በክፍል አንድ ጽሁፌ የፈጣሪ ሕልውናን በተመለከተ መከራከር እና የግል አቋም መያዝ እንጂ መደምደሚያ ላይ መድረስ እንደማይቻልና በሳይንሳዊ ሙግት የፈጣሪን ሕልውና (የቅዱሳን መጽሃፍትን ፍፅምና) ማረጋገጥ እንደማይቻል በጥቂት ነጥቦች መግለፄ ይታወሳል፡፡ ዛሬ ደግሞ ቃል በገባሁት መሰረት ጥቂት ስለዝግመተ ለውጥ እና ኢ-አማኒነት ለመነጋገር የሚያስችሉንን ነጥቦች ይዤ ቀርቤያለሁ፡፡ ጥቂት ስለዝግመተ ለውጥ በዝግመተ ለውጥ (evolution) እሳቤ ላይ ብዙ ተሳልቆዎች ተነግረዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ስላቆች የተነገሩት ባላዋቂነት መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ከቀልዶቹ መካከል አንዱን አንስተን ጥቂት እንነጋገርበት፡፡ አባትና ልጅ እያወሩ ነው፡፡ ልጅ፡- አባዬ፤ ሰው ከየት ነው የመጣው? አባት፡- እኛማ የአምላክ ፍጡሮች ነን፤ ልጅ፡- አስተማሪያችን ግን ሰው ከዝንጀሮ ነው የመጣው ብሎ ነገረን፤ አባት፡- እንግዲህ እሱ አባቱ ዝንጀሮ ይሆናል፤ እኔና አንተ ግን የአምላክ ፍጡሮች ነን፡፡ ቀልዱ ሊያስቅ ይችል ይሆናል እንጂ መሰረታዊ ችግር አለበት፡፡ ምክንያቱም የዝግመተ ለውጥ እሳቤ ሰው ከዝንጀሮ መጣ አይልም፡፡ የዘንድሮ ሰው እና የዘንድሮ ዝንጀሮ አንድ ዓይነት የዘርግንድ ነበራቸው የሚል መላምታዊ ድምዳሜ ግን ያስቀምጣል፡፡ ይሄ እንዴት ሊሆን ይችላል - ወደ መልሱ የሚያመራን ጥያቄ ነው፡፡
Passionate about the ideas of liberty and dignity, and of course prosperity too.