Pages

Saturday, April 30, 2011

ከሠራተኛ፣ ለማኝና ቀማኛ ማነው በላተኛ?


እንዲያው ለመንደርደር ያህል ‹‹ከለማኝና ከቀማኛ የቱ ይሻላል?›› ተብላችሁ ብትጠየቁ መልሳችሁ ምን ይሆናል? ነገሩ ከሁለት መጥፎ ነገሮች የተሻለ መጥፎ መምረጥ ነው፡፡ (የተሻለ መጥፎ ስንል ጉዳቱ ያልከፋ እንደማለት ነው፡፡) ስገምት፥ ብዙዎቻችሁ ለማኝ የምትመርጡ ይመስለኛል፤ ግን ለማኝ ከቀማኛ በምን ይሻላል? ሁለቱም የሰው ገንዘብ ፈላጊዎች አይደሉም?

ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል እንዲሉ፣ አንዴ የታዘብኩትን ላውጋችሁ፡፡ ከእለታት አንድ ቀን፣ ከአንድ ካፍሬተሪያ በረንዳ ላይ ቁጭ ብዬ ማኪያቶ እየጠጣሁ እቆዝም ነበር፡፡ ከፊት ለፊቴ ታክሲ ተራ አለ፡፡ ታክሲው ተራ አካባቢ፥ ከባለታክሲዎቹ ውጪ የዕለት እንጀራቸውን ለማግኘት የሚራወጡ ሦስት ተዋናዮች ነበሩ - ተራ አስከባሪው፣ ለማኝ እና ማስቲካ ቸርቻሪ፡፡
ተራ አስከባሪው በቅፅበት እየመጡ ከሚመለሱት ታክሲዎች የራሱን ቀረጥ ይሰበስባል፣ ለማኙ ከሚዘረጉ በርካታ እጆች ሳንቲም ይለቃቅማል፡፡ ምስኪኑ ማስቲካና ቺብስ አዟሪ ግን ከስንት አንዴ ማስቲካ ገዢ ያገኛል፡፡

ሦስቱንም አሰብኳቸው፡፡ ተራ አስከባሪው ለኔ ቀማኛ ነው፡፡ ግልፅ ያልሆነ ሥራ ሰርቶ ገንዘብ የሚያጋብስ (ንገረኝ ካላችሁ ሥራቸው ገንዘብ መቀበል ነው፤ ልብ ካላችሁ እኮ ተራ አስከባሪዎች ብዙ ጊዜ የሚያስከብሩት ተራ የለም) ለዚህ ነው ተራ አስከባሪዎች ጉልበተኛ መሆን የሚኖርባቸው - አፈንጋጭ ባለታክሲ ሲመጣ ለመደቆስ፡፡

ለማኙ በብዙዎቹ ልብ ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ በኢትዮጵያ፣ አሁንም ድረስ ብዙ ሰዎች ‹ለማኝ› ከማለት ‹የኔ ቢጤ› ማለት ይመርጣሉ፡፡ እኔ በበኩሌ የሰው ገንዘብ እንኳን ለምኜ ልወስድ፥ ተለምኜም ያቅረኛል፤ ስለዚህ በፍፁም ራሴን የለማኝ ቢጤ ብዬ አልጠራም፡፡ ለማኝ በሃገራችን የመንግሥተ ሰማያት መግቢያ ቁልፍ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ በርካታ ሰዎች የትህትናቸውን ጣሪያ ለለማኝ ክብርና ብር በመስጠት ያረጋግጣሉ፡፡ ውጤቱም የሃገሪቱ መለያ እስከመሆን የደረሰ የለማኝ ጋጋታ በየመንገዱ ዳርቻ ፈጥሯል፡፡

ሦስተኛው የማስቲካና ሶፍት ሱቁን ደረቱ ላይ ለጥፎ፥ ከሚመጣው ታክሲ ሁሉ ጋር እየተሯሯጠ ለመቸርቸር የሚታገለው ታዳጊ ነው፡፡ ይሄ ልጅ የሚሸጣቸውን ሸቀጦች የሚያተርፍባቸው ጥቂት ሳንቲሞች ነው፡፡ ያውም ገዢ ከተገኘ፡፡ ብዙዎች ከዚህ ልጅ የማስቲካ ዋጋ ላይ ሳንቲም ለማስቀነስ ይሞክራሉ፤ ከተሳካላቸው ያስቀነሷትን ሳንቲም ለለማኙ ይሰጣሉ፡፡

ሳስበው ቸርቻሪው በመጨረሻ ከተቻለ እንደተራ አስከባሪው ጉልበተኛ፣ ካልሆነ ደግሞ እንደለማኙ ምስኪን ለመሆን አብዝቶ የሚመኝ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም እሱ ተግቶ ሠርቶ ከሚያገኘው የበለጠ እነርሱ ቀምተውና ለምነው ያገኛሉ፡፡ እሱ ሠራተኛ፣ እነርሱ ደግሞ በላተኛ ናቸው፡፡

ይህንን በምሳሌ አነሳሁኝ እንጂ ሃገራችን በየመስኩ በቀማኞችና በለማኞች መወረሯን ዓይናችን ይመሰክራል፡፡ በየሄድንበት ትርጉሙ የማይታወቅ ‹‹የኮቴ›› የሚባል ነገር እንከፍላለን፡፡ ከፊት ለፊታችን የሚዘረጉ እጆችን ለማለፍም ቢሆን ጀባ እንላለን፡፡ በሥራ የሻከሩ እጆችን ግን እንጠየፋለን፡፡ በየት በኩል….?

No comments:

Post a Comment