የዕድገትና የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድ አንድ ዓመቱን ጨርሷል፡፡ ኢትዮጵያ እንደተጠበቀው በዓመት ከ11 እስከ 15 በመቶ የማደግ ሕልሟን አሳካች ወይስ ችግር አለ? በቅርቡ የምንሰማው ይሆናል፡፡ በርግጥ ‹‹ከዕቅዱ በታች ፈፅሞ የማያውቀው መንግስታችን›› ዘንድሮም የሁለት ዲጂት እንደሚያስመዘግብ መጠራጠር ከአሸባሪነት ያልተናነሰ ሃጢያት ነው የሚሆነው፡፡
የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድና UNECA
ስለትራንስፎርሜሽኑ የመጀመሪያ የስኬት ዓመት ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀብድ ቢጤ መስጠት ጀማምሯል፡፡ ሰሞኑን የምዕራባውያን ኢኮኖሚ እየፈረሰ ለቻይናዎች እጁን መስጠቱን የሚያትት ወሬ ካወሩልን በኋላ እንደ UNECA የአገሪቱ ዳይሬክተር ከሆነ ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት 10 በመቶ ታድጋለች፡፡ የUNECA ባለስልጣን እንዲህ ለማለት ከደፈሩ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንማ ኢትዮጵያን በሦስት ዲጂትም ሊያሳድጋት ይችላል የሚል ሐሳብ ያዘኝና ተውኩት፤ ምክንያቱም UNECA የሚጠቀምበት መረጃ ለካስ ከኢትዮጵያ መንግስት የተገኘ ነው፡፡
የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድና መለስ ዜናዊ
ብዙ የተወራለት የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድና መለስ ዜናዊ ዝምድና ይኖራቸው ይሆን ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ፡፡ እኔን ግን እያደር ዝምድናቸው እየገባኝ ነው፡፡ መለስ በፓርቲያቸው ውስጥ ከሙገሳ በላይ ይመለካሉ ማለት ይቀላል፡፡ ገጣሚው ቴዎድሮስ ፀጋዬ ካላወቁበት ‹‹ዝና ዘነዘና ነው ራስን የሚገሉበት›› እንዳለው እርሳቸውም ልዕለ-ሰብ እንደሆኑ ይታሰባቸው ጀምሯል መሰለኝ፡፡ ‹‹ያልተማከለው ብሔራዊ አስተዳደር›› ወደእርሳቸው የተማከለው በዚሁ ሳቢያ ነው - ከሳቸው ወዲያ ማን አዋቂ አለ እና የአመራሩ ስራ ወደ ሌሎች ይሄዳል? ወዳጆቻቸውም ቢሆን ሹመቱ ስለሚያጓጓቸው ይመስለኛል ድክመታቸውንና ለ20 ዓመታት ሞክረው ያልተሳኩላቸውን አይነግሯቸውም፡፡ ስለዚህ አይፈረድባቸውም፡፡
እናም ጠቅላይ ሚነስቴሩ (እርግጥ ባይሆንም፤ እንደ ‹‹አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በሚዲያ ሳልሰማ›› ቀርቼ ሳይሆን፣ ስላላመንኩበት) በአምስት ዓመቱ መጨረሻ ከስልጣን ይወርዳሉ ስለተባለ፤ አገሪቷ በሁለት እግሯ ሳትቆም መውረድ ከ‹‹አዋቂ›› የሚጠበቅ ስላልሆነ ደፋር እርምጃ ወሰዱ፡፡ ይኸውም በ19 ዓመታት ያልተሳካላቸውን አገሪቷን ወደመካከለኛ የኢኮኖሚ ደረጃ በአምስት ዓመት ማሸጋገር፡፡ በአንድ በኩል የእሳቸውን ችሎታ በመጠራጠር ስንተቻቸው የከረምነውን አፋችንን ለማስያዝ በሌላ በኩል ደግሞ ከመንበረ ስልጣናቸው ሲወርዱ ሃገሪቱ በትክክለኛው ትራክ ላይ ከተቀመጠች ተኪዎቻቸው መሪውን ጨብጠው ለማሽከርከር ብዙም አይቸገሩም፡፡
(እኔ ግን እዚህች ጋር ትንሽ መስመር ካዋሳችሁኝ የምናገረው አለኝ፡፡ እርሳቸውን የሚተካ ሰው የማግኘት ጉዳይ ለኢሕአዴግ የራስ ምታት የሆነበት ከእርሳቸው አመራር ችግር ነው ባይ ነኝ፡፡ ምክንያቱም እውነተኛ መሪ - መሪ እንጂ ተከታይ አያፈራምና፡፡)
የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድና ለጋሽ ሃገራት
ለጋሽ ሃገራት በተለይም ‹‹ኒዮ ሊበራሊስቶቹ›› በሚወረውሩልን ሳንቲም እና ስንዴ እጃችንን ለመጠምዘዝ ይሞክራሉ፤ ምንጭ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና መለስ ዜናዊ፡፡ እናም ይህንን የእጅ ጥምዘዛቸውን፣ ይህንን የሰብአዊ መብት ጥበቃ፣ የፍትሃዊ ምርጫ፣ የመናገር ነፃነት እያሉ የሚመፃደቁበትን እርዳታቸውን እንዳንጠብቅ ከተፈለገ፣ በዚሁ በትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድ ኢትዮጵያ የራሷን በጀት በራሷ እንድትሸፍን ታቅዷል፡፡ ምዕራባውያን ፖለቲካዊ ጫና አያደርጉም አይባልም፣ አገሪቷ የራሷን በጀት መሸፈኗም ፅድቅ ነው፡፡ ግን ከራሳችሁ ስጋ እየቆረጣችሁ ተመገቡ ዓይነት ታክስ እየሰበሰቡ ራስን መቻል አለ፡፡ ታክሱ ቅጥ አጥቷል፡፡
(አሁንም ጥቂት መስመር ካዋሳችሁኝ ይሄ ራስን የመቻል ጥያቄ እውን ከኒዮ ሊበራሎች እጅ ጥምዘዛ ለመዳን ነው፤ ወይስ የኢትዮጵያውያንን እጅ ያለማንም አለብኝነት ለመጠምዘዝ? ቢብራራልኝ፡፡)
የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድና ዕድሜው
በትራንስፎርሜሽኑ የመጀመሪያ ዓመት ውስጥ የኢቴቪን ሰዓት በመቆጣጠር ከፍተኛ ሪከርድ ያስመዘገበው የሕዳሴው ግድብ አንዱ ነው፡፡ የሕዳሴው ግድብ መጀመሪያ ሲተዋወቅ አራት ዓመት ይፈጃል ተብሎ የተነገረ ቢሆንም፣ አሁን ደግሞ ተከልሶ ሰባት ዓመት ሆኗል አሉ፡፡ (ማብራሪያው የለኝም! ምክንያቱም ኢቴቪ እንዲህ ያሉትን መርዶዎች የሚያብራራበት አሰራር የለውም፡፡)
እኔ የፈራሁት ግን ለሕዳሴው ግድብ ብቻ አይደለም፡፡ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድም በአምስት ዓመት ሊደረስበት የማይችል ስለሆነ ወደ….. ዓመት ተሸጋግሯል እንዳይባል ነው፡፡
የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድና የኢትዮጵያ ሕዝቦች
የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድ ከአንድ ዓመት በኋላም ቢሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ አልተዋጠለትም፡፡ የአምናው ቁምስቅል ትራንስፎርሜሽን ወዴት የሚያስብል እንጂ የሚያኮራ ሁኖ የታየው ሰው የለም - የኢሕአዴግ አመራሮችና የኢቴቪ ጋዜጠኞች ካልሆኑ በቀር፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አምሮት አጓጊ ዕቅድ (ambitious plan) መስማት አይደለም፤ አመርቂ ለውጥ ማየት ነው፡፡ (ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትራንስፎርሜሽንን ስርነቀል ለውጥ ሲሉ ተርጉመውታል) በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ ሕዝብ ‹‹እኔ አውቅልሃለው›› ከሚሉ መሪዎቹ የሚገላገልበትንና ለሕዝብ በሕዝብ ፈቃድ የሚሰሩ ሹመኞችን እንዲያይ ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልገዋል፤ ይገባዋልም፡፡
ስለዚህ ያነሳሁትን ጥያቄ ጮክ ብዬ እደግመዋለሁ፡-
ትራንስፎርሜሽኑ ወዴት፤ ወደፊት ወይስ ወደኋላ?
Comments
Post a Comment