Pages

Friday, October 28, 2011

“ይህ - የታገልንለትን ጉዳይ አለማወቅ ነው”

From Addis Ababa, Ethiopia
ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም በአንድ ወቅት በፈፀሙት ድርጊት ተፀፅተው ይቅርታ ይጠይቁ እንደሁ በገነት ‹ማስታወሻ› ላይ ሲጠየቁ ‹‹ማንን ነው ይቅርታ የምጠይቀው? ወያኔን? ወያኔ እኔን ይቅርታ ጠይቆኛል?...ይህ የታገልንለትን ጉዳይ አለማወቅ ነው›› በማለት ጥያቄውን በጥያቄ መልሰዋል፡፡ መንግስቱ በአስተዳደራቸው ማክተሚያ ሰሞንም፣ በመንግስት መገናኛ ብዙሐን እንዲህ ብለው ነበር፡፡ ‹‹ለአገሬና ለወገኔ ይበጃል ብዬ ባደረግኩትና በተሳተፍኩባቸው ተግባሮች ሁሉ በግሌ ሕሊናዬን የሚወቅሰኝ ነገር የለም›› ብለዋል፡፡

‹‹መ››ንግስቱ እና ‹‹መ››ለስ
መለስ በመንግስቱ ቆብ ውስጥ ገብተው ይሆን?

በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ዲሞክራት  መስለውን ነበር::
እኛን ብቻ ሳይሆን ምዕራባውያንንም በዚህ ሸውደዋቸዋል::
ምዕራብውያን ታዛዥነታቸውን ስለሚወዱላቸው ብቻ ተቀብለዋቸዋል::
የመለስ ታዛዥነት ለውጭ ኃይሎች ብቻ እንጂ ለአገራቸው ሕዝብ
አይደለም::  መለስ በውጭ ዲፕሎማሲ ጎበዝ የሚመስሉዋችሁ ከሆነ -
አይደሉም:: ሊደራደሩበት የሄዱትን ጉዳይ አሳልፈው በመስጠት
መስማማትን ይመርጣሉ::  ውጪያዊ ተቃውሞ የማይደመጥባቸውም
ለዚያ ነው::

በዴሞክራሲ ጉዳይ "ሙጋቤ የሚለው አፍሪካውያን የምዕራባውያን
ዓይነት ዴሞክራሲ  አያስፈልጋቸውም::" ብሎ ነው ብለው መለስ
ከጋዜጠኛ ጋር ከተሟገቱ በኋላ የዴሞክራሲ  በኢትዮጵያ ተስፋው
ተመናምኗል:: ሙጋቤ  መንግስቱን አስጠልለዋል - አሁን ደግሞ
መለስም  የርሳቸውን የዴሞክራሲ ቲዎሪ እየዘመሩ ነው::
መንግስቱና መለስ እያደር የሚያመሳስላቸው ነገር ተበራክቷል፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ነጋሶ ጊዳዳ ‹‹የነጋሶ መንገድ›› በተሰኘው ግለታሪካቸው እንደነገሩን የሕወሓት ተገንጣይ ቡድን ተሸንፎ ሲወጣ የነመለስ ቡድን (በተለይ አቶ መለስ) ‹‹ጃኬታቸውን አስወልቀን ሸኘናቸው›› እያሉ ሲፎክሩ ነጋሶ መለስን ‹‹መንግስቱን፣ መንግስቱን መሰልከኝ›› ብለዋቸዋል፡፡ እውነት ነው፤ (መ)ንግስቱና (መ)ለስ (መ)ንትያ ናቸው፡፡ እስኪ በዝርዝር እንመልከተው…
  • አነጋገር - መለስ ንግግር አዋቂ ናቸው፡፡ መንግስቱም ንግግር አዋቂ ነበሩ፡፡ መንግስቱ ለቃላት አመራረጥ አይጨነቁም ነበር፡፡ ስድብና ድንፋታ በየአደባባዩ አያሳፍራቸውም ነበር፡፡ መንግስቱ ከወረዱ ከ20 ዓመት በኋላ እርሳቸውን ከስልጣን ያስወገዱት አማፂያን መሪም ይኸው የሳቸውን ፈር እየተከተሉ ነው፡፡ መለስ በየፓርላማው አባሎቻቸውን በሚያስቀው ስድባቸው አንጀታቸው ስለማይርስ - አሁን፣ አሁን የእጅ እንቅስቃሴያቸው እና የትከሻቸው መናጥ የስድብ አምሮታቸውን ያሳብቅባቸዋል፡፡
  • ነፍስ ማጥፋት - የመንግስቱ ኃ/ማሪያም ኢሠፓ ከተቃዋሚዎቹ ኢሕአፓ ጋር በከተማ መሃል ሽምቅ ውጊያ የጀመረው ገና በስልጣኑ አፍላ ዘመን ነው፡፡ ቀይሽብር እና ነጭሽብርን በየበኩላቸው አውጀው ሲገዳደሉ ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ አላሰቡም ነበር፡፡ (ለመንግስቱ አምባገነንነት የኢሕአፓ ድርሻ ቀላል አይደለም) የአቶ መለስ ደግሞ ይብሳል፡፡ ደርግ አውጆ ሲገድል፣ ኢሕአዴግ ከቻለ በድብቅ/በሰበብ ካልቻለ ደግሞ ፕ/ር አለማየሁ ገብረማርያም በአንድ ጽሁፋቸው ላይ እንዳሉት ‹‹don’t kill them, break them›› የተሰኘ ዘዴ ይከተላል፡፡ የመለስ ዜናዊ ሰራዊት የጥይት አሩሩን ያሳረፈው እንደኢሕአፓ የመሳሪያ ትግል በጀመሩ ተቃዋሚዎች ላይ አይደለም፡፡ ከድንጋይ መወርወር በላይ አቅም በሌላቸው ወጣቶች ላይ ነው፡፡
  • ስልጣን - መንግስቱ ለ17 ዓመታት ያህል መተኪያ ያልተገኘላቸው መራሄ መንግስት ሆነው ነበር፤ አሁን ደግሞ መለስ 25ኛቸውን ዓልመው እየተጓዙ ነው፡፡
  • ነፃነት - በደርግ ጊዜ መንግስትን መቃወም ቀርቶ ለመቃወም ማሰብም የሚያስፈራ ነገር ነበር፡፡ አሁንም ነገሩ ብዙ የተለየ አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው መቃወም ይፈራል፤ በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ዋጋውን እንደሚቀምስ ያውቀዋል፡፡ የእንግሊዙ Legatum Institute አምና ባወጣው የProsperity Index ላይ ኢትዮጵያ በግለሰብ ነፃነት ከ110 አገሮች 93ኛ እና በሕዝቦቿ የደህንነት ስሜት ደግሞ 103ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች የፈሪዎች አገር ሁናለች - የነፃነቱ ብዛት፡፡
  • ኢኮኖሚ - በደርግ ዘመን (ዕድሜ ለአማፅያን) መንግስቱ አብዛኛውን የበጀት ፈሰሳቸውን ለጦርነት በማዋላቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ በረሃብና ችግር አለንጋ እየተገረፈ ነበር፡፡ አሁንም በመለስ ሕንፃዎች በሚፈሉበት፣ መንገዶች እየዘመኑ ባሉበት ዘመን ድህነት ከነኩራቱ ለ‹‹99 በመቶዎቹ›› ሕዝቦች ይታያቸዋል፡፡ ከላይ የጠቀስኩት ኢንዴክስም ይህንኑ ያረጋግጣል፤ ከ110ሩ ሃገራት 106ኛ ላይ የመለስ ኢትዮጵያ ትገኛለች፡፡

ስለዚህ መለስ ከመንግስቱ ይለያሉ ወይስ አይለዩም?

ማወዳደርን ምን አመጣው?
መለስ ራሳቸው አሁን፣ አሁን አስተዳደራቸውን ከመንግስቱ ዘመን አስተዳደር አንፃር መመዘን ጀምረዋል፡፡ ምነው እንኳን ባለፈው ኦስሎ ውስጥ ለገጠማቸው ተቃውሞ የሰጡት ማስተባበያ ‹‹በመንግስቱ ዘመን ሰዎች ሲገደሉ ለተገደሉበት ጥይት ሒሳብ ይከፍሉ ነበር›› አላሉም? ነገሩን የታዘቡት የአዲስ ነገር ጋዜጠኞች ‹የአገር ቤት ጋዜጦች› በተሰኘው ሳምንታዊ ክለሳቸው ‹‹መለስ ይህን ያሉት፣ አሁን እኛ ነን የጥይቱን ዋጋ የምንሸፍነው ለማለት ፈልገው ይሆን?›› ሲሉ ተሳልቀዋል፡፡

መለስ ማነፃፀር ከጀመሩ አይቀር እኔም አንድ ነገር ልጨምርላቸው፡፡ መንግስቱ ኃይለማርያም ሲታገሉ የነበረው ለምን እንደሆነ ማስታወስ ነበረባቸው፡፡ መንግስቱ ኃ/ማርያም ሲታገሉ የነበሩት፤ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ነበር፡፡ ከመለስ ሰራዊት ጋር ሲታገሉ በመክረማቸው ነበር አምባገነን አድርጎ ያስቀራቸው፡፡ (በርግጥ የርሳቸው፣ የፍላጎት ድርሻ ውስጡ ቢኖርም) የመንግስቱ አስተዳደር ከጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስትነቱ ለመላቀቅ እንኳን ፋታ ሳያገኝ ነው በትግል ወጥቶ በትግል የኮበለለው፡፡ መንግስቱ የፈሩት አልቀረም፤ የኢትዮጵያ አንድነት በብሔር ዘመም አስተሳሰቦች ከተናጋ ውሎ አድሯል፣ የባሕር በር ባለቤትነታችንም ድሮ ቀረ፡፡

ምናልባት የመንግስቱን የጭካኔ ዘመን ስላልደረስኩበት ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ለኔ ‹‹ለሰላም ሲባል›› የአገራቸውን ድንበር በሱዳንም፣ በሶማሌያም፣ በኬንያም፣ በኤርትራም በኩል እየቆረሱ ያልሰጡት፣ (መንገዱን ባያውቁበትም) ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያዊነት ያላቸው ፍቅር የማያጠያይቀው፣ ሚሊዬነር ሊሆኑ ቀርቶ ለራሳቸው ምንም ቅሪት ሳያጠራቅሙ የኖሩት መንግስቱ፣ ይህንን ሁሉ መሆን ካልቻሉትና ከእርሳቸው (ኮ/ል መንግስቱ) ስህተት መማር ካልቻሉት ከአቶ መለስ ይሻሉኛል፡፡

አሁን ደግሞ፤ ኮሎኔል መንግስቱ ‹ትግላችን› በሚል በፀሃይ አሳታሚ (ከአሜሪካ) አማካኝነት እያሳተሙት ባለው የመጀመሪያው ቅጽ መጽሃፋቸው ላይ ‹‹የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ መሪ ግለሰቦች የሚመጡና የሚሄዱ አላፊዎች ሲሆኑ ሃገርና ሕዝብ ግን ዘላለማዊ ናቸው፡፡ ይህም ቢሆን በአንድ ታሪካዊ ወቅት መንግስታት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ወይም ግለሰቦች ያከናወኗቸው ገንቢም ሆነ አፍራሽ ተግባሮች ማንም ወደደ ጠላ የዚያ ሃገርና ሕዝብ ታሪክ ናቸው›› ብለዋል፡፡

ታዲያ ለምን ይሆን መለስ ዜናዊ ከመንግስቱ የተሸሉ መሆን ባይችሉ እንኳን የመንግስቱ ኃ/ማርያምን ታሪክ መድገም ያስፈለጋቸው?

No comments:

Post a Comment