Skip to main content

ነውርን ማን ፈጠረው?


ሰሞኑን በሞት ስልጣናቸውን ስለለቀቁት ጠቅላይ ሚኒስትር  ያለኝን ትዝታ ‹የመለስ ሁለት መልክ› በሚል ጽፌው ነበር፡፡ ጽሑፉ ውስጥ የመለስ አስተዳደር በተለይ የተመቻቸው የብሔር አባላት እንዳሉ በስም በመጥቀሴ ‹‹ዘረኛ ነህ›› የሚል ብዙ አስተያየት ተሰንዝሮብኛል፡፡ እነሆ ይህ አስተያየትም ይህን ጽሑፍ ወልዷል፡፡ ነውርን ማን ፈጠረው? በመጀመሪያም፡-

ነፃነት እና ልቅነት

ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ለድርድር የማይቀመጡለት አጀንዳ ነው፡፡ ሆኖም ሁሉም ሰው ሐሳቤን በነፃነት የመግለፅ መብቴ በሕግ ተደንግጓል ወይም ተፈጥሮ ያጎናፀፈኝ ነው በማለት እንዳሻው አይናገርም፡፡ በተለይም ሐሳቡ የሚቀርብበት ሚዲየም ሰፊ ሲሆንና ብዙ ተደራሲዎች ሲኖሩት ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ጥንቃቄ የሚያስፈልግበት በርካታ ምክንያቶች አሉ፤ ከነዚህም ውስጥ የሕዝብን አቅጣጫ ላለማሳት፣ መረንነትን ወይም ልቅነትን ላለማስፋፋት እና አሁን ስለሆነው ሳይሆን ነገ እንዲሆን ስለምንፈልገው በመሳሳት (ሳ ላልቶ ይነበብ) ነው፡፡ ሁሉንም በሒደት ወደታች አብራራቸዋለሁ፡፡

‹የሕዝብን አቅጣጫ ላለማሳት› ያልኩት ሐሳባችንን የምንገልጽበት አገባብ (context) ተደራሲያኑ ጋር ሲደርስ ሌላ አንድምታ እንዳይኖረው የሚለውን ነው፡፡ ምናልባትም ያለፈው ጽሑፍ ውስጥ ‹ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት አዲስ አበባ ውስጥ ከተሰሩ ሕንፃዎች መካከል አብዛኛዎቹ የትግራይ ልጆች ንብረት ናቸው› ማለቴ በአንባቢው ዘንድ የትግራይ ልጆች ሁሉ በኢሕአዴግ ስርዓት ተጠቅሟል የሚል ትርጉም ከሰጠ አቅጣጫ አስቷል ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን እኔ በፃፍኩበት መንፈስ የትግራይ ተወላጆች ከኢትዮጵያ ሕዝብ አንፃር ካላቸው ድርሻ (proportion) ጋር ሲወዳደር በስልጣን እና በከተማ ሃብት ይዞታ ላይ ያላቸው ድርሻ ከፍ ያለ ነው የሚል ነው፡፡

ይሄንን እውነታ እንዳላነሳ የሚያስገድደኝ አካል ሊኖር አይችልም፤ የአገላለፁ አቀራረብ ላይ ውይይት ሊደረግ ግን እንደሚችል አልደራደርም፡፡ ይልቁንም ይህንን ጉዳይ የማይወራ ‹‹ነውር›› ነው የሚሉት (የሚያነውሩት) የስርዓቱ ፈጣሪዎች ወይም ተጠቃሚዎች ራሳቸው እንደሆኑም ይሰማኛል፡፡

‹መረንነትን ወይም ልቅነትን ላለማስፋፋት› ያልኩትን በወሲብ እና ወሲብ ነክ ጉዳዮች ብገልፀው ይበልጥ ይብራራልኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ በባሕላችን፣ መወሻሸምም ሆነ ወሲባዊ ውስልትናዎች ዝነኛ ናቸው፡፡ ነገር ግን በጥቅሉ ስለወሲብ ነክ ጉዳዮች በአደባባይ ማውራት ነውር ነው፤ ስለዚህ ስለመፍትሄዎቹ እንኳን ማውራት አልተቻለም፡፡ በመሰረቱ በኔ ሐሳብ፣ ከድርጊቱ የከፋ ወሬ ሊኖር አይችልም፡፡ ነገር ግን የድርጊቱ ፈፃሚዎች እንዲነውር አድርገው ስር አሰድደውታል ስለዚህ አይወራም፡፡ ለምን የሚል ጥያቄ ሲነሳ የሚሰጠው ዘመናዊ ተብዬ መልስ በዚህ ጉዳይ የሚወሩ ጉዳዮች ልቅነትን ወይም መረንነትን ያስከትላሉ ነው፡፡ እንዲህ አድርጉ ሌሎችም እንዲህ እያደረጉ ነው ካላሉ ወይም አደራረጉን የሚያስተዋውቅ ማስታወቂያ ካላወጡ ነውሩ ምኑ ላይ ነው፡፡ ይህ አጀንዳ ባደባባይ ላይ እንዳይውል የሚታገሉት የድርጊቱ ባለቤቶች እና ለውጡ እንዳይመጣ የሚፈልጉት ነውረኞች ራሳቸው ናቸው፡፡

ስለዚህ አስተሳሰቡ ራሱ የተሳሳተ ከሆነ (ከሕዝቦች ሕሊና ውስጥ መኖሩ እሙን ስለሆነ) በትክክለኛው ለማረም፣ አልያም ካልተሳሳተ መፍትሔ ሐሳቦችን ለማፍለቅ ሐሳብን በአግባቡ መግለፅ ሊያስፈርጅ ፈፅሞ አይገባም፡፡

እያስመሰሉ መኖር

ዛሬ የሆነውን እንዳልሆነ እያስመሰሉ መኖር ሕይወታችን ነው - ስለነገ ሲባል፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ የሕግ ስርዓቱ በፓርቲ ቁጥጥር ስር እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ገዢው ፓርቲ ያይናችንን ቀለም ካልወደደው፣ አንዱን የሽብር፣ ወይም የወንጀለኛ አንቀፅ መዝዞ፣ በራሱ ትርጓሜ ተርጉሞ አሊያም ካስፈለገ አዲስ አዋጅ አውጥቶ መቀመቅ ሊያወርደን ይችላል፣ እያደረገውም ነው፡፡ ነገር ግን ነገ ኢትዮጵያ እንዲህ ሆና ትቀጥላለች ብለን አናስብም፡፡ የሕግ የበላይነት ስለሚሰፍንባት የነገዋ ኢትዮጵያ ብለን ሕግ አክብረን እንንቀሳቀሳለን፣ አዋጅ ወይም መመሪያ ሲወጣ እንደማይቀየር እያወቅን ይህ መስተካከል አለበት እያልን እንፅፋለን፣ ምርጫዎች እንደሚጭበረበሩ እያወቅን እንመርጣለን… ሁሉም ዛሬ ስላለው ውሸት ሳይሆን ነገ እውን ትሆናለች ብለን ስለምናስባት ኢትዮጵያ ተብሎ የሚደረግ ማስመሰል ነው፡፡

በጎሳ ጉዳይም ቢሆን እንደዚያው ነው፡፡ እኔ በግሌ በቅጡ የማውቀው ብሔር እንኳን የለኝም፡፡ ነገር ግን በዚህ ስርዓት ውስጥ ግን የየትኛው ብሔር ተወላጆች ፈላጭ ቆራጮች እንደሆኑ አውቃለሁ፣ ማንም ያውቃል፡፡ ይህ ፍትሐዊ ያልሆነ የኃይል እና የሀብት ክፍፍል አገሪቱን እየጎዳት እንደሆነ እያወቅኩ እንኳን ብዙ ጊዜ ዝም ብያለሁ፣ ነገ የማስባት ኢትዮጵያ ሁሉም እኩል እንጂ ‹‹አንዳንዶች የበለጠ እኩል የሚሆኑባት›› አይደለችም፣ ስለዚህ ስለነገዋ ኢትዮጵያዬ ስል የዛሬውን ባልፈው ነገ ይረሳል በሚል ነው፡፡

ይህ ማስመሰል በጎ ቢሆንም፣ እውነቱ መነገሩ ግን ክፉ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ አልደረስኩም፡፡ መወራት አለበት፤ ካላወራነውማ የዛሬው ሲቀየር የነገ ባለተራ ደግሞ የራሱን ዓይነት ‹‹ዛሬ›› ሊደግም የማይችለው እንዴት ነው?

ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ ይህንን ፍትሐዊ ያልሆነ የአንድ ብሔር ተጠቃሚነት መናገር እርስ በእርስ መዘላለፍ የሚያስጀምረን ከሆነ መለስ እውነትም ነፍሱ በሰላም ታርፋለች፡፡ የታገገለት ዘረኝነት ግቡን መትቷል ማለት ነው፡፡

Comments

Popular posts from this blog

The "Corridor Development" is a Façade of the Prosperity Party

Befekadu Hailu I have seen a news report claiming that 40% of central Addis Ababa will be demolished for the corridor development; I am not able to confirm the validity of the news but it sounds real to me given the size of massive operations in the demolition of old neighborhoods and construction of bike lanes, green areas, and glittering street lights. I like to see some beauty added to my city but cannot help mourning the slow death of it too. Addis Ababa was already in a huge crisis of housing and the demolition of houses is exacerbating it. Apparently, Prime Minister Abiy Ahmed is eager to showcase his vision of prosperity by demonstrating how fast his administration can do magic by beautifying the front sides of the streets with lights, new pavements, and painted fences ("to fake it until he makes it" in my friend's words). Therefore, he and his party do not care about the miserable human stories behind the scenes and they will harass you if you tell it (Azeb Woku...

መጽሐፍ የሚወጣው፣ የተዋነይ ዘ ጎንጅ 5 መሥመር ቅኔ

ጎንጅ ቅኔ ያጠናበት ደብር ሥም ነው። ደብረ ጥበብ ጎንጅ ቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም። ተዋነይ የባለቅኔው ሥም ነው። (የግዕዝ ትርጉሙ "ዋናተኛ" ማለት ነው።) ሊቁ ተዋነይ የልኅቀቱን ያክል እምብዛም አይወራለትም፤ ነገር ግን በዘመኑ ወደር የሌለው ልኂቅ ስለመሆኑ ሥራው ይናገራል። የሕይወት ተፈራ "Mine to Win" የተሰኘ ድርሰት መቼቱን በዐፄ ዮሓንስ ንግሥና ዘመን፣ በጎጃም/ጎንደር የቅኔ መማሪያ ደብሮች ያደረገ ልብወለድ ነው። ልቦለዱ የቅኔ ትምህርት ስርዓትን ያስተዋውቀናል፤ በበኩሌ የቅኔ ትምህርትን እና የቅኔ ሊቃውንት ታላቅነት ቀድሞ ከነበረኝ ግንዛቤ የበለጠ እንዲሆን አድርጎኛል። በተለይ የተዋነይ ዘ ጎንጅ (በውኑ ዓለም የነበረ ባለቅኔ) ተከታይዋ አምስት መሥመር ቅኔ መጽሐፍ የሚወጣት እንደሆነች ልቦለዱ አሳሰበኝ። ወይም በአጭሩ ብዙ ምዕራባውያን ስንት መጽሐፍ የጻፉለት ፍልስፍናን በአምስት መሥመር ይዟል። የቅኔው ትርጓሜ የመጽሐፍ ቅዱስን እና የመጽሐፍ ቅዱሱን ፈጣሪ ኅልውና ይሞግታል። “የአምን ወይገኒ ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ ብዙኃን እንዘ ይገንዩ ይስግዱ ቅድሜሁ ለነጽሮ ዝኒ ነገር እሥራኤል ከመይፍርሑ ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ ወ ፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ።” (ተዋነይ ዘ ጎንጅ። ምንጭ፣ሕይወት ታደሰ ወደአማርኛ የተረጎመችው የሕይወት ተፈራ መጽሐፍ) ትርጉሙን በኋላ እመለስበታለሁ። ስለተዋነይ መጀመሪያ የሰማሁት የበውቀቱ መጽሐፍ ላይ ነበር። እሱም በጨረፍታ - “የሌሊት ዜማዎች” የሚለው ግጥሙ ውስጥ። በውቀቱ ተዋነይን በግጥሙ ግርጌ ማስታወሻው አስተዋውቆን ያልፋል፣ “ተዋነይ በቅኔ ቤት አፈ ታሪክ ሞትን በግዝት ለሰባት ዓመታት ያቆመ ጀግና ነው"። ከዚያ በኋላ፣ አዲስ አድማስ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ተዋነይ የተላከበትን ...

የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ

በፍቃዱ ዘ . ኃይሉ “የአዲስ አበባ ብሔርተኝነት” ቢኖር ኖሮ መሪው ልጅ ሚካኤል ይሆን ነበር። አሁን አሁን እሱ ስለ አዲስ አበባ የዘፈናቸውን ዘፈኖች ቁጥር ራሱ በትክክል መቁጠር ይቸግረኛል። ለአዲስ አበባ ከተዘፈኑ ዘፈኖቹ ውጪም በየዘፈኑ ውስጥ የሚጨማምራቸው መልዕክቶች በራሳቸው መወድሰ አዲስ አበባ ናቸው። ለምሳሌ፣ በቅርቡ በለቀቀው ‘አዲስ አራዳ’ በተሰኘው አልበሙ ውስጥ ‘የድሬ ልጅ’ የሚል ዘፈን አለው። ዘፈኑ የተዘጋጀው ያው የአዲስ አበባ እህት ተደርጋ የምትቆጠረውን ድሬ ዳዋን ለማወደስ ነበር። ልጅ ሚካኤል ግን የአዲስ አበባ ፍቅሩ ያመልጠውና የሚከተለውን ያቀነቅናል፦ “መጣልሽ በሏት፣ ድሬ ድረስ፣  ከአዱ ገነት፣ ከሸገር፣ ከአዲስ ደረሰ፣... የሸገር ልጅ አራዳ ነው፣ ሰው አክባሪ፣ ሰው ወዳዱ፣ ቀላጅና ተረበኛ፣ ፍቅር ይዞ የሚተኛ፣ ‘አለው’ የለ፣ ‘የለው’ የለ፣ ከሁሉ ጋ፣ ግባ ጀባ...፤” ፤ ልጅ ሚካኤል በዚህ አልበሙ ብቻ አዲስ አበባን የሚያውድሰባቸው ሌሎችም ዘፈኖች አሉ፤ ‘ አዲስ አራዳ ’ የሚለው የአልበሙ መጠሪያ እና ‘ሸገር’ የሚሉት ዘፈኖቹ ዋነኞቹ ናቸው። ታዲያ እንዲህ በአዲስ አበባ ፍቅር የሚቃጠለው ልጅ ሚካኤል "ሊነግረን የሚፈልገው ምንድን ነው?" የሚለው ጥያቄ ደጋግሞ ይመጣብኛል። ይህ የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ ምንነትን ለመረዳት የሚጥር ፖለቲካዊ መጣጥፍ ነው። ‘አዲሱ አራዳ’ ማነው? በዚህ ዘፈኑ በብዙዎቻችን ዕድሜ የትዝታ ማኅደር ውስጥ የሚገኙ ነገር ግን በአዲስ አበባ ልማት ሥም የፈረሱ እና እየተረሱ ያሉ ሰፈሮችን ሥም ያነሳሳል። ዘፈኑ በግጥሙም በዜማውም፣ የሐዘን እንጉርጉሮ ያለበት ነው። ምሳሌ እንውሰድ፦ “ጨርሰሽ ስትወጪ ከቡፌ ዳ’ላጋ፣ ጠብቂኝ እንዳልል፣ ቆመሽ መሐሙድ’ጋ፣ አገር ...