Pages

Saturday, February 8, 2014

መታወቂያዬ ላይ “ኢትዮጵያዊ" ተብሎ እንዲጻፍ እፈልጋለሁ

ራስን "ኢትዮጵያዊ" ብሎ መጥራት ነውር እንዲመስል ጠንክረው የሚሠሩ አሉ። አልተሳካላቸውም ብዬ አልዋሽም። ምክንያታቸው እስከዛሬ የነበረው ኢትዮጵያዊነት አማራ ለበስ ነው፤ የዘውግ ብሔርተኝነት አንጂ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት (ማንነት) ብሎ ነገር የለም የሚለው ነው። መነሻ ነጥቡ እውነት ላይ ቆሞ፣ መድረሻው ግን ተራ ድምዳሜ ነው። በዘመን ጥፋት ዘንድሮን መቅጣት! እርግጥ ብዙኃን ኢትዮጵያውያን ዘውጋቸውን የሚያስቀድሙ ብሔረተኞች ሊሆኑ ይችላሉ። እኔንና መሰሎቼን ግን እነሱ ሸንጎ በሉት ጨፌ ውስጥ አስገድዶ የመክተት ወንጀል ነው። የራስን ማንነት በዘውግ ብሔር መግለጽ መብትም ምርጫም የሆነውን ያክል በኢትዮጵያዊነት መግለጽም ነውር ሊደረግ አይገባውም።

እኔን እንደ ምሳሌ

እኔ ባጋጣሚ ከተውጣጡ ብሔሮች ነው የተወለድኩት። ያደግኩትም ከዚያ በበለጠ አካባቢ በመጡ ቤተሰቦች መሐል ነው። የአብሮ አደግ ጎረቤቶቼ ቤተሰቦች ሙስሊም ጉራጌዎች፣ ወሎዬ ሙስሊሞች፣ ክርስቲያን የወለጋ ኦሮሞዎች፣ ትግሬዎች… ናቸው። ልጅ እያለን ማን "ምን" እንደሆነ ትዝ ብሎን አያውቅም። ስናድግ ግን ስለዘውግ ማንነቶቻችን እንድንማር ብቻ ሳይሆን አንዱን እንድንመርጥ ተገደድን። (መማሩን ወደን መገደዱን ግን ከመጥላት ሌላ አማራጭ የለንም።)

ሁሉንም በቅጡ አልችላቸውም እንጂ የአማርኛም፣ ኦሮምኛም፣ ሶማልኛም፣ ትግርኛም፣ ጉራግኛም… ዘፈኖች ስሰማ ባለሁበት በስሜት እወዘወዛለሁ፤ በፍቅር የምበላቸው ምግቦች (ኪሴ ሁሌም አይፈቅድልኝም እንጂ) ክትፎ፣ ጨጨብሳ፣ (እና በተውሶ ፒዛ እና በርገር ሳይቀሩ) ናቸው። አክሱም፣ ላሊበላ፣ ጅማ፣ ጎንደር፣ ሐረርን የጎበኘሁት እና ሌሎችንም ልጎበኝ ቀናት የምቆጥረው የራሴ የሚል ውስጣዊ ስሜት ስላለኝ ነው። ለጉዞ ስወጣ "የእነርሱን ልጎብኝ" አልልም፤ "የአገሬን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ልጎብኝ" ብዬ ነው። ከኢትዮጵያ መውጣት የማልፈልገው እንደኢትዮጵያ የሚመጥነኝ እና የምመጥነው (fit የማደርግበት) ስፍራ እንደሌለኝ ስለማምን ነው። ልዩነታችን ጌጤ ነው። እኔ የሁሉም፣ ሁሉም የኔ ናቸው ብዬ ከልቤ አምናለሁ።

ነገር ግን ለፖለቲካ ግብአት ሲባል ኢትዮጵያዊ ማንነት ብሎ ነገር የለም አንዱን ማንነት ምረጥ ስባል ያመኛል። እንዳጋጣሚ በቤተሰቦቼ ካገኘሁት የዘውግ ማንነቶች ውስጥ የቱን ነው የምመርጠው? ካሳደጉኝ ጎረቤቶቼ የወረስኩትን ማንነትስ ለምን እቀማለሁ? አማራው ማንነቴስ? ኦሮሞው ማንነቴስ? ጉራጌው፣ ትግሬው፣… ማንነቴስ? ከድምር እኔነቴ አንዱን ብቻ መርጬ እኔ እንትን ነኝ አልልም፤ ነጠላ ማንነቶቼን በተናጠል አልወዳቸውም። ከድምሩ አንዱ ሲጎድል ያመኛል። ድምሩ ማንነቴ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ነው።

ኢትዮጵያዊነት እንደገና ይጤን

በታሪክ ሒደት ተጠቃሚ የነበሩ የዘውግ ማንነቶች አሉ። በተለይ አማርኛ ተናጋሪዎች (አማራዎች) ግምባር ቀደሞቹ ናቸው። ይህን መነሻ ይዘው ኢትዮጵያዊነትን ከአማራነት ጋር ቀላቅለው የሚደመድሙ ግን የራሳቸውን ትርጉም ይገምግሙ። የኔ ኢትዮጵያዊነት ግን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ካርታ የታቀፉ ማንነቶችን ሁሉ ያቀፈ፣ የሚያስተናግድ እና የሚያከብር ኢትዮጵያዊነት ነው።
ይህ ማለት ግን፣ አንድ ሰው አንድ ቋንቋ ብቻ ተናጋሪ በመሆኑ፣ የሚያውቀው ባሕልም የዚያን ዘውግ ብሔር ብቻ መሆኑ ኢትዮጵያዊ አያደርገውም ማለት አይደለም። ሙሉ ኢትዮጵያዊ ነው። ኢትዮጵያዊነት የሁሉም ነው። ነገር ግን ራሱን በዚያ የዘውግ ብሔር ማንነት ለመግለፅ ከፈለገ መብቱ ነው። የዘውጉ ብሔር ኢትዮጵያዊነት በሕግም (እንበል ከየትኛውም የአፍሪካ አገራት በረዘመ) የታሪክ ዕድሜም የፀደቀ ነው። ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒ ላንዱ የዘውግ ብሔር የተለየ ውስጠኝነት (belonging) የማይሰማው ሰውም ኢትዮጵያዊ ማንነቱን መነፈግ የለበትም።

ባለኝ መረጃ፣ መታወቂያ ላይ ብሔር የሚጻፈው አዲስ አበባ ብቻ ነው። እንዳጋጣሚ ደግሞ ከዘውግ ብሔርተኝነት ይልቅ ኢትዮጵያዊነትን የሚመርጠው የአዲስ አበባ እና የሌሎችም ከተሞች ነዋሪ የሆነው ሕዝብ ነው። አንድ ሰው ቀበሌ ሄዶ "እኔ ኦሮሞም፣ አማራም፣ ሶማሌም… አይደለሁ፤ ብሔር የሚለው ላይ ኢትዮጵያዊ ተብሎ ይጻፍልኝ" ብሎ ቢሟገት ፖለቲካዊ ወንጀል እንደሠራ ተቆጥሮ ስሙ በጥቁር መዝገብ ይሰፍራል። መታወቂያውን ሊከለከል ወይም ቤተሰብ ካለው የአንዱን በውርስ ተለጥፎ በግድ ሊሰጠው ይችላል። ይህ ጭቆና ነው።

ብዙዎች "ኢትዮጵያዊነት" በሚሉ የሚነሱ ጥያቄዎችን ሁሉ የሚያቀርቡት በፌዴራሊዝሙ እንደተሰነዘረ ጥቃት አስመስለው ነው። እንደዚያ የምር ማመናቸውን ግን እጠራጠራለሁ። እኔ ፌዴራሊዝሙ ላይ ከጥቃቅን ማስተካከያዎች በቀር ችግር የለብኝም። በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር አስፈላጊ ነው ከሚሉትም ወገን ነኝ። ይህ ሁሉ "ኢትዮጵያዊነት" እንዲያብብ እንጂ አንዲጠወልግ አያደርገውም። ኢትዮጵያዊነትን የሚያጠወልገው የዘውግ ብሔረተኞች የከረረ ጥላቻ እና የተዛባ፣ ያልታረመ የኢትዮጵያዊነት ፍቺ ነው።

ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ የየትኛውም የዘውግ ብሔር ሙሉ አድርጎ አይገልጸኝም። ስለዚህ መታወቂያዬ ላይ "ኢትዮጵያዊ" ተብሎ ይጻፍልኝ።

No comments:

Post a Comment