አንዳንድ ደፋሮች ‹‹ኢትዮጵያውያን ምቀኞች ናቸው›› ይሉና አንድ ተረት ይተርታሉ፡፡ እግዚአብሄር አንዱን ኢትዮጵያዊ ‹‹የፈለግከውን ጠይቀኝ እና አደርግልሃለሁ፤ ነገር ግን ላንተ የማደርገውን ነገር በእጥፉ ለጎረቤትህ አደርግለታለሁ›› ብሎ ሲለው ፣ ሰውየው በብርሃን ፍጥነት ‹‹እንግዲያውስ አንድ ዓይኔን አጥፋልኝ›› አለው ይባላል፡፡
የአባይ ግድብ እና የኢትዮጵያውያን ስሜታዊ መንዘርዘር - - -
ኢሕአዴግ የአዋሽ ወንዝን ገድቤ 5000 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል አመነጫለሁ ቢል ኖሮ በአባይ ጉዳይ እንደተወዘወዝነው በደስታ የምንፈነድቅ አይመስለኝም፡፡ ለምን? እውን የመንግስት ሚዲያው እንሚለፍፈው ‹‹ቁጭቱ›› ብቻ ነው? ‹‹አይመስለኝም›› እንዲያውም ያቺ እላይ የጠቀስናት ድብቅ የጋራ ባሕሪያችን አፈንግጣ ወጥታ ነው፡፡ አባይን መገደብ ግብፅን ዋጋዋን መስጠት ስለሚመስለን ነው፡፡ ‹‹የታባቷ›› ዓይነት ነገር!!!
የአባይ ግድብ እና የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድ - - -
እኔ የምለው? የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድ አባይን መገደብ ብቻ ነው እንዴ? ምክንያቱም አሁን የምንሰማው መፈክር እኮ ‹‹ቦንድ በመግዛት እና የወር ደሞዛችንን በመለገስ አባይን ገድበን የትራንስፎርሜሽኑን ዕቅድ እናሳካ›› የሚል ነው፡፡ ቀድሞ ነገር የአባይ ግድብ በትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ መቼ ተካተተና፡፡ ተጨማሪ ነገር አይደል እንዴ? ሕዝባዊ አመፅ ባለማስነሳታችን - ምርቃት!!!
የአባይ ግድብ እና የወር ደሞዝ - - -
ሰሞኑን አዲስ አድማስ ላይ ካነበብኩት ወገኛ አባባል አንዱ ‹‹አባይ ድሮ ግንድ ይዞ ይዞር ነበር፤ አሁን ደግሞ ደሞዛችንን ይዞ ይዞራል›› ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ እምብዛም ያልተዋጣለት በአብላጫ ድምፅ የመወሰን ጉዳይ ዘንድሮ ለደሞዝም ውሏል፡፡ በየመስራቤቱ አዳራሽ ቀድሞ የተወሰነው የደሞዝ ስጦታ አጀንዳ ይነሳና፣ የይስሙላ ውይይት ከተደረገበት በኋላ በአብላጫ ድምፅ የያንዳንዱ ሰው ደሞዝ ይወሰዳል፡፡ እኔ የምለው ‹‹የራስን ዕድል በራስ መወሰን›› የምትለዋ የሕገ መንግስታችን አወዛጋቢ ሐረግ ለወር ደሞዝ ሲሆን አትሰራም እንዴ?!
የአባይ ግድብ እና የባሕር በር - - -
የኢሕአዴግ መንግስት አባይን በመገደብ ብቻ ደርሶ አርበኛ ለመመስል ከመሞከሩ በፊት መመለስ ያለበት ጥያቄ ያለ አይመስላችሁም፡፡ ለኢትዮጵያ ከአባይ ግድብ እና ከባሕር በር የትኛው ያስፈልጋት ነበር? እውነቱን ለመናገር ከኤርትራ ጋር አብሮ የሸኘውን ወደባችንን በምንም ሊክስልን አይችልም፤ መቶ ብር ቀምቶ አንድ ብር የሰጠ ቸር አይሰኝም!!!
No comments:
Post a Comment