Pages

Friday, April 29, 2011

ኢትዮጵያ የኢስላምም የክርስቲያንም ደሴት ናት


የእስልምና እምነት ተከታይ አይደለሁም፤ ለነገሩ የክርስትና እምነት ተከታይም አይደለሁም፡፡ ነገር ግን ዛሬ ሙስሊም ሆኜ ሳስበው ‹‹ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት›› የሚለው ቃል ሳስበው ከፋኝ፡፡ ኢስላም እና ክርስቲያን ተጣጥመው በአንድ ጣሪያ ስር የሚያድሩባት እየተባለች የምትሞገሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ነች›› የሚል ቲሸርት ለብሶ መሄድ የፀብ አጫሪነት ጠባይ ነው፡፡ ይሄ ብቻም አይደለ፤ አሁን አሁን የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረት በሚስብ መልኩ በምዕራብ ኦሮሚያ ቤተክርስቲያናት እየተቃጠሉ፣ ክርስቲያኖች እየተሰደዱ ነው - ይህንንም ክርስቲያን ሁኜ ሳስበው ያስከፋል፡፡
           
በኢትዮጵያ ሙስሊሙና ክርስቲያኑ ተቃቅሯል ለማለት የሚያስደፍር ችግር አልተከሰተም፡፡ ምክንያቱም ጥቂቶች የሰሩት ስህተት የብዙሐኑን ልብ አያሸንፍም፣ ታሪክም አያስቀይርም፡፡ ነገር ግን ከስምምነት - ወደጠብ አጫሪነት እየተሸጋገረ የሚመስለው ግንኙነታቸው፣ የበፊቱን ወዳጅነታቸው ምን ገጥሞት ነው ብሎ ለመጠየቅ ጊዜው ነው፡፡ በመሠረቱ ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ የተነሳሳሁት ሙሉ መልስ ይዤ ሳይሆን አንድ መላምት መዝዤ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የሙስሊሙ ቁጥር ከክርስቲያኑ በእጅጉ የሚያንስ በመሆኑ ብዙሐኑ ክርስትናን እንደ-የጋራ እምነት ቢያየው የሚያስደንቅ አይሆንም፡፡ ሆኖም ግን ኢትዮጵያ የክርስትያኖች ብቻ ናት ብሎ መደምደም አንድም ታሪካዊ ስህተት ይሆናል፣ አንድም ደግሞ ሙስሊሙን ማሕበረሰብ ማግለል ይሆናል፡፡ ይህ ምናልባትም አንዳንድ ሙስሊሞችን የሚያበሳጭና ለበቀል የሚያነሳሳ ይሆናል፡፡ ስለክርስትና በኢትዮጵያ ብዙ፣ ብዙ ተብሏልና - ስለ ኢስላም በኢትዮጵያ ጥቂት ማለት የወደድኩትም ለዚሁ ነው፡፡

ነብዩ መሐመድ (ሶ.ዐ.ወ) ኢትዮጵያን ‹‹…land of righteousness where no one was wronged›› ሲሉ አወድሰዋታል፡፡ ነብዩ ኢስላምን መስበክ በጀመሩበት ጊዜ አረቦች ሊቀበሏቸው አልቻሉም ነበር እና ሲያሳድዷቸው ተከታዮቻቸውን ወደኢትዮጵያ ሔደው እንዲሸሸጉ ሲነግሯቸው ነው እንዲህ ያሏቸው፡፡ ይኸውም በነብዩ መሐመድ የሕይወት ታሪክ ቅፅ 1 - ገፅ 245 በግልፅ ሰፍሯል፡፡

ሐበሻ ውስጥ መልካም ንጉሥ አለ፡፡ ከሱ ዘንድ ማንም አይበደልም፡፡ እሷ የእውነት አገር ናት - አላህ ካላችሁበት ሰቆቃ መውጫ ቀዳዳ እስኪያበጅላችሁ ወደዚያው ሄዳችሁ ብትቆዩ መልካም ነው፡፡

በዚህ ጊዜ የኢስላም አስተምህሮ ተከታይ የነበሩት ከአንድ መቶ አንድ አይበልጡም ነበር፡፡ ወደኢትዮጵያ ከተሰደዱት መካከል የነብዩ ልጅ ሩቂያ እና ባለቤቷ ዑስማን ቢን አይፋ፣ እንደእናት የሚመለከቷት ሞግዚታቸው በረካ ኤም አማን፣ የሒጅራ (ስደት) ዘመናቸውን ከጨረሱ በኋላ ያገቡዋቸው ሚስቶቻቸው ኡሙ ሰላማ እና ኡሙ ሐቢባ ይገኙበታል፡፡

በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሥ የነበሩት ነጋሺ (ንጉሥ) አስሐማ ናቸው፡፡ አንዳንድ መጻሕፍት ንጉሥ አርማህ ሲሉ ይጠሯቸዋል፡፡ ንጉሡም የኢስላም ስደተኞችን አላሳፈሯቸውም፡፡ እንዲያውም ስደተኞቹን መልሰው እንዲሰጧቸው ለጠየቋቸው አረቦች የሰጡት ምላሽ አስደማሚ ነበር፡፡

እኔ ጋር የተሸሸጉትን ሰዎች ተራራ የሚያክል ወርቅ እንኳን ብታቀርቡልኝ አልሰጣችሁም፡፡

ነጋሺ ስደተኞቹን መልሰው የላኳቸው ኢስላም በአረቢያ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ሲሆን፣ ብዙ ስጦታዎችንም ለነብዩ ልከውላቸዋል፡፡

እንግዲህ ኢስላምም ሆነ ክርስትና ከመካከለኛው ምስራቅ የመጡ እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ የበቀሉ ሃይማኖቶች አይደሉም፡፡ ሁለቱም ጥንታዊ፣ ታሪካዊ ፋይዳ ያላቸው ሃይማኖቶች በመሆናቸው ማንም ኢትዮጵያ ለክርስቲያን ብቻ ወይም ለኢስላም ብቻ መስጠት አይቻለውም፡፡

ኢትዮጵያ ከክርስቶስ ጋር ንጉሥ ሰለሞን (በንግስተ ሳባ) በኩል እንደምትተሳሰር ሁሉ፣ ከኢስላምም ጋር የሚያገናኟት ሌሎችም ታሪኮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ኢስላምን በመቀበል ከከድጃ እና አቡበከር ቀጥሎ ሦስተኛ ሰው እንደሆነ የሚነገርለት ቢላል ቢን ራባህ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡

ተፃራሪ እውነታዎች
አንዳንዴ ግን በገለልተኛ ዓይን ስንመለከተው መጣ መለስ የሚለው የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች አለመስማማት ታሪክ የሰደደ ነው፡፡ ምንም እንኳን አሁን፣ አሁን ሁላችንም ኢትዮጵያ ኢስላም እና ክርስቲያን ቡና የሚጣጡባት አገር መሆኗን ብቻ ብናምንም አንዱ ሌላውን ለማሳመን የተለያዩ ጦርነት የገጠሙባትም አገር ናት፡፡ የነአሕመድ ግራኝ ጦርነት እና የሌሎቹም ክርስቲያን ነገሥታት ዘመቻዎች ያልተሻሩ ትዝታዎች ናቸው፡፡

ከዚህም ውጪ ግን በጣም አጠያያቂው፣ በመጽሐፍ ያልሰፈረው የኢስላም እና የክርስቲያን ስጋ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሙስሊሙ ክርስቲያን ያረደውን፣ ክርስቲያኑ ደግሞ ሙስሊሙ ያረደውን የማይበላባት ብቸኛዋ የዓለማችን ሃገር ናት፡፡ ይኼ ምናልባትም ለሃገራችን የሰጠናትን የመቻቻል ተምሳሌትነት የሚያደበዝዝ እና ልዩነታችንንም ፀንቶ እንዲኖር ያገዘው ሐቅ ይመስለኛል፡፡

2 comments:

  1. ደሴት ማለት በውሃ የተከበበ የመሬት ክፍል ማለት እንጅ በውስጡ ምንም አይነት የውሃ ዘር የለበትም ማለት አይደለም። በሐይቅ፣ ባህር፣ ውቅያኖስ የተከበበ ደሴት በውስጡ ወንዝ፣ ቧንቧ ፣ኩሬ ግድብ የሚባሉ ምናልባትም አንዳንዴ ከደረቁ የደሴቷ ክልል የሰፋ የውሃ ዓይነት ሊኖራቸው ይችላል። ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት ስንልም ግዙፍ ውሃ በተባለ እስልምና የተከበበች ሃገር ማለት እንጂ እስልምናም ሆነ ሌላው እምነት የሌለባት ሃገር ማለት አይደለም። ሰለዚህ ውሃው ማነው ያልከኝ እንደሆነ በጣኦት አምልኮ ላይ ያለው አፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅን ያጥለቀለቀው እስልምና ነው። እንዚህ የውሃ ዓይነቶች ኢትዮጵያ ውስጥ የሉም ወይ ? መልሱ አሉ ነው። ነገር ግን በዚያ ሁሉ ውሃ መሃል ለመርከብ መልህቅ የሚሆን ደረቅ ቦታ (ደሴት) አለ ነው ጉዳዩ።

    ReplyDelete
  2. http://befeqe.blogspot.com/fgjashj.html

    ReplyDelete