Pages

Wednesday, January 6, 2016

Bewketu Seyoum፤ የኔ ትውልድ Eyeኮነ!

በውቀቱ ብዙዎቻችሁ እንደምታውቁት ሰው መኮርኮር ይችላል። የተማረው ሳይኮሎጂ ነው። ሳይኮሎጂ የሳቅ ስስ ብልት የት እንደሆነ አስተምሮት ይሆን እላለሁ። ነገር ግን ማሳቅ የጀመረው ትምህርቱን ከመጨረሱ በፊት ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሳይኮሎጂስቶች ሲያስቁ ስላልገጠመኝ በዚህ ረገድ ግንኙነት (co-relation) መፈለጌን አቋርጫለሁ።

በውቀቱን እንደ ኮሜድያን አልቆጥረውም [ነበር]። እንደዛ እንድቆጥር የተገደድኩበት አንድ ጊዜ ቢኖር ሀብቴ ከሞተ በኋላ ሀብቴን ተክቶ ሲመጣ ነው፤ ደረጄና በውቄ ነገር ሁኖ። እዚያ ላይ በውቄ ሀብቴን ተክቶ መምጣቱ ከቀልዶቹ የተሻለ ያስቅ ነበር፤ የተሻለ። በውቀቱ ያንን ሚና ደግሞ ላይመለስበት ባደባባይ ቃል ገብቷል።

በውቀቱ ፈላስፋ ነው፤ ኮሜድያን አይደለም። በነገራችን ላይ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋም በውቀቱን ፈላስፋ ነው ይላል። "ስንት ፕሮፌሰሮች ሁለት ክላስ የሚያሰተምሩበትን ሐሳብ እሱ በሁለት መሥመር ቁጭ ያረገዋል፣" በማለት፦
ሉላዊነት
"የጋራችን ዓለም፣ የጋራችን ሰማይ
የብቻችን ሕመም፣ የብቻችን ስቃይ።"
***
"አገር ድንኳን ትሁን ፣ ጠቅልዬ የማዝላት
ስገፋ እንድነቅላት፣ ስረጋ እንድተክላት።"
***
"ከተመኙ ላይቀር ወንዝነት መመኘት፣
አገርን ሳይለቁ ሰው አገር መገኘት።"
በራሪ ቅጠሎች ላይ የመጀመሪያዋ ጽሑፍ ትመስለኛለች በሕይወት ላይ የሚስቅባት ገፀ–ባሕሪይ አለ። ሕይወት ግን ዝም ብላ የምታስቅ እንዳልሆነች የልቦለዱ መጨረሻ ይተርካል። በመጨረሻው መጽሐፉ (መውጣትና መግባት) መግቢያ ላይ ደግሞ፣ ግጥም ተርጉሞ እንደመግቢያ አስቀምጧል። ታዲያ ዘነበ ወላ አዲስ አድማስ ላይ መጽሐፉን ሲተቸው (መጽሐፉ እንደበፊቶቹ ሲሪዬስ አይደለም ብሎ በማሰብ ይመስላል) "ተመልሰህ ግባ በወጣህበት በር" ብሎ ነበር ትችቱን የቋጨው (ከመግቢያ ግጥሙ ስንኝ ተውሶ)። የበውቀቱ መግቢያ ግጥም አሁን በቃሌ እንደማስታውሳት እንዲህ ትላለች፣
“በወጣኒነቴ በድሜዬ አፍላ ጀምበር፣
የሊቅ የጣዲቁን ሐተታ ቁም ነገር፣
አዘወትር ነበር፣
እና ምን ተረፈኝ?
ተመልሼ ወጣሁ፣ በገባሁበት በር።”
ወጥቶ ከሆነ እንኳን ወጣ። ውጪው በጣም ሰፊ ነው። በውቀቱ ደሞ ሲሪዬስሊ የማትወስደንን ተፈጥሮ ሲሪዬስሊ የማይወስድ፣ ለጥፊና ካልቾዋ የማያለቅስ ጸሐፊ ነው (ቢያንስ እኔ እንደተረዳሁት)። በውቀቱ ለኔ የዘመናችን ‘አይከን’ ነው። በለበጣ የሚመለከተንን ዘመን በተመጣጣኝ ለበጣ የሚመክትልን አሽሙረኛ። የኛ ማርክ ትዌይን፣ ወይም የኛ ቮልቴር ነው – በውቀቱ ስዩም!

የበውቀቱ ግጥሞች (በተለይ የኗሪ አልባ ጎጆዎቹ) የሐዘን እንጉርጉሮ ይበዛባቸዋል። ያኔ ተረከዙ የተበሳ ጫማ አድርጌ አዲስ አበባን ስዞር እነሱን በቃሌ እየወጣሁ ነበር ዕጣ ፈንታን እተች የነበረው። ሎሬት ፀጋዬ «ወንድ ልጅ ብቻውን ነው የሚያለቅስ» ሲል፣ በውቀቱ ደግሞ፣
"እምባ ታዛዥ ሆኖ የሚገደብበት፣
ያባት ቅኔና ቀን አለፈ እንደዘበት" እያለ ከውነቱ ያጋፍጠናል።
በሳት ዳር ሐሳቦች ስብስቡ "ከንፍገት እጦትን ማካፈል ይሻላል” ብሎ በፈገግታ ሲመጣ፣ እኔም ዓለምን በሽሙጥ ፈገግታ መመልከት ጀምሬ ነበር። በውቀቱ ከጉርምስና ወደጉልምስና ሳዘግም እንደ ሳውንድ ትራክ ተከትሎኛል። የኔን ትውልድ የሚወክል አይከን ነው የምለውም በዚህ መመዘኛ ነው። ዓለም ሲሪዬስ ሲሆኑላት ሲሪዬስ እንደማትሆን አሳይቶኛል። “የፀጋዬ ቤት ከፀጋዬ በፊት" ብሎ ሲል ዛቻ፣ "እግር አልባው ባለ ክንፍ" ብሎ ሲል ቡጢ ነው የገጠመው። የተሻለው ሽሙጥ ነው። የገባው ቁም ነገሩን ይጨብጣል፤ ያልገባው ስቆ ያልፋል። መሳቅ፥ መሳቀቅን ተካ።

እንደ በውቀቱ በቃላት የሚቀናጣ ባለቅኔ የለም። “ለካስ ያባቶች faith ፌዝ ብቻ ነበረ” እያለ የማይተዋወቁትን ቃላት ድንገት ማዛመድ የሚችለው እሱ ብቻ ነው። በውቀቱ የዶ/ር እጓለ ምናባዊ ሥልጣኔ ቢሰፍን የሚገኘው ውጤት ነው። የአገር በቀል ዕውቀትን ከምዕራባውያኑ ጋር ያዋሃደ ሰው። ስትፈልጉ ከቅኔ ቤት ወጎች፣ ስትፈልጉ ከአቴና ሰማይ ላይ ፊሎዞፊያን ጎትተው ባወረዱ ሰዎች ወግ ያጨዋውታችኋል።

ከቁምነገር መጽሔት እስከ ሮዝ (አዲስ ጉዳይ) መጽሔት ድረስ ያሉ ጽሑፎቹን ደጋግሜ በማንበብ «ጽሑፎችህን ካንተ የበለጠ አውቃቸዋለሁ» ወደሚል ትምክህት ደርሼ ነበር። ተነፈስኩ እንጂ። አሁን ደሞ፣ ፌስቡክ ላይ መጥቷል። እንደ ኗሪ አልባ ጎጆዎቹ ዘመን ሰዎች ጎጆዎቹን መሬት ላይ ቀልሰው መሬት ላይ ብቻ ተጋበዙልኝ ብለው ድርቅ እንደሚሉት ጸሐፍት ሆኖ አልቀረም። ትውልዱ ፌስቡክ ላይ ሲወጣ እሱም ጎጆውን እዚያው ቀልሷል። ጎጆው ውስጥ በቀልድ እያስመሰለ የዘመናችንን እውነት ይተርክልናል። ጎጆውን መቀለስ በጀመረ ጊዜ እኔም እዚሁ ሰፈር ነበርኩ። ጓዙን ጠቅልሎ ፌስቡክ በከተመ ጊዜ ግን "እረፍት" ላይ ነበርኩ። ስለዚህ አሁን “እንኳን ደህና መጣህ” ብለው ረፈደብህ አልባልም። እዚህ ሰፈር ለማይደራደሩብህ አድናቂዎችህ ታስፈልገናለህ።
———
ግጥሞቹን በቃሌ ስለወጣኋቸው ቢሳሳቱ አያገባኝም።

No comments:

Post a Comment