አምባገነን መንግስታት ከአንድ ባሕር ይቀዳሉ፤ በርካታ የሚመሳሰሉባቸው ባሕርያት አሉዋቸው፡፡ በዚህች መዳፍ በምታክል ገጽ እና በእኔ ቁንፅል እውቀት ሁሉንም ዘርዝሮ መጨረስ ይከብዳል፡፡ ለነገሩ የአምባገነን መሪዎችን የጋራ ባሕርያት እነሱ ራሳቸው በቅጡ አያውቁትም፡፡ ነገር ግን በተለይ ጎልተው የሚለዩባቸውን ባሕርያቶች አንድ፣ ሁለት እያልን እስከአምስት መቁጠር እንችላለን፡፡ እነሆ፡-
1). የሥልጣን ዘመን ርዝመት
አምባገነኖችን ለማወቅ አንዳንዴ ጊዜ ይወስድብናል፡፡ የሥልጣን ዘመናቸውን ርዝመት ለማየት፡፡ ምክንያቱም ሁሉም መጀመሪያ ቅዱስ ናቸው፡፡ ኃ/ሥላሴ 44 ዓመት፣ ቃዳፊ 40 ዓመት፣ ሁስኒ ሙባረክ 30 ዓመት፣ መለስ ዜናዊ 20 (ገና የሚቀጥል) ዓመት፣ መንግስቱ ኃ/ማርያም 17 ዓመት፡፡ ሒደታቸውን እንመልከት ካልን - ኃ/ሥላሴ መጀመሪያ ተራማጅ፣ ኋላ ቁሞ ቀር፤ ቃዳፊ መጀመሪያ ነፃ አውጪ፣ ኋላ ቅኝ ገዢ፤ ሙባረክ መጀመሪያ ሃገር ወዳድ፣ ኋላ ስልጣን ወዳድ፤ መለስ መጀመሪያ የነፃነት ታጋይ፣ ኋላ የነፃነት አፋኝ እና የመንግስቱ ኃ/ማርያምን አልናገርም፡፡
2). መፈክር እና መወድስ
አምባገነን መንግስታትን ዝም ብላችሁ ከአደመጣችኋቸው ከዓመት፣ ዓመት ለአገራቸው የሚያበረክቱት መፈክር ነው፡፡ የዓመታዊ ዕቅዱን ከግብ እናደርሳለን፣ ጠላቶቻችንን አፈር እናበላለን፣ ከመሪያችን ጋር ወደፊት እንራመዳለን የሚሉ ቃላቶች ብርቅ አይሆንባችሁም - በአምባገነን መንግስታት ስር፡፡ ሌላው የመንግስት ሚዲያዎችና የመንግስታቱ ደጋፊዎች የመወድስ ቃላቶች ናቸው፡፡ እኛ አገር ኑና በቅርቡ ለመለስ የታተመውን “ኮርተንብሃል” ፖስተር አስታውሱ፣ በዋና-ዋና አደባባዮች የቆመውን ግዙፍ የሰውየውን ምስል ተመልከቱ፣ በግድ በሚጠሩት ሰልፎች ላይ ካሉት መፈክሮች ጎን የሚያዘውን ፎቶ ተመልከቱ፣ ከሕዳሴው ግድብ የፉከራ ቢልቦርድ ጎን ያለውን ፎቶ ተመልከቱ - ይሄ በተደጋጋሚ ያያችሁት ፎቶ የአንድ አምባገነን ካልሆነ በቀር በየቦታው መወድስ አያስፈልገውም ነበር:: በዴሞክራሲያዊ አገሮች እኮ የአገር መሪው ፎቶ በቢልቦርድ ላይ ተለጥፎ ካያችሁ፣ የምርጫ ቅስቀሳ አለ ማለት ነው፡፡ አምባገነኖች ግን የግል ገፅታቸውን ለመገንባት ከዓመት፣ ዓመት የማይወርድ ፎቷቸውን እንደጣኦት በየቦታው ይገትሩላችኋል:: አባቶቻችን “መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ” እንዲሉ፤ ‹ምግባረ ጥፉንም በፕሮፓጋንዳ ይደግፉ› መባል ነበረበት፡፡
3). የጠላት የሙት መንፈስ (Ghost Enemy)
በወታደራዊው ደርግ ዘመን ተጠሪ የሌላቸው ሟች ወታደሮች ደሞዛቸውን በየወሩ እየፈረሙ የሚቀበሉላቸው አለቆች እንደነበሩ ይነገራል፤ እነዚህን ሟች ደመወዝተኞ/ሰራተኞች Ghost Employees /የሰራተኞች የሙት መንፈስ/ ይሏቸዋል - ታዛቢዎች፡፡ Ghost Enemy (የጠላት የሙት መንፈስ) የሚለውን ስያሜ የተዋስኩትም ከዚያው ነው፡፡ ሌላው የአምባገነኖች መለያ ነው፡፡
አምባገነኖች ጀብዱ ሲያምራቸው፣ አገር ወዳድነታቸውን ማወጅ ሲያምራቸው፣ ተቃዋሚዎቻቸውን መደምሰስ ሲያሰኛቸው፥ አሸባሪ፣ አማፂ፣ ሃገር ከዳተኛ እያሉ የፈለጉትን ቡድን ይፈጥራሉ፡፡ በዚህ ቡድን ሳቢያ ሕዝቡን ከፈለጉ ራሳቸው አሸብረው ተቃዋሚዎቻቸውን በማሰር፣ በመግደል እና በማዳከም መንበረ ስልጣናቸውን ያጠናክራሉ፡፡ ልክ አሁን ሰሞን ቃዳፊ አንዴ አሜሪካን፣ አንዴ አልቃይዳን እንደወነጀሉት፤ ልክ የአገራችን መንግስት ኦነግ፣ ኦብነግ፣ ግንቦት ሰባት አያለ ያለሕዝቡ ፈቃድ በአሸባሪነት እንደፈረጃቸው ቡድኖችና ፓርቲዎች፡፡ እነዚህ የጠላት የሙት መንፈሶች (ያሉም-የሌሉም ጠላቶች) አምባገነኖቹን አገር ወዳድ የሚያስመስል ቅቤ ለመቀባት ሲጠቅሙ፣ የሕዝቡን ትኩረት ደግሞ ከጭቆና መላቀቅ እሳቤ ጠላትን ወደመከላከል የጋራ ዝንባሌ እንዲያዘምም ያደርጋል፡፡
4). ስታትስቲክ
አንድ አስቂኝ አባባል አለች፡፡ ባለቤቷ ማን እንደሆነ አላውቅም፡፡ ግን የአምባገነኖችን ውሸታምነት ቁልጭ አድርጋ ለማሳየት የተፈጠረች ነች፡፡
“There are three types of lies; lies, damn lies and statistics”“ሦስት አይነት ውሸቶች አሉ፤ ውሸቶች፣ የተረገሙ ውሸቶች እና ስታትስቲክ”
አምባገነኖች በየዓመቱ አገራቸውን እያበለፀጉ እንደሆነ የሚናገሩበት ስታትስቲክ አያጡም፡፡ በስታትስቲካቸው ኢኮኖሚው ያድጋል፤ ሕዝቦች ግን ይራባሉ፣ በጀት ግን ይጎድላል፣ የስራአጦችና የኢኮኖሚ ስደተኞች ቁጥር ግን ይጨምራል፡፡ በርግጥ በአምባገነኖች አገር ውስጥ ጥቂት በሃብት የሚመነደጉ ቡድኖች ይኖራሉ፤ ግን የሃብት ምንጫቸው አይታወቅም፡፡
ሌሎች የመለስ እውነታዎች
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር - መለስ “አምባገነን ናቸው ወይስ አይደሉም?” የሚለው ጥያቄ መልስ ለኔ አነታራኪ አይደለም፡፡ ግን ያሳዝኑኛል፤ ሞክረው፣ ሞክረው ያልተሳካላቸው መሪ ናቸው፡፡ እንደውም አሁን፣ አሁን ስልጣን ላይ በእልህ የተቀመጡት “ቆይ አሁን አንድ አማራጭ ልሞክርና፣ ችሎታዬን አሳያቸዋለሁ” በሚል የዋህ ስሜት ይመስለኛል፡፡ የሆነ ሆኖ ከ20 የሥልጣን ዓመታት በኋላ፣ በአድናቂዎቻቸው እንደ ጂኒየስ የሚቆጠሩት መለስ ያልተሳኩላቸው ጉዳዮች ከተሳኩላቸው ይበልጣሉ፡፡ ኢትዮጵያን ከድህነት ወደብልፅግና፣ ከመሃይምነት ወደ ምሁርነት ብሎም ከእስር ቤት ወደ ነፃ መድረክ መቀየሩ እምብዛም አልሆነላቸውም፡፡
መለስ ካልተሳኩላቸው ነገሮች ውስጥ የሚከተሉት ዛሬ ያስታወስኳቸው ናቸው፡፡
1). ግብርና መር ኢንዱስትሪ
ኢሕአዴግ ገና የቤተመንግስቱን ደጃፍ ከረገጠ ጀምሮ ያቀነቅነው የነበረው የጠቅላይ ሚኒስትሩን የግብርና መር ኢንዱስትሪ ስትራቴጂ ከ20 ዓመታት በኋላ እንኳን ገበሬውን ከበሬ አላላቀቀውም፣ ምርቱም ለምግብ ዋስትና ቀርቶ ለገበሬው አፍም አልበቃም፡፡ ኢንዱስትሪውም በግብርና አልተመራ፡፡ ካለፈው የወደፊቱን መተንበይ ይቻላል ከተባለ፣ የአሁኑ ልማታዊ ነጠላ ዜማም የሚዋጣለት አይመስልም፡፡
2). በቀን ሦስቴ ማብላት
መለስ የስልጣናቸው መባቻ ሰሞን “የኢትዮጵያን ሕዝብ በቀን ሦስቴ” እንደሚያበሉት ተናግረው ነበር፡፡ በቀልድ ‘ቁምሳ’ የሚባል ቁርስና ምሳን የሚያሸጋሽግ፣ 5/11 የተባለ (ቁርስና ምሳን፣ ምሳና ራትን የሚያቀራርብ) ስልት የተጀመረው በእርሳቸው አገዛዝ ዘመን ነው፡፡ ቀልዱ የእውነተኛው ዓለም ነፀብራቅ ነው እንጂ፣ እውነተኛው ዓለም የቀልዱ ነፀብራቅ አይደለም፡፡
3). ምርጫና ዴሞክራሲ
መለስ አምባገነnun የደርግ መንግስት ጥለው ዴሞክራሲያዊ እንደሚሆኑ ቃል ገብተው ነበር፡፡ አልሆነም፡፡ የይስሙላ ሳይሆን “እንከን የሌለበት” ምርጫም እንደሚያካሂዱ ቃል ገብተው ነበር - እሱም አልሆነም፡፡ መጀመሪያ በምርጫ ያሸነፏቸውን አሰሩ፣ የሕዝብን ተቃውሞ በተኩስ ዝም አሰኙ፤ ቆየት ብለው ግን ቅድመ ምርጫ ማዳከም የሚባል ስርዓት አበጁ፡፡ የተቃውሞ ድፍረት ያላቸውን ጋዜጦች ከረቸሙ፣ የመንግስትን ምስጢር የማይጠብቁ ደረዓምባዎችን (websites) ዘጉ – ወዘተርፈ::
4). የባንዲራ ‹‹ጨርቅነት››
አቶ መለስ ሕዝብን የመደለል ጥቅሙ ሳይገባቸው በፊት፣ አዳልጧቸው ከተናገሩት ውስጥ ‘ባንዲራ ጨርቅ ነው፤ እኛ ከባንዲራው በስተጀርባ ስላለው እንጂ…’ ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ይህ አባባላቸው፣ ባንዲራውን እንደማንነቱ መጠሪያ ለሚቆጥረው ኢትዮጵያዊ ግን እስከዛሬም ሳይዋጥለት በመቅረቱ፥ እንደገና የባንዲራ አንጋሽ ሁነው በየዓመቱ ‘የባንዲራ ቀን’ እንዲከበር አዝዘዋል፡፡ “ብልሕ ከሰው ስህተት ይማራል፣ ሞኝ ግን በራሱ ከደረሰበት በኋላ!”
5). የወደብ ‹‹ሸቀጥነት››
አቶ መለስ በጨቅላ የስልጣን ዘመናቸው ሊያሳምኑን የሞከሩት “የባንዲራን ጨርቅነትን” ብቻ አልነበረም፤ “ወደብ ሲያሻን የምንገዛው ሸቀጥ” እንደሆነም ነግረውናል፡፡ ከዓመታት ወደብ አልባነት ተሞክሯችን እንደተረዳነው ግን የአቶ መለስ ኀልዮት ውድቅ ሆኗል፡፡ የወደብ ጉዳይ (ወደ 2% የቀረበ) ዓመታዊ በጀታችንን የሚቀማ፣ የአገሪቱን የውጭ ንግድ የሚቆጣጠር መዘውር ብቻ ሳይሆን የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይም ነው፡፡ ወደብ ለርሳቸው ሲል ሸቀጥ ሊሆንላቸው አለመቻሉ ያሳዝናል፡፡
Comments
Post a Comment