Skip to main content

የሁለት እምነቶች ጦርነት… [ወግ አጥባቂዎች እንዲያነቡት የማይመከር - ክፍል ሁለት]

በክፍል አንድ ጽሁፌ የፈጣሪ ሕልውናን በተመለከተ መከራከር እና የግል አቋም መያዝ እንጂ መደምደሚያ ላይ መድረስ እንደማይቻልና በሳይንሳዊ ሙግት የፈጣሪን ሕልውና (የቅዱሳን መጽሃፍትን ፍፅምና) ማረጋገጥ እንደማይቻል በጥቂት ነጥቦች መግለፄ ይታወሳል፡፡ ዛሬ ደግሞ ቃል በገባሁት መሰረት ጥቂት ስለዝግመተ ለውጥ እና ኢ-አማኒነት ለመነጋገር የሚያስችሉንን ነጥቦች ይዤ ቀርቤያለሁ፡፡

ጥቂት ስለዝግመተ ለውጥ
በዝግመተ ለውጥ (evolution) እሳቤ ላይ ብዙ ተሳልቆዎች ተነግረዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ስላቆች የተነገሩት ባላዋቂነት መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ከቀልዶቹ መካከል አንዱን አንስተን ጥቂት እንነጋገርበት፡፡ አባትና ልጅ እያወሩ ነው፡፡
ልጅ፡- አባዬ፤ ሰው ከየት ነው የመጣው?
አባት፡- እኛማ የአምላክ ፍጡሮች ነን፤
ልጅ፡- አስተማሪያችን ግን ሰው ከዝንጀሮ ነው የመጣው ብሎ ነገረን፤
አባት፡- እንግዲህ እሱ አባቱ ዝንጀሮ ይሆናል፤ እኔና አንተ ግን የአምላክ ፍጡሮች ነን፡፡

ቀልዱ ሊያስቅ ይችል ይሆናል እንጂ መሰረታዊ ችግር አለበት፡፡ ምክንያቱም የዝግመተ ለውጥ እሳቤ ሰው ከዝንጀሮ መጣ አይልም፡፡ የዘንድሮ ሰው እና የዘንድሮ ዝንጀሮ አንድ ዓይነት የዘርግንድ ነበራቸው የሚል መላምታዊ ድምዳሜ ግን ያስቀምጣል፡፡ ይሄ እንዴት ሊሆን ይችላል - ወደ መልሱ የሚያመራን ጥያቄ ነው፡፡


በርግጥ የዝግመተ ለውጥ ሳይንስ በመላምቶች ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ መላምቶቹ ግን እንደሃይማኖታዊ ምልኪዎች በእምነት ላይ የተመሰረቱ ሳይሆን በነባራዊ ሁኔታዎች ላይ ነው፡፡ የመጽሃፍ ቅዱሶቹ አዳም እና ሔዋን (ወይም የቁርኣኖቹ አደም እና ሐዋ)፣ እንደተነገረን የመካከለኛው ምስራቅ ሰዎች ናቸውና ነጮች ወይም ፈረንጆች ናቸው እንበል፡፡ የሚወልዷቸውም ልጆች ፈረንጆች እንጂ ጥቁሮች ሊሆኑ አይችሉም፤ ስለዚህ የዓለም ሕዝብ በሙሉ ነጭ መሆን ነበረበት - ዝግመተ ለውጥ ከሌለ በቀር፡፡ (አለበለዚያማ የአዛውንቶች ክበብ የተሰኘው ያገራችን ቲያትር ላይ ‹‹ሁለት ሃበሾች ተጋብተው ሚስት ፈረንጅ ብትወልድ አባት የኔ ነው ሊል ነው?›› እንዳለው ገጸ ባሕሪ ዓይነት ችግር ሊገጥመን ነው፡፡) በጠቀስኳቸው መጽሃፍት የማያምኑ ወገኖች ግን ምናልባትም ዝግመተ ለውጥን የሚያካሒደው ራሱ ፈጣሪ ቢሆንስ የሚል አዲስ አምልኮ መመስረት ይችላሉ፡፡

ዝግመተ ለውጥ ከመላ ምት በላይ የሆነ እውነታ እንደሆነ የሚያረጋግጡ አራት ዓይነት ሳንሳዊ መንገዶች አሉ፡፡ እነዚህም የተፈጥሮ ምርጫ (natural selection)፣ የዘረመል ለውጥ (genetic drift)፣ ሙቴሽን (mutation) እና የዘረመል ፍሰት (gene flow) ናቸው፡፡ (የአማርኛ ትርጉሞችን ለወግ እንዲመቸኝ ራሴው ነኝ የሰጠሁት)

በተፈጥሮ ምርጫ በወቅታዊው አካባቢያዊ ሁኔታ፣ ለመራባት እና ዘርን ለመቀጠል የሚያስችል ብቃት ያላቸው ዝርያዎች ሲራ’ቡ እና ሲባዙ ይህንን ያልቻሉት ግን እየተመናመኑና እየጠፉ ይሄዳሉ፡፡ በዚህም የተፈጥሮ ምርጫ ዳይኖሶርን ጨምሮ በርካታ እንስሳትና እፅዋት ጠፍተዋል፡፡ የዘረመል ለውጥ (genetic drift) ሁለት (የወንዴ እና ሴቴ እንበለው) የዘረመል ቅንጣቶች ተዋህደው በመጠኑ የተለየ የዘረመል ቅንጣት መፍጠር ሲችሉ ነው፡፡ ሙቴሽን (mutation) የሚባለው በተፈጥሮአዊ፣ ወይም አካባቢያዊ ተፅዕኖ ሳቢያ ዘረመሎች ድንገታዊ ለውጥ ሲያመጡ ነው፡፡ የዘረመል ፍሰት (gene flow) የዘረ መል ባሕርያት ከአንድ ዝርያ ወደሌላው በሆነ መንገድ ሲገቡ የሚፈጠረው ለውጥ ነው፡፡ እነዚህ አራቱ መንስኤዎች በተለያዩ ጊዜያት የሚያስመዘግቧቸው ለውጦች በሚሊዮን ዓመታት ውስጥ በርካታ የተለያዩ ዝርያዎችን ለማፍራት ያስችላሉ፡፡

ዝግመተ ለውጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተስተዋለባቸው አጋጣሚዎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ የሰው ልጅ ከመቶ ዓመት በፊት የኢንፍሉዌንዛ (ጉንፋን) ቫይረስን መቋቋም የማይችል፤ ወይም ኢንፍሉዌንዛ ለሰው ልጅ ገዳይ የሆነ ቫይረስ ነበር፡፡ ዛሬ፤ ከመቶ ዓመት ብዙም ሳይርቅ ኢንፍሉዌንዛ (ጉንፋን) በተፈጥሯዊ መንገድ የሚድን፣ ግፋ ቢል የሳምንት በሽታ ነው፡፡ ከዚህ መረዳት የምንችለው የሰው ልጆች ሰውነት በመቶ ዓመት ዕድሜ ውስጥ እንኳን፣ በምድር ላይ ለመቀጠል የሚያስችለውን ባሕሪ በለውጥ እንዳዳበረ ነው፡፡ የዳርዊኑ የሚሊዮን ዓመታት ለውጥ ኀልዮት (the fittest will survive) የሚገለፀው በዚህ መንገድ ነው፡፡

ክፍል አንድ ጽሁፌ ላይ የጠቀስኩት መጽሄት ዓለም ለሕይወት የተመቸች ፍፁም (a planet perfect for life) እንደሆነች ሲነግረን የዘነጋው ነገር ይሄው ነው፡፡ በዓለማችን ያሉ ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ራሳቸውን ካሉበት አካባቢ ሁኔታ ጋር አስማምተው መኖር የቻሉ (survived fittest) ናቸው፡፡ በበረዶ ግግር ላይ መብቀል የሚችሉ ዕፅዋት በበረሃ፣ በውሃ የሚኖሩ በየብስ ወይም በተገላቢጦሽ መኖር አይችሉም፡፡

ጥቂት ስለ ኢ-አማኒነት (Atheism)
ኢ-አማኒነት በኢትዮጵያ መልካም ስም የለውም፡፡ ኢ-አማኒነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አጠራር አረመኔነት (paganism) - መጽሃፍ ቅዱስ ላልተሰበከላቸው እና ኑፋቄ/ክህደት (atheism) - ለተሰበከላቸው ተብሎ ይተረጎማል፡፡ በሁለቱም ስያሜዎች ውስጥ የምናነበው ጥላቻን ነው፤ በእኔ እምነት ሰዎች በአንድ የአምልኮ ስርዓት ውስጥ ሲቧደኑ ሌላኛውን ለማጥቃት ከማሰብ የበለጠ የሚያረካቸው ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ስያሜው አይገርምም፡፡ ስያሜው ኢ-አማኒዎችን ግን እንደማይመጥናቸው ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

ሃይማኖተኞች ኢ-አማኒዎች ሰዎችን ለሞራል እሴቶች ተገዢ የማይሆኑ ልቅ (መረን) እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል የሚል እምነት አላቸው፡፡ እኔ ግን ቅዱስ መጽሃፍቶች በሚባሉት ትዕዛዝ ብቻ ራሳቸውን መግዛት የሚችሉ ሰዎች፤ ክፉ ከሚባለው (ማሕበረሰቡ ከተስማማባቸው እሴቶች አፈንጋጭነት) ለመጠ’በቅ አለቃ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ ኢ-አማኒዎች ግን ራሳቸውን በማሕበረሰቡ ፍላጎቶች ለማስገዛት የቆረጡ፣ ለሰው ልጅ ክብር ያላቸው - ነፃ ነገር ግን የሕሊና ተገዢ ናቸው (ቢያንስ ብዙዎቹ፡፡)

ሃይማኖተኞች ኢ-አማኒዎች ለማሕበረሰቡ የሞራል እሴቶች ተገዢ አይደሉም እያሉ ቢከራከሩም፤ ብዙ ዓይነት ኢ-አማኒዎች እንዳሉ ለማመን ሲከጅሉ አይታዩም፡፡

ኢ-አማኒዎች እና የሞራል እሴቶች
ሁሉም ኢ-አማኒዎች ከሞላ ጎደል ከጊዜያዊ መከሰታችን ያለፈ ሕይወት የለንም፣ ሁላችንም የጊዜ የቁስ እና አጋጣሚ ድምሮች ነን ብለው ያምናሉ (እናምናለን፡፡) ስለሞራል እሴቶች (moral values) ባላቸው አመለካከት ኢ-አማኒዎችን በሶስት እንከፍላቸዋለን፡፡ Nihilistic atheists - የሚባሉት በምድር ላይ እስካለን ድረስ ምንም ልናሳካው የሚገባ ግብ የለም ብለው ያምናሉ፡፡ Humanistic atheists የሚባሉት ደግሞ ዓለማችን የአጋጣሚ ክስተት ብትሆንም ሰዎች ለሕይወት የራሳቸውን ትርጉም መስጠት ይችላሉ የሚሉት ናቸው፡፡ (እኔን እዚህ ታገኙኛላችሁ፡፡) ሦስተኛዎቹ ደግሞ Immanent atheists የሚባሉት ሲሆኑ፤ እነዚህኞቹ ዓለም ያለፈጣሪ የተገኘች ክስተት ብትሆንም በኑሮ ግን ሊተገበሩ እና ሊከበሩ የሚገባቸው ሞራላዊ እሴቶች አሉ ባዮች ናቸው፡፡ ኢማነንት ኤቲስቶች የሰው ልጅ ከሌላው የሰው ልጅ ባይማርም በውልደት (በሕገ ልቦና) እነዚህን የሞራል እሴቶች ያውቃቸዋል የሚል እምነት አላቸው፡፡

በሃይማኖት ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ የኔን ጽሁፍ በሚዛናዊ ስሜት ለመረዳት መሞከር ይከብድ ይሆናል፡፡ ‹‹ሊሆን ይችላል›› ብሎ ለማመዛዘን አንድም አምላክን የመካድ፣ አሊያም ‹‹ይጠብቀኛል፣ አይጥለኝም›› ሲሉት የነበረውን መመኪያ የማጣት ፍርሃት ሊያጭር ይችላል፡፡ በእኔ እምነት ግን እውነታውን ባለመጋፈጥ መደበቅ እንጂ ነፃ መውጣት አይቻልም፡፡

አማኒዎች Vs. ኢ-አማኒዎች
[አሁንም በእኔ እምነት] ፍረድ አትሉኝም እንጂ ፍረድ ካላችሁኝ፤ አማኒዎች ፈሪዎች ናቸው፡፡ አማኒዎች በምድር ላይ ለሚገጥማቸው ችግር ከለላ ይሆናቸው ዘንድ የሚመኩበት አምላክ ይፈልጋሉ፡፡ አማኒዎች ከሞት በኋላ እንደዋዛ መቅረት ስለሚያስፈራቸው ሕይወት (ያውም ዘላለማዊ) ያልማሉ፡፡ በጥቅሉ፤ እኔና ሌሎችም ኢ-አማኒዎች በምናምነው ሰዎች በፈጠሩት አምላክና ከሞት ኋላ በሚመጣ ሕይወት ተስፋ ይኖራሉ፡፡ ኢ-አማኒዎች ይህንን መጋፈጥ መቻላቸው ብቻ ከሚጣፍጥ ውሸት ይልቅ፣ የሚመር እውነት ለመጎንጨት ያላቸውን ቁርጠኝነት ያመላክታል፡፡

በተጨማሪም፣ የአገሬን የፖለቲካ ቋንቋ ልጠቀምና፤ አማኒዎች ከኢ-አማኒዎች አንፃር ሲስተዋሉ ጠባብነት ይስተዋልባቸዋል፡፡ ይሄንን አባባል ከድፍረትና ከማንአለብኝነት ወይም ከስድብ ነጥለው የማያዩት ብዙዎች እንደሆኑ ይሰማኛል፡፡ ቃሉን የሚተካ ትሁት ቃል ባገኝ እጠቀምበት ነበር፤ ቸግሮኝ ነው፡፡ ሆኖም እውነታው ነውና [ብዙዎቹ] አማኒዎች እነርሱ ያሉበት አምልኮኣዊ አስተሳሰብ ብቻ ብቸኛው እና እውነተኛው እንደሆነ ይደመድማሉ፣ መደምደሙን ይደምድሙ ሌላውም የነሱን መንገድ እንዲከተል ይወተውታሉ፣ መወትወቱን ይወትውቱ እነሱን ያልመሰሉትን ያገልላሉ፣ ያወግዛሉ መረር ሲልም ይቀጣሉ፡፡

ከመደምደሜ በፊት፤ ከኢ-አማኒዎች ይልቅ አማኒዎች በፈጣሪያቸው ላይ እንደሚጨክኑበት ማሳየት እፈልጋለሁ፡፡ ይሄ ማለት ደግሞ ምን ማለት ነው የሚለኝ እንደማይጠፋ እገምታለሁ፡፡ እነሆ የሚከተሉትን ባሕርያት ሃይማኖተኞች ፍፁም፣ ሁሉን ቻይ ለሚሉት ፈጣሪያቸው ሰጥተውት ይገኛሉ፡-
  • ቀናተኛነት፡- አምላክ በሃይማኖተኞች ዓይን ቀናተኛ ተደርጎ ተስሏል፤ ‹‹ፍጡሮቼ በሰራሁላቸሁ ነፃ አእምሮ ሌላ አመለኩ›› ብሎ ቁጣውን ያዘንባል ሲሉ መጽሃፈ አምልኮዎቹ ይነግሩናል
  • ጨካኝነት፡- የሃይማኖተኞች አምላክ በየዓለማቱ እየተከሰተ ላለው የተፈጥሮ አደጋ፣ ረሃብ፣ ጦርነትና ለሁሉም (ሰው አመጣሹ ችግርም ጭምር) ተጠያቂ ነው፤ ያለ ፈጣሪ እውቅና የሚከናወን ጉዳይ የለም ተብለን ተምረናልና፣
  • ማዳላት፡- በሃይማኖተኞች ዓለም ሁሉም ሰዎች የፈጣሪ ፍጡራን ቢሆኑም ጥቂቶቹ ግን የአምላክ ልጆች ናቸው፤ አንዳንዶቹ ፈጣሪ ቀድሞ በጻፈላቸው እኩይ ገፀ-ባሕሪ ተላብሰው ሲተውኑ ሌሎቹ ደግሞ ለመጽደቅ እንዲችሉ ሁነው ይመረጣሉ፣ አንዳንዶቹ አዕምሮ ዘገምተኛ ሁነው ሲፈጠሩ ሌሎቹ ባለብሩሕ አዕምሮ ይሆናሉ፣
  • ሁሉን አለመቻል፡- ሃይማኖተኞች የሚያመልኩት አምላክ ሁሉን እንደሚችል ይናገራሉ እንጂ አይሰብኩም፡፡ ሌላው ቀርቶ ከፍጡሮች ሁሉ አስበልጦ እንደሚወደው የሚነገርለትን የሰው ልጅን ራሱ መቆጣጠር አልቻለም፡፡ ዓለም ‹‹ቅዱሳት መጻህፍቱ›› እንደሚሉት መሄድ ካለባት፣ አሁን ከቁጥጥር ውጭ ነች፡፡
ርዕሰ ጉዳዩ እጅግ በጣም ሰፊ ነው፣ ይህ እንግዲህ በኔ ቁንጽል ዕውቀትና በዚች ቁንጽል ገጽ መጻፍ የሚቻለው ነው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ አማኒዎችን ለመተቸት ወይም ወደኔ መንገድ ለመምራት ጉጉት ኖሮኝ አይደለም፡፡ ነገር ግን በየዕለቱ እያገኙኝ፣ በመጽሃፍ ቅዱስ ጥቅስ ሊረቱኝ ለሚፈልጉ ወዳጆቼ ‹‹እባካችሁ ተዉኝ እኔና እናንተ የሁለት ዓለም ሰዎች ነን›› ለማለት ያክል ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን ብዙዎቹን በዚህ ጽሁፍ ላገኛቸው አለመቻሌ ነው፡፡ ያገኘሁዋቸውም ቢሆኑ አስተያየት ከመስጠት (ወይም አስተያየታቸውን በግልና በምስጢር በማድረግ) ተወስነዋል፡፡

እኔ ግን አስተያየት ጎደለ ብዬ ለመደምደም አልቸኩልም:: ብቻዬን መከራከሬን እቀጥላለሁ::

Comments

  1. wow! what a writing skill. Honestly, this is my first time to finish reading long articles. I will continue to visit your page. Now to my point...In my opinion you don't need to condemn religion to prove yourself right.Proving them wrong doesn't mean you are right. It is a logical fallacy. Try to write a stand-alone argument and declaration of your belief. I can't wait to read it. I am afraid you will see how 90% of Atheism is complaint and the rest pure science or philosophy. In my view, both sides (Theism and Atheism) are pure believers. One believes in existence and the other believe in Non-existence of deity.As Theist have no direct proof of God's existence, Atheists also has no direct proof of its Non-existence. What is the problem of saying, I DON'T KNOW ENOUGH to prove one or disprove the other, Just like Agnostics. If the problem is not about God and its existence, just make it a moral argument and let's learn!. I hope you don't mind my loud reply. btw, let me give you a link to look at and enjoy. I am not that much loud in my own blog.sorry! http://naodlive.blogspot.com/2011/03/blog-post_13.html.

    ReplyDelete

Post a Comment

Popular posts from this blog

The "Corridor Development" is a Façade of the Prosperity Party

Befekadu Hailu I have seen a news report claiming that 40% of central Addis Ababa will be demolished for the corridor development; I am not able to confirm the validity of the news but it sounds real to me given the size of massive operations in the demolition of old neighborhoods and construction of bike lanes, green areas, and glittering street lights. I like to see some beauty added to my city but cannot help mourning the slow death of it too. Addis Ababa was already in a huge crisis of housing and the demolition of houses is exacerbating it. Apparently, Prime Minister Abiy Ahmed is eager to showcase his vision of prosperity by demonstrating how fast his administration can do magic by beautifying the front sides of the streets with lights, new pavements, and painted fences ("to fake it until he makes it" in my friend's words). Therefore, he and his party do not care about the miserable human stories behind the scenes and they will harass you if you tell it (Azeb Woku...

መጽሐፍ የሚወጣው፣ የተዋነይ ዘ ጎንጅ 5 መሥመር ቅኔ

ጎንጅ ቅኔ ያጠናበት ደብር ሥም ነው። ደብረ ጥበብ ጎንጅ ቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም። ተዋነይ የባለቅኔው ሥም ነው። (የግዕዝ ትርጉሙ "ዋናተኛ" ማለት ነው።) ሊቁ ተዋነይ የልኅቀቱን ያክል እምብዛም አይወራለትም፤ ነገር ግን በዘመኑ ወደር የሌለው ልኂቅ ስለመሆኑ ሥራው ይናገራል። የሕይወት ተፈራ "Mine to Win" የተሰኘ ድርሰት መቼቱን በዐፄ ዮሓንስ ንግሥና ዘመን፣ በጎጃም/ጎንደር የቅኔ መማሪያ ደብሮች ያደረገ ልብወለድ ነው። ልቦለዱ የቅኔ ትምህርት ስርዓትን ያስተዋውቀናል፤ በበኩሌ የቅኔ ትምህርትን እና የቅኔ ሊቃውንት ታላቅነት ቀድሞ ከነበረኝ ግንዛቤ የበለጠ እንዲሆን አድርጎኛል። በተለይ የተዋነይ ዘ ጎንጅ (በውኑ ዓለም የነበረ ባለቅኔ) ተከታይዋ አምስት መሥመር ቅኔ መጽሐፍ የሚወጣት እንደሆነች ልቦለዱ አሳሰበኝ። ወይም በአጭሩ ብዙ ምዕራባውያን ስንት መጽሐፍ የጻፉለት ፍልስፍናን በአምስት መሥመር ይዟል። የቅኔው ትርጓሜ የመጽሐፍ ቅዱስን እና የመጽሐፍ ቅዱሱን ፈጣሪ ኅልውና ይሞግታል። “የአምን ወይገኒ ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ ብዙኃን እንዘ ይገንዩ ይስግዱ ቅድሜሁ ለነጽሮ ዝኒ ነገር እሥራኤል ከመይፍርሑ ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ ወ ፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ።” (ተዋነይ ዘ ጎንጅ። ምንጭ፣ሕይወት ታደሰ ወደአማርኛ የተረጎመችው የሕይወት ተፈራ መጽሐፍ) ትርጉሙን በኋላ እመለስበታለሁ። ስለተዋነይ መጀመሪያ የሰማሁት የበውቀቱ መጽሐፍ ላይ ነበር። እሱም በጨረፍታ - “የሌሊት ዜማዎች” የሚለው ግጥሙ ውስጥ። በውቀቱ ተዋነይን በግጥሙ ግርጌ ማስታወሻው አስተዋውቆን ያልፋል፣ “ተዋነይ በቅኔ ቤት አፈ ታሪክ ሞትን በግዝት ለሰባት ዓመታት ያቆመ ጀግና ነው"። ከዚያ በኋላ፣ አዲስ አድማስ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ተዋነይ የተላከበትን ...

የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ

በፍቃዱ ዘ . ኃይሉ “የአዲስ አበባ ብሔርተኝነት” ቢኖር ኖሮ መሪው ልጅ ሚካኤል ይሆን ነበር። አሁን አሁን እሱ ስለ አዲስ አበባ የዘፈናቸውን ዘፈኖች ቁጥር ራሱ በትክክል መቁጠር ይቸግረኛል። ለአዲስ አበባ ከተዘፈኑ ዘፈኖቹ ውጪም በየዘፈኑ ውስጥ የሚጨማምራቸው መልዕክቶች በራሳቸው መወድሰ አዲስ አበባ ናቸው። ለምሳሌ፣ በቅርቡ በለቀቀው ‘አዲስ አራዳ’ በተሰኘው አልበሙ ውስጥ ‘የድሬ ልጅ’ የሚል ዘፈን አለው። ዘፈኑ የተዘጋጀው ያው የአዲስ አበባ እህት ተደርጋ የምትቆጠረውን ድሬ ዳዋን ለማወደስ ነበር። ልጅ ሚካኤል ግን የአዲስ አበባ ፍቅሩ ያመልጠውና የሚከተለውን ያቀነቅናል፦ “መጣልሽ በሏት፣ ድሬ ድረስ፣  ከአዱ ገነት፣ ከሸገር፣ ከአዲስ ደረሰ፣... የሸገር ልጅ አራዳ ነው፣ ሰው አክባሪ፣ ሰው ወዳዱ፣ ቀላጅና ተረበኛ፣ ፍቅር ይዞ የሚተኛ፣ ‘አለው’ የለ፣ ‘የለው’ የለ፣ ከሁሉ ጋ፣ ግባ ጀባ...፤” ፤ ልጅ ሚካኤል በዚህ አልበሙ ብቻ አዲስ አበባን የሚያውድሰባቸው ሌሎችም ዘፈኖች አሉ፤ ‘ አዲስ አራዳ ’ የሚለው የአልበሙ መጠሪያ እና ‘ሸገር’ የሚሉት ዘፈኖቹ ዋነኞቹ ናቸው። ታዲያ እንዲህ በአዲስ አበባ ፍቅር የሚቃጠለው ልጅ ሚካኤል "ሊነግረን የሚፈልገው ምንድን ነው?" የሚለው ጥያቄ ደጋግሞ ይመጣብኛል። ይህ የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ ምንነትን ለመረዳት የሚጥር ፖለቲካዊ መጣጥፍ ነው። ‘አዲሱ አራዳ’ ማነው? በዚህ ዘፈኑ በብዙዎቻችን ዕድሜ የትዝታ ማኅደር ውስጥ የሚገኙ ነገር ግን በአዲስ አበባ ልማት ሥም የፈረሱ እና እየተረሱ ያሉ ሰፈሮችን ሥም ያነሳሳል። ዘፈኑ በግጥሙም በዜማውም፣ የሐዘን እንጉርጉሮ ያለበት ነው። ምሳሌ እንውሰድ፦ “ጨርሰሽ ስትወጪ ከቡፌ ዳ’ላጋ፣ ጠብቂኝ እንዳልል፣ ቆመሽ መሐሙድ’ጋ፣ አገር ...