ሰሞኑን በሞት ስልጣናቸውን ስለለቀቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ያለኝን ትዝታ ‹ የመለስ ሁለት መልክ › በሚል ጽፌው ነበር፡፡ ጽሑፉ ውስጥ የመለስ አስተዳደር በተለይ የተመቻቸው የብሔር አባላት እንዳሉ በስም በመጥቀሴ ‹‹ዘረኛ ነህ›› የሚል ብዙ አስተያየት ተሰንዝሮብኛል፡፡ እነሆ ይህ አስተያየትም ይህን ጽሑፍ ወልዷል፡፡ ነውርን ማን ፈጠረው? በመጀመሪያም፡- ነፃነት እና ልቅነት ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ለድርድር የማይቀመጡለት አጀንዳ ነው፡፡ ሆኖም ሁሉም ሰው ሐሳቤን በነፃነት የመግለፅ መብቴ በሕግ ተደንግጓል ወይም ተፈጥሮ ያጎናፀፈኝ ነው በማለት እንዳሻው አይናገርም፡፡ በተለይም ሐሳቡ የሚቀርብበት ሚዲየም ሰፊ ሲሆንና ብዙ ተደራሲዎች ሲኖሩት ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ጥንቃቄ የሚያስፈልግበት በርካታ ምክንያቶች አሉ፤ ከነዚህም ውስጥ የሕዝብን አቅጣጫ ላለማሳት፣ መረንነትን ወይም ልቅነትን ላለማስፋፋት እና አሁን ስለሆነው ሳይሆን ነገ እንዲሆን ስለምንፈልገው በመሳሳት (ሳ ላልቶ ይነበብ) ነው፡፡ ሁሉንም በሒደት ወደታች አብራራቸዋለሁ፡፡ ‹የሕዝብን አቅጣጫ ላለማሳት› ያልኩት ሐሳባችንን የምንገልጽበት አገባብ (context) ተደራሲያኑ ጋር ሲደርስ ሌላ አንድምታ እንዳይኖረው የሚለውን ነው፡፡ ምናልባትም ያለፈው ጽሑፍ ውስጥ ‹ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት አዲስ አበባ ውስጥ ከተሰሩ ሕንፃዎች መካከል አብዛኛዎቹ የትግራይ ልጆች ንብረት ናቸው› ማለቴ በአንባቢው ዘንድ የትግራይ ልጆች ሁሉ በኢሕአዴግ ስርዓት ተጠቅሟል የሚል ትርጉም ከሰጠ አቅጣጫ አስቷል ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን እኔ በፃፍኩበት መንፈስ የትግራይ ተወላጆች ከኢትዮጵያ ሕዝብ አንፃር ካላቸው ድርሻ (proportion) ጋር ሲወዳደር በስልጣን እና በከተማ ሃብት ይዞታ ላይ ያላቸው...
Passionate about the ideas of liberty and dignity, and of course prosperity too.