Pages

Monday, August 15, 2011

የሁለት እምነቶች ጦርነት… [ወግ አጥባቂዎች እንዲያነቡት የማይመከር]

ዓለማውያን በምክንያት ሲሟገቱ ኢትዮጵያውያን ግን ገና ‹‹የዘራፍ›› ዘመን ላይ ነን፡፡ ይህንን ለመናገር ያደፋፈረኝ በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ትችት መሰንዘር - በሃገራችን - ቡጢ የሚያስቀምስ ሃጢያት መሆኑን ስለማውቅ ነው፡፡ እኔ ኢ-አማኒ (atheist) ነኝ፡፡ በርግጥ እንደ ብዙሐኑ ሁሉ እኔም ቤተሰቦቼ በውልደት ያወረሱኝ አምልኮታዊ አስተሳሰብ ነበረኝ፡፡ ልዩነቱ ለአቅመ መጠየቅ ስደርስ የተነገረኝን መቀበል ስላልተቻለኝ የሆንኩትን ሆኛለሁ፡፡

ዛሬ በዚህ ጽሁፍ ላይ ትልቁ አጀንዳ የኔ ጉዳይ አይደለም፡፡ በርግጥ እኔ ኢ-አማኒ መሆኔን መግለፅ ያስፈለገኝ - ኢ-አማኒነት ከአማኒነት የተሻለ ምክንያታዊ ነው ብዬ ስለምከራከር ነው፡፡ ማንም አንባቢ ጽሁፌ ላይ የሚመለከተውን ሐሳባዊ ወይም አመክንዮአዊ ግድፈት በአስተያየቱ ሊጠቁመኝ ወይም በትችት ሊያር’ቀኝ (ር ይጠብቃል) የመሞከር መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡

ፈጣሪ አለ ወይስ የለም?

ይህንን ጥያቄ ማንሳቱ ራሱ ለብዙ አማኒዎች አምላክን እንደመዳፈር ያለ የሃፍረት ስሜት ይፈጥርባቸዋል፡፡ በመሰረቱ አማኒ እና ኢ-አማኒ እያልኩ የምጠቅሳቸው ሁለቱም ወገኖች ማረፊያቸው እምነት ነው፡፡ አማኒዎች በጥቅሉ ፈጣሪ አለ፤ በምድር ላይ ያለፈጣሪ የሚሆን አንድስ እንኳ የለም ብለው የሚያምኑት ናቸው፡፡ (በጥቅሉ የሚለውን ቃል የተጠቀምኩት ‹ፈጣሪ አለ፤ ሆኖም በምድር ላይ ስለሚሆነው የሚያገባው ነገር የለም - ከቁብም አይቆጥረው› የሚሉም ስላሉ ነው፡፡) ኢ-አማኒዎች በበኩላቸው ፈጣሪ የለም፤ ይህች ዓለም እና ሕይወት-በራሱ የአጋጣሚዎች ጥርቅም ናቸው ብለው ያምናሉ፡፡

አማኒዎች ‹‹ፈጣሪ ስለመኖሩ ምን ማረጋገጫ አላችሁ?›› ተብለው በኢ-አማኒዎች ሲጠየቁ፤ ‹‹እናንተስ ፈጣሪ ስላለመኖሩ ምን ማረጋገጫ አላችሁ?›› ብለው ጥያቄውን በጥያቄ ይመልሳሉ፡፡ ኢ-አማኒዎች ‹‹ሰማያዊ ፈረስ ስላለመኖሩ ማረጋገጫ ስለሌለ፣ ሰማያዊ ፈረስ አለ ማለት አይደለም›› ያሉ እንደሆን - አማኒዎችም ‹‹ሰማያዊ ፈረስ መኖሩን ማረጋገጫ ስለሌለ፤ ሰማያዊ ፈረስ የለም ማለት አይደለም›› ብለው ይመልሳሉ፡፡ የዚህ ምልልሶሽ ማሳረጊያ፤ የፈጣሪ ሕልውና (God’s existence) ሲያከራክር የሚኖር ጉዳይ እንጂ፤ ማንም እንዳሻው ተነስቶ በሙሉ ማስረጃ ድምዳሜ ሊሰጥበት የማይችል ሁለንተናዊ እውነታ (universal truth) አለመሆኑን ነው፡፡

ቶማስ ኤድሰንና አምፖሉ
በዓለማችን በእልፍ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሃይማኖቶችና አምልኮቶች ተፈጥረዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ገንነው የሚታወቁት ግን የመካከለኛው ምስራቅ በቀሎቹ ክርስትና፣ እስልምና፣ አይሁዳዊ እምነት እና ሩቅ ምስራቅ በቀሉ ቡዲዝም ናቸው፡፡ በጥቅሉ ሁሉም አምልኮአዊ እምነቶች በፈጣሪ ፍፁምነት ላይ የሚስማሙ ቢሆኑም በርካታ ልዩነቶችን በማስተናገድ እርስ በእርስ መቆራቆዛቸው የአደባባይ ሐቅ ነው፡፡

አማኒዎች ሆነው ‹አፈንጋጭ አማኒ› ብዬ በዚህ ጽሁፍ ልሰይማቸው የምፈልጋቸው ዓይነቶቹ ግን በፈጣሪ መኖርና በፍፁምነቱ ላይ የጋራ አቋም ይዘው ከሃይማኖታዊ የቡድን አስተሳሰብ የወጣ አምልኮ የሚያራምዱትን ነው፡፡ እነዚህኞቹ (አፈንጋጭ አማኒዎች) ፈጣሪ በፍጡሩ ወይም በአምልኮአዊ መጽሃፍት ሊገለጽ የማይችል ረቂቅ ፍጡር ነው ባዮች ናቸው፡፡ ለነሱ ፈጣሪን ለማወቅ መሞከር አምፖሉ ፈጣሪውን፣ ቶማስ ኤዲሰንን ለማወቅ ሲሞክር እንደማየት ነው፡፡

ሳይንስን በሳይንስ፤ ምን ያህል ያስኬዳል?
አበው ሲተርቱ ‹‹እሾህን በእሾህ›› ይሉ ነበር፡፡ United Church of God የተባለ የመጽሃፍ ቅዱስ አማኒዎች ማሕበርም የሚተገብረው ይህንኑ ነው፡፡ ሳይንስ፣ በተለይም ከ19ኛው ክፍለዘመን ወዲህ ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ በመምጣቱ፤ ማሕበሩ ሳይንሳዊ እውነታዎችን ይዞ አምልኮተ መጽሃፍ ቅዱስን የሚቃረኑ ድምዳሜዎችን ለመዋጋት መጽሄት በማሳተም ስራ ተጠምዷል፡፡

ማሕበሩ ጥሩ ዘይዷል፡፡ ዘመናችን ‹‹መሬት በፀሃይ ዙሪያ ትሽከረከራለች›› ብሎ የተናገረን ሰው በድንጋይ ለመውገር አይፈቅድም፤ ከቆይታ በኋላ እውነታው ሲረጋገጥ ወጋሪዎቹ በተራቸው ተወጋሪ የሚሆኑበትም አይደለም፡፡

ወደ ነጥቡ ስንመጣ፤ የጠቀስኩት ማሕበር የሚያሳትመው መጽሄት እ.ኤ.አ. የ2000 እትም የፈጣሪን መኖር ለማረጋገጥ ካሰፈረው ዝርዝር ውስጥ “A Planet Perfect for Life” የሚል ርዕሰ ወሬ ይገኝበታል፡፡ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የሚከተሉትና ሌሎችም ሳይንሳዊ እውነታዎች ተቀምጠዋል፡-
  • የመሬት ከባቤ አየር
    የመሬት ከባቤ አየር (atmosphere) ለሕይወት ጠቃሚ የሆኑ ቅይጦችን በተገቢው ምጣኔ ይዟል፡፡ ለምሳሌ የኦክስጅን መጠን በከባቤ አየር ውስጥ ከ21 በመቶ ቢበልጥ ኖሮ ዓለማችን በቀላሉ በእሳት የምትቀጣጠል፣ ብሎም መርዛማ ስፍራ ትሆን ነበር፡፡ የናይትሮጅን መጠን 78 በመቶ ባይሆን ኖሮ በዝናብ ታጥቦ የሚወርደው መብረቅ አመጣሽ ኬሚካዊ ውሁድ ስለማይኖር ወይም መጠኑ ስለሚያንስ ተክሎች ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ አያገኙም፤ ሕይወት አይኖራቸውም - ስለዚህ እንስሳትም አይኖሩም ነበር፡፡
  • የመሬት መጠንና በሕዋ ውስጥ ያላት ቦታ
    መሬት አሁን ካላት መጠን ትንሽ ብትገዝፍ የመሬት ስበት መጠን ስለሚጨምር ብዙ ሃይድሮጅን በመሬት ክበብ ላይ ይሰበሰብና ምድሪቱን ለሕይወት የማትመች ስፍራ ያደርጋታል፡፡ መጠኗ ካሁኑ ትንሽ አነስ ቢል ኖሮ ደግሞ ስበቷ ስለሚቀንስ ኦክስጅን ከከባቢ አየሩ ይርቃል፤ ውሃ በቀላሉ ይተናል ስለዚህ ለሕይወት የማትመች ስፍራ ትሆናለች፡፡ ሌላው መሬት በፀሀይ ዙሪያ የምትሾርበት 66,600 ማይል በሰዓት የሆነ ፍጥነት ጥቂት ቢቀንስ በፀሀይ ተስቦ ለመንደድ፣ አሊያም ቢጨምር ከፀሀይ ርቆ ወደበረዶነት (ለመቀዝቀዝ) መንስኤ ይሆን ነበር፡፡ በተጨማሪም አሁን መሬት ከፀሀይ አንፃር ያላት የ23.5 ዲግሪ ዝንባሌ ባይኖር ኖሮ ወቅቶች እንዳይፈራረቁ፣ ምድርም ለሕይወት የማትመች እንድትሆን የማድረግ ተፅዕኖ ይኖረው ነበር፡፡
  • ስርዓተ ፀሀይ (solar system)
    በስርዓት ፀሀይ ውስጥ ለምሳሌ ጁፒተር ትልቋ ፕላኔት መሆኗ ይታወቃል፡፡ ሁሉም እስከዛሬ የታወቁት ፕላኔቶች አንድላይ ቢጨመቁ እንኳን ጁፒተር ከእጥፋቸው ትበልጣለች፡፡ የጁፒተር ትልቅ መሆን ለምድር እስከዛሬ አለመጥፋት ባለውለታ ሆኗል፡፡ ምክንያቱም ጁፒተር በግዙፉ ሰውነቷ የበራሪ ከዋክብትን (comets) አቅጣጫ በማስቀየርና አንዳንዴም ራሷን ሰውታ በመጋጨት ምድርን ሊያጠፉ አቅም ካላቸው ግጭቶች ሰውራታለች፡፡

አማኒዎች እነዚህንና መሰሎቹን ተፈጥሯዊ - (ተፈጥሯዊ ስል natural ለማለት እንጂ የተፈጠሩ ለማለት ፈልጌ አለመሆኑን እንድትረዱኝ እፈልጋለሁ፤) እናም እነዚህን ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች በማጣቀስ በአጋጣሚ፣ በእውር ድንብር (blind watchmaker) የሆኑ ሳይሆን በአንድ ፍፁማዊ አካል (ፈጣሪ) የተሰሩ ናቸው የሚል ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ፡፡

ይሄ አመለካከት ሁለት መሰረታዊ ችግሮች አሉበት፡፡

አንደኛው ፕላኔታችን ለሕይወት ምቹ እንጂ ፍፁም (perfect) አይደለችም፡፡ ምንም እንኳን ከላይ የተጠቀሱት በተጠቀሱበት መጽሄት ዓላማ መሰረት ምቾቷን የሚያሳዩ ብቻ ቢሆኑም በርካታ ምድርን ለሕይወት ፈተና እንድትሆን የሚያደርጓት ባሕሪዎች አሏት፡፡ (ከእነዚህ ውስጥ ጥቂቶቹን - ጉዳዩ ከዝግመተ ለውጥ (evolution) ጋር የሚያገናቸው ነገር ስለሚኖር በቀጣዩ ክፍል ጽሁፌ ለመዘርዘር እሞክራለሁ፡፡)

ሁለተኛው ጉዳይ ከላይ የዘረዘርናቸው ነጥቦች ‹‹መሬት ለሕይወት ምቹ ተደርጋ መፈጠሯን ያሳያል›› ብለን ከመደምደማችን በፊት ‹‹ሕይወት ከላይ ለተዘረዘሩት የመሬት ባሕርያት ራሷን አስማምታ ቢሆንስ?›› የሚለውን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል፡፡ ሕይወት የሚገኝባቸውን ቦታዎች ተመልከቱ፤ በውሃ ውስጥ፣ በየብስ ላይ፣ በበረሃ ውስጥ፣ በአንታርክቲክ በረዶ ግግር ላይ - በሁሉም ቦታዎች ላይ ሕይወት ያላቸው አካላት አሉ፡፡ እነዚህ አካላት እንደየሚኖሩበት አካባቢ የተለያየ አካላዊ ባሕሪ ያላቸው ሲሆን፤ ልዩነቱ የተፈጠረው እነሱ ላሉበት አካባቢ ራሳቸውን በሚሊዮን ዓመታት ጥረት እና ሒደት (በዝግመተ ለውጥ እንበለው) አስማምተው ነው እንጂ መሬት ለሕይወት ተስማሚ ስለሆነች ብቻ አይደለም፡፡ ራሳቸውን ከማስማማታቸው በፊት እንዴት ኖሩ የሚል ጠያቂ ካለ፤ ዝግመተ ለውጥ የሚለውጠው ሕይወት ያላቸውን አካላት ብቻ ሳይሆን ምድርንም እራሷን መሆኑን ላስታውሰው እወዳለሁ፡፡ ምድር የዛሬ መልኳን ለመያዝ የቢሊዮን ዓመታት ውጣ ውረዶችን አሳልፋለች፡፡

በዚሁ ወደዝግመተ ለውጥ አከራካሪ ሐሳቦችና ጥቂት ስለ ኢ-አማኒነት (atheism) የሚያነጋግረን ምዕራፍ እንሻገራለን፡፡

[ይቀጥላል]

No comments:

Post a Comment