Skip to main content

የመለስ ፖለቲካ እና የኢትዮጵያ አበሳ ባሳለፍነው 20 ዓመት

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ መንግስት፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምናምን ማለት እየደበረኝ ነው፡፡ ምክንያቱም ለ20 ዓመታት ሲገዙ የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ የሁሉም ነገር ፈጣሪና ፈላጭ ቆራጭ ናቸው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ከተባለ እኛንም ስለሚወክል፤ የመለስ ማለትን መርጫለሁ፡፡ “Power corrupts; absolute power corrupts absolutely” (ስልጣን ያበላሻል፤ ፍፁም ስልጣን ደግሞ ፈፅሞ ያበላሻል) እንዲሉ የአቶ መለስ ስልጣን እንዳበላሻቸው ከመናገር አልቆጠብም፡፡ አቶ መለስ ግን ተበላሽተው አልቀሩም ያበላሹት ብዙ ጉዳይም አለ፡፡ ለምሳሌ የሚከተሉት፡-



የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ
አንድ አገር የነበሩት ኢትዮጵያና ኤርትራ በመለስ ድጋፍ ኤርትራ ስትገነጠል ሁለት ሆኑ፡፡ ወዲያውም በፍቅር ማሽቃበጥ ጀመሩ፡፡ ፍቅራቸው ግን ብዙ አልዘለቀም፤ ከሸፈ፡፡ ጦርነቱ የድሃዋን አገራችንን ብዙ ገንዘብና ብዙ ምስኪን ዜጎች ሕይወት ነጠቀ፡፡ ምን ዋጋ አለው? ተወረረብን የተባለውን መሬት በገንዘብና በደም ማስመለስ ለአቶ መለስ አልተቻላቸውም፡፡ የሔጉ ፍርድ ቤት ውሳኔ የመለስ ፖለቲካ አንዱ ውድቀት ነው፡፡
  
የጎሳ ፌዴራሊዝም  
የመለስ ፖለቲካ ያመጣው የጎሳ ፌዴራሊዝም መልካም ገጽታ የሚታየው በኢቴቪ ብቻ ነው፡፡ ከኢሕአዴግ ዘመን በኋላ ብሔር መጠያየቅ (ጠ ይጠብቃል) እና በብሔር ማሰብ ብርቅ አይደለም፡፡ ብሔር በመታወቂያ ላይ ሳይቀር የዜግነትን ቦታ ወስዷል፡፡ ትልልቅ የመንግስት ወንበሮችን የያዙት ሰዎች ብሔርም ዝነኛ እና የተለየ ክብር አለው፡፡ ወዘተርፈ፡፡ ከዚህ የዘር አስተሳሰብ አባዜ ተከትሎ ብዙ የጎሳ ግጭቶች ተቀስቅሰዋል፡፡ ለምሳሌ በጋምቤላ ክልል በተነሳ የጎሣ ግጭት በአንድ ቀን ብቻ 61 አኙዋኮች ተገድለዋል፡፡ በዚህ ግድያ የመንግስት እጅ እንዳለበት ዓለምአቀፍ ተሰሚነት ያላቸው የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች አረጋግጠዋል፤ ለምሳሌ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፡፡ የመለስ መንግስት ይህን አስተባብሏል፡፡

ድኅረ ምርጫ 97
ከምርጫ ዘጠና ሰባት በኋላ በተነሳው አመፅ ላይ የአቶ መለስ መንግስት ባመነው ብቻ 193 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ የምርጫ 97ን ነገር ማስታወስ ለብዙዎቻችን የተዳፈነ ቁስል መቀስቀስ ነው፡፡ ግን አሁን ያን ዓይነት ዕድል ለመፍጠር በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም የፖለቲካ ምሕዳሩ ጠቧል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የገዢው ፓርቲ አጫፋሪ ከመሆን የተሻገረ ዕድል አይሰጣቸውም፡፡ የተቃውሞ ሰልፍ ማድረግ በአዋጅ ሳይከለከል ተከልክሏል፡፡ መንግስትን በፅሁፍ መተቸት ራስን ለአደጋ ማጋለጥ ሁኗል፡፡ ይሄ ሁሉ መለስ አመጣሽ ፖለቲካ ነው፡፡ እነርሱ ታግለንለታል የሚሉት ስልጣንን የሕዝብ ማድረግ ዘበት ነው ብሏል ሕዝቡ፡፡ ለነገሩ የስልጣን ነገር እንኳን ለቀሪው ሕዝብ አብረው ለታገሉት ራሱ አይቀመሴ ሆኗል፡፡ አሁን ሕዝቡ ለውጥ በምርጫ እንደማይመጣ ታውቆት ለውጥ የሚመጣው በነውጥ እና በነፍጥ ነው የሚል ልባዊ አቋም ይዟል፡፡ የድኅረ ምርጫ 97 አሩር ውል እያለበት አይደፍርም እንጂ፡፡

እስር
ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማሰር ለአቶ መለስ መንግስት ከባድ ጉዳይ አይደለም፡፡ ወ/ሪት ብርቱካን አቶ ስዬን እንዲፈቱ ፈርዳላቸው ስታበቃ እዚያው በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ራሷ ብርቱካን ታስራ በነበረችበት ወቅት በዘመድ አዝማድ የመጠየቅ መብቷን ተከራክራ ካስመሰከረች በኋላ ማረሚያ ቤቱ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ በተግባር ሽሮታል፡፡ አሁን፣ አሁን ግን ፍርድ ቤቱ ራሱ የአቶ መለስ መንግስት ታዛዥ እንጂ የሕግ ተገዢ አይደለም፡፡ በየጊዜው የፖለቲካ እስረኞች በየእስር ቤቱ ይታጎራሉ፤ አንዳቸውም ግን የፖለቲካ እስረኛ እንዳልሆኑ የኢሕአዴግ ልሳን በሆነው ኢቴቪ ይነገራል፡፡ ሃገርን በመክዳት በሉት፤ በማሸበር፣ ለጥፋት በማነሳሳት የሚል ባጅ ይለጥፍባቸዋል፡፡የዚህና መሰል የመለስ ፖለቲካ ብዙዎችን ፖለቲካ በኢትዮጵያ ከኤሌክትሪክም የከፋ እንደሆነ እንዲያስቡ አድርጓቸዋል፡፡ ለምሳሌ እኔ በምፅፋቸው የተቃውሞ እና የብሶት ሐሳቦችን በመፍራት ሳይቀር የኔ የፌስቡክ ጓደኛ መሆን የማይፈልጉ ጓደኞች አሉኝ፤ አስተያየታቸውን ማስፈር የሚያሸብራቸውማ ብዙዎች ናቸው፡፡ እንዲያውም ብዙዎቹ እንዳልታሰር ከፈለግኩ አርፌ እንድቀመጥ ይመክሩኛል፡፡ ተቃውሞ ያሳስራል የሚል እምነት ነግሷል፡፡ በርግጥ በተግባርም እየታየ ነው፡፡

የኑሮ ውድነትን እና ረሃብን የማጥፋት ጉዳይ
መለስ የኢትዮጵያን ሕዝብ በቀን ሦስቴ እንደሚያበሉ ቃል ገብተው ነበር፡፡ አልተሳካም፡፡ የከተማውን ሕዝብ የኑሮ ውድነቱ የገጠሩን ሕዝብ ደግሞ ድርቅ ለረሃብ እያጋለጡት ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱ በየዕለቱ እያደገ ነው፡፡ የሚራበው ሰው ቁጥር በየአመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር እንደሆነ መንግስታቸው አይክድም፡፡ ኢንዱስትሪውን ይመራል የተባለው ግብርና እስካሁን ከገበሬውና ከበሬው ጫንቃ ላይ አልወረደም፡፡ የኑሮ ውድነቱን ለመቆጣጠር የአቶ መለስ መንግስት የሚወስዳቸው ርምጃዎች ሁሉ እየወደቁ ነው፡፡ ይሄ ግን መንግስታቸውን ከጉሮሮአችን ሳይቀር እየነጠቀ ተእታ (VAT) ከመውሰድ አላገደውም፡፡

የአሸባሪነት ሕግ
የመለስ ፖለቲካ በኢሳያስ መንግስት ላይ መጨከን አይደፍርም፡፡ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅትም ቢሆን የስዬን አቋም ወስደው የራሳቸው እንዳደረጉት በተስፋዬ ገብረአብ ‹‹የደራሲው ማስታወሻ›› ላይ አንብበናል፡፡ የኢሳያስን መንግስት ለመገልበጥ ከየመን ወደቀይ ባሕር ሊሻገር የነበረ መሳሪያም እንዲያዝ ያደረጉት መለስ እንደሆኑ ሰምተናል፡፡ ይሄ የመለስ አቋም በሕወኀት አባላት ሳይቀር አስተችቷቸዋል፡፡ አሁን ደግሞ ‹‹አዲስ አበባን እንደባግዳድ›› ሊያሸብራት ነበር ያሉንን ሻዕቢያን በአሸባሪነት ዝርዝር ውስጥ ሳያካትቱ ደርሶብን የማያውቀውን አልቃይዳን የኢትዮጵያ አሸባሪዎች ብለው ፈረጇቸው፡፡ የፈለጉትን ይበሉ፤ የሆነ ሆኖ ከዚህ አሸባሪዎች ፍረጃ በኋላ እየተንገዳገደች የነበረችውን በፅሁፍ የመታገል መብት ረሽነው መቀመቅ አውርደዋታል፡፡ ይሄ በኔ ዕይታ የመለስ scandal ነው፡፡ ቅሌት ማለት ባማርኛ ይደብራል መሰል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

The "Corridor Development" is a Façade of the Prosperity Party

Befekadu Hailu I have seen a news report claiming that 40% of central Addis Ababa will be demolished for the corridor development; I am not able to confirm the validity of the news but it sounds real to me given the size of massive operations in the demolition of old neighborhoods and construction of bike lanes, green areas, and glittering street lights. I like to see some beauty added to my city but cannot help mourning the slow death of it too. Addis Ababa was already in a huge crisis of housing and the demolition of houses is exacerbating it. Apparently, Prime Minister Abiy Ahmed is eager to showcase his vision of prosperity by demonstrating how fast his administration can do magic by beautifying the front sides of the streets with lights, new pavements, and painted fences ("to fake it until he makes it" in my friend's words). Therefore, he and his party do not care about the miserable human stories behind the scenes and they will harass you if you tell it (Azeb Woku...

መጽሐፍ የሚወጣው፣ የተዋነይ ዘ ጎንጅ 5 መሥመር ቅኔ

ጎንጅ ቅኔ ያጠናበት ደብር ሥም ነው። ደብረ ጥበብ ጎንጅ ቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም። ተዋነይ የባለቅኔው ሥም ነው። (የግዕዝ ትርጉሙ "ዋናተኛ" ማለት ነው።) ሊቁ ተዋነይ የልኅቀቱን ያክል እምብዛም አይወራለትም፤ ነገር ግን በዘመኑ ወደር የሌለው ልኂቅ ስለመሆኑ ሥራው ይናገራል። የሕይወት ተፈራ "Mine to Win" የተሰኘ ድርሰት መቼቱን በዐፄ ዮሓንስ ንግሥና ዘመን፣ በጎጃም/ጎንደር የቅኔ መማሪያ ደብሮች ያደረገ ልብወለድ ነው። ልቦለዱ የቅኔ ትምህርት ስርዓትን ያስተዋውቀናል፤ በበኩሌ የቅኔ ትምህርትን እና የቅኔ ሊቃውንት ታላቅነት ቀድሞ ከነበረኝ ግንዛቤ የበለጠ እንዲሆን አድርጎኛል። በተለይ የተዋነይ ዘ ጎንጅ (በውኑ ዓለም የነበረ ባለቅኔ) ተከታይዋ አምስት መሥመር ቅኔ መጽሐፍ የሚወጣት እንደሆነች ልቦለዱ አሳሰበኝ። ወይም በአጭሩ ብዙ ምዕራባውያን ስንት መጽሐፍ የጻፉለት ፍልስፍናን በአምስት መሥመር ይዟል። የቅኔው ትርጓሜ የመጽሐፍ ቅዱስን እና የመጽሐፍ ቅዱሱን ፈጣሪ ኅልውና ይሞግታል። “የአምን ወይገኒ ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ ብዙኃን እንዘ ይገንዩ ይስግዱ ቅድሜሁ ለነጽሮ ዝኒ ነገር እሥራኤል ከመይፍርሑ ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ ወ ፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ።” (ተዋነይ ዘ ጎንጅ። ምንጭ፣ሕይወት ታደሰ ወደአማርኛ የተረጎመችው የሕይወት ተፈራ መጽሐፍ) ትርጉሙን በኋላ እመለስበታለሁ። ስለተዋነይ መጀመሪያ የሰማሁት የበውቀቱ መጽሐፍ ላይ ነበር። እሱም በጨረፍታ - “የሌሊት ዜማዎች” የሚለው ግጥሙ ውስጥ። በውቀቱ ተዋነይን በግጥሙ ግርጌ ማስታወሻው አስተዋውቆን ያልፋል፣ “ተዋነይ በቅኔ ቤት አፈ ታሪክ ሞትን በግዝት ለሰባት ዓመታት ያቆመ ጀግና ነው"። ከዚያ በኋላ፣ አዲስ አድማስ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ተዋነይ የተላከበትን ...

የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ

በፍቃዱ ዘ . ኃይሉ “የአዲስ አበባ ብሔርተኝነት” ቢኖር ኖሮ መሪው ልጅ ሚካኤል ይሆን ነበር። አሁን አሁን እሱ ስለ አዲስ አበባ የዘፈናቸውን ዘፈኖች ቁጥር ራሱ በትክክል መቁጠር ይቸግረኛል። ለአዲስ አበባ ከተዘፈኑ ዘፈኖቹ ውጪም በየዘፈኑ ውስጥ የሚጨማምራቸው መልዕክቶች በራሳቸው መወድሰ አዲስ አበባ ናቸው። ለምሳሌ፣ በቅርቡ በለቀቀው ‘አዲስ አራዳ’ በተሰኘው አልበሙ ውስጥ ‘የድሬ ልጅ’ የሚል ዘፈን አለው። ዘፈኑ የተዘጋጀው ያው የአዲስ አበባ እህት ተደርጋ የምትቆጠረውን ድሬ ዳዋን ለማወደስ ነበር። ልጅ ሚካኤል ግን የአዲስ አበባ ፍቅሩ ያመልጠውና የሚከተለውን ያቀነቅናል፦ “መጣልሽ በሏት፣ ድሬ ድረስ፣  ከአዱ ገነት፣ ከሸገር፣ ከአዲስ ደረሰ፣... የሸገር ልጅ አራዳ ነው፣ ሰው አክባሪ፣ ሰው ወዳዱ፣ ቀላጅና ተረበኛ፣ ፍቅር ይዞ የሚተኛ፣ ‘አለው’ የለ፣ ‘የለው’ የለ፣ ከሁሉ ጋ፣ ግባ ጀባ...፤” ፤ ልጅ ሚካኤል በዚህ አልበሙ ብቻ አዲስ አበባን የሚያውድሰባቸው ሌሎችም ዘፈኖች አሉ፤ ‘ አዲስ አራዳ ’ የሚለው የአልበሙ መጠሪያ እና ‘ሸገር’ የሚሉት ዘፈኖቹ ዋነኞቹ ናቸው። ታዲያ እንዲህ በአዲስ አበባ ፍቅር የሚቃጠለው ልጅ ሚካኤል "ሊነግረን የሚፈልገው ምንድን ነው?" የሚለው ጥያቄ ደጋግሞ ይመጣብኛል። ይህ የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ ምንነትን ለመረዳት የሚጥር ፖለቲካዊ መጣጥፍ ነው። ‘አዲሱ አራዳ’ ማነው? በዚህ ዘፈኑ በብዙዎቻችን ዕድሜ የትዝታ ማኅደር ውስጥ የሚገኙ ነገር ግን በአዲስ አበባ ልማት ሥም የፈረሱ እና እየተረሱ ያሉ ሰፈሮችን ሥም ያነሳሳል። ዘፈኑ በግጥሙም በዜማውም፣ የሐዘን እንጉርጉሮ ያለበት ነው። ምሳሌ እንውሰድ፦ “ጨርሰሽ ስትወጪ ከቡፌ ዳ’ላጋ፣ ጠብቂኝ እንዳልል፣ ቆመሽ መሐሙድ’ጋ፣ አገር ...