Pages

Tuesday, April 12, 2011

አማርኛ ሃይማኖቱ ምንድን ነው?

አማርኛ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋ የሚል ማዕረግ ባይኖረውም፣ የፌዴራል መንግስት የስራ ቋንቋ ነው፡፡ ልክ ከ፹ በላይ እንደሆኑት ቋንቋዎቻችን ሁሉ
ኢትዮጵዊነት በአማርኛ፣ አማርኛም በኢትዮጵያዊነት ይገለፃሉ፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በሃይማኖት መቻቻል አንቱ የተሰኘች ሃገር ናት - ‘ተብሏል፣ ብለናል፣ አስብለናል፡፡’ ታዲያ አማርኛስ ምን ያህል የሃይማኖታዊ መቻቻል ‘ሙድ’ ገብቶታል? ‘እንጠይቃለን፣ እንመልሳለን፡፡’
1 - ሠላምታ
‘ጤና ይስጥልኝ’ በሚለው የኢ-አማኒ ጓዶች ተመራጭ አማርኛ እንኳን ብንጀምር በውስጡ ሰጪ አለ፡፡ ስለዚህ አማርኛ ሃይማኖት ባይኖረው እንኳን እምነት እንዳለው ከአጀማመራችን እንረዳለን፡፡ ስንቀጥል፡- ‘እንደምን አደርክ፣ ዋልክ?’ ለሚለው ምላሹ ‘እግዚአብሔር ይመስገን’ ይሆናል፡፡ አሁን አማርኛ ክርስቲያን ነው ለማለት የሚያስችል ፍንጭ መረጃ አገኛችሁ ማለት አይደለም? ክርስቲያን ያልሆኑ አማርኛ ተናጋሪዎች የአምላካቸውን ስም ተክተው ሊናገሩ ይችላሉ ግን አማርኛ አይመስልም፡፡ ‘ደህና’ የሚል ምላሽ ብቻ ብትሰጡ ደግሞ ባዶ ይመስላል፡፡ እኔ ለሰላምታ ‘ደህና’ የሚል ምላሽ አዳብሬያለሁ፡፡ ሰዎች ግን ‘ደህና’ የሚለውን ቃል በጥርጣሬ ነው የሚያዩት - ‘ደህና አይደለህም እንዴ?’ ደህንነት በአማርኛ በ‘እግዚአብሔር ይመስገን’ ብቻ ነው የሚረጋገጠው፡፡ ስለዚህ የታከተኝ ጊዜ ‘ኧረ ደህና ነኝ! እግዚአብሔር ይመስገን’ ብዬ እገላለገላለሁ፡፡

2 - መልካም ምኞት መግለጫ
ኢ-አማኒ የአማርኛ ተናጋሪ የመልካም ምኞት መግለጫ እጥረት አይቸግረውም፡፡ ከ‘እንኳን ደስ አለሽ/አለህ’ በስተቀር ሌላ ሃይማኖት ቀመስ ያልሆነ ቃል/ሐረግ የለም፡፡ ‘እንኳን ደስ አለሽ/አለህ’ ደግሞ ለተሳካ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ በርግጥ ‘ይቅናህ’ የሚል ቁጥብ አማርኛም አለ፡፡ ቁጥብ ያልኩት እሱም ቢሆን በውስጡ ‘እንዲሳካልህ ያድርግልህ’ የሚል አገባብ ስላለው ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ‘እንኳን አደረሰሽ/አደረሰህ’ - አድራሽ ኃይል ያለበት መተኪያ የሌለው አማርኛ ነው፡፡ መልሱ ደግሞ ‘እንኳን አብሮ አደረሰን’ ነው - ለማያምኑ ሰዎች ግን ‘ማን ነው ያደረሰኝ?’ ዓይነት ጥያቄ ማጫሩ አይቀርም፡፡

ከመልካም ምኞት መግለጫ ጋር በተያያዘ አማርኛ አንዳንዴ ከክርስትናም መርጦ ኦርቶዶክስ የሚሆንበት አጋጣሚም አለ፡፡ ለምሳሌ ‘እንኳን ማርያም ማረችሽ! - ማርያም በሽልም ታውጣሽ፡፡’ አራስ መጠየቂያና መሰናበቻ አማርኛ ነው፡፡ ‘ማርያም ታኑርሽ/ታኑርህ’ ደግሞ የአራሷ መልስ፡፡

3 - ማፅናኛ
ሃይማኖተኛ ያልሆነ የአማርኛ የማፅናኛ ቃል ማግኘት የምንግዜም ፈተና ነው፡፡ ሰው አንድ ችግር ገጥሞት ወይም ታምሞ መጠየቅ ካለባችሁ፣ የምትጠቀሙት አማርኛ ‘እግዚአብሔር ይርዳህ፣ እንኳን እግዚአብሔር አተረፈህ፣ እግዚአብሔር ይማርህ፣እግዚአብሔር ያውቃል’ እና የመሳሰሉት ሐረጎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ቃላቶች ለአማኙ ሰው ተስፋ ሰጪ ናቸው፤ ምንም መፍትሄ ሳትሰጡ እንደመፍትሔ ሰጪ ያስቆጥሯችኋል፡፡ እነዚህን ቃላት አለመጠቀም ደግሞ ከችግሩ ተካፋይነት ይልቅ በችግሩ አካልነት ሊያስፈርጃችሁ ይችላል፡፡ በተለይ ኢ-አማኒ ለሆነ ሰው ቃላቱ የሽንገላ ያህል ለሚወዱት ሰው መናገር ለአፍ ይከብዳል፡፡ እኔ በበኩሌ አማኝ ባልሆንም ቅሉ አንዳንዴ፣ ቢያንስ አማኙ ስለሚያምንበት ቃላቱን ተናግሬ ‘ሸነገልኩት’ ብዬ መፀፀትን እመርጣለሁ፡፡

ሌላም፣ ሌላም፡- ምስጋናው ‘እግዚአብሔር ይስጥልኝ’፣ ምርቃቱ ‘እግዚአብሔር ይማርህ’፡፡ በጥቅሉ ቋንቋው ከሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ጋር ያለውን ቁርኝት በማየት ብቻ ጥሩ ወይም መጥፎ ብሎ መፈረጅ አይቻልም፡፡ ሆኖም የግል እምነትን ወይም ፍልስፍናን የሚደግፍ ነው ለማለትም ይከብዳል፡፡ ይህ መሆኑ ግን አማርኛን ጎዶሎ ያደርገዋል ማለት አይደለም፤ አማርኛ እንደማንኛውም ቋንቋ ሙሉ ነው - ሃሳብን ከመግለፅ አንፃር፡፡

አሁን እያወራን ያለነው ስለአማርኛ ቋንቋ ብቻ ባይሆን ኖሮ ሩቅ ሳንሄድ የእንግሊዝኛዋን ‘Oh my God’ ብንመለከት እንኳን መተኪያ የሌላት ምርጥ ሐረግ እንደሆነች በማሰብ ችግሩ የአማርኛ ቋንቋ ብቻ አለመሆኑን ማስታወሳችን አይቀርም ነበር፡፡ አንዳንዴ በስምምነት ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸውን ቃላት ከመንፈሳዊ ይዘታቸው አንፃር ሳይሆን ስሜታችንን ከማስተላለፍ አቅማቸው አንፃር ብቻ ብንጠቀምባቸው ምንም ችግር የለውም - ልክ ታላቁ የፊልም ሰው ሉዊስ ባኑኤል እንዲህ እንዳለው ‘Thank God I’m an Athiest’፤ ችግሩ ሃይማኖተኛ ያልሆንን ሰዎች ቋንቋችን ውስጥ ሃይማኖት ሲገባ ይከፋናል፡፡

ይሄ በሰፊ ጥናት ሳይሆን በቅፅበታዊ የሐሳብ ምልልሶሽ ላይ የተመሰረተ መደዴ ድምዳሜ ነው፡፡ ጠለቅ እያላችሁ ብትሄዱ ግን ሌላም፣ ሌላም ሃይማኖተኛ አማርኛዎችን ከየንግግራችሁ መሃል ትለቅማላችሁ፡፡ ለምሳሌ ‘Nature’ የሚለውን የእንግሊዘኛ ቃል የሚተካ አማርኛ ቃል አፋልጉኝ፡፡ የለም፡፡ የግድ መተርጎም ሲኖርብን እንኳን ‘ተፈጥሮ’ ብለን ነው የምንተረጉመው፡፡ የተፈጠረ (ፈጣሪ ያለው ነገር) ብለን::

በአንድ ወቅት አንድ አሜሪካዊ ምሁር ባደረጉት ጥናት አማርኛ ቋንቋ የመቻቻል ፖለቲካን የሚያበረታቱ ቃላት እጥረት እንዳለበት በጥናታቸው ጠቁመዋል፡፡ በእዚችኛዋ የእኔ ፅሁፍ ደግሞ አማርኛ የፓለቲካ ብቻ ሳይሆን የሃይማኖታዊ መቻቻልን የሚያበረታታ ቃላት እጥረት አለበት ይሆን? እያልኩ እጠይቃለሁ፡፡ “A language can tell us what is important in a particular culture.” (ቋንቋ በአንድ ባሕል ውስጥ ተፈላጊነት ያለውን ነገር ይነግረናል) ይለናል አንትሮፖሎጂስቱ ማካን ጃ - ሶሻል አንትሮፖሎጂ በተሰኘው መፅሃፉ ስለቋንቋና የማሕበረሰብ አስተሳሰብ ቁርኝት ሲያወራ፡፡


እኔም እንደኔ በመጨረሻ አማርኛ ክርስቲያን ነው፤ ያውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ በማለት አራት ነጥቤን አስከትላለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment