Gene Sharp የአረቡን ዓለም አብዮት አቀጣጥሏል የሚባልለትን From DICTATORSHIP to DEMOCRACY: a Conceptual Framework for Liberation የተሰኘ ጥናት ጸሃፊ ናቸው፡፡ ጥናቱ የአምባገነኖችን ዓይነት ሲዘረዝር ሚሊቴሪ አምባነገን፣ ከአባት ወደልጅ የሚተላለፍ የንግስና ሥርዓት፣ አሃዳዊ የፖለቲካ ፓርቲ የሚመራው እና የውጭ ወራሪዎች ብሎ ይመድባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን በየትውልዱ አራቱንም ዓይነት አምባገነኖች ለመሸከም ተዳርገናል፡፡ ይኸው አሁንም በአሃዳዊ የፖለቲካ ፓርቲ የሚመራው አምባገነናዊ አስተዳደር ላይ እንገኛለን፡፡
የመለስ ዜናዊን እና ፓርቲያቸውን አምባገነንነት የሚጠራጠር ኢትዮጵያዊ ካለ (ምንም እንኳን የአባይን መገደብ የማይደግፍ ‹‹ኢትዮጵያዊነቱን በገዛ ፈቃዱ ሰርዞታል›› እንደተባለው፣ ኢትዮጵያዊነቱ ይሰረዝ ለማለት ባልደፍርም፤) የአምባገነን ትርጉሙን ሊነግረን ይገባል፡፡
መለስ ዜናዊና ፓርቲያቸው ተለሳልሰው ቦታ፣ ቦታቸውን ከያዙ በኋላ የሚነቀንቃቸው ጠፍቷል፡፡ መጀመሪያ ላይ ብዙው ሕዝብ በጨዋታቸው ተሸውዶ ነበር፤ የምርጫ 97 ድራማ እስኪያጋልጣቸው ድረስ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ለወንበራቸው ምን ያህል ቀናኢ እንደሆኑ በግልፅ አስመስክረዋል፡፡ በመሰረቱ እነመለስ በአናሳ ቡድን አመራራቸው ትልቅ ‹ኢምፓየር› መስርተዋል፡፡ ከስልጣናቸው በምርጫ ከወረዱ ከተጠያቂነት የማያስተርፋቸው ነገር አይጠፋም ስለዚህ በምርጫ ይወርዳሉ ብሎ መመኘት ልጅነት ወይም ጅልነት ነው፡፡
በጥንታዊው የቹ ፊውዳል ሥርዓተ-መንግስት ውስጥ ዝንጀሮዎችን አገልጋይ አድርጎ የሚኖር አንድ ሽማግሌ ነበር፡፡ የቹ ሕዝቦች ‹‹ጁ ጎንግ›› (የዝንጀሮ ጌታ) እያሉ ይጠሩታል፡፡
በየማለዳው፣ ሽማግሌው ዝንጀሮዎቹን ሸንጎ ይጠራቸውና ከመሃከላቸው በእድሜ ትልቁን መርጦ፥ በእርሱ መሪነት ከጫካው ፍራፍሬ ሰብስበው እንዲያመጡ ይልካቸዋል፡፡ እያንዳንዱ ዝንጀሮ ከሚሰበስበው ፍራፍሬ ውስጥ አንድ አስረኛውን ለሽማግሌው እንዲሰጥ የሚያስገድድ መመሪያ አለ፡፡ ይህን ማድረግ ያልቻሉ ያለምንም ምክንያት ክፉ ቅጣት ይጠብቃቸዋል፡፡
አንድ ቀን፣ አንድ ትንሽ ዝንጀሮ ‹‹እነዚህን የፍራፍሬ ተክሎች ያበቀላቸው ሽማግሌው ነው?›› ሲል ጠየቀ፡፡ ሌሎቹ ‹‹አይ፤ በተፈጥሮ የበቀሉ ናቸው›› ሲሉ መለሱለት፡፡ ትንሹ ዝንጀሮ ‹‹ያለሽማግሌው ፈቃድ ፍራፍሬዎቹን መውሰድ አንችልም?›› በማለት ተጨማሪ ጥያቄ አመጣ፡፡ ሌሎቹም ‹‹አዎ፤ እንችላለን›› አሉ፡፡ ‹‹ታዲያ ለምንድነው በሽማግሌው ላይ ጥገኛ የሆንነው? ለምን የሱ አገልጋይ እንሆናለን?›› ትንሹ ዝንጀሮ ጠየቀ፤ እሱ ጠይቆ ሳይጨርስ ሁሉም ዝንጀሮዎች ተገለፀላቸው፡፡
የዛኑ ዕለት ምሽት፣ ሽማግሌው እንቅልፍ ሲተኛ፣ የታሸጉበትን አጥር ግድግዳ ደረማምሱት፡፡ ሽማግሌው በጎተራው አስቀምጦት የነበረውንም የፍራፍሬ ክምችት ጠራርገው ወሰዱበት፡፡ በመጨረሻም ሽማግሌው በርሃብ ሞተ፡፡
በተመሳሳይ መንገድ ይላል ጸሃፊው ‹‹አንዳንድ ሰዎች በእውነተኛ መርሖች ሳይሆን በማታለል ዓለምን ይገዛሉ፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰዎች የዝንጀሮ ጌታ አይደሉም? የገዛ ድክመታቸውን እንኳን አያውቁም፤ ሕዝብ የነቃባቸው ‘ለታ፣ ማታለያቸው በሙሉ ይከሽፋል፡፡››
አምባገነንነት የሕዝብን ወኔ የሚሰልብ በሽታ ነው፡፡ ማሕበረሰቡ አቅም ሲያጣ፣ በራስ መተማመን ሲያጣ፣ በፍርሐት ሲሸበብ እና በአገሩ ተስፋ ሲቆርጥ (ስደትን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ ሲቆጥር) ያኔ አምባገነናዊ አስተዳደር ውስጥ እንዳለ ማወቅ ይቻላል፡፡ዛሬ በኢትዮጵያ እየሆነ ያለውን ልብ ይሏል::
አምባገነን መንግስታትን የውጭ ኃይሎች ይጥሏቸዋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ሁሉም የውጭ ኃይሎች አምባገነኖችን የፖለቲካና የኢኮኖሚ መጠቀሚያ ያደርጓቸዋል እንጂ በዓይናቸው ካልመጡባቸው በቀር ሊነኳቸው አይፈቅዱም፡፡ የኢትዮጵያን እና የአሜሪካን መንግስት ወዳጅነት መመልከት በቂ ነው፡፡ የአሜሪካ የሰብአዊ መብት ሪፖርት ኢትዮጵያን ከመስመር በታች ቢጥላትም፣ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ተባባሪነታቸውን ግን በይፋ ከሚናገሩለት የሰብአዊ መብት ጥብቅናቸው ተቃራኒ ከዓመት፣ ዓመት ያጠብቁታል፡፡
የአምባገነንነት መመሪያው ግልፅ ነው፡፡ አምባገነኖች የሕዝቡን ድጋፍ ይፈልጋሉ፡፡ በማስፈራራትም ይሁን በጥቅም በነርሱ ጥገኝነት የወደቀና የሚታዘዝላቸው ሕዝብ ከሌለ አምባገነኖች ቦታ አይኖራቸውም፡፡
Comments
Post a Comment