሃንና ሰላም አዲስ የስምምነት ደንብ በፊት) ምንም ዓይነት የተጻፈ የሳንሱር ደንብ አልነበረም፡፡ ሆኖም የተዘዋዋሪ ዛቻ፣ ማስፈራሪያና ሽንቆጣዎች አሉ፡፡ ይህንን መረዳት ያልቻሉት (ያልፈለጉት) የደራሲያን ማሕበር አባል (በርግጥ ውይይቱ ላይ የተገኙት ማሕበሩን ወክለው እንዳልሆነ መግቢያቸው ላይ ገልፀዋል፤) ከታዳሚው ጋር በቅድመ ምርመራ ‹አለ!-የለም!› እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡

ቀራፂ በቀለ ንግግሩን ከመጀመሩ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአርቲስቶች ጋር ሲወያዩ መገኘቱን ገልፆ ‹‹እዚያ ልሄድ እንደሆነ የሰሙ ሰዎች ‹እሱ ነገር እኮ አደጋ አለው› ብለውኝ ነበር፡፡ አሁንም እዚህ ልመጣ እንደሆነ ሲሰሙ ‹እሱ ነገር እኮ አደጋ አለው› አሉኝ፤›› ካለ በኋላ ‹‹የት ነው ታዲያ አደጋ የሌለው?›› የሚል ጥያቄ አንስቶ ነበር፡፡ እኔም ይህንን ጽሁፍ መደምደም የምፈልገው በተመሳሳይ ጥያቄ ነው - የት ነው አደጋ የሌለው?

1 comment:

  1. ለምን ሀሳብህን አልጨረከውም?የመፈረጅ ፍራቻ እና የመፈረጅ አደጋ ነው?

    ReplyDelete