Skip to main content

EthiopiaProtests: ‘የበሰለው ፍሬ’

ሐምሌ 2006 ከማዕከላዊ ወደ ቂሊንጦ ስዛወር፣ ዞን ሁለት ነበር የተመደብኩት። በወቅቱ በሽብር የተከሰሱ ብዙ ጎንደሬዎች ነበሩ። አልጋው ሥር "ደቦቃ" በማስተኛት ያስተናገደኝም ቢራራ የተባለ ጎንደሬ ነበር። ከዚያ በፊት ከሥሙ በስተቀር የማላውቀውን ፋሲል ደሞዝን አንድ ዘፈን ያስተዋወቀኝ እሱ ነው። ዘፈኑን እስከዛሬ ባልሰማውም ሁለቱን ስንኞች ግን በቃሌ ይዣቸዋለሁ። "አረሱትን አልሰማኸውም?" አለኝ ድጋሚ 'አልሰማሁትም' አልኩት ባለማወቄ ሲገረም አይቼ እያፈርኩ፤ ስንኞቹን ነገረኝ።

"አረሱት ይሉኛል የመተማን መሬት፣
ያውም የኛን ዕጣ
እነሱ ምን ያርጉ ከኛ ሰው ሲታጣ።"

ሰሞኑን 17 ያህል አርቲስቶች ለአዲስ ዓመት ዋዜማ አቅደውት የነበረውን የሙዚቃ ድግስ በሐዘናችን ምክንያት መሰረዛቸውን ሰማሁ። አርቲስቶቻችን ሰው እየወጣቸው ነው ማለት ነው የሚል ስሜት ተሰማኝ። እኛው ያከበርናቸው አርቲስቶች የሕዝባችንን ሐዘን ማክበር ከጀመሩ ትግላችንንም የሚቀላቀሉበት ግዜ ሩቅ አይሆንም፣ እኛም 'አርቲስት' የሚለውን ቃል ስድብ ከማድረግ እንቆጠባለን እያልኩ ሳስብ ሳልሰማቸው ያመለጡኝ ብዙ የትግል ዘፈኖች እንዳሉ ተረዳሁ።

የኦሮምኛ ዘፋኞች ዘፈንን የትግል መሣሪያ ማድረግ ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል። ሁሉም ዕኩል መደመጥ አልቻሉም እንጂ ባለፈው አንድ ዓመት በአማካይ በቀን አንድ የትግል ዘፈን እየለቀቁ ነበር። ከሁሉም ግን በጣም ተወዳጅ የሆነውና ቋንቋውን የማታውቁትን ሳይቀር የሚወዘውዘው የሀጫሉ 'ማለን ጅራ' ነበር፤ ስለዚህ ዘፈንም መጀመሪያ የሰማሁት እዚያው ቂሊንጦ በመጣ ወሬ ነው።

ኪነ ጥበብ ትግሉን ሲቀላቀል የትግሉን መብሰል የሚያሳይ ምልክት አድርጌ ነው የማየው። በአዲስ አበባ መንግሥትን በገደምዳሜ የሚወርፉ ትያትሮች ከሌሎቹ የበለጠ ብዙ ተመልካች አላቸው፣ የመግቢያ ዋጋቸውም ውድ ነው። ምክንያቱም የሕዝቡን ዝምታ ይናገራሉና። አሁንም፣ አርቲስቶቻችን የትግል ዘፈኖችን ሲዘፍኑ በሕዝብ ልብ ውስጥ ያላቸው ዋጋ ይጨምራል።

ስለፋሲል ደሞዝ እነዚያ ስንኞች ሳወራ ወንድሜ "‹እንቆቅልሽ› የሚለውን አታውቀውም?" አለኝ። አላውቀውም ነበር። ይገርማል ፋሲልን ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ዘፈኑ ሰማሁት፣ አየሁት። ክሊፑ ላይ፣ ሴቲቱ እንቆቅልሽ ትጠይቀውና መልሱን ባለማወቁ "አገር ስጠኝ" ትለዋለች፣ እሱ ግን እንዲህ ይላታል።

"እንቆቅልሽ፣
በሰም ለበስ ቅኔ፣
አሁን ገና፣ መጣሽብኝ ባይኔ።"

ፋሲል "በይ ደስም አላልሽኝ ጨዋታ ቀይሪ" እያለ ሲያንጎራጉር የሆነ ልብን የሚኮረኩር ኃይል አለው። ወንድሜ "ይሄ ይገርምሃል እንዴ?" አለኝና የይሁኔ በላይ አዲሱን ዘፈን አስደመጠኝ። ለወትሮው፣ ይሁኔን ከፍቼ የማዳምጠው ዘፋኝ አልነበረም። ይሄንን 'ሰከን' የሚለውን ዘፈኑን ስሰማው ግን የማላውቀው ስሜት ልቤን አተራመሰው።

"…ሰከን በል፣
ሰከን ማለት፣
ነው ጨዋነት
ሰከን ማለት፣
ነው ጀግንነት
ወታደሩ፣ ሰከን በል
አፈሙዙን ሰከን አርገው፣
ቃታህንም እንዳትስበው፣
ባዶ እጁን ነው፣ የሚጮኸው፣
ሠላማዊ፣ ወንድምህ ነው፣
ሰከን በሉ፣ ሕዝቤን ተዉት
ድምፁን ስሙት፣ አትግደሉት…"

በማለት የመንግሥትን ሀጢያት "…ውጉዝ ከመአርዮስ" ብሎ በማውገዝ፣ ስለኅብረት ሲባል፣ "በወላጁ ጥፋት፣ አይወቀስ ልጁ" እያለ መስከንን ይመክራል።

ናቲ ማን ቀጠለ። ናቲ ደግሞ በኦሮምኛ ስልተ ምት "አሁን ተነካሁ" እያለ፣ እሽክም፣ እሽክም አስባለኝ።

"ኦሮሞን፣ ኦሮሞን ሲከፋው
አሁን ተነካሁ
አማራን፣ አማራን ሲከፋው
አሁን ተነካሁ…"

ከዚያ ደግሞ የመስፍን በቀለ ዜማ ቀጠለ። በቀረርቶ የሚጀምረው የመስፍን "ሠላም ለኢትዮጵያ" አዲስ ትውልድ መጥቷል ይላል። ወራደሩንም እንዲህ ይለዋል፦

"ወታደሩ ጓዴ፣ አንተ ያገሬ ሰው፣
ወንድምክን አትግደል፣ ብረትክን መልሰው።…"

ሌንሴ ለሜሳ ደግሞ ጆሮ በሚለሰልስ ድምፅዋ፣ "ተነቃንቋል" ትላለች፣

"ተነቃንቋል ጥርሱ ይነቀል፣
ይነቀል፣
ይነቀል ይውለቅ
የአሉላ የጆቴን ትከሉበት ወርቅ፣
ክፍተቱ እንዲሞላ ውበቱ እንዲደምቅ።…"

መክፈቻዬ ላይ የጠቀስኩትን ፋሲል ደሞዝን መዝጊያም ላድርገው። በቅርቡ በለቀቀው ዘፈኑ እንዲህ ይላል፣

"…ኧረግ ወዲያልኝ (ወዲያልኝ)
ኧረግ ወዲያልኝ (ወዲያልኝ)
በቃ ሒድልኝ (ሒድልኝ)
25 ዓመት አላገጥክብኝ።…"

ክብር ለእነዚህ አርቲስቶች ይሁን!
አሜን።

Comments

Popular posts from this blog

The "Corridor Development" is a Façade of the Prosperity Party

Befekadu Hailu I have seen a news report claiming that 40% of central Addis Ababa will be demolished for the corridor development; I am not able to confirm the validity of the news but it sounds real to me given the size of massive operations in the demolition of old neighborhoods and construction of bike lanes, green areas, and glittering street lights. I like to see some beauty added to my city but cannot help mourning the slow death of it too. Addis Ababa was already in a huge crisis of housing and the demolition of houses is exacerbating it. Apparently, Prime Minister Abiy Ahmed is eager to showcase his vision of prosperity by demonstrating how fast his administration can do magic by beautifying the front sides of the streets with lights, new pavements, and painted fences ("to fake it until he makes it" in my friend's words). Therefore, he and his party do not care about the miserable human stories behind the scenes and they will harass you if you tell it (Azeb Woku...

መጽሐፍ የሚወጣው፣ የተዋነይ ዘ ጎንጅ 5 መሥመር ቅኔ

ጎንጅ ቅኔ ያጠናበት ደብር ሥም ነው። ደብረ ጥበብ ጎንጅ ቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም። ተዋነይ የባለቅኔው ሥም ነው። (የግዕዝ ትርጉሙ "ዋናተኛ" ማለት ነው።) ሊቁ ተዋነይ የልኅቀቱን ያክል እምብዛም አይወራለትም፤ ነገር ግን በዘመኑ ወደር የሌለው ልኂቅ ስለመሆኑ ሥራው ይናገራል። የሕይወት ተፈራ "Mine to Win" የተሰኘ ድርሰት መቼቱን በዐፄ ዮሓንስ ንግሥና ዘመን፣ በጎጃም/ጎንደር የቅኔ መማሪያ ደብሮች ያደረገ ልብወለድ ነው። ልቦለዱ የቅኔ ትምህርት ስርዓትን ያስተዋውቀናል፤ በበኩሌ የቅኔ ትምህርትን እና የቅኔ ሊቃውንት ታላቅነት ቀድሞ ከነበረኝ ግንዛቤ የበለጠ እንዲሆን አድርጎኛል። በተለይ የተዋነይ ዘ ጎንጅ (በውኑ ዓለም የነበረ ባለቅኔ) ተከታይዋ አምስት መሥመር ቅኔ መጽሐፍ የሚወጣት እንደሆነች ልቦለዱ አሳሰበኝ። ወይም በአጭሩ ብዙ ምዕራባውያን ስንት መጽሐፍ የጻፉለት ፍልስፍናን በአምስት መሥመር ይዟል። የቅኔው ትርጓሜ የመጽሐፍ ቅዱስን እና የመጽሐፍ ቅዱሱን ፈጣሪ ኅልውና ይሞግታል። “የአምን ወይገኒ ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ ብዙኃን እንዘ ይገንዩ ይስግዱ ቅድሜሁ ለነጽሮ ዝኒ ነገር እሥራኤል ከመይፍርሑ ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ ወ ፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ።” (ተዋነይ ዘ ጎንጅ። ምንጭ፣ሕይወት ታደሰ ወደአማርኛ የተረጎመችው የሕይወት ተፈራ መጽሐፍ) ትርጉሙን በኋላ እመለስበታለሁ። ስለተዋነይ መጀመሪያ የሰማሁት የበውቀቱ መጽሐፍ ላይ ነበር። እሱም በጨረፍታ - “የሌሊት ዜማዎች” የሚለው ግጥሙ ውስጥ። በውቀቱ ተዋነይን በግጥሙ ግርጌ ማስታወሻው አስተዋውቆን ያልፋል፣ “ተዋነይ በቅኔ ቤት አፈ ታሪክ ሞትን በግዝት ለሰባት ዓመታት ያቆመ ጀግና ነው"። ከዚያ በኋላ፣ አዲስ አድማስ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ተዋነይ የተላከበትን ...

የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ

በፍቃዱ ዘ . ኃይሉ “የአዲስ አበባ ብሔርተኝነት” ቢኖር ኖሮ መሪው ልጅ ሚካኤል ይሆን ነበር። አሁን አሁን እሱ ስለ አዲስ አበባ የዘፈናቸውን ዘፈኖች ቁጥር ራሱ በትክክል መቁጠር ይቸግረኛል። ለአዲስ አበባ ከተዘፈኑ ዘፈኖቹ ውጪም በየዘፈኑ ውስጥ የሚጨማምራቸው መልዕክቶች በራሳቸው መወድሰ አዲስ አበባ ናቸው። ለምሳሌ፣ በቅርቡ በለቀቀው ‘አዲስ አራዳ’ በተሰኘው አልበሙ ውስጥ ‘የድሬ ልጅ’ የሚል ዘፈን አለው። ዘፈኑ የተዘጋጀው ያው የአዲስ አበባ እህት ተደርጋ የምትቆጠረውን ድሬ ዳዋን ለማወደስ ነበር። ልጅ ሚካኤል ግን የአዲስ አበባ ፍቅሩ ያመልጠውና የሚከተለውን ያቀነቅናል፦ “መጣልሽ በሏት፣ ድሬ ድረስ፣  ከአዱ ገነት፣ ከሸገር፣ ከአዲስ ደረሰ፣... የሸገር ልጅ አራዳ ነው፣ ሰው አክባሪ፣ ሰው ወዳዱ፣ ቀላጅና ተረበኛ፣ ፍቅር ይዞ የሚተኛ፣ ‘አለው’ የለ፣ ‘የለው’ የለ፣ ከሁሉ ጋ፣ ግባ ጀባ...፤” ፤ ልጅ ሚካኤል በዚህ አልበሙ ብቻ አዲስ አበባን የሚያውድሰባቸው ሌሎችም ዘፈኖች አሉ፤ ‘ አዲስ አራዳ ’ የሚለው የአልበሙ መጠሪያ እና ‘ሸገር’ የሚሉት ዘፈኖቹ ዋነኞቹ ናቸው። ታዲያ እንዲህ በአዲስ አበባ ፍቅር የሚቃጠለው ልጅ ሚካኤል "ሊነግረን የሚፈልገው ምንድን ነው?" የሚለው ጥያቄ ደጋግሞ ይመጣብኛል። ይህ የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ ምንነትን ለመረዳት የሚጥር ፖለቲካዊ መጣጥፍ ነው። ‘አዲሱ አራዳ’ ማነው? በዚህ ዘፈኑ በብዙዎቻችን ዕድሜ የትዝታ ማኅደር ውስጥ የሚገኙ ነገር ግን በአዲስ አበባ ልማት ሥም የፈረሱ እና እየተረሱ ያሉ ሰፈሮችን ሥም ያነሳሳል። ዘፈኑ በግጥሙም በዜማውም፣ የሐዘን እንጉርጉሮ ያለበት ነው። ምሳሌ እንውሰድ፦ “ጨርሰሽ ስትወጪ ከቡፌ ዳ’ላጋ፣ ጠብቂኝ እንዳልል፣ ቆመሽ መሐሙድ’ጋ፣ አገር ...