Pages

Saturday, November 10, 2018

ምርጫ፦ ቄሮ ‘መንግሥት’ ይሁን ‘ፅንፈኛ’?

በቄሮ ምንነት እና "ድርጊቶች" ላይ በርካታ ውዝግቦች እየተነሱ ነው። ውዝግቦቹ የሚነሱት በሁለት ፅንፎች ነው፦ ፩ኛው ፅንፍ ያሉት ሰዎች "ቄሮ ቅዱስ ነው" ሲሉ፣ ፪ኛው ፅንፍ ያሉት  ሰዎች ደግሞ "ቄሮ እርኩስ ነው" ይላሉ። እኔ ደግሞ ቄሮ እኛ ነህ የምንለውን ይሆናል ባይ ነኝ።

እንደኔ እንደኔ የውዝግቡ ሁሉ መንስዔ የቄሮን ምንነት እና የንቅናቄውን ዓይነት፣ እንዲሁም "የትግሉን" ወይም ደግሞ "የድሉን" ባለቤት ካለመረዳት የመጣ ነገር ይሆን ይሆናል በማለት ነው ይህንን ጽሑፍ ለአማራጭ አስረጅነት ያዘጋጀሁት። እግረመንገዴንም ለውዝግቡም ይሁን ለውዝግቡ መንስዔ የሆኑ ተቃርኖዎችን እዳስሳለሁ። ዓላማዬ ከፅንፉ እና ከፅንፉ ወዲህ ዓለም እንዳለ ለማሳየት እንጂ መሞከር ብቻ ሳይሆን ፍረጃችን ተፅዕኖ እንዳለው ማስታወስም ጭምር ነው።

ቄሮ - ሥያሜው ምን ይነግረናል?

'ቄሮ' ቃሉ 'ያላገባ፣ ያልወለደ' ወጣትን ይወክላል። ነገር ግን ወጣት የሚለውን ቃል የሚተኩ ሌሎች የኦሮምኛ ቃላት አሉ። እነዚህም 'ደርደሩማ'፣ 'ደርገጌሳ' እና 'ጎሮምሳ' የሚሉት ቃላት ምሳሌ ይሆናሉ። ቄሮ የሚለው ቃል ምንጩ 'ቄረንሳ' ከሚለው እና ነብር የሚል ትርጉም ካለው ቃል የተቀዳ እንደሆነ ይነገራል። ስለዚህ ቄሮ ማለት እንደነብር ያለ ብርቱ ወጣት ማለት ነው፣ ማለት እንችላለን። ይሁን እንጂ አሁን በተለይ በኦሮሞ ፖለቲከኞች ዘንድ 'ቄሮ የሚለው ቃል ፍቺ 'አብዮተኛ ወጣት' የሚል ትርጉም አለው።

"የቄሮ ንቅናቄ" ውልደት እና ዕድገት

ቄሮ የሚለው ቃል የፖለቲካ መድረኩ ውስጥ የገባው እ.ኤ.አ. በ2011 የአረቡ አብዮት በፈነዳበት ወቅት ነበር። መቀመጫውን ዳያስፖራ ያደረገው ንቅናቄ ከዩንቨርስቲ ተማሪዎች ጋር ግንኙነት በመመሥረት 'ቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞ' የሚባል ኢመደበኛ ማኅበር ፈጠረ። የዚህ ማኅበር አባላት መረጃዎችን በኢሜይል እና በድረገጻቸው እየተለዋወጡ በርካታ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ቀጠሉ። ሥማቸው በይፋ የተነሳው ግን በ2006 የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር  ፕላንን ተከትሎ በተነሳው እና ዩኒቨርስቲዎችን ባዳረሰው የተቃውሞ ሰልፍ ወቅት ነው።

ከዚያ በኋላ የተጋጋለው የተቃውሞ ሰልፍ መላው ኦሮሚያን ሲያዳርስ በየአካባቢው ያሉ ወጣቶች ራሳቸውን ቄሮ ብለው መጥራት ጀመሩ። የመጀመሪያው የቄሮ አደራጅ የነበረው (qeerroo.org የተባለ) ድረአምባም ይሁን የፌስቡክ ገጹ አሁን እምብዛም ተከታታይ የላቸውም። ይልቁንም የወጣቶቹ ኅብረት መሪ ተደርጎ በዘልማድ የሚወሰደው የኦኤምኤን ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጃዋር መሐመድ ነው።

ከዚያ በኋላ በኦሮሚያ ክልል፣ በየአካባቢው የሚነሱት ተቃውሞዎች ውስጥ የሚሳተፉ የተደራጁም ይሁኑ ያልተደራጁ ወጣቶች በሙሉ - ራሳቸውን ሲገልጹም ይሁን ሌሎች ሲገልጿቸው - ቄሮ በሚል ሥያሜ ሆነ። ቄሮ በዚህ አካሔድ በማንም ግለሰብ ወይም ቡድን ቁጥጥር ሥር ያልሆነ፣ ነጻ ነገር ግን በኦሮሙማ (ኦሮሞነት) የተሰባሰበ ኢመደበኛ ቡድን ሆነ። ይህ ማለት ግን ወጣቶቹ በፖለቲካ ፍልስፈፍናቸውም ይሁን ብስለታቸው፣ በኢትዮጵያ እና ኦሮሚያ ታሪክም ይሁን ፖለቲካ አረዳዳቸው ወጥ አቋም አላቸው ማለት አይደለም።

ይህ በእንዲህ እያለ በአማራ ክልል የነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ ላይ የሚሳተፉትን ወጣቶች ሥም ለመስጠት ተሞከረ። 'ፋኖ' የሚለው ሥያሜ 'ቄሮ' ከሚለው ጎን ለጎን መጠቀሱ የተለመደ ነገር ሆነ። ያን ጊዜ በቄሮ ሥምም ሆነ በፋኖ ሥም የሚደረገው ነገር በሙሉ፣ ማዕከላዊ መንግሥቱን እስካስጨነቀ ድረስ "ትክክል" ነበር። ይሁን እንጂ መሬት ላይ "ቄሮ ነኝ" የሚሉትን ያክል፥ "ፋኖ ነኝ" የሚሉ ወጣቶች እምብዛም አልነበሩም። እንዲያውም 'ፋኖ' የግንቦት ሰባት ፈጠራ ነው የሚሉ የአማራ ብሔርተኞች ገጥመውኛል። ይሁንና የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀሩ አሁን ለምናየው የለውጥ አዝማሚያ አስተዋፅዖ ያበረከቱ ወጣቶችን ሲጠሩ "ቄሮ፣ ፋኖ፣ ዘርማ…" እያሉ መጥራትን 'ፕሮቶኮል' አድርገውታል።

የትግሉ እንዲሁም የድሉ "ባለቤቶች"

የያኔዎቹ ኦሕዴድ እና ብአዴን ተባብሮ ትሕነግ ላይ ማበይ፥ ከወጣቶቹ አመፅ ባልተናነሰ (ወይም በበለጠ መልኩ) ኢሕአዴግን ነቀነቀው። የፓርቲዎቹ ከወጣቶቹ ጋር ያልተጻፈ መግባባት ላይ መድረስ ደግሞ የቀድሞውን ኢሕአዴግን ገድሎ፣ አዲሱን ኢሕአዴግ ወለደ። አሁን ከትሕነግ/ኢሕአዴግ ወደ ኦዴፓ/አዴፓ/ኢሕአዴግ አገዛዝ ተሸጋግረናል። ይሁንና ገና አመፁ አልሰከነም። የትግሉ ባለቤት ተቃዋሚዎች በሙሉ፣ በተለይም አደባባይ የወጡት የኢትዮጵያ ወጣት አመፀኞች ናቸው፤ የድሉ ባለቤቶች ግን የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች፣ በተለይም ኦዴፓ እና አዴፓ ናቸው። ያለእነሱ ከቀድሞ አቋማቸው መቀልበስ፣ እንዲሁም ለማበር መወሰን በኢሕአዴግ ቤት አሁን ያለው ወደ ዴሞክራሲ የመሸጋገር ዕድል ፈፅሞ አይመጣም ነበር ብዬ እገምታለሁ።

ይሁንና ወጣቶቹ የልኂቃን ተቃዋሚዎችን ጥያቄ ከማስተጋባት ባሻገር ለእንዲህ ያለ ነፍስን አሳልፎ እስከመስጠት የሚደርስ ብሶት የዳረጋቸው ሥራ አጥነት እና 'የሪከግኒሽን' ጥያቄ መልስ ቢሰጠው ኖሮ፥ ድሉን የጋራ ድል አድርገን መቁጠር የምንችልበት ዕድል ይኖር ነበር።

አሁን ባለው ሁኔታ ብዙኃን ሥራ አጦች በየአደባባዩ በከፈሉት መስዋዕትነት፥ 'እነዚህ ሥራ ፈቶች ደግሞ መረበሽ ጀመሩ' እያሉ ይበሳጩባቸው የነበሩ ልኂቃን በአንድ በኩል፣ እንዲሁም በሌላ በኩል ደግሞ 'እስከመቼ እንዲህ ተዋርዳችሁ ትኖራላችሁ፣ ታግላችሁ ነጻ ውጡ እንጂ' እያሉ ሲቆሰቁሷቸው የነበሩ ልኂቃን ሥልጣን እየተቆጣጠሩ ሲመጡ ወጣቶቹ ችላ መባላቸው ሐቅ ነው።

ይህ ነገር ምናልባትም የትግሉ "ባለቤቶች" እና የድሉ "ባለቤቶች" ወይም "ተጠቃሚዎች" መካከል መቃቃር ሳያስከትል አይቀርም። ይህ ጉዳይ አዲስ ብሶት የሚወልድ መሆኑም የጊዜ ጉዳይ ነው።

"ጀግኖች" የነበሩ "ፅንፈኞች"
(የውክልና ጦርነት መሣሪያዎች)

በየአካባቢው በሥራ አጥነታቸው ምክንያት ዋጋ አጥተው፣ በአደገኛ ቦዘኔነት ተፈርጀው ከፊሉ ስደት እየበላቸው፣ ከፊሉ ሱስ እየዋጣቸው የነበሩ ወጣቶች ድንገት የተቀጣጠለው ሕዝባዊ አመፅ ማገዶ ነበሩ። ያኔ "ጀግኖች" ተብለዋል። ምክንያቱም ለልኂቃኑ ፖለቲካ ሁነኛ መሣሪያ ነበሩ። ወጣቶቹ ምናልባትም አእምሮ ከሚያላሽቅ የሥራ አጥነት ስሜት ወጥተው፥ ለራሳቸው ያላቸው ዋጋ እና ግምት የጨመረው በዚህ አመፅ ባደረጉት ተሳትፎ ይሆናል። ሕዝባዊ አመፁ ቆሞ ድንገት አገር መረጋጋት ሲጀምር ግን ወደ "መንደር ያሰለቹ አደገኛ ቦዘኔነት" መመለሳቸው ሆነ። ከተሰጣቸው ሥም መውረድ ከባድ ነው። ስለሆነም የአብዮታቸው ጠባቂ ሆኑ - ከሳሽ፣ ፈራጅ እና ቀጪ። የደቦ ፍርድ፤ በዚህ ወቅት ነው በፅንፈኝነት መፈረጅ የጀመሩት።

በዕውቁ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የምትመራው 'ኢትዮጲስ' ጋዜጣ (በጥቅምት 24, 2011 እትሟ) በርዕሰ አንቀፅዋ ቄሮዎችን ለዘብተኛ እና ፅንፈኛ በሚል ከለያየቻቸው በኋላ ፅንፈኞቹን የማስቆም ሥራ መሠራት እንደሚገባ ጠቁማለች። የኢትዮጲስ ስህተት ምናልባት (አንድም) በአገሪቱ የደቦ ፍርዶች እና ወደ ስርዓት አልበኝነት የሚወስዱ እንቅስቃሴዎችን ለቄሮ ብቻ ለይታ መስጠቷ ነው። መቼም በድንጋይ ወግሮ መግደል እና በእንጨት ላይ ዘቅዝቆ መስቀልን የመሳሰሉ የደቦ ፍርዶች አንዱ ከሌላው የሚሻሉበት መንገድ አለ ተብሎ አይታመንም። በዚህ ረገድ ጉዳዩ 'ወጣት ፅንፈኞች' በሚል ሊጠቃለል ይችል ነበር ብዬ አምናለሁ። (ሁለትም) ቄሮ የተጻፈ ፕሮግራም የሌለው፣ አባላቱ በዝርዝር የማይታወቁ፣ አንድ ስትራቴጂ እና ግብ የሌለው የግፉአን ማኅበር መሆኑን ከግምት ውስጥ ያላስገባ መደምደሚያ መሆኑ ስህተት ያደርገዋል። ይህም ማለት ማንም ተነስቶ ቄሮ ነኝ ብሎ ማወጅ እና በዚያ ሥም ወንጀልም ይሁን መልካም ጀብዱ መፈፀም ያስችለዋል ማለት ነው። ብዙኃን መገናኛዎች ግን ቡድኑን ግልጽ ቅርፅ እና መዋቅር እንዳለው እንዲሁም "ተግባሩን" አቅዶ እንደፈፀመ ማኅበር ተመልክቶ "እንዲህ ነው" ወይም "እንዲያ ነው" ማለት የተሳሳተ ትርጉም ይሰጣል። (ሦስትም) የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች - ለምሳሌ የጃዋር "የቄሮ መንግሥት" እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ "ፀጉረ ልውጦችን መቆጣጠር" የመሳሰሉ - ንግግሮች ወጣቶቹን የውክልና ጦርነት ውስጥ እንደከተታቸው ከግንዛቤ ያላስገባ መደምደሚያ መሆኑ ነው።

ፍረጃ እና ተፅዕኖው፤
እስመ ሥሙ ይመርሖ ሀበ ግብሩ
(nomen est omen)

ቄሮንም ይሁን ፋኖን ወይም ሌላ የፖለቲካ ቡድኖችን በተመለከተ ለምናደርጋቸው ፍረጃዎች ማድረግ የሚገባን ጥንቃቄ አለ። ፍረጃ (labeling) በሥነ-ልቦና ግንባታ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንዳለ በርካታ ጥናቶች ያሳያሉ። «እነ እከሌ ይህን አያደርጉም»፣ «እንትን ሆኜ እንዲህ አላደርግም» የሚሉ አባባሎች የሚያስረዱን ቁምነገር ቢኖር የሆኑ ሰዎች ስብስብን የሚገልጽ ማንነትን የምንበይንበት (labeling/defining) መንገድ መልሶ የአባላቱን ድርጊት እንደሚወስን መረዳት እንደሚያሻን ነው። "ቄሮ አብዮተኛ ወጣት ነው" በተባለ ጊዜ አደባባዮችን በተቃውሞ ሰልፎች ንጧል። የለውጥ ጀምበር ሲከፈት "ለውጡን ጠብቁ" ሲባል እንደዚያው ለማድረግ እየሞከረ ነው። ወጣቶቹ በልኂቃኑ የሚሰጣቸውን ሥያሜ ለመመጠን እየተፍጨረጨሩ ነው። "ቄሮ መንግሥት ነው" ብለን ከአቅሙ በላይ ሥራ ከምናሸክመው፣ "ቄሮ የዴሞክራሲ እና የሥልጡን ፖለቲካ ጠበቃ ነው" ብለን በዚህ አቅጣጫ እንዲተጋ ብናደርገው ይመረጣል። "ቄሮ ፅንፈኛ ነው" እያልን ወደዚያ ከምንገፋው "ቄሮ ይህንን አያደርግም" ብለን ብንገስፀው ይሻላል።

ቺርስ ለጥንቃቄ!

7 comments:

  1. ቃለ ህይዎት ያሰማልን! ድንቅ!

    ReplyDelete
  2. Though not an in-depth analysis, it's much better than what the hate mongers like Eskinder are vomiting about Qeerroo. Time will tell the who of Qeerroo!

    ReplyDelete
  3. This is a good observations. Thanks.

    ReplyDelete
  4. Great observation but so called ehhiopis is neftegna mentality

    ReplyDelete
  5. To generalize all qerros as this or that obviously is not right. But some of their violent acts such as banditry, robbery and hanging an innocent youngster to death as well as brutalizing Muslim elders such as the recent Shashemene incident deserve more than mere condemnation. To hurl insult at Eskindir for calling the spade a spade is utter rubbish.
    One commentator referred to Eskindir as a neftenga. So am I. He is what he is because of Neftengas. It is a badge of honour for most.
    Yes, many who use the veiled term Neftenga envy the Amaras. They are indignant that they were not created Amaras. So, it is a deep sense of inferiority that prompts the semi-literate fellow to label Eskindir a neftenga. It is an honour, an extra-ordinary honour at that to be called one.

    ReplyDelete
  6. i don't like if you from qerroo group because most of qerrro are rude and terrorist .....the real meaning of qerroo is treason!

    ReplyDelete