Skip to main content

የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ

በፍቃዱ ዘ. ኃይሉ

“የአዲስ አበባ ብሔርተኝነት” ቢኖር ኖሮ መሪው ልጅ ሚካኤል ይሆን ነበር። አሁን አሁን እሱ ስለ አዲስ አበባ የዘፈናቸውን ዘፈኖች ቁጥር ራሱ በትክክል መቁጠር ይቸግረኛል። ለአዲስ አበባ ከተዘፈኑ ዘፈኖቹ ውጪም በየዘፈኑ ውስጥ የሚጨማምራቸው መልዕክቶች በራሳቸው መወድሰ አዲስ አበባ ናቸው። ለምሳሌ፣ በቅርቡ በለቀቀው ‘አዲስ አራዳ’ በተሰኘው አልበሙ ውስጥ ‘የድሬ ልጅ’ የሚል ዘፈን አለው። ዘፈኑ የተዘጋጀው ያው የአዲስ አበባ እህት ተደርጋ የምትቆጠረውን ድሬ ዳዋን ለማወደስ ነበር። ልጅ ሚካኤል ግን የአዲስ አበባ ፍቅሩ ያመልጠውና የሚከተለውን ያቀነቅናል፦

“መጣልሽ በሏት፣ ድሬ ድረስ፣

 ከአዱ ገነት፣ ከሸገር፣ ከአዲስ ደረሰ፣...

የሸገር ልጅ አራዳ ነው፣ ሰው አክባሪ፣ ሰው ወዳዱ፣

ቀላጅና ተረበኛ፣

ፍቅር ይዞ የሚተኛ፣

‘አለው’ የለ፣ ‘የለው’ የለ፣

ከሁሉ ጋ፣ ግባ ጀባ...፤”

ልጅ ሚካኤል በዚህ አልበሙ ብቻ አዲስ አበባን የሚያውድሰባቸው ሌሎችም ዘፈኖች አሉ፤ ‘አዲስ አራዳ’ የሚለው የአልበሙ መጠሪያ እና ‘ሸገር’ የሚሉት ዘፈኖቹ ዋነኞቹ ናቸው። ታዲያ እንዲህ በአዲስ አበባ ፍቅር የሚቃጠለው ልጅ ሚካኤል "ሊነግረን የሚፈልገው ምንድን ነው?" የሚለው ጥያቄ ደጋግሞ ይመጣብኛል። ይህ የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ ምንነትን ለመረዳት የሚጥር ፖለቲካዊ መጣጥፍ ነው።


‘አዲሱ አራዳ’ ማነው?
በዚህ ዘፈኑ በብዙዎቻችን ዕድሜ የትዝታ ማኅደር ውስጥ የሚገኙ ነገር ግን በአዲስ አበባ ልማት ሥም የፈረሱ እና እየተረሱ ያሉ ሰፈሮችን ሥም ያነሳሳል። ዘፈኑ በግጥሙም በዜማውም፣ የሐዘን እንጉርጉሮ ያለበት ነው። ምሳሌ እንውሰድ፦

“ጨርሰሽ ስትወጪ ከቡፌ ዳ’ላጋ፣

ጠብቂኝ እንዳልል፣ ቆመሽ መሐሙድ’ጋ፣

አገር ተቀይሯል፣ ተኝቼ ሲነጋ”

ቡፌ ዳ’ ላጋር እና መሐሙድ ሙዚቃ ቤት ቢያንስ በአንድ የታክሲ ጉዞ ይራራቃሉ። አንድ ያደረጋቸው ሁለቱም መፍረሳቸው ነው። ቡፌ ደ’ላጋር የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ “በኢትዮጵያ መንግሥት እና በዱባዩ ኤግል ሒልስ ትብብር” ይሠራል ለተባል ዘመናዊ መንደር የፈረሰ ሬስቶራንት (እና ሰፈር) ነው። በሌላ በኩል መሐሙድ ሙዚቃ ቤት የፒያሳ ማዕከላዊ መቀጠጣጠሪያ ቦታ ነበር። መሐመድ ሰልማን ለፒያሳ የጻፈው መጽሐፍ ርዕስ “መሐሙድ’ጋ ጠብቂኝ” ነበር። ሙዚቃ ቤቱ ቀድሞ ቢዘጋም፣ ሰፈሩ ሥሙን እና ትዝታውን ይዞ ቀጥሎ ነበር። ይህም በሰሞኑ “የኮሪደር ልማት” ፈርሷል። ልጅ ሚካኤል ለፈረሱ ‘ላንድማርኮች' ናፍቆቱን አቅመ ቢስነት በተጫነው ዜማ ሲያቀነቅን ይደመጣል።

በዚህ ዘፈን ልጅ ሚካኤል ከተማዋን በሚወዳት ቆንጆ ይመስላታል። ቆንጂቱን “የክቴ አበባ” እያለ ነው የሚያንቆላምጣት። ሆኖም የክቱን አበባ ‘አዲስ አራዳ’ ወስዶበታል። ስለዚህ አዲስ የሚለው ቃል ‘አዲስ አበባ’ ከሚለው ቃል የተወሰደ ሆኖ ሳለ፣ የቆንጂቱን አዲስ ትዳር ለመጥቀስ የተጠቀመበት ነው። ይቀጥልና ደሞ፣ ለሌላ ሰው መወሰዷን ለማመን ሲቸገር እናገኘዋለን፦

“ሲሰጡሽ ተቀበይ፣ ማጌጫ እና ጥሎሽ

እኔም አይከፋኝም፣ አንቺ ላማረብሽ

ችግሩ ወዲህ ነው፣ ካሉሽ ነው ልዳርሽ

እኔም ያንቺ ሆኜ፣ አንቺም የኔ ሳለሽ።”

እንዲህ እንዲህ እያለ አዲስ አበባ በማማሯ እየተደሰተ፣ ከከተሜው ተነጥቃ ለገጠሬው መዳሯን ላለማመን ይግደረደራል። ይህ ዘፈን የአዲስ አበቤውን ባይተዋርነት የሚያሳይ ይመስለኛል። አዲስ አበባ እንደከተማ በብዝኃነቷ እንድትኮራ ከመደረግ ይልቅ በብሔር ጥብቆ በተሰፋ እና ቅይጥ ማንነት (non-territorial diversity) እና አመለካከት ያላቸውን ኅብረተሰቦች በሲቪክ እሴቶች (civic virtues) ማስተናገድ የሚቸግረው የብሔር ፖለቲካ እጅ መውደቋን የሚነግረን ይመስለኛል። የክቱ አበባ ዓይኑ እያየ ለሌላ ተድራልች።

ከተሜነት እንደ ሲቪልነት

ልጅ ሚካኤል ከተሜነትን እንደ ሲቪክ እሴት ማዳበሪያነት አድርጎ በዘፈኑ ሊያሳይ ሲሞክር ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ወርቀዘቦ የሚለው የዛሬ ሰባት ዓመት ገደማ የተለቀቀወ ነጠላ ዜማ ከተሜነትን የሲቪክ እሴት ከሆነው ነውጥ-አልበኝነት ጋር ያለውን ዝምድና በፍቅር አሳብቦ ያቀነቅነዋል። በዚህ ዘፈኑ፣ ተፈቃሪዋ ሴት ከሱ ከከተሜው ይልቅ በገጠሬው ፍቅር ትወድቃለች። የሱ ተቃውሞ የፍቅር መለኪያዋ ነውጠኝነት መሆኑ ላይ ነው።

“ፍቅር በጠመንጃ ከሚዘመርበት፣ ከዚያ ሀገር ወጥተሽ፣

የከተሜው ወዳጅ፣ ወዳጅ አይመስልሽ፣

ታዲያ ላንቺ ሲባል፣ የከተማው ልጅ፣

ምን ያንግትልሽ?” ይላታል።

በዘፈኑ የመሐል አገር ሰው ለቁም ነገር አይሆንም ማለቷን ይጠቅስና እንዴት ታጣቂ፣ አዳኝ፣ ገዳይ፣ ተኳሽ አለመሆኔ ከቁም ነገር ተራ ያወርደኛል ብሎ ይሟገታል። በየትኛውም ፖለቲካዊ ስርዓት ውስጥ ከተሜነትን ማሳደግ ግብ ነው። ነውጠኝነትም ሕግ እና ስርዓት በሌለበት ጊዜ የኅልውና መሣሪያ ነበር። የኢትዮጵያ ፖለቲካ በገጠር እሴት ከተማ ለመምራት የሚያስብ ነው። እኒህን ሁሉ ሐሳቦች ከልጅ ሚካኤል በቀር እንዲህ አሳምሮና ቀምሮ ማንም አላሰፈራቸውም።

‘ፍቅር ይዘህ ግባ’

ልጅ ሚካኤል በዚህ በዘውጌኝነት እና ገጠሬነት የተቃኘውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትርክት በብዝኃነት፣ አቃፊነት እና ከተሜነት ትርክት (civil counter narrative) ለመመከት በዘፈኖቹ ይታገላል። ለምሳሌ፣ “አትገባም አሉኝ” በሚለው አልበሙ ላይ “አዲስ አበባ” የሚል ዘፈን አለው። ዘፈኑ በአዝማሪ ድምፅ “ሁሉም ያገር ልጅ ነው፣ አዲስ አበባ ላይ” የሚል መፈክር ይዞ ይጀምራል። ሌላ ተቀባይ “ማንም አይክፋው” እያለች በድምፅ ትገባለች። ወቅቱ የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ነው። በየክልሉ፣ ከክልሌ ውጣ የሚል መፈክር እና ነውጥ የበዛበት ጊዜ ነበር። ልጅ ሚካኤል ግን እንዲህ እያለ ይጠይቃል፦

“ከሰሜን ነህ እንዴ? ናና...

ወይ ከደቡብ፣ ናና...

ከምሥራቅ ነህ እንዴ? ናና...

ወይ ከምዕራብ፣ ናና...”

[...]

“አበብሽ አበባ፣

ወደ አዲስ አበባ፣ ፍቅር ይዘህ ግባ”።

ይህ ለዘብተኛ የሚመስል ትርክት ሁሉም “ውጣልኝ” የሚል አንብሮ (thesis) ለማኖር በነውጥ ደግፎ በሚፍጭረጨርበት በዚህ ክፉ ወቅት “ፍቅር ይዘህ ግባ” የሚል የተፃርሮ (anti-thesis) ትርክት ለማኖር ይሞክራል። ከዘውግ ሥያሜ አፈንግጦ አዲስ አበባ ሁሉም፣ ከሁሉም አቅጣጫ እየመጡ ጎጆ የሚቀልሱባት ቤታቸው መሆኗን ያቀነቅናል። በአዲሱ አልበሙም ይኸው ትርክቱ ይቀጥላል። ሸገር በሚለው ዘፈኑ ውስጥ፣ “ሀገር ማለት ሸገር፣ ከፍ አርጎ ዘማሪ ኢትዮጵያን እንዳገር” እያለ ይጀምራል። ትርክቱን ስሰማው አዲስ አበቤው እና ቢጤዎቹ ከተሜዎች የመጨረሻው ‘የኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት’ አቀንቃኝ እንደሆኑ ይሰማኛል። ዘፈኑን “ጎንደር፣ ጎንደር፣ የአንዲት ኢትዮጵያ ዋልታና ማገር” ከሚለው የቴዲ አፍሮ ዘፈን ትይዩ ነገር ግን ሞጋችነት በሆነ አንፃር ነው የሚታየኝ። ልጅ ሚካኤል በዚህ ዘፈን፦

ሸገር፣ ሸገር፣ የሁሉ አገር” እያለ ይቀጥላል።

እዚህም ዘፈን ላይ አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን መሰባሰቢያ እንደሆነች በገደምዳሜ እንደሚከተለው ያስታውሰናል፦

“ዘመድ አለን ሰሜኑ ላይ፣ የለን አባይ፣

ዘመድ አለን ደቡቡ ላይ፣ የለን አባይ፣

ዘመድ አለን ምሥራቁ ላይ፣ የለን አባይ፣

ዘመድ አለን ምዕራቡ ላይ፣ የለን አባይ”

 በስተመጨረሻም፣ የተሻለ ቀን እንደሚመጣ ተስፋውን ይገልጻል፦

“መጭም ይፎክራል፣ ሒያጁም ይሸርባል፣

አዱ ገንዋ ላይ፣ አፉ ይበረታል፣

እመነኝ ቃሌ ነው፣ ቃልም አንድ ይሆናል፣

ሰው ወዳድ የሀገር ሰው ለሸገር ይቆማል...

...ያኔ ፍቅርም ይነግሣል፣

ሀገርም ይነሣል።”

በጥቅሉ የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ ዘውግ-ዘለል፣ ነው-አልባ፣ እና አሰባሳቢ ከተማ ነች።

እንደማንኛውም ብሔርተኛ ልጅ ሚካኤልም አዲስ አበባን ከሆነችው በላይ እያየላት እና እየተመኘላት ነው። ምናልባትም ከተማዋን “ከአቅሟ እና ከእውነታው በላይ ያሞካሻታል” ሊባል ይችላል። እንደሚመስለኝ ልጅ ሚካኤል የሚዘፍነው ለከተማዋ እሴት እና ራዕይ እንጂ ነባራዊው እውነታው አይደለም፤ ምክንያቱም በነባራዊው ሁኔታ ላይ ያለውን ቅሬታ እና ቁጭትም ከመግለጽ አይቆጠብም። ወደኋላ ለመመለስ የሚጓጓ ዓይነት ሆኖም አይታይም። በልጅ ሚካኤል ራዕይ አዲስ አበባ፣ የቱንም ያህል የከተሜነት እሴት ቢኖራት ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ሕመም ብቻዋን ልትድን የምትችል ደሴት አይደለችም። ቢሆንም፣ ኢትዮጵያን በሲቪክ የፖለቲካ እሴቶች እንዳዲስ ማዋቀር ከተፈለገ፣ ንቅናቄው ከአዲስ አበባ በተሻለ የትም ሊጀመር እንደማይችል ልጅ ሚካኤል የገባው ይመስለኛል።

Comments

  1. amazing and well versed.
    Thank you

    ReplyDelete
  2. For me the 97 remark he made on his Addis Ababa song (Posture posted above) was amazing

    ReplyDelete

Post a Comment

Popular posts from this blog

The "Corridor Development" is a Façade of the Prosperity Party

Befekadu Hailu I have seen a news report claiming that 40% of central Addis Ababa will be demolished for the corridor development; I am not able to confirm the validity of the news but it sounds real to me given the size of massive operations in the demolition of old neighborhoods and construction of bike lanes, green areas, and glittering street lights. I like to see some beauty added to my city but cannot help mourning the slow death of it too. Addis Ababa was already in a huge crisis of housing and the demolition of houses is exacerbating it. Apparently, Prime Minister Abiy Ahmed is eager to showcase his vision of prosperity by demonstrating how fast his administration can do magic by beautifying the front sides of the streets with lights, new pavements, and painted fences ("to fake it until he makes it" in my friend's words). Therefore, he and his party do not care about the miserable human stories behind the scenes and they will harass you if you tell it (Azeb Woku...

መጽሐፍ የሚወጣው፣ የተዋነይ ዘ ጎንጅ 5 መሥመር ቅኔ

ጎንጅ ቅኔ ያጠናበት ደብር ሥም ነው። ደብረ ጥበብ ጎንጅ ቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም። ተዋነይ የባለቅኔው ሥም ነው። (የግዕዝ ትርጉሙ "ዋናተኛ" ማለት ነው።) ሊቁ ተዋነይ የልኅቀቱን ያክል እምብዛም አይወራለትም፤ ነገር ግን በዘመኑ ወደር የሌለው ልኂቅ ስለመሆኑ ሥራው ይናገራል። የሕይወት ተፈራ "Mine to Win" የተሰኘ ድርሰት መቼቱን በዐፄ ዮሓንስ ንግሥና ዘመን፣ በጎጃም/ጎንደር የቅኔ መማሪያ ደብሮች ያደረገ ልብወለድ ነው። ልቦለዱ የቅኔ ትምህርት ስርዓትን ያስተዋውቀናል፤ በበኩሌ የቅኔ ትምህርትን እና የቅኔ ሊቃውንት ታላቅነት ቀድሞ ከነበረኝ ግንዛቤ የበለጠ እንዲሆን አድርጎኛል። በተለይ የተዋነይ ዘ ጎንጅ (በውኑ ዓለም የነበረ ባለቅኔ) ተከታይዋ አምስት መሥመር ቅኔ መጽሐፍ የሚወጣት እንደሆነች ልቦለዱ አሳሰበኝ። ወይም በአጭሩ ብዙ ምዕራባውያን ስንት መጽሐፍ የጻፉለት ፍልስፍናን በአምስት መሥመር ይዟል። የቅኔው ትርጓሜ የመጽሐፍ ቅዱስን እና የመጽሐፍ ቅዱሱን ፈጣሪ ኅልውና ይሞግታል። “የአምን ወይገኒ ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ ብዙኃን እንዘ ይገንዩ ይስግዱ ቅድሜሁ ለነጽሮ ዝኒ ነገር እሥራኤል ከመይፍርሑ ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ ወ ፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ።” (ተዋነይ ዘ ጎንጅ። ምንጭ፣ሕይወት ታደሰ ወደአማርኛ የተረጎመችው የሕይወት ተፈራ መጽሐፍ) ትርጉሙን በኋላ እመለስበታለሁ። ስለተዋነይ መጀመሪያ የሰማሁት የበውቀቱ መጽሐፍ ላይ ነበር። እሱም በጨረፍታ - “የሌሊት ዜማዎች” የሚለው ግጥሙ ውስጥ። በውቀቱ ተዋነይን በግጥሙ ግርጌ ማስታወሻው አስተዋውቆን ያልፋል፣ “ተዋነይ በቅኔ ቤት አፈ ታሪክ ሞትን በግዝት ለሰባት ዓመታት ያቆመ ጀግና ነው"። ከዚያ በኋላ፣ አዲስ አድማስ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ተዋነይ የተላከበትን ...