ከአብዮት ስሜት ቀመሱ (‹‹የተቀለበሰው አብዮት›› ብንለውም
ችግር የለውም) ምርጫ 97 ወዲህ በርካታ ኩነቶች ተከስተዋል፡፡ መንግሰት ሁለተኛ ያንን ዓይነት ገጠመኝ እንዳይከሰት ቀዳዳዎችን
ሁሉ በመድፈን ሥራ ተጠምዷል፤ ተቃዋሚዎችም በበኩላቸው ያንን ዓይነት ገጠመኝ ድጋሚ ለመፍጠር የቻሉትን ያህል ደክመዋል፡፡
እስካሁን ባለው ሒደት የመንግስት ሙከራ የተሳካ ይመስላል፡፡
የብዙዎች ጥያቄ፡-
‹‹ሕዝቡ ምን ነካው? ጭቆና ተስማምቶት ነው? ፈርቶ ነው? በተቃዋሚዎች እምነት አጥቆ ነው? ወይስ...?››
በርግጥ ለነዚህ ጥያቄዎች የሚሆን አጥጋቢ መልስ ለማቅረብ
ሰማንያ ሚሊዮን ሕዝብን ያካተተ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ጥናት ሳያደርጉ (በኔ የማስተዋል ደረጃ) የግልን ግምገማ ብቻ
በማስቀደም ሊደረስበት የሚችለውን ድምዳሜ ነው እዚህ የማስነብባችሁ፡፡
አብዮት ምንድን
ነው?
አብዮት - ከዚህ ቀደም እንዳወራነው - የእንግሊዝኛውን Revolution
እንዲተካ ‹‹በደርግ›› የተመረጠ፣ የግዕዙን ቃል ‹አበየ› (Revolut) መሠረት አድርጎ የተሰየመ ቃል ነው፡፡ አብዮት -
መንግሰትን ወይም ርዕዮተ ዓለምን የመተካት ሒደት ነው፤ አብዮት - ድንገታዊ እና ፈጣን ክስተት ነው፡፡
አብዮት እያንዳንዱ ትውልድ ቢያንስ አንዴ ሊያልፍበት የሚገባ
ከድሮ ተነስቶ ዘንድሮ ላይ የሚያርፍበት ድልድይ ነው፡፡ አብዮት የታመቀ የሕዝብ ጩኸት የሚፈነዳበት አጋጣሚ ነው፡፡
አብዮት ድንገተኛ እና ፈጣን ክስተት ቢሆንም መሪ አለው፡፡
እንደምሳሌ የምርጫ 97ቱን ‹‹የተቀለበሰ አብዮት›› ብንመለከት÷ የቅንጅት አመራሮቸን እንደመሪ ልንመለከታቸው እንችላለን፡፡
በርግጥ አብዮት ተከታይ የለውም፡፡ ለዚህም ነው በዚሁ ምርጫ ወቅት ሕዝቡ ንቁ ተሳታፊ፣ አደራጊ ፈጣሪ ሆኖ የተስተዋለው፡፡
የሚደግፈውን አካል (ቅንጅትን) ስሜት ሲመራ የነበረው - በዚህ የመሪነት ሚና ነው፡፡
‹‹ያ አብዮት ባይቀለበስ›› ኖሮ÷ ሕዝቡ ይመጣል ብሎ
የሚያስበውን ለውጥ እንዲያመጡ በአደራ የሚያስረክባቸው አካላት አሉት፣ ይመጣል ብሎ የሚያስበው ለውጥም አለ፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ
የዛኔው አብዮት ሳይሳካ በመቅረቱ ይህ ትውልድ እስካሁን ድረስ አብዮት እንደናፈቀው ቀርቷል፡፡ ነገር ግን ትውልዳዊ ግዴታ ነውና
‹‹መፈንዳቱ›› አይቀሬ ነው፡፡
አሁን በፌስቡክ አብዮት ‹‹ያፈነዳሉ›› ተብለው የተፈጠሩ በርካታ
አባላት ያሏቸው፣ ብዙ ቡድኖች አሉ፡፡ እነዚህ የተናጠል እርምጃዎች ግን መሠረታዊ የአብዮት ባሕሪ እንደሚጎድላቸው ለመረዳት ብዙ
ማሰብ አያስፈልገንም፡፡ እነዚህ የፌስቡክ አብዮት አማጪ ቡድኖች፡-
- መሪ የላቸውም፡- በርካታ የአብዮት ጥሪዎች ተካሒደዋል፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ ሕዝባዊ ነውጥ የሚጀመርበትን ቀን ቆርጠው ነበር፡፡ ለምን ከሸፉ? ምክንያቱም ያ ቀን የተቆረተለትን አብዮት እንዲጀምሩ ሕዝቦች ቢጋበዙም - ቀን የቆረጡት ሰዎች ማንነት በውል አይታወቅም? ቢታወቅም አብዮት ከሕዝቡ ጋር ተቀላቅለው ሊመሩት አልተዘጋጁም? ቢዘጋጁም አብዮቱን ተከትሎ ሊመጣ የሚችለው የለውጥ ዓይነት ምን እንደሆነ? ማን እንደሚተካ እና እንዴት እንደሚተካ በግልጽ ያሳወቁበት መንገድ የለም፡፡ አብዮት የሕዝብ ጥያቄ በሕዝብ የሚቀርብበት እና መልሱም በሕዝብ ግፊት የሚገኝ ቢሆንም፣ አስፈፃሚዎቹ ጥቂቶች ናቸው፣ መሆንም አለባቸው፡፡ ሁሉም ሰው አስፈፃሚ መሆን አይችልምና!
- መንስኤ የላቸውም፡- ሕዝብ የተጠራቀመ ብሶት ሊኖረው ይችላል፡፡ ሆኖም ሕዝብ አብዮት እያሰበ አይኖርም፡፡ ሕዝብ ኑሮውን ለማሸነፍ ሲፍጨረጨር ብዙ ነገሮችን ሊያመልጡት ይችላል፡፡ አዋጆች አይሰማም፤ ሌላው ቀርቶ የኑሮው ማሽቆልቆል የአስተዳደር ችግር ውጤት መሆኑን አያስተውልም፡፡ ስለዚህ አብዮት በቀጠሮ የሚቀሰቀስ ሳይሆን የሆነ መንስኤን ተከትሎ የሚቀሰቀስ (‹‹የሚፈነዳ››) ሲሆን÷ ያንን መንስኤ ደግሞ እንደመልካም አጋጣሚ በመቁጠር ተቃውሞው ግለቱን እየጨመረ ሄዶ የመንግስትን መቀመጫ የሚያናጋ እንዲሆን የሚያደርግ ጠንካራ ቡድን ያስፈልጋል፡፡ ግን እሰካሁን መንስኤዎችን የሚገጠም የተዘጋጀ ቡድን የለም!
- አቀንቃኞች የሉም፡- አብዮት እንዲቀሰቀስ ሕዝቡ የሚያምንባቸው፣ ያሁኑን ክፉ፣ የመጪውን ደግሞ ደግ ቁልጭ ባለ አገላለፅ የሚያሳዩ፣ ወኔያቸው የማይበርድ፣ ጀግንነታቸው የሚጋባ አቀንቃኞች (activists) ያስፈልጋሉ፡፡ በመሠረቱ አብዮት የሚቀነባበረው በነዚሁ አቀንቃኞች ነው፡፡ በእኛ አገር (በተለይም በፌስቡክ) የምናያቸው ‹‹አቀንቃኞች›› አንዳንዶቹ ጭፍን ጥላቻን የሚነዙ፣ አንዳንዶቹ በእውነተኛ ስማቸው እና ማንነታቸው የማይታወቁ፣ አንዳንዶቹ ከሃገር እና ሃገራዊ አጀንዳዎች የራቁ - በጥቅሉ እምነት የሚጣልባቸው ዓይነት አይደሉም፡፡
እነዚህና መሰል ችግሮች በአሁኑ ይዘቱ፣ ፌስቡክን በጥቅሉ ወይም
እስካሁን የተፈጠሩትን ቡድኖች በተለይ አብዮት ለመቀስቀስ የሚችል ብቃት ላይ አያስቀምጣቸውም፡፡ ነገር ግን የተደራጁ፣ ግልፅ
አካሄድ እና ዓላማ ያላቸው የአቀንቃኞች ቡድን ራሱን አዘጋጅቶ - መፍጠር የሚገባውን ብሔራዊ ግንዛቤ እየፈጠረ መቆየት ከቻለ -
አብዮት ወረት ነው - አንዴ ከተቀሰቀሰ ያልሰማው ላልሰማው እያስተላለፈ - እንደ ሰደድ እሳት ሃገሩን በሙሉ ማቀጣጠል
ይችላል፡፡
ብዙዎች የኢትዮጵያ የፌስቡክ ማሕበረሰብ አንድ ሚሊዮን
እንደማይሞላ፣ ካለውም ውስጥ ፖለቲካዊ ዒላማ ያለው ከአሥር ሺኅዎች እንደማይዘል አበክረው ይናገራሉ፡፡ እውነት ነው፡፡ ቢሆንም
በዓለማችን ግዙፍ የተባሉ አብዮቶች በሙሉ የተለኮሱት ማሕበረሰቦቹ ውስጥ ንቃት ያላቸው፣ ጥቂት ከተሜ ወጣቶች ቡድን አማካይነት
ነው፡፡
የንጉሣዊውን ሥርዓት የገረሰሰው አብዮት የተለኮሰው በተማሪዎች
አማካይነት ነው፡፡ ጥያቄው ግን የብዙሐኑ ገበሬ እና ጭሰኞች ነበር፡፡ የዛን ጊዜው አብዮት የፊውዳሉን ሥርዓት በመደምሰስ ወደ ‹ሕብረተሰባዊነት›
ተሸጋግሯል፡፡ ኢሕአዴግ ደርግን ሲጥል የነበረው ሒደት ከጥንት ጀምሮ የበረታው ነፍጠኛ፣ የደከመውን እያሸነፈ ራሱን ከሚያነግስበት
የረዥም ጊዜ የትግል ውጤት የተለየ አይደለም፡፡ ስለዚህ አብዮት ልንለው አንችልም፡፡
የአሁኑ ትውልድ የሚያስፈልገው አብዮት የዚያን አይነት ብረት-መር
ለውጥ አይደለም፡፡ አሁን ሕዝቡ የተጠማው ሰላማዊ፣ ያለ ደም መፋሰስ የሕዝቡን ፈቃድ ለሚፈፅም አካል ኃላፊነቱን ማስረከብ ነው፡፡
ይህንን ከግብ ለማድረስ ከዚህ በፊት (በምርጫ 97) ሞክሮ አልተሳካለትም፡፡ በምርጫ ያለው ተስፋ በመሟጠጡ በተቃውሞ አብዮት ሌላ
ሥርዓት የመተካት ፍላጎት መኖሩ ተፈጥሯዊም አይቀሬም ነው፡፡ በዚህ ጽሁፍ መግቢያ ላይ ስለሕዝቡ ለቀረቡት ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ
ሊሆን የሚችለው የሚከተለው ነው፡-
‹‹ግለሰቦች ሊልቁ ይችላሉ፤ የሚበጀውን የሚያውቀው ግን ሕዝቡ ነው፡፡ ሕዝብ ጭቆና አይስማማውም፣ ነገር ግን የተሻለ አማራጭ የሚመስለውን እሰከሚያይ ድረስ ዝም ብሎ ኑሮውን ይኖራል፡፡››
ግሩም ጽሑፍ፡፡ብረት-መር አብዬትን መቃወምህ ይደገፋል፡፡ የነጥቦችህ ሎጂካል ቅደም ተከተል ግን…መንስዔ…አቀንቃኝ…እና መሪ ቢሆን ይሻለኛል፡፡
ReplyDeleteየመንስዔ ነጥብህ ትክክል ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለን ‹‹ምግባችን ይሻሻል›› ‹‹ወጡ አልጣፈጠንም›› ብለን ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተን ጥያቄያችን ድንገት ወደ ‹‹ሥርዓተ ትምህርት ይሻሻል›› ጥያቄ እንደተቀየረ አስታውሳለሁ፡፡
ከዚያ ዓይናችን እያየ ያ ግብታዊ ሰላማዊ ሰልፍ መፈክር ባዬችን፤ ዘፋኞችን፤ ተናጋሪዎችን ፈጠረ (በጽሑፍ አቀንቃኝ ያልካቸው ይመስላሉ)፡፡
መጨረሻ ግን የዩኒቨርሲቲው ሴኔት የቀረቡት፤ በተማሪው የተሞገሱት፤ በኋላም የተቀጡት ጥቂት ተማሪዎች ናቸው፡፡ አንዱም ተባረረ፡፡ መሪዎችም በአብዬት ይፈጠራሉ እንጂ አብዬትን አይፈጥሩም የሚል አስተያየት አለኝ፡፡ መሪ አብዬትን ከፈጠረማ፤ መሪ ራሱ መንስዔ ሆነ ማለት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ሌላ ፍልስፍናዊ ሙግት ያስነሳል መሰለኝ…