Pages

Friday, August 24, 2012

የመለስ ሁለት መልክ

From አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሞት ‹‹ድንገተኝነት›› ብዙ ድራማዎችን አስከትሏል፡፡ መጀመሪያ ላይ ብዙዎች ተደሰቱ፣ ማታ ላይ ኢቴቪ ያነጋገራቸው ‹‹አንዳንድ ሰዎች›› የሰውየውን ታላቅ መሪነት ሲዘክሩ ያድናቂዎቻቸው ቁጥር ጨመረ፣ በጣም ማታ ላይ ወ/ሮ አዜብ ‹‹ተቀጣሁ፤ ምን አጥፍቼ ነው?›› በማለት ሙሾ ሲያወርዱ ‹‹የመለስ ታላቅነት›› የተገለፀላቸው ሰዎች ቁጥር በእጥፍ አደገ፡፡ ልብ በሉ በሞታቸው የመጀመሪያ ዕለት ብቻ ሁለት የተለያየ ገጽታ ለመያዝ የበቁት መለስ ዜናዊ ብቻ ናቸው፡፡ ነገርዬው ግን አብሯቸው የኖረ ነው፡፡

ዴሞክራሲያዊ-አምባገነን

መለስ ዴሞክራሲያዊ መንግስት የሚመስል ነገር መስርተዋል፡፡ ‹‹ዴሞክራሲ›› የሚለው ቃል በሚዲያ ተደጋግሞ እንዲነገርም ይፈልጋሉ፤ ያለ እንዲመስል፡፡ በምርጫ ማሸነፍ ያለበት የእርሳቸው ፓርቲ ብቻ እንደሆነ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የገዢው ፓርቲ ደጋፊ እንዲሆኑ፣ ጋዜጦችና ጋዜጠኞ ስኬታቸውን ብቻ እንዲያወሩ ይፈልጋሉ፡፡ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሲሄድም የሚወስዱትን እርምጃ በ21 ዓመታት አመራራቸው አሳይተውናል፡፡

መለስ ሳያነቡት እንደማያመልጣቸው የነገሩን The Economist ከሞታቸው በኋላ በጻፈው ጽሑፍ ‹‹መለስ አምባገነንነት ተቀባይነት እንዲያገኝ ሰርተዋል›› በማለት አስታውሷቸዋል፡፡


ኢትዮ-ኤርትራዊነት

መለስ ኦነግ፣ ኦብነግንና ምንም ሪፖርት የተደረገ ጥፋት ሰርቶ የማያውቀውን ግንቦት ሰባትን በአሸባሪነት ሲፈርጁ ለስንት እልቂት ሰበብ የሆነውን ‹‹ሻዕቢያ››ን አሸባሪ ያላሉት በእርሳቸው መስፈርት ስላልሆነ ከመሰላችሁ አትሸወዱ፡፡ ቤተሰባቸው ስለሆነ ነው፡፡ መለስ ለኤርትራ እና ለኢሳይያስ ጥልቅ ፍቅር ነበራቸው፡፡ የ‹‹ትሮይ ፈረስ›› የሚለውን መጽሐፍ ካነበባችሁ ‹‹ኅወሓት››ን ማን ጠፍጥፎ እንደሰራው ይገባችኋል፡፡ በእናታቸው ኤርትራዊ የሆኑት መለስ ኅወሓት ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ በኋላ ለኢሳይያስ ኤርትራን የመገንጠል እና የአሰብ ወደብን የመቀማት ሕልም ተባባሪ ሆነዋል፡፡ በትግል ወቅት የሚሰነዘሩ ሐሳቦችን ‹‹የኤርትራ ሕዝብ ትግል ባፍጢሙ አይደፋም›› የሚል መጽሐፍ በመጻፍ በጠብመንጃም በጽሑፍም ታግለዋል፡፡
አገር ወዳድ - የአገር ጠላት

መለስ - በተለይ በስልጣናቸው መጨረሻ ሰሞን አገር ወዳድ ለመምሰል ይጥሩ ነበር፡፡ በተቃራኒው ታሪካችንን በመቶ ዓመት ሲቀጩት፣ ባንዲራችንን ከተራ ጨርቅ በላይ ፋይዳ እንደሌለው ሲነግሩን ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ‹‹አገር ማለት ሕዝቡ ነው›› ባሉበት አፋቸው ‹ለልማቱ (ለሕንፃና መንገዱ) ሲባል ሕዝቡ ይጎሳቆል› ብለውበታል፡፡ ልዩነቱ የሚጎሳቆለው ሕዝብ እና የሚጣሰው ሰብአዊነት የእርሳቸውን እና የቤተሰባቸውን በር አያንኳኳም፡፡ ኤርትራን ያህል ሃገር እና አሰብን የሚያህል ወደብ አሳልፈው ሰጥተው፣ መልሰው ደግሞ ባድሜን ለምታክል ቁራጭ መሬት 120 ሺ ሰው ይገብሩብናል፡፡

ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ድህነት

የመለስ ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ዓመታት ‹‹በሁለት ዲጂት›› አድጋለች፡፡ ሕዝቡ ግን ከመቼውም የበለጠ ድህነት ውስጥ ገብቷል፡፡ የገንዘብ ግዥበቱ ዕድገት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ አይታወቅም፡፡ እርግጥ ነው በርካታ መንገዶች ተሰርተዋል፣ ብዙ ሕንፃዎች ቆመዋል ነገር ግን ኢሕአዴግ በገባ በ10 ዓመቱ በቀን ሦስቴ አበላዋለሁ ብለው ቃል ገብተውለት የነበረውን ሕዝብ በ20 ዓመታቸውም አላበሉትም፡፡

እውነቱን እየተነጋገርን ስለሆነ የተሰሩት ሕንፃዎች የማን ናቸው የሚለውን ጥያቄም መልሰን እንለፍ፡፡ በፊት በታታሪ ሰራተኝነታቸው የኢዲስ አበባን ግማሽ ሃብት ተቆጣጥረው የነበሩት ነጋዴዎችና ባለሃብቶች ጉራጌዎች ነበሩ፡፡ ዛሬስ? ኢሕአዴግ ከገባ ወዲህ የተሰሩትን ሕንፃዎች ብትቆጥሩ ከግማሽ በላይ ለሚሆኑት ባለቤት የትግራይ ልጆች ናቸው፡፡ በ20 ዓመት ይህን ሁሉ ሀብት ያፈሩት በምን ጥበብ ነው?

ንግግር አዋቂው ተሳዳቢ

ንግግር አዋቂ (አንደበተ ርቱዕ) ሰዎች አይሳደቡም፤ ምክንያቱም በንግግራቸው ማሳመን ይችላሉ፡፡ ስድብ በንግግር ማሳመን ያልቻለ ሰው ውጤት ነው፡፡ መለስ ዜናዊ ንግግር ሆነ እንዲሁም በጥቅሉ አዋቂነታቸው በሰፊው ይወራላቸዋል፡፡ ይህንን ግን በቅጡ ላጤነው የቱ’ጋ እንደሆነ ለማወቅ ይቸግራል፡፡ አንደበተ ርቱዕነት በንግግር ለዛ ማሳመን እንጂ ቃላትን በመሰንጠቅ፣ አዳዲስ የስያሜ ባጅ በመለጠፍና በማደናገር የሚፈጠር አይደለም፡፡ ስለፖሊሲያቸው ሲጠየቁ ‹ፊዚካል ፖሊሲ› የሚባል የለም ‹ፊስካል ፖሊሲ› ነው የሚባለው የሚል ዋና መስመሩን የሳተ ‹‹የፉጨት›› ሌክቸር መስጠት ያምራቸዋል፡፡ ከአንደበተ ርቱዕ ሰዎች በማይጠበቅ መልኩ ‹‹የገማ፣ የበከተ፣ የበሰበሰ፣ ደደብ…›› የሚሉ ስድቦችን በሕዝብ ፊት ደጋግመው ተሳድበዋል፡፡

አሁን መለስ ሞተዋል፡፡ ቀብራቸው በእልፍ ሺህ (እውነት እየተነጋገርን አይደል፤ ከነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በትግራይ ተወላጆች፣ ወደሩብ  በሚጠጉ አባሎቻቸውና የስርዓቱ ተጠቃሚዎች እና ወደሩብ በሚጠጉ ግራ የገባቸው ሰዎች) አጀባ፣ በኢቴቪ እና ሬዲዮዎች ፕሮፓጋንዳ ይካሄዳል፡፡ የፕሮፓጋንዳው መዓት ‹‹ሳያዩ የሚያምኑትን›› ብዙሐን ኢትዮጵያውያንን ለኢሕአዴግ እንደሚመለምል አልጠራጠርም፡፡ ቢሆንም ግን መለስ ሲሞቱ (የመሪ ሳይሆን የስርዓት ለውጥ ነው በማለት) ንቄው የነበረውን የሕልፈታቸውን ብስራት ዛሬ አግኝቸዋለሁ፡፡

ከመቶ፣ ሁለት መቶ ዓመት በኋላ መለስ ሲታወሱ በሕንፃና ቀለበት መንገድ ሊታወሱ አይችሉም፣ ዘመኑ አይፈቅድላቸውም፡፡ የኤርትራ ጉዳይም ቢሆን አሉታዊ ነው፡፡ ሊታወሱ የሚችሉበት አንድ ብቸኛ አማራጫቸውን ተፈጥሮ ነጥቋቸዋል፡፡ መለስ ሦስት ዓመት ቢቆዩና እንዳሉትም ስልጣን ቢለቁ ኖሮ በኢትዮጵያ ታሪክ ስልጣኑን ‹‹በፈቃዱ›› የለቀቀ የመጀመሪያው መሪ ይሆኑ ነበር፤ አመለጣቸው፡፡

2 comments:

  1. የሶሻሊስታዊው ሀዘን ስርዓት ሲያበቃ፤ ሕዝባዊው የመርሳት በሽታ /mass amnesia/ ሲያልፍ፤ ሰው የመለስን ሁለት ገጽ ያስታውሰዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

    ReplyDelete
  2. ኧረ አንተ ሰውዬ አንተም physical policy የሚለው አባባል ትክክል ነው ልትለን ነው እንዴ ?

    ReplyDelete