(የዓለማችንን ሕዳሴ ለማፋጠን የቀረበ ምክረ ሐሳብ) እስከዛሬ የጻፍኳቸው ሁሉ የግል አቋሜን የሚያንጸባርቁ አልነበሩም፡፡ ነገርዬዎቹ “ኪራይ ሰብሳቢ” የተባለ ሰይጣን ለክፎኝ የተናገርኳቸው ነበሩ፡፡ ሰይጣኑ የለከፋቸው ሰዎች በኢትዮጵያ የተገነቡት ፎቆችና መንገዶች፣ የሰፈነው መልካም አስተዳር፣ በ11.4% የሚመነደገው ኢኮኖሚ አይታያቸውም፡፡ ለነሱ የሚታያቸው ድንጋይ ሲወረውሩ÷ ፓሊሶች ራሳቸውን ለመከላከል በሚተኩሱት ጥይት የሚሞቱ አደገኛ ቦዘኔዎች፣ ከስንት አንዴ የሚገለበጡ የምርጫ ኮሮጆዎች፣ የመንግስትን ሕልውና በስክርቢቶና ወረቀት የሚያናጉ ጋዜጠኞች መታሰር፣ የኢኮኖሚውን ዕድገት ተከትሎ የተከሰተው የዋጋ ግሽበት ብቻ ነው፡፡
ቻይናዊው ዕውቅ ኮሚኒስትና የፖለቲካ ጠቢብ ኪል ሃንግ÷ ጥርነፋ ወከመ ለስልጣን በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሃፋቸው ላይ በኪራይ ሰብሳቢ ሰይጣን የተለከፉ ዜጎች ነፃ ሊወጡ የሚችሉባቸውን መንገዶች ሦስቱ ‘መ’ዎች በማለት ሰይመዋቸዋል፤ እነሱም መጠመቅ፣ መታረም ወይም መሰደድ ናቸው፡፡
መጠመቅ፡- በሚባለው መንገድ ኪራይ ሰብሳቢዎች በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዶክትሪን ከተሰበኩና ካመኑ በኋላ “የልማታዊ ዜግነት” ጠበል ተረጭተው (ተጠምቀው) ካለፈው ሃጢያታቸው ተሰርየው÷ ምቹ ወንበርና ስልጣን፣ በቂ ደሞዝና ጥቅማጥቅም አግኝተው በሰላም የሚኖሩበት ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ ያለፈው ሃጢያተቸውን ያነሳም “ውሾ ይሁን” ተብሎ ይረገማል፡፡ (በዚህ መንገድ እነ ሽመልስ ከማል፣ እነ ሬድዋን እና እኔ የዚህ ጠመቃ ተጠቃሚዎች ነን፡፡)
መታረም፡- ሁለተኛው ኪራይ ሰብሳቢ የሰይጣን መንፈስን ከዜጎች ውስጥ ለማስወጣት የሚደረግ መፍትሄ ስራይ ሲሆን፤ ኪራይ ሰብሳቢነት የተጠናወተው ግለሰብ በፖሊሶችና በፍርድ ቤት መልካም ፈቃድ በመንግስት ቁጥጥር ስር እንዲሆን ይደረግና ዕውቅ፣ ቻይና አፈራሽ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም፣ አካልን በሚያደክም ስግደት፣ ቁጭ ብድግ፣ በተጨማሪም በተለያዩ ገዳማት እንደሚደረገው በአለንጋ አሳሳች ስጋን በመግረፍ፣ ከዓለምና መረጃ በመገለል ሰይጣኑ እንዲወገድና ታራሚዎቹም “የኢትዮጵያ ሕዝብንና መንግስትን ይቅርታ ጠይቀው” እና ውግዘት ተቀብለው አሊያም ጠቃሚ የምስክርነት መረጃ ሰጥተው እንዲወጡ የሚደረግበት መንገድ ነው፡፡ (በዚህ መንገድ የቅንጅት አመራሮች፣ ብርቱኳን ሚዴቅሳ እና ደበበ እሸቱን የመሳሰሉት “ታርመዋል” ሆነዋል)
መሰደድ፡- የሚባለው መንገድ የላይኞቹ ሁለት መንገዶች ካልተሳኩ የሚመረጠው መንገድ ሲሆን÷ ልማታውያን ኪራይ ሰብሳቢ ሰይጣን የተጠናወታቸው ዜጎች ሰይጣኑን ወደልማታውያን እና መሃል ሰፋሪዎች ከማጋባታቸው በፊት፣ በተለያዩ ጫናዎችና ግፊቶች÷ ሳያስነቁ በሊማሊሞ እንዲያቋርጡ የሚደረግበት መንገድ ነው፡፡ ብዙዎቹ መሰደድን የሚመርጡ ዜጎች ኪራይ ሰብሳቢነቱ የማይለቃቸው ቢሆንም ከሃገር ከወጡ በኋላ በሃገሪቱ ውስጥ ያሉ ዜጎች ላይ ሰይጣኑን ስለማያስተላልፉ፣ በሌላ በኩል ቢሄዱ ቢሄዱ ወዳጅ አገር ወደሆነችው ቻይና ስለማይሄዱ ችግር የለውም፡፡ (በዚህ መንገድ የአዲስ ነገር ጋዜጠኞችን ጨምሮ እነዳዊት ከበደ፣ አበበ ቶላ፣ አርጋው አሽኔ … እና ወዘተርፈዎች ተጠቅመዋል)
እናም እኔ መጠመቅ የተሰኘው መፍትሄ ስራይ ኤክስቴንሽን ተጠቃሚ ከሆንኩ በኋላ፣ ዓለም በኢኮኖሚ ቀውስ እየታመሰች ባለችበት ጊዜ ሃገራችን ለስምንት ተከታታይ ዓመታት ኢኮኖሚዋ በሁለት ዲጂት እያደገ መምጣቱን ምሳሌ አድርገው ቢንቀሳቀሱ፣ ሌሎችም ሃገራት የፈንጠዝያችን ተጠቃሚ ይሆናሉ የሚል ስሜት ተሰማኝ፡፡ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለመቀየር የሚያስችለው በኢኮኖሚ ማደግ ብቻ ሳይሆን ዓለምን በኢኮኖሚ ማሳደግ መሆን እንዳለበት ታውቆኛል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ አድጋ፣ አድጋ እላይ ስትደርስ - ድንበር እየሰበሩ እና ዲቪ እየሞሉ ወደኢትዮጵያ ለመግባት የሚሞክሩት የድሃ ሃገር ሕዝቦች መልሰው ለኛው ሸክም መሆናቸው እንደማይቀር ታይቶኛል፡፡
የኢትዮጵያን ተሞክሮ ለማካፈል ስናስብ ታዲያ÷ “ከባድ ስራ ወስደው፣ ከባድ ስራ በሚሰጡት” ጠቅላይ ሚኒስትራችን ፊት አውራሪነት የሚመራው ፓርላማችን ግንባር ቀደም ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ስለዚህ የሚከተሉትን ነጥቦች የዓለማችን ሃገራት ፓርላማዎች ቢተገብሩ፣ ዕድገታቸው እንደኢትዮጵያ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ሁላችሁም አንባብያን ይህንን መልዕክት ‘የሰማህ ላልሰማ አሰማ’ በሚል መርኅ “አምስት ለአንድ በመደራጀት”፣ መረጃውን በማሰራጨት የዓለማችንን ሕዳሴ እናፋጥን!!!
1. አለመጨቃጨቅ፤ ጭቅጭቅ እንኳን ሃገርን ትዳርን የሚያፈርስ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ፓርላማዎች በጠቅላይ ሰብሳቢያቸው የሚቀርበውን ሐሳብ ያለምንም ጭቅጭቅ መቀበል አለባቸው፡፡ የሚጨቃጨቁ ካሉ አፈጉባኤው በዲሲፕሊን ሰበብ ማስቆም ይችላል፣ ጠቅላይ ሰብሳቢው ደግሞ በስድብ መወረፍ አለባቸው፡፡ በዚህ መንገድ ኢትዮጵያ እስከዛሬ ፓርላማ ቀርቦ አንድም ረቂቅ አዋጅ ሳይጸድቅ ያልቀረባት ሃገር በመሆን በዓለም አንደኛ ሆናለች፡፡ የፓርላማ አባላት በሚቀርቡ ሞሽኖችም ላይ ሆነ ረቂቅ አዋጆች ላይ ማቅረብ የሚገባቸው ሙገሳ ብቻ ነው፡፡ ጥያቄ ካላቸው፣ ሊኖራቸው የሚገባው በረቂቅ አዋጁ ፍጽምና ላይ ሳይሆን ዜጎች አዋጁን እንዲቀበሉ ምን ማድረግ ይገባል፣ ኪራይ ሰብሳቢዎች አዋጁን እንዳይቃወሙ እንዴት ዝም ማሰኘት ይቻላል፣ አዋጁ ከጸደቀ በኋላ ዜጎችን እንዴት ማወያየት ይቻላል በሚሉት ተጓዳኝ ጉዳዮች ላይ ብቻ ከሆነ ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡
2. እንቅልፍ፤ የፓርላማ አባላት እንቅልፍ የሚወዱ ቢሆን ይመረጣል፡፡ ለአገራቸው ሲሠሩ እያመሹ ቢሆንም ባይሆንም፣ አባላቱ (መጽደቁ በማይቀረው) ረዥም እና ለዛቢስ የረቂቅ አዋጅ ንባብ ተሰላችተው እንቅልፍ ቢያሸልባቸው ችግር የለውም፤ ምክንያቱም ፓርላማ ውስጥ በመተኛቱ ደሞዙ የተቆረጠበት አባል እስካሁን የለም፡፡ ይሄም ሕዝቦች ከዚህ አጋጣሚ በገዛ ጉዳያቸው ላይ መተኛት ምንም ጉዳት እንደማያስከትልባቸው እንዲማሩ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚ አይኖርም! እንቅልፍ መተኛት፣ ሰውነትን ዘና በማድረግ በስራ ውጤታማ ያደርጋል፤ ይህም በኢትዮጵያ ፓርላማ የተረጋገጠው÷ አሸልበው የነበሩ አባላት በድምጽ ቆጠራ ወቅት እጃቸውን ካላሸለቡት ይልቅ ዘለግ አድርገው ሲያወጡ በመስተዋሉ ነው፡፡
3. መሃይምነት፤ መሃይምነት ለፓርላማ በጣም አስፈላጊ ነገር መሆኑ በአገራችን ተሞክሮ ተረጋግጧል፡፡ የአገራችን አብዛኛው ሕዝብ የትምህርት ዕድል ያልገጠመው በመሆኑ በፓርላማ የሚወክሉት ሕዝቦችም መሃይማን እንዲሆኑ መደረጉ ጠቅሞታል፡፡ ፓርላማው ያለምንም አማራጭ ሐሳብና ውዝግብ፣ በአንድ ዓይነት ሐሳብ መግባባት የቻለው መሃይምነትን በመምረጡ ነው፡፡ የፓርላማ አባላት አንዳንድ የውጭ ቃላትን በመጠቀም የሚነገሩ ንግግሮች የበሰሉ እንደሆኑ ስለሚያምኑ - ጠቅላይ ሰብሳቢው እንግሊዝኛ ቢችሉ ይጠቅማል፡፡ ተቃራኒ ሐሳብ የሚያፈልቁ ሰዎች ቢከሰቱም - ጠቅላይ ሰብሳቢው ቀልድ አዘል ስድብ በመሳደብ፣ መሃይማኑን በማሳቅ ማሳመን ይችላሉ፡፡
እነዚህ ሦስቱ የኢትዮጵያ ፓርላማ ዋነኛ ገጽታ፣ የዕድገታችን ዋልታ በመሆናቸው ሌሎችም ተሞክሮውን ለበጎ ዓላማ እንዲያውሉት በማካፈሌ ኩራት ይሰማኛል፡፡
No comments:
Post a Comment