Pages

Tuesday, February 25, 2014

ብዙአየሁ “የማ[ላ]ቃትን" ሴት አስናፈቀኝ

"የሚጣፍጥ ሕመም ስሜት ነው፣ ቅር የሚል ደስታ፣
ሙሉው ጎዶሎ ነው ትርጉሙ ትዝታ፤"
ወትሮም፣ እመንገዴ ላይ "ትዝታ" ሙዚቃ የተከፈተ እንደሆን ሁሉም ነገር ቅዝቅዝ፣ ፍዝዝ፣ ድንግዝ ይልብኛል። አረማመዴ፣ የጄ ውዝዋዜ፣ ሁለ ነገሬ ስክን ብሎ ልክ እንደ ዝግታ የተንቀሳቃሽ ምስል እንቅስቀሴ (slow motion) ይሆንብኛል።
"ከኔ አንጀት ይመስል፥ የተሰራው ክሩ
ይረበሻል ሆዴ፥ ሲገረፍ ክራሩ፤"
የላይኞቹን የግጥሙን [የሕዝብ?] ስንኞች ከመስማቴ በፊት የብዙአየሁ 2ተኛው ትራክ የሰጠኝ ስሜት ይህንኑ ነው። መጀመሪያ ላይ ያደመጥኩት ጠዋት፣ ጠዋት ማኪያቶ የምጠጣበት ካፌ ውስጥ ነበር። የዚህ ጽሑፍ ከፊሉ የተጻፈውም እዚያው ነው። ዲጄውም የኔ ዕጣ ሳይገጥመው አይቀርም፤ ይደጋግመዋል። አስተናገጋጆቹም አብረው እያዜሙ ያስተናግዳሉ። በኋላ ላይ ግን በየታክሲው ሁሉ አደምጠው ጀመር።

አሁን በዚሁ ዜማ የተሰየመው 'ሳላይሽ' የተሰኘው ሙሉ አልበም አለኝ፤ ነገር ግን ከዚህንኛው ዘፈን በቀር ትዝ የሚለኝ ሌላ ዘፈን የለም። እርግጥ ዘፈን ሳደምጥ የሆነ ሥራ እየሠራሁ ወይም የሆነ ዐሳብ እያሰብኩ ስለሚሆን ሙሉ ልቤን አልሰጠውም። ልክ እንደዚህኛው ልቤን የሚገዘግዘኝ  ካልመጣ በቀር የሰማሁት ምን እንደሆነ የማወቅ ዕድሉም ላይኖረኝ ይችላል።

ሙዚቃ ለኔ ስሜት ቆስቋሽ ከሆነ አሪፍ ሙዚቃ ነው ማለት ነው። የሚቀሰቅሰው ስሜት የምንም ይሁን፣ የምን በዜማው ሰው ማስቆዘምም ሆነ የሙድ ማፍታታት ማድረግ ከቻለ አለቀ! በእነሰርፀ ፍሬ ስብሐት ግምገማ ግን ከዚህ የተለየ ሊሆን ይችላል።…

ወደተነሳንበት ወግ ስንመለስ ብዙአየሁ እንዲህ ይላል፦
"ተስለሻል እንዴ ባይኔ በመሐሉ፣
አንቺ ብቻ እኮ ነሽ በሚታየኝ ሁሉ፤"
ዓይኔን ጨፍኜ ትታየኛለች እንዴ ብዬ ሳስብ አትታየኝም። ከዚያ ዘፈኑን የወደድኩት በዜማው ውበት እንጂ በገዛ ትዝታዬ አይደለም ብዬ አልኩ፤ ጥያቄው ግን "ትታየኛለች/አትታየኝም" ብዬ ያልኳት በስመ ፆታ ሔዋን ነው ወይስ…? ከዚህ ጥያቄ በኋላ ነው የዚችን ጽሑፍ ርዕስ "የማላውቃትን" ካልኩት በኋላ 'ቃ'ን ለይቼ በሳጥን ቅንፍ ውስጥ ያሰርኳት፤ ብትወጣም ስህተት የለውም እንደማለት።

ግጥም ያለው ዜማ ስንሰማ የምንወደው ግጥሙን ነው ዜማውን የሚለው ጥያቄ ሁሌም እንደፈተነኝ ነው። ብዙ ጊዜ ራሴን፣ ከዘፈን ግጥሞች ጋር አቆራኝቼ አገኘዋለሁ። ለምሳሌ የአብዱ ኪያርን ዜማዎች የምወዳቸው በግጥሞቹ ነው። ግን ደግሞ መልሼ ግጥሞቹን ያለዜማ ስሰማቸው ጣዕም አልባ ይሆኑብኛል። ስለዚህ ዜማ የሚወደደው ከግጥሙ ተጣምሮ ነው ወደሚለው ድምዳሜ ያጠጋጋኛል።
ሙዚቃ በጥቅሉ ባይኖር ኖሮ ዓለማችን የተለየ ማኅበራዊ ገጽታ ይኖራት ነበር ብዬ አምናለሁ። ገጽታው ምን ዓይነት ሊሆን እንደሚችል አልገምትም፤ እኔ ግን የምወደው ዓይነት የሚሆን አይመስለኝም። 

ትዝታ ግን አሁንም ይለያል። ትዝታን የኢትዮጵያውያን typical መለያ አድርጌ እወስደው ነበር። ያለፈ ነገር እንወዳለን። ዛሬ የፈለገ ቢሻል እንኳ "የዛሬን አያርገውና…" ማለታችን አይቀርም፤ "ድሮ ቀረ" ከአፋችን አይጠፋም። ከዛሬ ይልቅ የድሮው ትዝታ ይመስጠናል፣ ልጆቻችንን ዘመናዊ ዥዋዥዌ እያጫወትን የራሳችን የአፈር ሸርተቴ ይናፍቀናል። ተረስቶ እንዲቀር አንፈልግም። የትዝታ ዜማ ነገር ግን አሁንም ይለያል። ሌሎቹ ዓለማት ባይኖራቸው እንጂ ቢኖራቸው ኖሮ እንደሚወዱት አያጠራጥርም። በተለይ ጎልማሳ ለሆነ ሰው፣ ትዝታ ፍቱን መድኃኒት ነው። እንደኛ ሕመሞቹን ያለ ምንም ሥነልቦናዊ ዕርዳታ ለሚያክም ሰው፣ የትዝታ ዜማ ከሙድ አራቂነትም በላይ ነው። ለዚህም ነው የትዝታ ንጉሡ ማሕሙድ 'መዝገበ ቃላቱ ትዝታ ባይኖር ኖሮ የፍቅር ዕድሜው ያጥር ነበር' ያለን በዜማው።

በቃ የብዙአየሁ ዜማ ማለት ከላይ የቀባጠርኩትን ሁሉ የሚያስቀባጥር ነው።

No comments:

Post a Comment