(መግባቢያ፤ በዚህ ጽሁፍ ‘ሐበሻ’ ማለት ኢትዮጵያዊ፣ ‘አምልኮ’ ማለትም የተጋነነ አድንቆት የሚል ትርጉም ብቻ አላቸው፡፡) ‹የፈረረንጅ አምልኮበኢትዮጵያ› በሚል በጻፍኩት ጽሁፍ ተበሳጭተው÷ ጠንከር ያለ ነቀፌታቸውን ያደረሱኝ በርካቶች ናቸው፡፡ (በተለይም ethiopianreview.com ላይ!) የዚያን ቀጣይ ጽሁፍ በዚህ ርዕስ ለመጻፍ የተገደድኩት ያለፈው ጽሁፍ ስህተት መሆኑን አምኜ በተቃራኒው ለማረም ቢሆን ‹‹መልካም ነበር፡፡›› ግን አይደለም፤ ያም ሆነ ይህ ጽሁፍ ማሕበረሰባችንን መነቀፍ ባለበት ጉዳይ ለመንቀፍ የማይሳሱ ጽሁፎች ናቸው፡፡
በመጀመሪያ የቀደመው ጽሁፍ ለምን ነቃፊ በዛበት የሚል ጥያቄ ማንሳቱ ተገቢ መስሎ ይሰማኛል፡፡ የሁሉንም አስተያየት ሰጪዎች መልዕክት ያለምንም ማንገራገር በአንድ ጨፍልቆ መረዳት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያውያን ለባዕድ (ማለትም ለፈረንጅ) አምልኮ ወይም አድንቆ እጃቸውን የሰጡት ከመቼ ጀምሮ ነው በሚለው ጥያቄ ውስጥ እኔ መልስ ይሆናል ያልኩት ክርስትና ወደኢትዮጵያ መግባት ከጀመረ ወዲህ ነው የሚለውን ነው፡፡ ብዙዎች ክርስትና መነካቷን አይወዱምና የቁጣ ናዳ አወረዱብኝ ማለት ይቀላል፡፡ (ለጨዋታ ያህል ይሄ ጽሁፍ ‹‹ናዳን ለማቆም የተሮጠ ግለሰባዊ ሩጫ›› ነው ልንለው አንችላለን፡፡) እንዲያውም ክርስትና ለኢትዮጵያውያን የተሰፋ (ከባዕድ ያልወረስነው) እንደሆነ ሊያስረዱኝ የሞከሩ ሰዎችም አልጠፉም፡፡ ይሄ ሐሳብ ነው ወደዛሬው ጽሁፌ የሚያንደረድረኝ - የሐበሻ አምልኮ ብዬዋለሁ፡፡
በመጀመሪያ ማነው የመጀመሪያው?
በዕውቀቱ ስዩም ከአስቂኝ ወጎቹ መካከል በአንዱ÷ ኢትዮጵያውያን ያለቅጥ አንደኝነታችንን ማውራት እንደምንወድ አትቷል፡፡ ‹‹አሁን ለምሳሌ›› ብሎ ነገሩን በቀልድ ያጠናክረዋል፤ ‹‹እኔ በቤተሰቤ ውስጥ ሁለተኛ ልጅ በመሆን የመጀመሪያው ነኝ፡፡›› አይሁዶች ክርስትናን ሳይቀበሉት እኛ በመቀበላችን ወይም አረቦች እስልምናን ሳይቀበሉት እኛ በመቀበላችን÷ እኛ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ወይም ሙስሊሞች ነን ብሎ መደምደም እኛን ማምለክ ነው፡፡ በሌላ በኩል እኛ ከሌሎቹ ቀድመን መቀበላችን (ወይም ተቀብለን መቅረታችን) ማሕበረሰባችን ለማመን ወይም የሌሎችን ተጽዕኖ በቀላሉ ለመቀበል የተፈጠረ እንዲመስል ያደርገዋል፡፡
በአርኪዮሎጂ ሉሲ አለች፣ በመጽሃፍ ቅዱስ የጊዮን ወንዝ (አባይ አለ፤ ‹‹ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከኤደን ይወጣ ነበር…..የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል።›› /ዘፍ. 2÷10-13/ እንዲል)፣ በታሪክም እንዲሁ እስከሦስት ሺኅ ዓመት ወደኋላ ተጉዘን ኢትዮጵያን ማግኘት እንችላለን፡፡ እንደኢትዮጵያዊ ዋንጫ ባያሸልምም ‹‹አንደኝነታችንን›› መዘከር ያስደስታል፡፡ ሌሎችም ሃገራት የራሳቸውን ‹‹አንደኝነት›› የሚዘክሩ ነገሮችን እንደሚያጣቅሱ ልብ ማለትም ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ባሳለፍናቸው የኢትዮጵያ የታሪክ ዓመታት÷ ከወግና ከትዝታ በቀር ለዚህ ትውልድ የተረፈው ምንድር ነው? ከዚያም በላይ የሚያሳፍረው ደግሞ እኛስ ለመጪው ትውልድ ምንድር ነው የምናወርሰው የሚለው ነው? ሌላው ቀርቶ ሉሲን እንኳን ቆፍረው ያወጡልን ባዕዳን ናቸው፡፡ አሁንም የአክሱምን ስልጣኔ፣ የላሊበላን ምስጢር እየቆፈሩ የሚነግሩን እነርሱው ናቸው፡፡
የትኛው ኢንዱስትሪያችን ነው ትውፊታዊውን የሸክላ ሥራ እና የሽመና ጥበብ ወደዘመናዊነት ያሸጋገረው? የእጅ ጥበበኞችን ‹‹አንጥረኛ/ቡዳ/ሞረቴ/ባለእጅ›› የሚሉ ከደረጃ የሚያዋርዱ ስሞችን እየሰጠ እንዲከስሙ ያደረገው ማነው? ‹‹ካልለመኑ ይቆመጣሉ›› በሚል እየለመኑ ብቻ የሚተዳደሩ ማሕበረሰቦች ያሉባት አገር የማን ናት? ሥራ የማይነካባቸው ‹‹በዓላት›› እንደጉድ ያሏት ሃገር የማን ናት?
የሁሉም ሰው ምርጫ ሆነና÷ በታሪካችን የሚነገረውም ሆነ እንዲነገር የምንፈልገው በጎ፣ በጎውን ብቻ ነው፡፡ ዘወትር የምንዘክረው በዓለም ቀዳሚ የሚያሰኘንን እውነታ ብቻ ነው፡፡ ይምረር እንጂ ይሄም እውነታችን ነው፡፡ ሠራተኛ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በማንኳሰስም የመጀመሪያዎቹ ነን፡፡
አሁን በዚህ ትውልድ ዘንድ ኢትዮጵያ በዚህ፣ በዚህ ቀዳሚ ነበረች የሚል ነገር ሳይሆን የሚያስፈልገን ‹‹ቀድማ ጀምራ ለምን ኋላ ቀረች?›› የሚል ነው፣ ‹‹መልሳ ለመቅደም ምን ታድርግ?›› ማለት ነው የሚያስፈልገን፡፡
የሚመለክ ‹‹ሐበሻ›› ለመፍጠር
የወደፊቷን ኢትዮጵያ ራዕይ አድርጎ ለሚጓዝ ሰው÷ መንገዱ ቀላል ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንን ወደኋላ ያስቀረንን ኋላ ቀር የአሠራር ዘዴ እና የሥራ ባሕል ብሎም ሠራተኝነትን የማንቋሸሽ ልማድ ቀርፈነዋል ወይ ብሎ መጠየቅ የመጀመሪያው ርምጃ ነው፡፡ በማሕበረሰቡ ‹‹ዝቅተኛ›› በሚባሉ የሥራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን የምናይበት ዓይን ከአባቶቻችን ይለያል?
የሐበሻ ቀሚስ ከቻይና ማስገባት ከመጀመራችን በፊት የሽመና ሥራን በዘመናዊ አሠራር የሚለውጡ ኢትዮጵያዊ መሃንዲሶች የታሉ? የሸክላ፣ የመሶብ እና እርቦ ሥራዎች ከየመቃብራቸው ተነስተው ማደግ ካልጀመሩ ሐበሻም የለ! ትንሳኤም የለ!
የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ‹‹እኔ ምን ማድረግ እችላለሁ?›› ብሎ ጠያቂ እና ተግባሪን መቀስቀስ ነው፡፡ እኔ እንደመሃንዲስ ከአለፈው ታሪካችንና ከሕዝባችን ወቅታዊ ፍላጎት በመነሳት ምን መፈልሰፍ እችላለሁ? እኔ እንደሐኪም ከባሕላዊ ሕክምናዎች በመነሳት ምን ዓይነት ፈውስ አሊያም ግንዛቤ መፍጠር እችላለሁ? እኔ እንደፖለቲከኛ ምን ዓይነት ለውጥ ማምጣት እችላለሁ? እኔ እንደጸሃፊ አመለካከትን በመቀየር፣ መረጃ በመስጠት እና ወዘተርፈ ምን ማድረግ እችላለሁ? እኔ ምን ማድረግ እችላለሁ በማለት - ብዙ ነገር ማድረግ እንችላለን!!!
No comments:
Post a Comment