‹አዳሪ› የሚለውን ቃል የተዋስኩት ከአበባው መላኩ ጣፋጭ የግጥም ስብስብ ውስጥ ነው፡፡ ከግጥሞቹ ስንኞች ጥቂት ቆንጥሬ ጀባ ልበላችሁና ወደጽሁፌ ልንደርደር፡፡
‹‹… ሴትነቴን ወደው፣ እኔነቴን ንቀው፣በፍቅሬ ተማርከው ገላዬ ስር ወድቀው፣‹እን’ደር› ይሉኛል በስሜት ታውረው፣እነሱ ቀድመውኝ በወንድነት አድረው፡፡…››
ጽሁፉ ወንደኛና ሴተኛ አዳሪዎችን ይመለከታል፡፡ በዚህ ወግ ውስጥ እስከዘለቅን ድረስ ‹አዳሪ› ማለት በሴሰኝነት የተጠመዱ ወንዶችና ሴቶችን እንጂ ከተቃራኒ ፆታ ጓደኛቸው ጋር ያደሩ እና የሚያድሩ ሰዎችን አይመለከትም፡፡
ተላፅቆ፣ ግብረስጋ ግንኙነት፣ ሩካቤ ስጋ ወይም ወሲብ የሚሉ ቃላቶች ተመሳሳይ ትርጉም ይሰጡታል - እኔ ግን ፍቅር መስራት የሚለውን መጠቀም እመርጣለሁ፡፡ ምክንያቱም ፍቅር መስራት በሁለት የሚፋቀሩ ጥንዶች መካከል የሚፈፀም፣ ጥንዶችን የእውነትም አንድ የሚያደርጋቸው ተፈጥሯዊ ስጦታ ነው፡፡
ወሲብ ተፈጥሯዊ ነገር ነው፤ የሰው ልጅ በእውኑ ቢታቀብ በሕልሙ ይወስባል፡፡ ነገር ግን ካገኙት ሰው ጋር ሁሉ ቢወድቁ በሃይማኖታዊ ሚዛን አመንዝራነት፣ በማሕበራዊ እሴትና ስነልቦና ሚዛን ሴሰኝነት፣ በጤና ሳይንስ ሚዛን ለበሽታ ራስን አሳልፎ መስጠት ነው፡፡ በሁሉም መመዘኛ ሲለካ ‹ትክክል አይደለም፡፡› ለዚህ ነው ተፈጥሯዊ የወሲብ ጥያቄን በፍቅር መስራት ልንወጣው የምንገደደው፡፡
ሆኖም ግን ስህተቱ [ቢያንስ በዚህ ዘመን ስሌት] ከሁሉም ጋር መውደቅና ገላንም፣ ራስንም ማርከሱ እንጂ ከሚወዱት ሰው ጋር ፍቅር መስራቱ አይደለም፡፡ በእኔ አመለካከት 18 ዓመት የሞላው ማንኛውም ሰው እድሜዋ ከደረሰች ሴት ጋር ፍቅር ከሰራ፥ ሁለቱም ተፈጥሮ የለገሳቸውን መክሊት ተጠቀሙበት እንጂ ምንም ስህተት አልሰሩም፡፡
የወሲብ ኮንትሮባንድ
በእኛ የኢትዮጵያውያን የአፍ ባሕል ፍቅር መስራት አጠያፊ ነገር ነው፡፡ አጠያፊነቱ ግን ተግባራዊነቱን አላገደውም፡፡ በገጠሪቷ ኢትዮጵያ መወሻሸም የሚያኮራ እሴት ያህል በርካታ ግጥሞች ይገጠሙለታል፣ ቅኔ ይዘረፍለታል፣ ዘፈን ይዘፈንለታል፡፡
ከሕዝብ ተውሳ ባለክራሯ አስናቀች ወርቁ ካቀነቀነችው ውስጥ ለአብነት እንጥቀስ፡-
‹‹… ባልም አላገባ እጅግም አልቸኩል፣የነእሜትዬን ባል እገባለሁ የእኩል፡፡…ባልም አላገባ ጨውም አልደቁስ፣እንዲሁ እኖራለሁ ዓለምን ሳጨስ፡፡››
በከተማዎች፣ ከአዲስ አበባ ወጣ ያላችሁ እንደሆነ ደግሞ (በተለይም ወደደብረዘይት እና ናዝሬት)፣ የጭፈራ ቤቶቹና የሴተኛ አዳሪዎቹን ሁሉ ስትመለከቱ ‹እነዚህ ሁሉ በልተው ያድራሉ?› ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል - ሁሉም በየፊናቸው አትራፊ ናቸውና አትስጉ፡፡ የስርቆሽ ቤቱቹ አበዛዝ ደግሞ የጉድ ነው፡፡ ታዲያ የእነዚህን የስርቆሽ ቤቶች ስታዩ ‹የሚሰርቁት እነማን ናቸው?› ለሚለው ጥያቄ መልሱ ባለትዳሮች ሁኖ ታገኙታላችሁ፡፡ እዚህ ጋር ቆም በሉና የሚከተለውን ጠይቁ፡-
‹‹እስኪ ግን ራሳችንን ‹ጨዋ› አድርገን ከምንቆጥረው ኢትዮጵያውያን የፈለቁ ባለትዳሮች ውስጥ ስንቶቹ በፍቅር ይሰርቃሉ? ስንቶቹ አባቶች ከውጪ ልጅ አምጥተው ቤተሰብ በጥብጠዋል? ስንቶቹ እናቶች የልጆቻቸውን አባት ከልጆቻቸውም፣ ከባሎቻቸውም ደብቀው ዘልቀዋል? ስንቶቹ ልጆች - ወላጅ ልጄ ሴት/ወንድ አያውቅም/አታውቅም - ሲላቸው ከርመው ያልተጠበቀ ልጅ ይዘው ከች ብለዋል? ስንቶቹ በስርቆሽ ወሲብ በሽታ ሸምተዋል?››
የማይከፈላቸው አዳሪዎች
በእኔ እምነት የሚከፈላቸው አዳሪዎች አንድኛውን እንጀራ አድርገውታልና አይፈረድባቸውም፡፡ ብዙዎቹ የሚከፈላቸው አዳሪዎች ችግር ተፈጥሯቸውን እንዲቸበችቡ አስገድዷቸዋልና ይሻላሉ፡፡ የዚህ ጽሁፍ ትኩረት ዓላማ የሆኑት ግን የማይከፈላቸው አዳሪዎች ናቸው፡፡
የማይከፈላቸው አዳሪዎች ወሲብን እንደጀብዱ የሚቆጥሩት፣ ካገኙት ወንድ እና ሴት ጋር በቅፅበት አንሶላ የሚጋፈፉት፣ ፍቅረኛ ወይም የትዳር አጋራቸውን ሸውደው እቤት ያለውን ውጪ የሚፈልጉት ናቸው፡፡ እስኪ ዛሬ እንኳን መደባበቅ ይቅርና እውነቱን እንጠያየቅ፤ ‹‹በፍቅረኛዋ ወይም በትዳር አጋሩ ላይ የማይወሰለት ማን አለ?››
እውነቱን ለማውራት ከቆረጥን የሚወሰልቱ ሰዎች በመዲናችን ከሃምሳ በመቶ መብለጣቸው የማያጠራጥር ነው፡፡ እንዲያውም አሁን ‹ወስላታ› የሆነ እና ‹ወስላታ ያልሆነ› ሰው ልዩነታቸው - ‹የተነቃበት› እና ‹ያልተነቃበት› ወስላች ወደመሆን እየተሸጋገረ ነው፡፡ ፍቅረኛዋን ‹የት ገባህ? የት ወጣህ?› እያለች የምትቆጣጠረዋ ሴት በአገኘችው ክፍተት ከሥራ ባልደረባዋ፣ ከጎረቤቷ ትሰርቃለች፡፡ በመስክ ስራ ከአዲስ አበባ የሚወጣው አባወራ ከተገኘችው ሴት ጋር አሸሸ ገዳሜ ሲል ያድራል፡፡
አሁን በሃገራችን የሚበዙት የሚከፈላቸው አዳሪዎች ሳይሆኑ የማይከፈላቸው አዳሪዎች ናቸው፡፡
ችግሩ መኖሩን እያንዳንዳችን እናውቀዋለን፡፡ መንስኤውን አናውቀው ይሆናል፡፡ በኔ እምነት የማይከፈላቸው አዳሪዎችን የፈጠረው መታፈን የበዛበት ባሕላችን ነው፡፡
- በተፈጥሯዊ የወሲብ ጉዳዮች ላይ በግልጽ ማውራት አለመቻላችን ከአንዱ ቤት ሌላው ቤት የተለየ ነገር ያለ እንዲመስለን ያደርጋል፣
- ጥንዶች ወይም ባለትዳሮች በወሲብ ፍላጎቶቻቸው ዙሪያ በግልጽ መወያየትን እንደነውር በመቁጠራቸው እርካታ ፍለጋ ውጪ እንዲያማትሩ ያደርጋል፣
- ልጆች የተፈጥሮ ጥያቄን በጥንቃቄ እንዲመልሱ በመመከር ፋንታ ‹‹እንዳታደርግ/እንዳታደርጊ›› ብሎ ማፈኑ ላልተፈለገ እርግዝና ወይም በሽታ ሊዳርጋቸው በሚችል ስርቆት ውስጥ እንዲወድቁ ያደርጋል እና
- ሌላም፣ ሌላም፡፡
ታዲያ ችግሩ ይኼ ነው ካልን መፍትሄውስ ብለን መጠየቃችን አይቀርምና መፍትሄ የምለውን ልጠቁማችሁ፡፡ እናንተም የራሳችሁን መንስኤና መፍትሄዎች በአስተያየቶቻችሁ እንደምትጠቁሙ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
Well said. I agree with your proposition that the problem is 'በወሲብ ጉዳዮች ላይ በግልጽ አለማውራት'. If so, then the solution will be 'በግልፅ ማውራት'.
ReplyDelete