Skip to main content

ኑሮ በአገርኛ÷ ጾም ይበዛበታል!


ባሕር ማዶ ካሉ ሰዎችጋ ስናወራ አንዳንድ የማይገቡን ወሬዎችን እየሰማን ጭንቅላታችንን እየናጥን “ወቸ ጉድ!” ማለታችን አይቀሬ ነው፡፡ ለኛ ባዳ ከሆነው ከቀላሉ “GPS” ጀምሮ፣ credit card ቢሉ፣ ምን ቢሉ ሁሉም ለኛ እንቆቅልሾች ናቸው፡፡ ወጉ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ እንዲሉ “GPS” ቀርቶብኝ እበላው ባገኘሁ የሚለው እስኪታወሰን ድረስ እንደመማለን፡፡ እዚህ GPS የለም፣ credit card የለም፣ ባቡር (ወይም subway station ብሎ ቋንቋ) የለም፣ smart phone የለም፣ wi-fi የለም (አለ እንዴ?) ለነገሩ የዚህ ጫወታ ጉዳዮች እነዚህ ሁሉ ስላልሆኑ እንኳን ደስ ያላችሁ፡፡ በርግጥ ግን ወደጫወታው አጀንዳ ለመድረስ አሁንም ዳር፣ ዳሩን መነካካት የግድ ነው፡፡ ‹አሜሪካኖች ለምን ወፋፍራም ሆኑ? ኢትዮጵያውያኖች ለምን ቀጫጭን ሆኑ?› ብለን ብንጀምርስ!
ያልተመጣጠነ ውፍረት ለ75 በመቶ አሜሪካውያን የጤና እክል እየፈጠረ ነው፤ ለ75 በመቶ ኢትዮጵያውያን ደግሞ (ይህ ቁጥር በጥናት አልተረጋገጠም እንጂ፣) ችግራችን ቅጥነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በobesity ሳይሆን በምግብ እጥረት፣ በጨጓራ ሕመም የሚሰቃዩ ሰዎችን ነው ማግኘት የሚቻለው፡፡ ለምን ብለን የጠየቅን እንደሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስልጣናቸው አፍላ ዘመን ቃል በገቡት መሠረት “በቀን ሦስቴ መብላት” ባለመቻላችን ነው፡፡ በቀን ሦስቴ መብላት ማለት አሰሱን ገሰሱን ማግበስበስ ማለት አይደለም፡፡ በሦስተኛ ክፍል ሳይንስ ላይ እንደተማርነው የተመጣጠነ ምግብ መብላት ማለት ነው፡፡ የተመጣጠነ ምግብ ደግሞ ፕሮቲን፣ ካርቦሃይድሬት፣ ፋት፣ ቫይታሚኖችና ማዕድኖችን መያዝ አለበት፡፡

የኢትዮጵያውያንን አመጋገብ በጥቅሉ በአንድ መስመር መተረክ ይቻላል፡፡ ቁርስ፤ ዳቦ በሻይ (ሻይ ከተገኘ!)፣ ምሳ፤ እንጀራ በሽሮ ወጥ፣ እራት፤ እንጀራ በሽሮ ወጥ፡፡ በዚህ የአመጋገብ ልምድ ውስጥ የሚካተቱት ጤፍ፣ ስንዴ፣ ባቄላ እና ውሃ ናቸው፡፡ በርግጥ በስንዴ ውስጥ ካርቦሃይድሬት፣ በጤፍ ውስጥ iron (ብረት ነክ ማዕድን)፣ በባቄላ ውስጥ ፕሮቲን አለ፡፡ ፋት ግን ምናልባት እንደሽሮፕ በማንኪያ በምትጨመረው ዘይት ውስጥ ካልሆነ በቀር የለም፤ ስለዚህ የሚያወፍረን ምንም ነገር የለም፡፡ በምግብ ዝርዝራችን ውስጥ የሚያወፍር ነገር አለመኖሩ እሰዬው፣ ነገር ግን በሽታ የመከላከል አቅማችንን የሚያጎለብት÷ የፍራፍሬና የአትክልት dessert እንዳይኖር እርጥብ አገራችንን ያደረቃት ማነው?

የልምድ Vegetarians
ኢትዮጵያውያን የኑሮ ነገር ሁኖብን ከጥንትም ጀምሮ የምንመገበው የምግብ ዓይነት vegetarian የሚያሰኘን ነው፡፡ የጤፍና ባቄላ ድምር!!! በርግጥ ብዙዎቻችን የምግብ ምርጫችን ምን እንደሆነ ስንጠየቅ ቁርጥ ወይም ክትፎ ልንል እንችላለን፡፡ የምግብ ምርጫችን ግን አምሮታችን እንጂ÷ ‘የምናዘወትረው የምግብ ዓይነት ነው’ የሚል ትርጉም እንደሌለው ሁላችንም ይገባናል፡፡

ቬጂቴሪያንነትም ሆነ ቅጥነት ዕድሜን እንደሚቀጥል ምሁራኑ ይናገራሉ፤ ይሁን እንጂ የወፋፍራሞቹ አሜሪካውያን አማካይ ዕድሜ 70ን ሲዘልቅ፣ የቀጫጭኖቹና የልምድ ቬጂቴሪያኖቹ ኢትዮጵያውያን ዕድሜ ግን ሃምሳ መድረስ አቅቶታል፡፡ ‹የዘመኑ ምርጫ፣ ምን እና ቀጫጫ› የተባለውን እውነታ አፈርድሜ አስበልቶ፣ ውፍረትን እንደምቾትና እንደጤነኝነት ባገራችን እንዲቆጠር ያደረገው ማነው?

“ምግብ አጥቂውን ነው የሚያጠቃው”
ይህች አባባል አገልግሎት ላይ የምትውለው ብዙ በሊታ ከሲታዎችን ለመተቸት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ‹እውን በሊታ ከሲታዎች አሉ?› ብለን ከጠየቅን ውዥንብር ውስጥ መውደቃችን አይቀሬ ነው፡፡ አንዳንዴ አሰሱን ገሰሱን ማግበስበስ ሆድን ከመቆዘርና፣ ጨጓራን ለበሽታ ከመዳረግ ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡

“ምግብ አጥቂውን ነው የሚያጠቃው” የሚለው አባባል እንደየሃገሩ የተለያየ ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ምንም እንኳን እኛጋ ብዙ የሚበሉት ናቸው የሚከሱት ብሎ ለመሳለቅ ቢያገለግልም፤ ወፋፍራሞቹ ዓለም ግን ብዙ መብላት ለውፍረት፤ ውፍረት ደግሞ ለበሽታ ወይም ሞት ይዳርጋል የሚል አንድምታ አለው፡፡ ዞሮ ዞሮ ምግብ አጥቂውን ነው የሚያጠቃው፡፡

እኛ አገር ግን ምግብ ይከበራል፡፡ “ገበታ ንጉሥ ነው” ነው ከነአባባሉ፡፡ ሁሉም ንጉሥ ከሚሊዮን አንድ ነው፤ ታዲያ ገበታን ከንጉሥ እኩል ምን አደረገው ብለን ስንጠይቅ መልስ ሊሆን የሚችለው “ገበታ በሃገራችን ከሚሊዮን አንድ ነው” የሚል ይሆናል፡፡ ሌላው ዓለም በሌለ መልኩ ኢትዮጵያ ውስጥ ምግብ ከንጉሥ እኩል ይከበራል፣ ይዘፈንለታል፡፡ በዘፈን ክሊፖቻችን ሳይቀር ለእንቁልልጭ ይቀርባል፡፡ ለምን? ምግብ ብርቅ ነዋ! ምግብን ከጥንት እስከዛሬ በሃገራችን ብርቅ ሆኖ እንዲቀር ያደረገው ማነው?


‘ማነው’ ማነው?
ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ዓይነት ጾመኞች አሉ፡፡ የውዴታ እና የግዴታ! በሃይማኖታዊ ሰበብ የሚጾሙት ምናልባት ወደጽድቅ ይጠጋሉ፡፡ ሳይጾሙ በእጦት የሚጾሙት ደግሞ ባይኮነኑም ይህ እንደበጎ ምግባር ተቆጥሮ ለጽድቅ ነጥብ አያስይዝላቸውም፡፡ የሆነ ሆኖ ኢትዮጵያውያን (በተለይም ከተሜዎቹ) ከገቢያቸው በአማካይ 60 በመቶ ለምግብ ያወጣሉ፡፡ (ገጠሬዎቹ አንዳንዴ ገቢያቸው ሆዳቸው ላይ ብቻ ሊውል ይችላል!) ይሄ አማካይ ለብዙሐኑና ገቢያቸው ዝቅተኛ ለሆነ ሰዎች ገላጭ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ምግብ ውድ ነው፡፡ ሙሉ ገቢያቸውን ለምግብ ብቻ የሚያውሉ ዜጎች አሉ፡፡ ሠርቶ ለምግብ ይሏችኋል ይሄው ነው፡፡

በአሜሪካ የማክዶናልድን በርገር (እዚያ በርገር ለምሳ መዳረሻ መሆኑን ልብ ይሏል!) ከ2 ዶላር በላይ አይከፍሉም፡፡ እኛ አገር በርገር ከተበላ፣ ምሳ ተበላ ማለት ቢሆንም ዋጋው (በማክዶናልድ ደረጃ ካሰብነው፤) በ40 ብርስ ይገኛል? አንዳንዶች ዶላርን በብር እየመነዘሩ ተመጣጣኝ ነው ሊሉ ይዳዳቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ያልገባቸው ነገር፣ ኢትዮጵያውያን ምንዳ የሚከፈላቸውም ሆነ የሚገበያዩት በብር መሆኑ ነው፡፡ 80 በመቶ ሕዝቦቿ አርሶ እና አርብቶ አደር በሆኑባት አገር ውስጥ ውዱ ነገር ምግብ መሆኑ አያሳዝንም? ግብርና መር ኢንዱስትሪ እየተከተልኩ ነው በምትል ሃገር ውስጥ በምግብ ራስን መቻል ቀርቶ ዘመናዊ የከተማ ችጋር ሰንሰለት ውስጥ መግባት፣ ባለሰማያዊ መስታወት ፎቆች እና የቀለበት መንገድ ስር ራሱን በራሱ የሚፈጭ ጨጓራ ይዘው የሚንከራተቱ ዜጎችን ማፍራትስ የማን ጥፋት ነው? ‘ከነገሩ፤ ጦም እደሩ’ ብለን ካልተውነው በስተቀር ከድህነት አረንቋችን እንዳንላቀቅ የሁለት አሥርት ዓመታት ድርሻውን የተጫወተው ማን እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የኑሮ ውድነቱ መንስኤ የውጭ (ያደጉ ሃገራት) የኢኮኖሚ ቀውስ ነው ይለናል፡፡ የዋጋ ንረቱ አንደኛ ተጠያቂ ግን በሃገር ውስጥ የሚመረተው ምግብ ነው፡፡ ለዚህ እማኝ መጥቀስ ካስፈለገ የአክሰስ ካፒታል የምርምር ክንፍ ያወጣውን ሪፖርት ማገላበጥ ይቻላል፡፡ በጥናቱ ውስጥ አገራችን ከቤላሩስ ቀጥሎ በዓለማችን ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት በማስተናገድ ላይ ያለች ሁለተኛዋ አገር ተብላ ተጠቅሳለች፡፡ (በነገራችን ላይ የአክሰስ ካፒታል መስራች አቶ ኤርምያስ አመልጋ ከብሔራዊ ባንክ ጋር የተቀያየሙት “በማያገባቸው” የአገር ጉዳይ ስለሚገቡ ይሆን እንዴ?)

የዋጋ ግሽበቱ ዓመታዊ ንጽጽር በጥር ወር በጣት በሚቆጠሩ ፐርሰንቶች መቀነሱን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ (ጉዳዩን አስቀድመው ለሰሙት የፓርቲ አጋሮቻቸው) በፓርላማ በኩል ሲናገሩ÷ የመንግስት እርምጃዎች ውጤት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ እውነታው ግን ሌላ ነው፡፡ አርሶ አደሮቻችን ምርታቸውን ለገበያ በገፍ የሚያቀርቡት ከታሕሳስ ወር ጀምሮ በመሆኑ፣ በጥር ወር የእህል ዋጋ በመጠኑ መቀነሱ የተለመደ ታሪካችን ነው፡፡ የዋጋ ግሽበቱ ዓመታዊ ንጽጽርም የዚሁ የአርሶ አደሮቻችን ውጤት አንጂ የመንግስት ግራ ገብቶት፣ ግራ የሚያጋባን ፖሊሲ ውጤት አለመሆኑን ግንቦት ላይ የምንመለስበት ይሆናል፡፡

ወቅቱ የጾም ነው፣ ስለምግብ ይህን ያህል ማውራት አልነበረብኝም፡፡ ነገር ግን ፋሲካ ይመጣል፡፡ ፋሲካ ሲመጣ ብቻውን አይመጣም፤ የመብላት ፍላጎት ይዞ ይመጣል፡፡ ወሩ ደግሞ ግንቦት የሚቃረብበት ነው፡፡ ገበሬዎች ለመጪው ክረምት እህላቸውን ይቆጥባሉ፡፡ እንደተለመደው የምግብ ዋጋ ይንራል፤ ኑሮ ያሻቅባል፡፡ እንደተለመደው የዘንድሮም ፋሲካ ከአምናው የከፋ ይሆናል፡፡ እንደተለመደው እስከመች ይኖራል?

እንደተለመደው ሳይሆን የተሻለ ኑሮ ለመኖር፣ ፋሲካንም ለመፈሰክ፣ መፈንቅለ መንግስት ብቻ ሳይሆን መፈንቅለ አእምሮም ያስፈልገናል፡፡ [አሁን ደግሞ እመርቃችኋለሁ፤] ሁለት ወር ሁዳዴ፣ ስለሰማዩ መንግስታችን ብቻ ሳይሆን ስለምድራዊው መብታችንም በአርምሞ የምናስብበት ይሁን፣ ያለመንግስት ተመርታ የማታውቀው ሃገራችን በሕዝቦቿ ፈቃደኝነት የምትመራበት ዘመንን የሚያመጣ አዕምሮ “ይስጠን”፣ መጾም መጸለይ ብቻ ሳይሆን መሥራትና መታገልም እንወቅበት፣ ፋሲካ ብቻ ሳይሆን freedomም ይናፍቀን፣ ስልጣኔም ይናፍቀን፡፡ አሜን!

Comments

Popular posts from this blog

The "Corridor Development" is a Façade of the Prosperity Party

Befekadu Hailu I have seen a news report claiming that 40% of central Addis Ababa will be demolished for the corridor development; I am not able to confirm the validity of the news but it sounds real to me given the size of massive operations in the demolition of old neighborhoods and construction of bike lanes, green areas, and glittering street lights. I like to see some beauty added to my city but cannot help mourning the slow death of it too. Addis Ababa was already in a huge crisis of housing and the demolition of houses is exacerbating it. Apparently, Prime Minister Abiy Ahmed is eager to showcase his vision of prosperity by demonstrating how fast his administration can do magic by beautifying the front sides of the streets with lights, new pavements, and painted fences ("to fake it until he makes it" in my friend's words). Therefore, he and his party do not care about the miserable human stories behind the scenes and they will harass you if you tell it (Azeb Woku...

የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ

በፍቃዱ ዘ . ኃይሉ “የአዲስ አበባ ብሔርተኝነት” ቢኖር ኖሮ መሪው ልጅ ሚካኤል ይሆን ነበር። አሁን አሁን እሱ ስለ አዲስ አበባ የዘፈናቸውን ዘፈኖች ቁጥር ራሱ በትክክል መቁጠር ይቸግረኛል። ለአዲስ አበባ ከተዘፈኑ ዘፈኖቹ ውጪም በየዘፈኑ ውስጥ የሚጨማምራቸው መልዕክቶች በራሳቸው መወድሰ አዲስ አበባ ናቸው። ለምሳሌ፣ በቅርቡ በለቀቀው ‘አዲስ አራዳ’ በተሰኘው አልበሙ ውስጥ ‘የድሬ ልጅ’ የሚል ዘፈን አለው። ዘፈኑ የተዘጋጀው ያው የአዲስ አበባ እህት ተደርጋ የምትቆጠረውን ድሬ ዳዋን ለማወደስ ነበር። ልጅ ሚካኤል ግን የአዲስ አበባ ፍቅሩ ያመልጠውና የሚከተለውን ያቀነቅናል፦ “መጣልሽ በሏት፣ ድሬ ድረስ፣  ከአዱ ገነት፣ ከሸገር፣ ከአዲስ ደረሰ፣... የሸገር ልጅ አራዳ ነው፣ ሰው አክባሪ፣ ሰው ወዳዱ፣ ቀላጅና ተረበኛ፣ ፍቅር ይዞ የሚተኛ፣ ‘አለው’ የለ፣ ‘የለው’ የለ፣ ከሁሉ ጋ፣ ግባ ጀባ...፤” ፤ ልጅ ሚካኤል በዚህ አልበሙ ብቻ አዲስ አበባን የሚያውድሰባቸው ሌሎችም ዘፈኖች አሉ፤ ‘ አዲስ አራዳ ’ የሚለው የአልበሙ መጠሪያ እና ‘ሸገር’ የሚሉት ዘፈኖቹ ዋነኞቹ ናቸው። ታዲያ እንዲህ በአዲስ አበባ ፍቅር የሚቃጠለው ልጅ ሚካኤል "ሊነግረን የሚፈልገው ምንድን ነው?" የሚለው ጥያቄ ደጋግሞ ይመጣብኛል። ይህ የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ ምንነትን ለመረዳት የሚጥር ፖለቲካዊ መጣጥፍ ነው። ‘አዲሱ አራዳ’ ማነው? በዚህ ዘፈኑ በብዙዎቻችን ዕድሜ የትዝታ ማኅደር ውስጥ የሚገኙ ነገር ግን በአዲስ አበባ ልማት ሥም የፈረሱ እና እየተረሱ ያሉ ሰፈሮችን ሥም ያነሳሳል። ዘፈኑ በግጥሙም በዜማውም፣ የሐዘን እንጉርጉሮ ያለበት ነው። ምሳሌ እንውሰድ፦ “ጨርሰሽ ስትወጪ ከቡፌ ዳ’ላጋ፣ ጠብቂኝ እንዳልል፣ ቆመሽ መሐሙድ’ጋ፣ አገር ...

መጽሐፍ የሚወጣው፣ የተዋነይ ዘ ጎንጅ 5 መሥመር ቅኔ

ጎንጅ ቅኔ ያጠናበት ደብር ሥም ነው። ደብረ ጥበብ ጎንጅ ቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም። ተዋነይ የባለቅኔው ሥም ነው። (የግዕዝ ትርጉሙ "ዋናተኛ" ማለት ነው።) ሊቁ ተዋነይ የልኅቀቱን ያክል እምብዛም አይወራለትም፤ ነገር ግን በዘመኑ ወደር የሌለው ልኂቅ ስለመሆኑ ሥራው ይናገራል። የሕይወት ተፈራ "Mine to Win" የተሰኘ ድርሰት መቼቱን በዐፄ ዮሓንስ ንግሥና ዘመን፣ በጎጃም/ጎንደር የቅኔ መማሪያ ደብሮች ያደረገ ልብወለድ ነው። ልቦለዱ የቅኔ ትምህርት ስርዓትን ያስተዋውቀናል፤ በበኩሌ የቅኔ ትምህርትን እና የቅኔ ሊቃውንት ታላቅነት ቀድሞ ከነበረኝ ግንዛቤ የበለጠ እንዲሆን አድርጎኛል። በተለይ የተዋነይ ዘ ጎንጅ (በውኑ ዓለም የነበረ ባለቅኔ) ተከታይዋ አምስት መሥመር ቅኔ መጽሐፍ የሚወጣት እንደሆነች ልቦለዱ አሳሰበኝ። ወይም በአጭሩ ብዙ ምዕራባውያን ስንት መጽሐፍ የጻፉለት ፍልስፍናን በአምስት መሥመር ይዟል። የቅኔው ትርጓሜ የመጽሐፍ ቅዱስን እና የመጽሐፍ ቅዱሱን ፈጣሪ ኅልውና ይሞግታል። “የአምን ወይገኒ ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ ብዙኃን እንዘ ይገንዩ ይስግዱ ቅድሜሁ ለነጽሮ ዝኒ ነገር እሥራኤል ከመይፍርሑ ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ ወ ፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ።” (ተዋነይ ዘ ጎንጅ። ምንጭ፣ሕይወት ታደሰ ወደአማርኛ የተረጎመችው የሕይወት ተፈራ መጽሐፍ) ትርጉሙን በኋላ እመለስበታለሁ። ስለተዋነይ መጀመሪያ የሰማሁት የበውቀቱ መጽሐፍ ላይ ነበር። እሱም በጨረፍታ - “የሌሊት ዜማዎች” የሚለው ግጥሙ ውስጥ። በውቀቱ ተዋነይን በግጥሙ ግርጌ ማስታወሻው አስተዋውቆን ያልፋል፣ “ተዋነይ በቅኔ ቤት አፈ ታሪክ ሞትን በግዝት ለሰባት ዓመታት ያቆመ ጀግና ነው"። ከዚያ በኋላ፣ አዲስ አድማስ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ተዋነይ የተላከበትን ...