Skip to main content

አድዋን መዘከር፤ በአርበኞቹ መንገድ!


በመጀመሪያ እንዲህ ነበር - የሬይሞንድ ጆናስ ‘The Battle of Adwa” (የሙሉቀን ታሪኩ ትርጉም)፣ ቅድመ አድዋ ላይ የነበረውን የአውሮጳውያን ስሜት ሲገልጽ የአሜሪካኑ አትላንታ ኮንስቲቲውሽን ጋዜጣ የጻፈውን አጣቅሶ ነበር፤
‹‹መላዋ አፍሪካ በአውሮጳ መንግሥታት ቅርምት የምትጠናቀቅበት ቀን ቀርቧል፤ አውሮጳውያኑ በአሜሪካ ያሳኩትን የዘር የበላይነት በአፍሪካ ለመድገም ተዘጋጅተዋል፡፡ በአሜሪካ ቀይ ሕንዶችን በማስወገድ ለራሳቸው ዝርያ መኖሪያ መፍጠር የቻሉበትን ብቃት በአፍሪካ ለመድገም የጥቁር አፍሪካ ዝርያዎችን በቅርቡ ማጥፋት ይጀምራሉ፡፡››
ይህ የአውሮጳውያን ሕልም ቅዠት ሁኖ የቀረው በአድዋ ድል ድባቅ ሲመቱ ጀምሮ ነው፡፡ ይህ የድል በዓል ከየትኞችም የድል በዓላት በላይ ደምቆ ቢከበር አያንስበትም፡፡ ለነገሩ፣ ይህንን በቅጡ የተረዱ እና እውን ለማድረግ የሚፍጨረጨሩ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡

የካቲት 23፣ 1988 በአድዋ ተራሮች በተካሄደው ጦርነት የተደመደመው እና ጥቁሮች በታሪካቸው ለመጀመሪያ ግዜ ነጭ ወራሪን በጦር ሜዳ አሸንፈው የታዩበት ‹‹የአድዋ [ዕ]ድል›› በዓል ዘንድሮ በልዩ ሁኔታ 118ኛውን ልደቱን ያከብራል፡፡ የዘንድሮው አከባበር ለከርሞው እና ለ120ኛው ደማቅ አፍሪካ አቀፍ አከባበር መሠረት ይጥላል ተብሎ ይታሰባል፡፡ በዓሉን ለማድመቅ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ ካሉት ሰዎች በአንዱ የተለመደ አባባል የዚህን ጽሑፍ ዓላማ በመጠየቅ ልጀምር፤ ‹‹በዓሉን ከወትሮው የሚለየው ምንድን ነው? የበዓሉ አከባበር አስተባባሪዎች እነማን ናቸው? በዓሉን በሚያስተባብሩበት ወቅት ምን ፈተና ገጠማቸው?›› ለሚሉትና ሌሎችም ጥያቄዎች መልስ፥ ከአስተባባሪዎቹ አንዱ የሆነውን ያሬድ ሹመቴን ከሚገኝበት አድዋ አካባቢ በስልክ አነጋግሬዋለሁ፡፡ ዝርዝሩን እነሆ፡-

ጉዞ አድዋ

የአድዋ ከተማ ከአዲስ አበባ 1000 ኪሎ ሜትር ይርቃል፡፡ ከጥቂት ፈረሰኞች በቀር አብዛኛዎቹ አርበኞች ጣልያንን ለመግጠም ወደስፍራው የተጓዙት በእግራቸው ነበር፡፡ ያንን የተጋድሎና የነጻነት ጉዞ ከጦርነት ወዲህ ያለውን ለመድገም የተዘጋጁ አምስት ሰዎች ድንኳናቸውን አዝለው በእግር ተጉዘው አድዋ በድሉ መታሰቢያ ዕለት ሊገቡ በማቀድ ጥር 10፣ 2006 ጀምረው እየገሰገሱ ነው፡፡ እነዚህ እግረኞች በኢትዮፒካሊንክ አዘጋጅነቱ የምናውቀው ብርሃኔ ንጉሤን ጨምሮ፣ መሐመድ ካሣ፣ ኤርምያስ ዓለሙ፣ ሙሉጌታ መገርሣ እና ዓለምዘውድ ካሣሁን ናቸው፡፡ በደጀንነት (በማስተባበር) ያሬድ ሹመቴን ጨምሮ ሌሎች ሦስት ሰዎች በመኪና እያጀቧቸው፣ ሒደቱን እየተከታተሉ እና በካሜራ እያስቀሩ ነው፡፡

ያሬድ ሹመቴ የ‹‹ጉዞ አድዋ›› ዓላማ ሁለት ነው ይላል፤ የመጀመሪያው የአድዋ ድልን እና የተከፈለለትን መስዋዕትነት መዘከር ሲሆን፥ ሁለተኛው ይህንን ድንቅ ታሪካዊ ድል እስከ ‹‹ጥምቀት በዓል አከባበር›› የሚደርስ ያለ ደማቅ አከባበር እንዲያገኝ ፈር ለመቅደድ ሲባል የተዘጋጀ ነው፡፡

የ‹‹ጉዞ አድዋ›› አርበኞች መንገዳቸውን ከጀመሩ ዛሬ 41ኛ ቀናቸው ነው፡፡ ጠቅላላ ጉዞው ይፈጃል ተብሎ የተገመተው 43 ቀናት ሲሆን እስካሁን የተጓዙት በታቀደው መሠረት ነው፡፡ በየዕለቱ ከ25 እስከ 30 ኪሜ ድረስ እየተጓዙ ነው፡፡ አጭር የተጓዙበት ዕለት 12 ኪሜ ብቻ የተጓዙበት ዕለት ነው፡፡ ረዥም ጉዟቸው ደግሞ አጭር የተጓዙበትን አራት እጥፍ ይጠጋል፤ 47 ኪሎ ሜትር በአንድ ቀን! ይህንን ጉዞ ያደረጉት ከካራቆሬ እስከ ከሚሴ ድረስ ነበር፡፡

እግረኞቹ የሚያድሩት በአብዛኛው ተሸክመውት በሚዞሩት ድንኳን ውስጥ የሳር ፍራሽ ላይ ነው፡፡ የጉዟቸው የመጀመሪያ ጥቂት ቀናት እና ሌሎችም ጊዜ በተቀባዮች ግብዣ ሆቴል ውስጥ እንዲያርፉ ከተደረጉበት ጊዜያት በቀር በአብዛኛው በየደረሱበት አካባቢ ባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በየድንኳኖቻቸው እና በሳር ፍራሾቻቸው ላይ ነው፡፡

ፈታኝ ሁኔታዎች

ከብርሃኔ ንጉሤ ትዊተር ገጽ የተወሰደ
የ‹‹አድዋ ጉዞ›› የከተማ ኑሮ ለለመዱት ጀብደኛ እግረኞች መንገዱ ጨርቅ አልነበረም፡፡ በተለይ የመጀመሪያዎቹ ቀናት በፈተና የተሞሉ ነበሩ፡፡ ምንም እንኳን ሲነሱ በሐኪም ጤንነታቸው እና የአካል ብቃታቸው ተረጋግጦ ጉዞ ቢጀምሩም፣ ጉዞው እንደተጀመረ የውስጥ እግር እና የጭን መጋጠሚያ መላላጥ ገጥሟቸው ሕመሙን እያቻቻሉ ጉዟቸውን ለመቀጠል ተገድደው ነበር፡፡ በዚያ ላይ የጫማ አለመመቸት ረዘም ያለ ጉዞ ባደረጉ ቁጥር እየጨመረ ሲያሰቃያቸው ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ሰውነታቸው እንግልቱን እየለመደ የአባት አርበኞቻችንን ብቃት ወደመጠጋጋት ደርሰዋል፡፡

ሌላው፣ በጉዟቸው መሐል ጨፋ ሮቢት የተባለ አካባቢ ሲደርሱ (ከአስፋልቱ ወጣ ብለው አርበኞቹ በሚጓዙበት የውስጥ ለውስጥ መንገድ በሚሄዱበት ጊዜ) የአካባቢው ፖሊስ በማስቆም ‹‹ማናችሁ? ምንድን ናችሁ? ወዴት ናችሁ?›› በሚል ለፖሊስ ቃል ሳትሰጡ አትሄዱም በማለት ወደአስፋልት መልሰው ዙሪያ ጥምጥም ሊያስኬዷቸው ከጀመሩ በኋላ፣ ጉዳዩን ሲረዱ ይቅርታ ጠይቀው መልሰው ፈቅደውላቸዋል፡፡ ሌሎችም ቦታዎች ላይ ጉዞውን ጥቂት የሚያንጓትቱ ገጠመኞች አሏቸው፡፡

ስንቃታን በርሃብ

ስንቃታ ከአዲስ አበባ 870 ኪሜ ርቀት ላይ የምትገኝ፣ በጦርነቱ ወቅት ከተለያዩ አካባቢዎች መጥተው የተሰባሰበ አርበኞች ረሃብ የገጠማቸው ስፍራ ነው፡፡ ያንን ታሪካዊ ሰቆቃ ለማሰብ እግረኞቹ ዕለቱን ያለምንም ምግብ ለማሳለፍ ጥረዋል፡፡ ምንም ስንቅ ሳይይዙ ስለተንቀሳቀሱ ከጉዞው ጋር ተያይዞ ድካም እና ረሃብ ሲጠናባቸው ከአካባቢው ነዋሪዎች የምግብ ምፅዋት በመለመን እየበሉ የችግሩን ጥልቀት ለማስታወስ እና ለማሰብ ሞክረዋል፡፡

የጉዞው ፋይዳ

መግቢያችን ላይ ያጣቀስነው መጽሐፍ መደምደሚያው አካባቢ እንዲህ ይላል፤
‹‹ድሉ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን መፃኢ ዕድል የወሰነ ነበር፡፡ በዚህም የአድዋ ጦርነት የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱም በቀጣይ መቶ ዓመታት የአውሮፓ የበላይነት እና አገዛዝ በአፍሪካ አክትሟል፡፡ የዘመናዊት አፍሪካ የሉዓላዊነት መሠረት ድንጋይ የጣለው አድዋ ላይ ነበር፡፡››
የጉዞው ፋይዳ የካቲት 23፣ 2006 ማለዳ 12፡30 ጀምሮ በአድዋ… ሶሎዳ ተራራ ላይ በባንዲራ የመስቀል ደማቅ አከባበር ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ጉዞው አርበኞቹ ያለፉበትን ፈተና ለመረዳት ጥረት በማድረግ ለተከፈለው መስዋትነት የሚገባውን ዋጋ መስጠት ነው፡፡ የተጓዦቹ ዕቅድ የሚቀጥለው ዓመት ከመላው የአገሪቱ ክልሎች የተውጣጡ ሰዎች ከየአካባቢያቸው ተነስተው በተመሳሳይ የእግር መንገድ ተጉዘው አድዋ ላይ እንዲገናኙ እና የበለጠ በድምቀት እንዲከበር፤ ከዚያም 120ኛውን የድሉን በዓል በመላው አፍሪካ በሚደረግ ታላቅ አገር አቋራጭ የእግር ጉዞ አፍሪካዊ አከባበር እንዲጎናፀፍ ልምድ ለመቅሰም እየተደረገ ያለ የሚደነቅ ተግባራዊ ተጋድሎ ነው፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከጥቂት ዓመታት በፊት ተራራው ላይ ይቆማል ተብሎ የነበረውን ግዙፍ ‹ላንድማርክ› በተመለከተ ምን ደረጃ ደርሶ እንደነበር ያሬድ ሹመቴን ጠይቄው ነበር፡፡ ቢዘገይ እንኳን፣እስከ120ኛው በዓል ድረስ እንደሚጠናቀቅ ያለውን መረጃ አጣቅሶ ተስፋ ሰጥቶኛል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

The "Corridor Development" is a Façade of the Prosperity Party

Befekadu Hailu I have seen a news report claiming that 40% of central Addis Ababa will be demolished for the corridor development; I am not able to confirm the validity of the news but it sounds real to me given the size of massive operations in the demolition of old neighborhoods and construction of bike lanes, green areas, and glittering street lights. I like to see some beauty added to my city but cannot help mourning the slow death of it too. Addis Ababa was already in a huge crisis of housing and the demolition of houses is exacerbating it. Apparently, Prime Minister Abiy Ahmed is eager to showcase his vision of prosperity by demonstrating how fast his administration can do magic by beautifying the front sides of the streets with lights, new pavements, and painted fences ("to fake it until he makes it" in my friend's words). Therefore, he and his party do not care about the miserable human stories behind the scenes and they will harass you if you tell it (Azeb Woku...

መጽሐፍ የሚወጣው፣ የተዋነይ ዘ ጎንጅ 5 መሥመር ቅኔ

ጎንጅ ቅኔ ያጠናበት ደብር ሥም ነው። ደብረ ጥበብ ጎንጅ ቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም። ተዋነይ የባለቅኔው ሥም ነው። (የግዕዝ ትርጉሙ "ዋናተኛ" ማለት ነው።) ሊቁ ተዋነይ የልኅቀቱን ያክል እምብዛም አይወራለትም፤ ነገር ግን በዘመኑ ወደር የሌለው ልኂቅ ስለመሆኑ ሥራው ይናገራል። የሕይወት ተፈራ "Mine to Win" የተሰኘ ድርሰት መቼቱን በዐፄ ዮሓንስ ንግሥና ዘመን፣ በጎጃም/ጎንደር የቅኔ መማሪያ ደብሮች ያደረገ ልብወለድ ነው። ልቦለዱ የቅኔ ትምህርት ስርዓትን ያስተዋውቀናል፤ በበኩሌ የቅኔ ትምህርትን እና የቅኔ ሊቃውንት ታላቅነት ቀድሞ ከነበረኝ ግንዛቤ የበለጠ እንዲሆን አድርጎኛል። በተለይ የተዋነይ ዘ ጎንጅ (በውኑ ዓለም የነበረ ባለቅኔ) ተከታይዋ አምስት መሥመር ቅኔ መጽሐፍ የሚወጣት እንደሆነች ልቦለዱ አሳሰበኝ። ወይም በአጭሩ ብዙ ምዕራባውያን ስንት መጽሐፍ የጻፉለት ፍልስፍናን በአምስት መሥመር ይዟል። የቅኔው ትርጓሜ የመጽሐፍ ቅዱስን እና የመጽሐፍ ቅዱሱን ፈጣሪ ኅልውና ይሞግታል። “የአምን ወይገኒ ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ ብዙኃን እንዘ ይገንዩ ይስግዱ ቅድሜሁ ለነጽሮ ዝኒ ነገር እሥራኤል ከመይፍርሑ ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ ወ ፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ።” (ተዋነይ ዘ ጎንጅ። ምንጭ፣ሕይወት ታደሰ ወደአማርኛ የተረጎመችው የሕይወት ተፈራ መጽሐፍ) ትርጉሙን በኋላ እመለስበታለሁ። ስለተዋነይ መጀመሪያ የሰማሁት የበውቀቱ መጽሐፍ ላይ ነበር። እሱም በጨረፍታ - “የሌሊት ዜማዎች” የሚለው ግጥሙ ውስጥ። በውቀቱ ተዋነይን በግጥሙ ግርጌ ማስታወሻው አስተዋውቆን ያልፋል፣ “ተዋነይ በቅኔ ቤት አፈ ታሪክ ሞትን በግዝት ለሰባት ዓመታት ያቆመ ጀግና ነው"። ከዚያ በኋላ፣ አዲስ አድማስ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ተዋነይ የተላከበትን ...

የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ

በፍቃዱ ዘ . ኃይሉ “የአዲስ አበባ ብሔርተኝነት” ቢኖር ኖሮ መሪው ልጅ ሚካኤል ይሆን ነበር። አሁን አሁን እሱ ስለ አዲስ አበባ የዘፈናቸውን ዘፈኖች ቁጥር ራሱ በትክክል መቁጠር ይቸግረኛል። ለአዲስ አበባ ከተዘፈኑ ዘፈኖቹ ውጪም በየዘፈኑ ውስጥ የሚጨማምራቸው መልዕክቶች በራሳቸው መወድሰ አዲስ አበባ ናቸው። ለምሳሌ፣ በቅርቡ በለቀቀው ‘አዲስ አራዳ’ በተሰኘው አልበሙ ውስጥ ‘የድሬ ልጅ’ የሚል ዘፈን አለው። ዘፈኑ የተዘጋጀው ያው የአዲስ አበባ እህት ተደርጋ የምትቆጠረውን ድሬ ዳዋን ለማወደስ ነበር። ልጅ ሚካኤል ግን የአዲስ አበባ ፍቅሩ ያመልጠውና የሚከተለውን ያቀነቅናል፦ “መጣልሽ በሏት፣ ድሬ ድረስ፣  ከአዱ ገነት፣ ከሸገር፣ ከአዲስ ደረሰ፣... የሸገር ልጅ አራዳ ነው፣ ሰው አክባሪ፣ ሰው ወዳዱ፣ ቀላጅና ተረበኛ፣ ፍቅር ይዞ የሚተኛ፣ ‘አለው’ የለ፣ ‘የለው’ የለ፣ ከሁሉ ጋ፣ ግባ ጀባ...፤” ፤ ልጅ ሚካኤል በዚህ አልበሙ ብቻ አዲስ አበባን የሚያውድሰባቸው ሌሎችም ዘፈኖች አሉ፤ ‘ አዲስ አራዳ ’ የሚለው የአልበሙ መጠሪያ እና ‘ሸገር’ የሚሉት ዘፈኖቹ ዋነኞቹ ናቸው። ታዲያ እንዲህ በአዲስ አበባ ፍቅር የሚቃጠለው ልጅ ሚካኤል "ሊነግረን የሚፈልገው ምንድን ነው?" የሚለው ጥያቄ ደጋግሞ ይመጣብኛል። ይህ የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ ምንነትን ለመረዳት የሚጥር ፖለቲካዊ መጣጥፍ ነው። ‘አዲሱ አራዳ’ ማነው? በዚህ ዘፈኑ በብዙዎቻችን ዕድሜ የትዝታ ማኅደር ውስጥ የሚገኙ ነገር ግን በአዲስ አበባ ልማት ሥም የፈረሱ እና እየተረሱ ያሉ ሰፈሮችን ሥም ያነሳሳል። ዘፈኑ በግጥሙም በዜማውም፣ የሐዘን እንጉርጉሮ ያለበት ነው። ምሳሌ እንውሰድ፦ “ጨርሰሽ ስትወጪ ከቡፌ ዳ’ላጋ፣ ጠብቂኝ እንዳልል፣ ቆመሽ መሐሙድ’ጋ፣ አገር ...