በአገራችን ሰው ተመርቆ ሲያበቃ ዝም ማለት የለበትም - ‹‹ከአሜን ይቀራል!›› ይባላል፡፡ አሜን በፀጋ መቀበል፣ ይሁንልኝ፣ ይደረግልኝ እንደማለት ነው፡፡ ይሄ የዓለማችን ዕውቅ ደራሲዎች ‹አዎንታዊ አስተሳሰብ› ወይም ‹ተስፈኝነት› (optimism) የሚሉት ዓይነት እሳቤ ነው፡፡ ሰሞኑን ‹ተኣምራዊው ኃይል› በሚል የተተረጎመውን የርሆንዳ ባይርኔን መጽሃፍ እያነበብኩ ነበር፡፡ የአዎንታዊ አስተሳሰብ አቀንቃኝ ነች፡፡ እኔም የአዎንታዊ አስተሳሰብ አቀንቃኝ ነኝ ባይ ነኝ፤ ሰዎች ግን ብዙ ብሶት ሳወራ ስለሚሰሙ ከአሉታዊዎች ተርታ ያሰልፉኛል፡፡ ለዚያ ነው ዛሬ የ‹አሉታዊ አስተሳሰብ› ወይመ ‹ጨለምተኝነት› (pessimism) አቀንቃኝ ሁኜ ልሟገት የተነሳሁት፡፡ Pessimism ስሙ አያምርም፤ ጨለምተኝነት ነው፡፡ ነገር ግን የስሙን ያህል ክፉ ነው ወይ? ዓለማችንንስ ያቀኗት እውን አዎንታዊ አሳቢዎች (optimists) ብቻ ናቸው? የሁላችንም ጥያቄ ነው፡፡ አዎንታዊ አሳቢዎች(optimists) ስለ አሉታዊ አሳቢዎች (pessimists) ያላቸው አመለካከት ራሱ ጨለምተኛ (pessimist) ነው፡፡ የአሉታዊ አሳቢዎች ድርሻ በአዎንታዊ አሳቢዎች እይታ አፈር ድሜውን በልቷል፤ እየበላ ነው፡፡ በአንድ አስቂኝ አባባል እንጀምር፡-