ኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ዕርስ በዕርስ ተከባብረው እና ተሳስበው የሚኖሩባት ሃገር ነች፡፡ የኢትዮጵያውያንን ማሕበራዊ ጋርዮሽ የሃይማኖት ልዩነታቸው አላወከውም፡፡ በዚህ ስሌት የሚከተለው የእኔ እምነትም Aክባሪ እንደማያጣ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በእምነትና በሃይማኖት መካከል የተሰመረ መስመር መኖሩን በእርግጠኝነት መናገር አልችልም፡፡
ሃይማኖት ያለእምነት ምንም ነውና፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ሃይማኖተኛ ለመሆን እምነት/ማመን ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡ አምላኩን ማመን፣ ቅዱሳት መፃሕፍት የሚናገሩትን ማመን፣ ወይም በዕጣፈንታው ቀድሞ መፃፍ ማመን፡፡
ሃይማኖት ያለ እምነት መኖር የማይችል ቢሆንም ቅሉ እምነት ግን ያለሃይማኖት መኖር ይችላል፡፡ አሁን ለምሳሌ እኔ በዝንጀሮ ቁንጅና ለማመን ብፈልግ የሆነ ሃይማኖት ሊኖረኝ ግድ አይደለም፡፡ ስለዚህ የጫወታዬ አጀንዳ ፅድቅና ኩነኔን የተመለከቱ እምነቶች ሳወራ በሃይማኖት ጥላ ስር የተከለሉ ወይም ያልተከለሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እንደተለያዩ እምነቶች ከሆነ የተለያዩ አማልክት ለፅድቅና ኩነኔ የተለያዩ መስፈርቶች ከተለያዩ ሽልማቶችና ቅጣቶች ጋር አዘጋጅተው ሰዎች በተቻላቸው መጠን መልካም ስነምግባርን እንዲይዙ ‹‹ካሮትና አለንጋ›› የተሰኘ አመራር ይከተላሉ፡፡
‹‹ካሮትና አለንጋ›› አህያን የሚነዳ አንድ ሰው የሚጠቀምባቸው መንገዶች ናቸው፡፡ ከፊት ከፊቱ ካሮት እያሳዩ የተሸከመውን ከሚፈለግበት እንዲያደርስ ማበረታታት አሊያም በአለጋ ከበስተኋላው እየዠለጡ ወደፊት የማስጋለብ አመራር ዓይነቶች ናቸው፡፡ በአንዳንድ ሃይማኖቶች ውስጥ ተመላኪው አካል ፍጡሮቹን እንደማይቀጣ በግልፅ ይነገራል፡፡ ኩነኔ የለም ማለት ነው፡፡ መልካም የሰሩ ሰዎች ግን ከሞት በኋላ ህይወት እንዲኖራቸው ይደረጋል፡፡ በብዙዎቹ ሃይማኖቶች እምነት ፅድቅም ኩነኔም (ሽልማቱም ሆነ ቅጣቱ) ከሞት በኋላ ነው፡፡
የፅድቅና ኩነኔ ሒሳብ የሚወራረደው ምድራዊ እማኝ በሌለበት እንደመሆኑ ተአማኒነቱን ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል፡፡ ሆኖም በሃይማኖታዊ አካሄድ መጠራጠር አይፈቀድም፡፡ ይሁን እንጂ እንዴት አለመጠራጠር እንደሚቻል የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ከተጠራጠሩ በኋላ ጥርጣሬን አፍኖ በመቆየት የሚገኘው ሽልማትም አይታወቅም፡፡
በአንዳንድ ሃይማኖታዊ እምነቶች ውስጥ ፍርድ የሚሰጠው ከሞት በኋላ እንደሆነ ቢታወቅም ተከታዮቹ ግን በምድር ላይ ሕይወት እንዲሰምርላቸው ተስፋ የሚጥሉት፣ ለስኬታቸው የሚያመሰግኑት አምላካቸውን ነው፡፡ ይህ አካሄድ በከፊል ሽልማቱ በምድር ላይ እንደሚጀመር አመላካች ነው ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ለስንክልናቸውም የAምላካቸውን ተፃራሪ አካል እንደምክንያት ይጠቅሳሉ እንጂ በነሱ የሚፈጠር ምንም ስህተት የለም፡፡ ይህ እንግዲህ የሰው ልጅ በራሱ ፈቃድ የሚሰራውም ሆነ የሚያጠፋው እንደሌለ አመላካች ሲሆን የፅድቅና ኩነኔ Aስፈላጊነቱ ለምን እንደሆነም በአንፃሩ ግልፅ አለመሆኑን ያሳያል ማለት ነው፡፡
በሌሎች ሃይማኖቶች የፅድቅና ኩነኔ ሽልማትና ቅጣቶች በዳግም ውልደት ጊዜ እንደሚወሰኑ ይታመናል፡፡ አንዳንዶቹ ፃድቃን ሃብታምና ጤነኛ ኩንኖች ደግሞ ድሃና በሽተኛ ሆነው ድጋሚ እንደሚወለዱ ያስተምራሉ፡፡ በዚህ አስተማመን ዛሬ በምድር ላይ የምናያቸው ሰዎች በቀደመው ዘመናቸው ምን ዓይነት መልካምና መጥፎ ሰዎች እንደሆኑ መገመት ይቻለናል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም አሜሪካ በዓለማችን ብዙ የድሮ ዘመን ፃድቃን የሚገኙባት ሃገር መሆኗን መገመት አያዳግትም፡፡ ከነዚህም መካከል ቢልጌትስ በጣም ፃድቁ ሰው ነበር ማለት ነው - ብሎ መቀለድ ይቻላል፡፡ የዚህ እምነት ጠቃሚ ጎኑ ድጋሚ የመወለድ ዕድል የሚሰጥ መሆኑ ነው፡፡ ሌሎቹ ሃይማኖቶች ባለፈው የሕይወት ዘመናቸው ፅድቅን ከሰሩ ደግመው በሚወለዱበት ጊዜ ሰው ሁነው ይወለዳሉ፡፡
ሰው ሆኖ መወለድም በራሱ የፅድቅ ምልክት ነው - እንደነዚህኞቹ እምነት፡፡ ኩነኔን ሰርተው የሚያልፉ ሰዎች ግን በዳግም ውልደታቸው ሌሎች እንስሳትን ሆነው ይወለዳሉ (ነፍሶቻቸው በአዲስ የሚወለዱ እንስሳት ውስጥ ይገባሉ፡፡) ስለዚህ በዚህ እምነት እሳቤ ላይ ቆሜ መልእክት ማስተላለፍ እወዳለሁ፡፡ ‹አሁን በእንስሳት ላይ የምታደርሱት በደል ወደፊት በሰራችሁት ኩነኔ እንስሳ ሁናችሁ ዳግም ስትፈጠሩ እንዳይደርስባችሁ› የሚል ማሳሰቢያ!!!
ከላይ በጫወታ ያነሳሁዋቸው የፅድቅና ኩነኔ ውጤቶችን የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር አለ፡፡ በሁሉም ውስጥ ፈራጅ አለ፣ ፍርዱም ከሞት በኋላ የሚሰጥ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ከኔ የግል የፅድቅና ኩነኔ እምነቶች ጋር እንዳይስማሙ ያደርጋቸዋል፡፡ በእኔ እምነት የፅድቅና ኩነኔ ሽልማትና ቅጣት አለ፡፡ ፈራጁ ግን ሁለተኛ አካል አይደለም፡፡ ፍርዱም ከሞት በኋላ አይደለም፡፡ ታዲያ መስፈርቱ ምንድነው? ፍርዱስ እንዴት ይፈፀማል?
በመሰረቱ የእኔ እምነት ስም የለውም እንጂ ቢኖረው ኖሮ ‹በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም› የሚል ይሆን ነበር (ወይም ቢባል የተሻለ ይገልፀው ነበር፡፡) የሰው ልጅ ከእንስሳት የሚለየው የማሰብ ደረጃው ነው፡፡ ያለፈውን ድርጊቱን መገምገም ይችላል፡፡ በሌላ በኩል የሰው ልጅ ማሕበራዊ እንስሳ እንደመሆኑ ዕርስ በዕርስ የሚገማገምበት ያልተፃፉ ሕግጋትን አበጅቷል፡፡ ለምሳሌ ቁንጅና እንዲህ ነው ብሎ የነገረን ሰው የለም ነገር ግን ብዙዎቻችን ሎጋ ቁመት፣ ሰልካካ አፍንጫ፣ መቃ አንገት እያልን እንፈልጋለን፡፡
ምናልባት ይሄ የተለየ እሴት ባላቸው ማሕበረሰቦች ቦታ ላይሰጠው የሚችል መስፈርት ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም በመልካም (የፅድቅ) ሥራና በመጥፎ (የኩነኔ) ሥራ ላይም እንዲሁ እንደማህበረሰቡ አመለካከት የተለያዩ መለኪያዎች አሉ፡፡
እያንዳንዱ የማህበረሰቡ አባል ያልተፃፉትን ሕግጋት ያውቃቸዋል፡፡ ሲያጠፋ ይፀፀታል፣ ሲያለማ ደግሞ ይደሰታል፡፡ እነዚህ ስሜቶች የሚታይ ቅጣት ስለሚጠብቀን ወይም ስለምንሸለም ብቻ የምንፈጥራቸው ስሜቶች አይደሉም፡፡ እነዚህ ስሜቶች የማህበረሰቡ አካል እንደመሆናችን ሳናውቅ በውዴታችን በጋራ ያፀደቅናቸውን ሕግጋት በማክበርና በመጣሳችን የሚፈጠሩ የኩራትና የሐፍረት ስሜቶች ናቸው፡፡
የደስታና የፀፀትን ስሜት ጥሩ ወይም መጥፎ በመሆን ማምለጥ አይቻልም፡፡ ሰዎች ሟች ፍጡሮች ናቸው፡፡ ሟችነትን አምኖ መቀበል በጣም ከባድ ነገር ነው፡፡ ከሞት በኋላ ሕይወት አለ ብሎ ማመን መፍትሄ የሚሆኖውም ከዚህ ፍርሃት ለማምለጥ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሰዎች ሟች መሆናቸውን አምነው መቀበል ካለመቻላቸው የተነሳ የማሕበረሰቡን ሕግጋት ይጥሳሉ፣ እንኳን አንድ ሁለት፣ ሦስት የሰው ዕድሜ ቢሰጣቸው የማይጨርሱትን ሃብት ለማካበት የሌላ ሰው ነፍስ እስከመንጠቅ ይደርሳሉ፡፡ በእኔ እምነት እንግዲህ ለዚህ ምግባራቸው ቅጣታቸውን እዚሁ መቀበላቸው አይቀሬ ነው፡፡
የክፋትንና ደግነትን መለኪያ ለናንተ ልተውና ጫወታዬን ለማሳረግ ያህል የሎሬቱን ቅኔ ልዋስ፣
‹‹ፅድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም፣ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም፡፡››
No comments:
Post a Comment