Pages

Tuesday, March 20, 2012

ሕዝቦች ግለሰብን ይጨቁናሉ!

From አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

ሕዝባዊ እሳቤ (popular imagination?) ስለሚባል ነገር ልናወራ ነው፡፡ የሰው ልጅ ሐሳብ ልክ በኖረበትና ባለፈበት ሕዝብ የአስተሳሰብ አድማስ የተቀነበበ ነው፡፡ ቢሆንም ግለሰቦች የረቀቁ የሕዝብ ቅንጣቶች ናቸው፤ ከሕዝባዊ አስተሳሰብ ሊያመልጡ ይችላሉ፡፡ በዘመነ ሉላዊነት (globalization) ደግሞ የግለሰቦች ለመረጃ ተዳራሽነት ከሕዝቦች ይቀድማል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በሐሳብ ሲያፈነግጡ ግን ሐሳባቸው በሕዝቦች ሐሳብ ይጨቆናል፡፡

ሕዝብ ባሕል እና እሴት የሚባሉ ያልተጻፉ ባሕረመዝገቦች አሉት፡፡ እነዚህ ባሕረመዝገቦች ትክክል፣ ተገቢና ነውር የሆኑና ያልሆኑ ነገሮች በዘልማድ ይደነግጋሉ፡፡ የሕዝቡ አባል የሆኑ ግለሰቦች ሁለት ፈተናዎች አሉባቸው፡፡ አንደኛ፤ በዚህ የአስተሳሰብ ቅርጫት ታቅፈው፣ ከቅርጫቱ አሻግረው ማሰብ የሚችሉበት ዕድላቸው ጠባብ ነው፡፡ እነዚህኞቹ ፈተና ውስጥ ቢሆኑም ፈተና ውስጥ መሆናቸውን ሳያውቁ፣ እዚያው የተፈጠሩበት እንቁላል ውስጥ (ቅርፊቱን ሰብረው ውጪውን ዓለም ለማየት ሳይታደሉ) ያልፋሉ፡፡ ሁለተኛ፤ የእንቁላሉን ቅርፊት ሰብረው ለመውጣት አጋጣሚ ያደላቸውም ቢሆኑ እንቁላሉ ውስጥ ካሉ ሰዎች’ጋ አብረው የመኖር ዕድላቸው የዚያን ጊዜ ያከትማል፤ አንድም ሐሳባቸውን በመናገራቸው ከሕዝባቸው ይነጠላሉ፣ አሊያም ሐሳባቸውን አፍነው በልብ ሳይሆን በአካል ብቻ ከሕዝቦቻቸው’ጋ ይኖራሉ፡፡

የተማረና ያልተማረ፣ ሃብታም እና ድሃ፣ የሰለጠነ እና ያልሰለጠነ ዓለምን ብናወዳድር የተማረ፣ ሃብታም እና የሰለጠነ የሚባሉት ምድቦች ውስጥ ጥቂቶችን ብቻ እናገኛለን፡፡ እነዚህ ጥቂቶች (አጋጣሚ የረዳቸው ቢኖሩም እንኳን) ባብዛኛው ጥረት (ድካም) ያፈራቸው ናቸው፡፡ ሕዝብ ብዙሃኑን ይወክላልና የተማረ፣ ሃብታምና የሰለጠነ የሚባለው ምድብ ውስጥ ያሉት ጥቂት ሰዎች ደግሞ ያልተማረ፣ ድሃና ያልሰለጠነውን ሕዝብ ኑሮ እንዲኖሩ ይገደዳሉ፡፡ ማስገደጃው ደግሞ ‘moral’ (‘ስነምግባር’ እንበለው?) የሚባል ነገር ነው፡፡ ታላቁ መንግስተ ስነምግባር ደግሞ ሃይማኖት ይባላል፡፡ ሰዎች ከሞራል አንግል የሃይማኖትን በጎ ነገር ብቻ መመልከት ቢችሉም (ቢፈልጉም፤) ሃይማኖት የግለሰቦችን የሐሳብ አድማስ በመስበር የሚጫወተውን ሚና እውነትነት አያስክደውም፡፡

Moral (ስነምግባር) ብዙሐኑ ተጎጂ አናሳውን ተጠቃሚ የሚያስርበት ገመድ ነው፡፡ ይሉኝታ መፍጠሪያ መንገድ ነው ልንለውም እንችላለን፡፡ የቴዲ አፍሮ አድናቂዎች የሚበዙበት አገር ውስጥ ሆኖ ‹ቴዲ አፍሮ ከቴዎድሮስ ታደሰ ዜማ ቆንጥሮ ወስዷል፤› ብሎ መናገር፣ ወይም በሃይማኖተኞች አገር ውስጥ እየኖሩ ‹ሃይማኖት ሰዎች ከፍርሃታቸው የሚሸሹበት ተቋም ነው፤› ብሎ መናገር፣ ወይም በድሆች አገር ውስጥ እየኖሩ ‹ድህነት የሰነፎች/ያላዋቂዎች እርሻ ነው፤› ብሎ ማለት ያስቀስፋል፣ ያስገልላል፣ ያስወግዛል፡፡

ብዙ ሰው ስለሚወደው/ስለሚያደንቀው ‹ቴዲ አፍሮ ዜማ አይሰርቅም›፣ ብዙ ሰው ስለሚያምንበት ‹ሃይማኖት አማራጭ የሌለው የሕይወት መንገድ ነው›፣ ብዙ ሰው ድሃ ስለሆነ ‹ሃብታም ሆኖ ድሃን አለመመጽወት ስህተት ነው› ብሎ መደምደም ነው ‹ሕዝቦችን የግለሰቦች ጨቋኝ› የሚያሰኘው፡፡

‹የሰለጠኑ› ለሚለው ብያኔ ማስቀመጥ ቢከብደም፣ ሁላችንም ሊገባን በሚችለው ልክ በተለይ ‹ያልሰለጠኑ› ሕዝቦች  አዲስ ሐሳብ ለማስተናገድ ዝግጁነቱም/አቅሙም የላቸውም፡፡ ‘ብዙሐኑ የሚስማማበት ብቻ እውነት ነው፤ ሌላው ሁሉ ስህተት ነው’ የሚል አቋም በማወቅም፣ ባለማወቅም ያራምዳሉ፡፡ ብዙሐኑ የብዙሐኑ እሳቤ ሰለባ ነው ማለት ይሄው ነው፡፡ ጥቂቶች ብቻ ያንን የአስተሳሰብ ቀንበር ሰብረው ይወጣሉ፡፡ ሰብረው የወጡት ጥቂቶች ራሳቸውን እና ሐሳባቸውን መግለፅ የሚችሉት ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህኞቹ ከጥቂትነት ወደብዙነት እስኪሸጋገሩ ብዙሐኑ መሳሳታቸውን ወይም እብደታቸውን አረጋግጦ ይኖራል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ በግፍ ተሰቀለ፣ ሶቅራጠስ በሔምሎክ ተገደለ፤ አንድ ዓይነት ድራማ፡፡ ሁለቱንም ያፈራቸው ሕዝብ አልተቀበላቸውም፡፡ ምክንያቱም የወቅቱን ሕዝባዊ አስተሳሰብ ቀንበር ሰብረዋልና፣ ሰብረውም ዝም ማለት አልቻሉምና፡፡ ከሞታቸው በኋላ ግን አስተሳሰባቸው ዘመናት ተሻግሮ ሕዝባዊ አስተሳሰብ ለመሆን በቅቷል፡፡ በተራው የሌሎች፣ የዚህ ዘመን ግለሰብ (በእኔ አስተያየት የመጪው ዘመን ግን ሕዝቦችን) አስተሳሰብ የሚጨቁን ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው ሐሳብ ሆኗል፡፡

ይህንን ሐሳባዊ ሐረግ ተከትለን ስናቆለቁል፣ አንድ ሐቅ ላይ እንደርሳለን፡፡ “ነብይ ባገሩ አይከበርም፤” (ማቴ. 13÷ 57) ‘ነቢይ በገዛ ዘመኑ አይከበርም’ ብንለውም ያው ነው፡፡ ቢሆንም ግን ይወለዳል - ነብይ መውለድ የሚችል ሕዝብ ካለ! የሐሳብ አፈንጋጮችን መፍጠር የሚችል ሕዝባዊ አስተሳሰብ ያለው ሕዝብ ከሌለ ግን አዲስ ነገርም ሆነ ሐሳብ ፈጣሪ ግለሰቦች አይኖሩም፡፡

የዚህ ውጤት ነው ሕገ መንግስታችን ላይ የሚንፀባረቀው “ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” ብሎ ጭጭ! ግለሰብ የት ነው ሃገሩ?

No comments:

Post a Comment