Skip to main content

“አሰብ የማን ናት?”ን በጨረፍታ


በ260 ገጾች ተቀንብቦ የተጻፈው የዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም ‹‹አሰብ የማን ናት?›› ዶ/ሩን የሚያስመሰግን፣ ኢትዮጵያውያንን የሚያነቃቃ ነው፡፡ መጽሃፉን እያነበብኩ እያለሁ ይሰማኝ የነበረው ስሜት በመዳን ላይ ያለ ቁስል ዳርዳሩን ሲያኩት የሚሰጠውን ዓይነት ስሜት ነበር፡፡ (የምታውቁት ካላችሁ)

የመጽሃፉ መግቢያ፣ የመጀመሪያው አንቀጽ ‹‹ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የታሪክ ወቅቶች በአገር ውስጥ ብቅ ያሉ አምባገነን መሪዎች የጫኑባቸውን በደሎች ሰው ሰራሽም ሆኑ ተፈጥሮ የወለደቻቸውን ችግሮች በትዕግስት ያስተናገዱ ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያን በትዕግሰት የማይመለከቱት ነገር ቢኖር የድንበር መደፈርን ነው ማለት ይቻላል፡፡›› ይላል፡፡

የመጽሃፉ ዓላማ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሰብ የኢትዮጵያ መሆኗን አውቆ የባሕር በራችንን ማስመለስ ብሔራዊ ግዴታችን እንደሆነ ለማስታወስ መጣር መሆኑም በመግቢያው ላይ ተገልጧል፡፡
ምዕራፍ አንድ፤ የባሕር በርና ፋይዳው
ኢትዮጵያ የምትከራያቸው የጎረቤት አገር ወደቦች ርቀታቸው ከአዲስ አበባ፣ ከ910 ኪ.ሜ. (ጅቡቲ) እስከ 1804 ኪ.ሜ. (ሞምባሳ) ይደርሳሉ፡፡ የአሰብ ወደብን ብንጠቀም ግን 640 ኪ.ሜ. ብቻ (ከኢትዮጵያ የአሁኑ ክልል ደግሞ 60 ኪ.ሜ. /የእግር መንገድ ርቀት/) ወይም ከጅቡቲ አንፃር የአንድ ቀን የመኪና ጉዞ መቅረብ ትችላለች፡፡

ወደብ የሌላቸው ድሃ ሃገራት የውጭ ንግዳቸው ከ33 እሰከ 43 በመቶ ሊቀንስ ይችላል፡፡ ከዚህም በላይ ኢትዮጵያ ለወደብ ኪራይ በየቀኑ ከ3 ሚሊዮን ዶላር (ልብ በሉ ብር አላልኩም በየቀኑ 3 ሚሊዮን ዶላር) ታወጣለች፡፡ ከዚህም በከፋ መንገድ በኢኮኖሚ ዕድገት አንድ ወደብ ያለው አገር በ24 ዓመት ኢኮኖሚው እጥፍ ማደግ ሲችል፣ ወደብ የሌለው ግን 36 ዓመት ይፈጅበታል፡፡

ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ከሆኑ አገራት መካከል በሕዝብ ብዛት አንደኛዋ ስትሆን ብሔራዊ ደህንነቷ በዚሁ ምክንያት ስጋት ላይ ወድቋል፡፡

‹‹…ኢትዮጵያ ያለወደብ ቀረች ብለን የምንቆጭበትና የምናዝንበት ምክንያት የለም፡፡…›› - ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፡፡

ምዕራፍ ሁለት፤ የባሕር በርና ታሪካችን
ዶ/ር ያዕቆብ በዚህ ምዕራፍ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርና የአሰብ ወደብ ባለቤት መሆኗን የሚያረጋግጡ በርካታ ጽሁፎችን ያጣቀሱ ሲሆን ከሁሉም የሚገርመው ደግሞ ከአጼ ዮሐንስ እስከ መንግሰቱ ኃ/ማሪያም ያሉ መሪዎቻችን ለባሕር በር ያላቸውን ተቆርቋሪነት በማስረጃ እያስደገፉ ካስነበቡን በኋላ በመጨረሻው ንዑስ ምዕራፍ ኢሕአዴግ በተቃራኒው አሰብን በተናጠል እና ኤርትራን በጥቅሉ ለማስገንጠል ያደረገውን ተጋድሎ ከብዙ አቅጣጫዎች ይተነትናሉ፡፡ በዚህም ኢትዮጵያን የባሕር በር አልባ ለማድረግ የተጉትን አቶ መለስንና ሕወሓትን እንድንታዘባቸው፣ ብሎም ‹‹ኢትዮጵያዊነታቸውን›› የሚያጠራጥረን ጥሬ ሃቆችን ያስቀምጡልናል፡፡

‹‹በአንድ ሰው (የመለስ) የዓይን ጥቅሻ ኢትዮጵያ በ60 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቀይ ባሕረ ሰላጤ ሙሉ ለሙሉ ተገለለች፡›› - ፕሮፌሰር ፀጋዬ መብራሕቱ፡፡

ምዕራፍ ሦስት፤ አሰብ የኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት ስለመሆኗ
የኤርትራ መገንጠል እና የድንበር ማካለሉ ጉዳይ ኤርትራ በጣሊያን አገዛዝ ስር በነበረችበት ጊዜ ከነበረው እውነታ  በመነሳት የተካሔደ እንደሆነ ኢሕአዴጎች ሲነግሩን ቢቆዩም ዶ/ር ያዕቆብ ግን ይህ ሕጋዊ ዕውቅና እንደሌለው በማስረጃ አስደግፈው በመጽሃፋቸው ያስረዱናል፡፡

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጣሊያንን ያሸነፉትና ኤርትራን የተረከቡት አራቱ ኃያላን መንግስታት (አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ሶቪየት ሕብረት) አሰብ ወደኢትዮጵያ መጠቃለል እንደሚገባው በሐሳብ ደረጃ (በ1947ዓ.ም.) ከተስማሙ በኋላ የተባበሩት መንግስታት በጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ ቁጥር 390(V) መሰረት ኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤት ለማድረግ ሲባል ኢትዮጵያና ኤርትራ በፌዴሬሽን እንዲቀላቀሉ ተወሰነ፡፡ በ1952ዓ.ም. ተቀላቀሉ፤ ፌዴሬሽኑ በ1962ዓ.ም. ወደ ውህደት ተቀየረ፡፡


‹‹…ሰሜንና ደቡብ ሱዳን መለያየት አልነበረባቸውም፡፡…..ይህ የሆነው ለሱዳናውያን ታስቦ ሳይሆን ሱዳንን ለመበታተን ነው፡፡›› - ኢሳያስ አፈወርቂ፡፡

ምዕራፍ አራት፤ ስለኤርትራ መገንጠል ኢ-ሕጋዊነት
የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል የሚባለው መብት በሕግ የሚረጋገጠው በሦስት መንገዶች እንደሆነ ዶ/ር ያዕቆብ ይገልፃሉ፡፡ አንደኛ፡- አገሪቷ በቅኝ ግዛት ተይዛ ከነበር፣ ሁለተኛ፡- በባዕድ ጦር ትተዳደር ከነበር እና ሦስተኛ፡- ብዙ ዘሮች ያሉበት አገር አንዱን ዘር ካገለለና ከጨቆነ - ተጨቋኟ አገር መገንጠል ትችላለች፡፡ ኤርትራም የተገነጠለችው ሕወሓት አገሪቱ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት ብሎ በመመስከሩ ነው፡፡

ይሄ ግን እውነታና ሕጋዊነት የጎደለው መሆኑን ጸሃፊው ይከራከራሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ኤርትራ በተገነጠለችበት ወቅት አገልግሎት ይሰጥ የነበረውን የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 253 እና የአፍሪካ አንድነት ቻርተር አንቀፅ ሁለትን የሚጥስ ቢሆንም በኢትዮጵያ መንግስት ያላሰለሰ ጥረት የአፍሪካ አንድነትና የተባበሩት መንግስታት የኤርትራን መገንጠል ማፅደቅ ሳያስፈልጋቸው ተቀብለውታል፡፡

‹‹ታሪክና ሕግ የሚሉት ዝባዝንኬ ለትምህርት ቤት ይተዉት ይህ ፖለቲካዊ ጉዳይ በጦር ሜዳ ተፈትቷል፡፡›› - ኢሳያስ አፈወርቂ በ1983ዓ.ም. ፕሮፌሰር አስራት የአሰብ ወደብ ወደኢትዮጵያ መካለል እንዳለበት ታሪክም፣ ሕግም ያስገድዳል ባሉ ጊዜ የተሳለቁባቸው፡፡

ምዕራፍ አምስት፤ የአልጀርስ ስምምነት ኢ-ፍትሐዊነት ሲገመገም
የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበር ማካለልን በተመለከተ ብያኔ የተካሔደበት የአልጀርሱ ስምምነት መሠረት ያደረገው የኢትዮ-ጣሊያን የቅኝ ግዛትን ስምምነት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ መጽሃፉ ይህንን ውል ከወቅቱ የተዋዋዮቹ አቅም ልዩነት፣ ከውሉ ኢ-ፍትሐዊነትና ሌሎችም አንፃር ውድቅ ያደርገዋል፡፡

እነዚህ ጥንታዊ ውሎች ኢትዮጵያ ላይ በጣሊያን በግድ በመጣላቸው፣ ጣሊያን ውሉን ጥሳ ኢትዮጵያን በመውረሯ፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጣሊያን ቅኝ ግዛቷን በመነጠቋ እና ኢትዮጵያና ኤርትራ የኋላ ኋላ በመዋሃዳቸው የተሰረዙ በተደጋጋሚ የተሰረዙ ውሎች ናቸው፡፡ የኢሕአዴግ መንግስት ግን ይህንን እውነታ ሽሮ በአልጀርሱ ስምምነት በኢትዮ-ጣሊያን በተሻሩ ውሎች ለመቀጠል መስማማቱ በድንበር ማካለሉ ሥራ የወደብ ባለቤትነታችን ሊረጋገጥ ቀርቶ ቤተክስትያንና የመቃብር ቦታው ከዚያም በላይ አንድ ትምህርት ቤት ለሁለት እንዲከፋፈሉ ሁነዋል፡፡

ይህንንም ዶ/ር ያዕቆብ ሲገልጹት ‹‹አንድም ስህተት፥ ሲከፋም ክህደት›› ነበር ብለው ነው፡፡

ምዕራፍ ስድስት፤ የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ሲገመገም
ሁለቱ ‹‹የሐበሽ›› መሪዎች ተኮራርፈው የታዩበት የአልጀርሱ ስምምነት፣ በርካታ ግድፈቶች እንደነበሩበት ጸሃፊው ገልፀዋል፡፡ አገራቱ ለድርድሩ ተወካዮችን ሲሾሙ ኢትዮጵያ ከ14ቱ ተወካዮቿ 11ዱ እጅግ ብዙ ገንዘብ የገዛቸው የውጭ ዜጎች መሆናቸው (በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ለድርድሩ 9 ሚሊዮን ዶላር አባክናለች) በኢትዮጵያ ተቆርቋሪነት እንዳይከራከሩ አግዷቸዋል፤ የባሕር በርን የሚዘጋ፣ ባድመን፣ ኢሮብን፣ ጾረናን፣ ከፊል አፋርንና ሌሎችም የኢትዮጵያ ግዛቶችን ለኤርትራ አሳልፎ የሚሰጥ ውዝግብ በ285 ቀናት ውስጥ መጠናቀቁ የጊዜ ሰሌዳውን አጠያያቂ ያደርገዋል፤ በሌላ በኩል ድርድሩ የተካሄደባት አገር አልጀርስ (አልጄሪያ) የኤርትራን መገንጠል ከጥንስሱ ጀምሮ ትደግፍ የነበረች ከመሆኗም ባሻገር የድርድሩ አጋፋሪ የነበሩት ሚስተር አብዱል አዚዝ ቡተፍሊካ (የወቅቱ የአ.አ.ድ ሊቀመንበር) ለኤርትራ መገንጠል የሃገራቸው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በነበሩበት ጊዜ የሰሩ ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከኢትዮጵያ እንዲነሳ ጥረው አልተሳካላቸውም፡፡

ዳኞቹ ለውሳኔ የቀደሙትን ውሎች እንዲጠቀሙ ከመገደዳቸውም በላይ የክርክሩ ፍሬ ነገር በተለይ በኢትዮጵያውያን ወገን የወደብ ጥያቄ ላይ ትንፋሽ አለማሰማቱ በመጽሃፉ ተገልጧል፡፡

‹‹የጦር ሜዳው ድል በዓለም አቀፍ መድረክም ተደገመ፤ ባድመ ለኢትዮጵያ ተፈርዶላታል፣ ባድመ የኢትዮጵያ ሉዐላዊ ግዛት መሆንዋ ተረጋገጠ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደስ ይበልህ፤ ደስታህን አደባባይ ወጥተህ ግለጽ፡፡›› - የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስዩም መስፍን (ውሸት ወይም ስህተት ነበር)

ምዕራፍ ሰባት፤ በድርድሩ ኢትዮጵያ ለኤርትራ ያስረከበቻቸው መብቶች
በአልጀርሱ ድርድር ወቅት ኢትዮጵያን የወከለው ቡድን ባብዛኛው ይከራከር የነበረው ለኤርትራ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ድንበር በተሰረዘው ‹‹ውል›› መሰረት ከምስራቅ 60 ኪሜ ገባ ብሎ ስለነበረ የምስራቅ ጠረፍ የሚባለውን ከደሴቶቹ ሳይሆን ባሕሩ ከሚያልቅበት የየብሱ ጫፍ እንዲጀምር ተከራክረዋል፣ ከዚህም በላይ ቡሬን ድንበር አድርጎ በማካለል ከ60ኪሜ በላይ ወደኢትዮጵያ ዘልቀዋል፡፡ ኢትዮጵያን የወከለው ቡድን ጾረና የኤርትራ ነች ብሎ ድርቅ በማለቱ ካርታው ልዩ ቅርጽ ሠርቶ ጾረና ወደኤርትራ መከለሏ በካርታ ሳይቀር በመጽሃፉ ላይ ተመላቷል፡፡

በዚህ መንገድ ከኢጣልያ የተቀላቀለችው ኤርትራ ‹‹የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት›› ተብላ ስትገነጠል ‹‹ባለህበት እርጋ›› የተሰኘው የድህረ ቅኝ ግዛት መርሕም አልተከበረም፡፡

የድንበር ኮሚሽኑ መሬቱን ሲያከፋፍል የተለያዩ የሰብአዊ መብቶችን (የዜግነት መብቶችን) እንዳሻው በመከፋፈል ጥሷል፡፡ የኢትዮጵያ ሰራዊትም በጦርነቱ ወቅት የአሰብ ወደብን መቆጣጠር ሲችል በገዢዎቻችን ትዕዛዝ ወደኋላ አፈግፍጓል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ሽንፈትን ከድል መንጋጋ ፈልቅቃ አወጣች›› - ፕሮፌሰር ክላፋም

ምዕራፍ ስምንት፤ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ስለመሰረዝ
የኢሕአዴግ መንግስት ባድመ ለኤርትራ መሰጠቷን ካወቀ በኋላ በጣም ደንግጦ ነበር፡፡ ሆኖም የኮሚሽኑን ውሳኔ ለመሰረዝ የሚያመቹ በርካታ ዕድሎች አጋጥመውት ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል፡፡

ከነዚህ ዕድሎች አንዱ ኢሕአዴግ እንደጠቀሰው የኤርትራ መንግስት የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለመጣስ ያደረገው ሙከራ ነው፤ ሌላው ኮሚሽኑ ድንበር በማካለል ወቅት ችካል የመቸከል ኃላፊነት ቢሰጠውም ምናባዊ ማካለል (virtual demarcation) በመጠቀም ኃላፊነቱን አጓድሏል፡፡ በተጨማሪም የኤርትራ መንግስት አንዳንድ የሰላም አስከባሪ አባላትን ማባረሩን አስመልክቶ ውሳኔው ባይሰረዝም ለኢትዮጵያ ግን ውሳኔውን የመሰረዝ መልካም አጋጣሚ ነበር፡፡

ምዕራፍ ዘጠኝ፤ የሌሎች ኢትዮጵያዊ አካላት ትግል
በአሰብ ኢትዮጵያዊነት ዙሪያ በርካታ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማሕበራትና ሕዝባዊ ድርጅቶች እየታገሉ ነው፡፡ መድረክና በውስጡ ያሉት ሁሉም ፓርቲዎች፣ ኢዴፓ እና ሌሎችም በርካቶች በአሰብ ኢትዮጵያዊነት ላይ የጸና አቋም አላቸው፡፡ ሆኖም በዚህ ወቅት ሕዝቡን በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥና ለማንቃት እየሰሩ ነው ማለት አይቻልም፡፡

‹‹የዛሬው ትውልድ ትግሉን ይጀምር፤ ቀጣዩ ትውልድ ደግሞ ይጨርሰዋል›› - አቶ ልደቱ አያሌው

ምዕራፍ አሥር፤ አሰብ - የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ባሕር
በዚህ ምዕራፍ አሰብ የኢትዮጵያ ንዋይ የፈሰሰባት ወደብ ብቻ ሳትሆን በግድ የኤርትራና የኢትዮጵያ ተብለው የተከፈሉት ነገር ግን በተፈጥሮ፣ ባሕልና ሃይማኖት አንድ የሆኑት የአፋር ሕዝቦች ንብረት መሆኗ ይታወቃል፡፡

የጅቡቲ ወደብ በርቀቱ፣ በየጊዜው በሚጨማመረውና በሚለዋወጠው ታሪፉ፣ በዱባይ ኩባንያ በመተዳደሩ፣ ኢትዮጵያ ማንኛውንም ነገር ለማስገባት የጅቡቲን ይሁንታ መጠበቅ ስለሚኖርባትና በሌሎችም ፈፅሞ የአሰብን መተካት አይችልም፡፡ በሌላ በኩል በአባይ ጉዳይ በዓይነ ቁራኛ የምትከታተለን ግብፅ እና ወዳጆቿ አረብ አገራት ኢትዮጵያ የራሷ ወደብ ኖሯት እንድትረጋጋና እንድትበለጽግ አይፈልጉም - ተባብረውም ያሴራሉ፡፡

የኢሕአዴግ መሪዎች አንዲት አገር ያለወደብ ታላቅ መሆን እንደምትችል ቢለፍፉም ወደብ የሌላቸው እነኦስትሪያ፣ ስዊዘርላንድ እና ሉክሰምበርግ በጎረቤቶቻቸው ብልጽግናና የንግድ ሽርክና (እኛጋ የሌለ) ተደግፈው ሃብታም ሆኑ እንጂ ታላቅ አልሆኑም፡፡

‹‹የአፋር ሕዝብ ወሰን ቀይ ባሕር ነው፡፡ ግመሎቻችን እንኳን የኢትዮጵያን ባንዲራ ያውቋታል›› - ክቡር ቢትወደድ ሡልጣን አሊ ሚራህ

ምዕራፍ አሥራ አንድ፤ ካሜሩንና ናይጄሪያ Vs. ኢትዮጵያና ኤርትራ
ካሜሩንና ናይጄሪያ ሞልቶ ከተረፋቸው ወደብ ባካሲ በምትባለዋ ወደብ ባለቤትነት ተጋጭተው ጉዳዩን ወደዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ወስደውና በሚገባ ተከራክረው ወደቧ ለካሜሩን የተፈረደችበት ሒደት በሁለቱም አገራት ምን ያህል ሃገራዊ ቀናኢነት እንዳላቸው በሚያስመሰክር መንገድ ነበር፡፡ በዚያ ላይ ከፍርዱ በኋላ በባካሲ የሚኖሩት ሕዝቦች በመረጡት ዜግነት ያለምንም መዋከብ እዚያው እንዲኖሩ አገራቱ መስማማታቸው የሚያስቀናቱ ነው፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግስት የተወሳሰበ አካሔድ፣ ለሕግ እምቢተኝነትና የኢትዮጵያ መንግስት ግዴለሽነት የካሜሩንና የናይጄሪያ ተቃራ ነው ለማለት ይቻላል፡፡

‹‹For us Bakasi is real. It is men, women and children. It is people living in their homes, on their land. We are Nigerian citizens. We do not have any other place to go›› - ናይጄሪያውያን ውሳኔውን የተቃወሙበት

ምዕራፍ አሥራ ሁለት፤ የመፍትሔ ጥቆማዎች
ዶ/ር ያዕቆብ የኢትዮጵያውያንን እና ኤርትራውያን አንድነት የገለፁት ‹‹ተመሳሳይ ፊደል፣ ቋንቋ፣ አለባበስ፣ ምግብ፣ ስሞች፣ አስተራረስ፣ የኑሮ ዘይቤና አስተሳሰብ›› ያላቸው ሲሉ ነበር፡፡ የእነዚህን ሕዝቦች ተፈጥሯዊ አንድነት በማገናዘብም ነው የመፍትሔ ሐሳቦቹን የጠቆሙት፡-
  • አሰብን ከነደሴቶቹ ወደ ኢትዮጵያ አጥፎ ሁለቱ አገራት ጤናማ የንግድ እና ማሕበራዊ ግንኙነት እንዲኖራቸው ማድረግ፣
  • (የአሰብ ኢትዮጵያዊነት ባያጠያይቅም ለሰላም ሲባል) ኤርትራ የእርሻ መሬት ስለሚያስፈልጋት ከኢትዮጵያ ክልል ቆርሶ ሰጥቶ በምትኩ አሰብን እና ደሴቶቹን መውሰድ፣
  • አሰብን ከነደሴቶቹ ሁለቱም አገራት ይዘውት ጣምራ ሉዐላዊነት (Joint sovereignty) እንዲኖራቸው መስማማት፡፡

በነዚህ መንገዶች ብዙ አገራት የወደብ ባለቤት ሆነው በፍቅርም መኖር ችለዋል፡፡ እንኳን የገዛ ወደብን መውሰድ ቀርቶ ወደብ ለሌለው መስጠትም ተደርጎ ያውቃል ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከአንጎላ፣ ፖላንድ ከጀርመን ወደብ ተሰጥቷቸው የወደብ ባለቤት ለመሆን በቅተዋል፡፡

መጽሃፉ ከዚህም በላይ ሊነበብ ይገባዋል፡፡ እኔ ግን ዶ/ር ያዕቆብን እያመሰገንኩ በዚሁ ልቋጨው፡፡

Comments

  1. እንደማትመለስ ሆዴ እያወቀው፤
    መምጫዋን አያለሁ እንደቀጠረ ሰው፡፡
    …ብለህ አልቅስ አልቅስ አለኝ፡፡

    ReplyDelete

Post a Comment

Popular posts from this blog

The "Corridor Development" is a Façade of the Prosperity Party

Befekadu Hailu I have seen a news report claiming that 40% of central Addis Ababa will be demolished for the corridor development; I am not able to confirm the validity of the news but it sounds real to me given the size of massive operations in the demolition of old neighborhoods and construction of bike lanes, green areas, and glittering street lights. I like to see some beauty added to my city but cannot help mourning the slow death of it too. Addis Ababa was already in a huge crisis of housing and the demolition of houses is exacerbating it. Apparently, Prime Minister Abiy Ahmed is eager to showcase his vision of prosperity by demonstrating how fast his administration can do magic by beautifying the front sides of the streets with lights, new pavements, and painted fences ("to fake it until he makes it" in my friend's words). Therefore, he and his party do not care about the miserable human stories behind the scenes and they will harass you if you tell it (Azeb Woku...

መጽሐፍ የሚወጣው፣ የተዋነይ ዘ ጎንጅ 5 መሥመር ቅኔ

ጎንጅ ቅኔ ያጠናበት ደብር ሥም ነው። ደብረ ጥበብ ጎንጅ ቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም። ተዋነይ የባለቅኔው ሥም ነው። (የግዕዝ ትርጉሙ "ዋናተኛ" ማለት ነው።) ሊቁ ተዋነይ የልኅቀቱን ያክል እምብዛም አይወራለትም፤ ነገር ግን በዘመኑ ወደር የሌለው ልኂቅ ስለመሆኑ ሥራው ይናገራል። የሕይወት ተፈራ "Mine to Win" የተሰኘ ድርሰት መቼቱን በዐፄ ዮሓንስ ንግሥና ዘመን፣ በጎጃም/ጎንደር የቅኔ መማሪያ ደብሮች ያደረገ ልብወለድ ነው። ልቦለዱ የቅኔ ትምህርት ስርዓትን ያስተዋውቀናል፤ በበኩሌ የቅኔ ትምህርትን እና የቅኔ ሊቃውንት ታላቅነት ቀድሞ ከነበረኝ ግንዛቤ የበለጠ እንዲሆን አድርጎኛል። በተለይ የተዋነይ ዘ ጎንጅ (በውኑ ዓለም የነበረ ባለቅኔ) ተከታይዋ አምስት መሥመር ቅኔ መጽሐፍ የሚወጣት እንደሆነች ልቦለዱ አሳሰበኝ። ወይም በአጭሩ ብዙ ምዕራባውያን ስንት መጽሐፍ የጻፉለት ፍልስፍናን በአምስት መሥመር ይዟል። የቅኔው ትርጓሜ የመጽሐፍ ቅዱስን እና የመጽሐፍ ቅዱሱን ፈጣሪ ኅልውና ይሞግታል። “የአምን ወይገኒ ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ ብዙኃን እንዘ ይገንዩ ይስግዱ ቅድሜሁ ለነጽሮ ዝኒ ነገር እሥራኤል ከመይፍርሑ ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ ወ ፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ።” (ተዋነይ ዘ ጎንጅ። ምንጭ፣ሕይወት ታደሰ ወደአማርኛ የተረጎመችው የሕይወት ተፈራ መጽሐፍ) ትርጉሙን በኋላ እመለስበታለሁ። ስለተዋነይ መጀመሪያ የሰማሁት የበውቀቱ መጽሐፍ ላይ ነበር። እሱም በጨረፍታ - “የሌሊት ዜማዎች” የሚለው ግጥሙ ውስጥ። በውቀቱ ተዋነይን በግጥሙ ግርጌ ማስታወሻው አስተዋውቆን ያልፋል፣ “ተዋነይ በቅኔ ቤት አፈ ታሪክ ሞትን በግዝት ለሰባት ዓመታት ያቆመ ጀግና ነው"። ከዚያ በኋላ፣ አዲስ አድማስ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ተዋነይ የተላከበትን ...

የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ

በፍቃዱ ዘ . ኃይሉ “የአዲስ አበባ ብሔርተኝነት” ቢኖር ኖሮ መሪው ልጅ ሚካኤል ይሆን ነበር። አሁን አሁን እሱ ስለ አዲስ አበባ የዘፈናቸውን ዘፈኖች ቁጥር ራሱ በትክክል መቁጠር ይቸግረኛል። ለአዲስ አበባ ከተዘፈኑ ዘፈኖቹ ውጪም በየዘፈኑ ውስጥ የሚጨማምራቸው መልዕክቶች በራሳቸው መወድሰ አዲስ አበባ ናቸው። ለምሳሌ፣ በቅርቡ በለቀቀው ‘አዲስ አራዳ’ በተሰኘው አልበሙ ውስጥ ‘የድሬ ልጅ’ የሚል ዘፈን አለው። ዘፈኑ የተዘጋጀው ያው የአዲስ አበባ እህት ተደርጋ የምትቆጠረውን ድሬ ዳዋን ለማወደስ ነበር። ልጅ ሚካኤል ግን የአዲስ አበባ ፍቅሩ ያመልጠውና የሚከተለውን ያቀነቅናል፦ “መጣልሽ በሏት፣ ድሬ ድረስ፣  ከአዱ ገነት፣ ከሸገር፣ ከአዲስ ደረሰ፣... የሸገር ልጅ አራዳ ነው፣ ሰው አክባሪ፣ ሰው ወዳዱ፣ ቀላጅና ተረበኛ፣ ፍቅር ይዞ የሚተኛ፣ ‘አለው’ የለ፣ ‘የለው’ የለ፣ ከሁሉ ጋ፣ ግባ ጀባ...፤” ፤ ልጅ ሚካኤል በዚህ አልበሙ ብቻ አዲስ አበባን የሚያውድሰባቸው ሌሎችም ዘፈኖች አሉ፤ ‘ አዲስ አራዳ ’ የሚለው የአልበሙ መጠሪያ እና ‘ሸገር’ የሚሉት ዘፈኖቹ ዋነኞቹ ናቸው። ታዲያ እንዲህ በአዲስ አበባ ፍቅር የሚቃጠለው ልጅ ሚካኤል "ሊነግረን የሚፈልገው ምንድን ነው?" የሚለው ጥያቄ ደጋግሞ ይመጣብኛል። ይህ የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ ምንነትን ለመረዳት የሚጥር ፖለቲካዊ መጣጥፍ ነው። ‘አዲሱ አራዳ’ ማነው? በዚህ ዘፈኑ በብዙዎቻችን ዕድሜ የትዝታ ማኅደር ውስጥ የሚገኙ ነገር ግን በአዲስ አበባ ልማት ሥም የፈረሱ እና እየተረሱ ያሉ ሰፈሮችን ሥም ያነሳሳል። ዘፈኑ በግጥሙም በዜማውም፣ የሐዘን እንጉርጉሮ ያለበት ነው። ምሳሌ እንውሰድ፦ “ጨርሰሽ ስትወጪ ከቡፌ ዳ’ላጋ፣ ጠብቂኝ እንዳልል፣ ቆመሽ መሐሙድ’ጋ፣ አገር ...