Pages

Monday, August 20, 2012

ፋጡማ ኖረች አልኖረች፣ ጳጳሱ ኖሩ አልኖሩ…?


አቡነ ጳውሎስን እጅግ በጣም አወዛጋቢ ከሆኑ ኢትዮጵያውያን ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ተርታ እመድባቸዋለሁ፡፡ ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ለክብራቸው የቆመላቸው ሐውልት ሲገነባ አገር ምድሩ ሌላ አጀንዳ አጥቶ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ‹ሰው በቁሙ ለምን ሐውልት ያሰራል?› የተሰኘ ጽሑፍ በአንባቢ ቁጥር ተወዳዳሪ የተገኘለት ባለፈው ሳምንት የታወጀው የሞታቸው ዜና ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ የተቀረጸበት የስነ ምግባር ወግ ሰው ከሞተ በኋላ ማክበር ላይ ስለተመሰረተ፣ ሙት ወቃሽነት ከነውሮች ሁሉ የከፋ ነውር ነው፡፡ ስለዚህ ሰሞኑን የማይወዷቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ ምዕመናን ሳይቀሩ ‹‹ነፍስ ይማር›› መባባልን እንደትልቅ ቁምነገር፣ በተቃራኒው ደግሞ ‹‹ሞታቸውን እንደመልካም አጋጣሚ›› የሚቆጥሩትን እንደ አጥፊ በመታዘብ ላይ ናቸው፡፡ እኔም በበኩሌ ስለአቡኑ አወዛጋቢ ዐበይት የታሪክ ትውስታዎች ከአወራሁ በኋላ፣ ሃይማኖተኛ ባልሆንም ስለ‹በሰላም ይረፉ ማለት ማንን ገደለ?› ለሚለው ጥያቄ የራሴን እምቢታ ለመስጠት በዚህ ጽሑፍ መጥቻለሁ፡፡

ማዕረጋቸው አንድ አንቀጽ የሚደርስላቸው አቡነ ጳውሎስ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ውጪ ላሉት ሁሉ የተመቹ ነበሩ፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ አማኞች ዘንድ ግን መልካም ስም የላቸውም፡፡ የስማቸው መበላሸት የሚጀምረው ደግሞ ወደ መንበረ ጵጵስናው የመጡበት መንገድ ላይ ይጀምራል፡፡

ጳጳሱ እንደአብዛኛዎቹ የፖለቲካ መሪዎቻችን ሁሉ፣ ከትግራይ ክልል ያውም ከአድዋ ነው የፈለቁት፡፡ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን በተቆጣጠረ በዓመቱ፣ አቡነ መርቆርዮስ ተሰድደው እርሳቸው ጳጳስ ለመሆን በቁ፡፡ ከዚያ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ከየትኛውም ቤተ ሃይማኖት የበለጠ መስዋእትነት ስትከፍል ነበር፡፡ Haustein & Østebø የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ቁጥር በኢትዮጵያ ከ54 በመቶ ወደ 43.5 በመቶ የወረደው በኢሕአዴግ ወይም በአቡነ ጳውሎስ ዘመን እንደሆነ ይነግሩናል፡፡

አቡነ ጳውሎስ በ1993 ተነስቶ በነበረው የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች አመጽ ወቅት የፌዴራል ፖሊሶችን ቆመጥ ሸሽተው ወደ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በመግባት ለመሸሸግ የሞከሩ ምዕመኖቻቸውን እንደወንጀለኛ አሳልፈው በመስጠት አሳፍረዋቸዋል፡፡ በመሰረቱ፣ በአንደበተ ርቱዕነታቸው እና በሰበካ ችሎታቸው የማይታሙት አቡን ምዕመኖቹ ወንጀለኞች ቢሆኑ እንኳን በሚሰብኩት ትምህርት መሰረት ለንስሐ ማብቃት እንጂ ለሌላ ‹ደብዳቢ› ወንጀለኛ አሳልፈው መስጠት አልነበረባቸውም፡፡ እንዲሰብኩ በተሾሙበት እምነት ውስጥ በቅጽበታዊ ንስሐ ብቻ ‹‹እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከኔ ጋር በገነት ትሆናለህ›› (ሉቃስ 23፡43) እንደሚባል ዘንግተውታል የሚል እምነት የለኝም - የሚበልጥባቸውን መርጠው እንጂ፡፡

በአቡነ ጳውሎስ አስተዳደር ቤተክህነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በሙስና እንደተርመጠመጠች እሙን ነው፡፡ አቡኑም ቢሆኑ በፎር ዊል ድራይቮቻቸው፣ በኩርፍቱ አባልነታቸው እና ከእርሳቸው በፊት ተደርጎ በማይታወቅ ሁኔታ በጠብደል ቦዲጋርዶች ጥበቃ አዝማሚያ የሚነግሩን የሃብታቸውን ብዛትም ጭምር ነው፡፡ ‹‹ቤተ መንግስታቸውም›› ቢሆን የቢሊዬነሮችን ቪላ ይፎካከራል፡፡ ይሄ ብዙም አይከፋም፣ ነገር ግን (እንደ ‹እጅጋየሁ› ባሉ) አገልጋዮቻቸው ስም እራሳቸውን (ልክ እንደጠቅላይ ሚኒስትሩ) ወደተመላኪ ፍጡርነት በመቀየር ሒደት ላይ ሳሉ ነው ሞት የቀደማቸው፡፡

በየቤተ ክርስቲያናቱ ደጃፍ ለመሳለም ማማተብ ስትጀምሩ የርሳቸውን ትልልቅ ፎቶዎች ፊለፊት ማየታችሁ አይቀርም፣ የዛሬ ሁለት ዓመትም በዓለ ሲመታቸወን ለማክበር ቦሌ መድሀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ፊትለፊት የቆመላቸው ሐውልት በ‹‹ዴሞክራሲያዊው›› ሲኖዶስ በ20 ቀን ውስጥ እንዲፈርስ ተፈርዶበት በአስተዳደራቸው ለገምተኝነት እንደቆመ ቀርቷል፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊት በሸራተን አዲስ ሆቴል ያከበሩትም የ20ኛ ዓመት በዓለ ሲመታቸው እንዲሁ አወዛጋቢ ነበር፡፡ ጣሪያቸው የሚያፈስ ቤተመቅደሶች በሞሉባት አገር የጳጳሱን ‹‹ሹመት ያዳብር›› ለመብላት ያንን ሁሉ ገንዘብ ማባከን ከ‹‹ሃይማኖተኛ›› ቀርቶ ከተራ ነጋዴም አይጠበቅም፡፡

የሆነ ሆኖ፣ በድንገት ዜና ሕልፈታቸው ባለፈው ሳምንት ተሰማ፡፡ እሱን ተከትሎ የተዘባረቀ ስሜት በተለይ በማሕበራዊ አውታሮች ዙሪያ ይደመጥ ጀመር፡፡ ብዙዎች ደስታቸውን መደበቅ አልቻሉም፣ ይህም ሃጢያት ሆነ/እንደ ሃጢያት ተቆጠረ፡፡ በመሰረቱ በአቡኑ ሞት መደሰትን እንደስህተት የቆጠሩት ወገኖች መሳሳታቸውን የሚናገሩ ምክንያቶች እንዳሉ ከበርካታ ውይይቶች ውስጥ ነቅሼ አውጥቻለሁ፡፡ እነርሱም፡-
  • በቤተ ክርስቲያን እምነት ሁሉም እርምጃ (ሞትን ጨምሮ)፣ የሚወሰደው በእግዚአብሔር ነውና በእግዚአብሔር ውሳኔ መደሰት ነውር የለውም፤ አለዚያ ደግሞ ፀጉሬን ካልነጨሁ (ፀጉርክን ካልነጨህ) ብሎ ማለት የእዜአብሔርን ውሳኔ ከመገዳደር የማይተናነስ እንደሆነ በአማኞች ስለሚቆጠር፣
  • ቀናኢ-ቤተክርስቲያን የሆኑ ሰዎች በጳጳሱ ፈቃድ በቤተክርስቲያኒቱ እና ምዕመኑ ላይ እየደረሰ ያለው በደል ማብቂያ ነው ብለው አስበዋል እና የደስታቸው ምንጭ የጳጳሱ ሞት ሳይሆን የመጻኢው ዕድል ተስፋ ስለሆነ፣
  • ሐዘንም ሆነ ደስታ ልቦና ፈቅዶ የሚከሰቱ እንጂ ለሰው ይምሰል የሚገለፁ ባለመሆናቸው፤ ያዘነው ‹‹አዘንኩ›› የተደሰተውም ‹‹ተደሰትኩ›› የማለት የማይገሰሰ ሰብአዊ መብት ስለሆነ እና… ወዘተ ናቸው፡፡

ቀጣዩ ጉዳይ
ለኔ አሳሳቢው አጀንዳ፣ ቀጣዩ ጳጳስ ማን ይሆኑ ይሆን የሚለው ነው፡፡ በሕገ ቤተክርስቲያን አንቀጽ 13 መሰረት (ይለናል ዕንቁ መጽሔት) ጳጳሳት የሚመረጡት በየቤተክርስቲያናቱ ቀሳውስት እና ሰንበት ተማሪዎች በየቤተክርስትያናቱ እና ገዳማቱ (በቀበሌ ይሁን ካልተባለ) ነው፡፡ ስለሆነም በቅርቡ ምርጫ እንደሚካሄድ እና አንድ ጳጳስ አቡኑን እንደሚተኳቸው ይታመናል፡፡ የጳጳሱ ሞት እና የምትካቸው ጉዳይ ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮችን ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ነው እኔም እዚህ መጻፌ!

ሌሎችን እንዴት ይመለከታቸዋል ለሚለው ጥያቄ፣ ቤተክርስትያኒቱ በቁጥር ከሁሉም የበለጠ ተከታዮች ያሏት እንደመሆኑ እና ካለፈው ተሞክሮም፣ በኢሕአዴግም ዘመን ቢሆን ከፖለቲካው ጋር ልትፋታ ስላልቻለች ማነው የሚመጣው የሚለው ጥያቄ የራስ ምታት እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ ኢሕአዴግ ልክ አቡነ ጳውሎስን ባመጣበት መንገድ አሁንም የራሴ የሚለውን ለማስቀመጥ መጣሩ የማያጠራጥር እውነታ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ተቃውሞ የቤተክርስቲያኒቱ ተከታዮች እራሳቸውን ነፃ ለማውጣት፣ ተከታይ ያልሆኑትም የቤተክርስቲያን እና የመንግስትን ፍቺ ለማረጋገጥ በንቃት ሊከታተሉት ይገባል፡፡ አለበለዚያ ግን ‹‹ፋጡማ ኖረች አልኖረች፣ ጳጳሱ ኖሩም አልኖሩ፣ ተቀየሩም አልተቀየሩ…›› ቤተ ክርስትያኗም ከፖለቲካ፣ አገሪቱም ከእምነት ነፃ አይወጡም፡፡

3 comments:

  1. ትክክል፡፡ በጽሑፍ የታዘብከው ሪአክሽን መነሻ፤ የነገ ስጋት ነው፡፡ ምንም ብትል ምን፤ የሞተን ሰው አብዝቶ ለመውቀስ የሚነሳ ጥሩ ድረ ገጽ እንጂ ጥሩ ሀበሻ አታገኝም፡፡ የሞተ የማይወቀሰው፤ ሟች አንገተ ረጅም ስለሆነ ወይም ስለማይጠቅም ስለማይጎዳ ብቻ አይደለም፤ በምትኩ አዲስ የሚመጣው ከሞተው የተሻለ ይሁን አይሁን ስለማይታወቅም እንጂ፡፡ ወንድሜ፤ ማረኝ የሚያሰኝ ሊመጣም ይችላልና (ግን አይሁንብን)፡፡ፋጡማ ብትሾምብንስ?፡)

    ReplyDelete
  2. እጠቅሳለው;
    "...ጳጳሳት የሚመረጡት በየቤተክርስቲያናቱ ቀሳውስት እና ሰንበት ተማሪዎች በየቤተክርስትያናቱ እና ገዳማቱ (በቀበሌ ይሁን ካልተባለ) ነው:: አንድ በሉ፤
    "...ሌሎችን እንዴት ይመለከታቸዋል ለሚለው ጥያቄ፣ ... በኢሕአዴግም ዘመን ቢሆን ከፖለቲካው ጋር ልትፋታ ስላልቻለች " ሁለት በሉ፤
    "...ይህንን ተቃውሞ የቤተክርስቲያኒቱ ተከታዮች እራሳቸውን ነፃ ለማውጣት፣ ተከታይ ያልሆኑትም የቤተክርስቲያን እና የመንግስትን ፍቺ ለማረጋገጥ በንቃት ሊከታተሉት ይገባል፡፡" ጨረስኩ

    ReplyDelete
  3. that cruel the so called pope I am glad he is gone for ever, his monument will be destroyed soon he was a # 1 queer.he was catholic he wasn't ORTHODOX christian at all very happy when I heard that both meles's and paulos's death. and still I am waiting for the others to follow it will happened if the mighty GOD permits it.

    ReplyDelete