All you heard about Ethiopia is not true
ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ CBC News የተሰኘው የካናዳ መገናኛ ብዙሐን በድረ ዓምባው ‹‹ለጋሽ ሃገራት በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያደርጉ›› Human Rights Watch የተሰኘው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች መጠየቁን የሚያመለክት ዜና ይዞ ወጥቶ ነበር፡፡ በዘገባው ላይ ካናዳ ለምስራቅ አፍሪቃ 4ኛ ለጋሽ ሃገር መሆኗን ገልጧል፡፡ ከዜናው ቀጥሎ በርካታ ካናዳውያን አስተያየታቸውን አስፍረው ነበር፡፡ እነዚያን አስተያየቶች ማንበብ ‹‹ኩራት እራቴ› ለሚለው የኢትዮጵያ ሕዝብ አሸማቃቂ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከተመፅዋችነትም በላይ በባዕድ ሃገራት ዜጎች የተሰለቹ ስደተኞች ማፍራቷን ከአስተያየቶቹ መረዳት ይቻላል፡፡
ሁሌም በኢትዮጵያ ጉዳዮች እንደማደርገው ዛሬም ተብሰከሰኩ፡፡ ኢትዮጵያ ‹ቀደምት› የሚለውን ስሟን ብቻ ይዛ ዛሬ ላይ በኋላ ቀርነት ለመፈረጅ ያበቃት ነገር እንደው ምን ይሆን? ለዚህ ዓይነቱ ጥያቄ በየጊዜው የተለያየ መልስ አገኛለሁ፡፡ ዛሬም እንደዛው፣ ልዩነቱ የዛሬውን መልሴን በሌላ አማራጭ ከመቀየሬ በፊት ለናንተ ማስነበቤ ነው፡፡
1 - ኢትዮጵያውያን ጠንካራ ማሕበራዊ ግንኙነት አላቸው
ጠንካራ ማሕበራዊ ግንኙነት ደግሞ ምን አደረገ? የሚል ጥያቄ ካላችሁ ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ማሕበራዊ ትስስራችን እጅግ የጠበቀ ከመሆኑ የተነሳ ሲደላንም ሆነ ስንጎሳቆል በጋራ ነው፡፡ ኑሮውን በኢትዮጵያ ያደረገው አሜሪካዊ ሙዚቀኛ ኬኒ አለን በአንድ ወቅት ለጋዜጠኞች ስለኢትዮጵያ ማሕበራዊ ኑሮ ሲናገር ‹‹ምሳ የምበላበት ሳንቲም እንኳን ኪሴ ውስጥ ባይኖርም ምሳ ሳልበላ እንደማልውል እርግጠኛ ነኝ፡፡›› ብሎ ነበር፡፡ ‹‹አንዱ ኢትዮጵያዊ ይመጣና ያለኔ ጥያቄ ምሳ ይጋብዘኛል›› ማለቱ የሚያስቀና ይመስላል፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ላይ ክፉ ጡጫ አሳርፏል፡፡
ይህ አይነቱ ማሕበራዊ ትስስሮሽ የጋርዮሽ ስርዓት ነው፡፡ አንድ ሰው የሚሰራው ለራሱ ብቻ ሳይሆን በዙሪያው ላሉት ነው፡፡ ስለዚህ ብዙሐኑ በጥቂት ጠንካሮች ጫንቃ ላይ እንዲከመሩ ያበረታታል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰው ሰርቶ ለሌላ እንደሚሆን ማሰቡ ጠንክሮ መስራትን አያበረታታም፡፡ የዚህ ዓይነቱ ትስስሮሽ ባይኖር ኖሮ ሁሉም ሰው ኑሮን ለማሸነፍ አዳዲስ መላ ስለሚዘይድ ድምሩ የሃገር ብልፅግና ይሆን ነበር፡፡
2 - የኢትዮጵያ ተስማሚ ተፈጥሮአዊ ገፅታ
የኢትዮጵያ የአየር ንብረት አመት ሙሉ ለሰው ልጅ አኗኗር ተስማሚ ነው፡፡ ክረምቱ በጣም አይቀዘቅዝም፣ በጋው በጣም አይሞቅም፡፡ ኢትዮጵያውያን ‘snow’ ለሚለው ቃል ራሱ ተስማሚ ትርጉም የለንም፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ የአየር ንብረት፣ በበርካታ ወንዞቿ እና በሰብል አብቃይ መሬቷ እንኳን ሕዝቦቿን አለምን መቀለብ ትችላለች፡፡
እውነታው ግን ይህ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የረሃብተኞች አገር ናት፡፡ ለምን? በአስቸጋሪ የተፈጥሮ ሁኔታ ውስጥ ለመኖር የተገደዱት ምዕራባውያን የኑሮ ሁኔታቸውን ተስማሚ ለማድረግ መሥራት ብቸኛ አማራጫቸው ነበር፡፡ እነሆ ዛሬ ለነርሱ ኑሮ ማለት የሥራ ውጤት ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ግን በተፈጥሮ ድጎማ ከሥራ ይልቅ ‹ወፍ ዘራሽ› እየተመገብን እዚህ ደረስን፡፡ ይህ ዘመን ደግሞ ለወፍ ዘራሽ በሊታዎች የሚሆን አይደለምና ተስማሚ ተፈጥሮ ያጎናፀፈን ስንፍና ለባዕዳን መዛበቻነት ጥሎን እብስ አለ፡፡ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ወይም ድርቅ፣ ሰብል ለመስጠት የሚለግም መሬት፣ ያልተለመደ ጎርፍም ያየንበት ጊዜ አለ፡፡
3 - ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ ክብረበዓሎች እየተጋነኑ መጥተዋል፡፡ የጥምቀት ዕለት አውራ ጎዳናዎች ሳይቀሩ በቀለማት ባበዱ ጨርቆች ያሸበርቃሉ፡፡ በ2001 በተከበረው የጥምቀት በአል ላይ ብዙ ወጣቶች ‹‹ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት›› የሚል ቲ-ሸርት ለብሰው ነበር፡፡
ክርስትና ለዘመናዊ ስልጣኔ መነሾ እንደሆነ ምዕራባውያን ተመራማሪዎች ያምናሉ፡፡ የኢትዮጵያ የስልጣኔ ታሪክ የሚጀምረው ከክርስትና 1000 ዓመት ቀደም ብሎ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ክርስትናን ከተቀበለች በኋላ ግን አንዴ አክራሪ ክርስቲያኖች አንዴ ደግሞ ለዘብተኞ ሲቀባበሉባት መቆየቷ ይታወቃል፡፡ ሆኖም አክራሪ ክርስቲያኖች በገዟት ቁጥር ለአለም ስልጣ በር ከፋች የነበረው የንግድ ልውውጥ ውስጥ ከመሳተፍ ይልቅ ‹ሃይማኖቴን ያጠፋብኛል› በሚል ስሜት በሯን ትዘጋ ነበር፡፡
ለዚህም ይመስላል አውሮጳዊው ፀሃፊ ‹‹ኢትዮጵያ ከሃይማኖት ጠላቶቿ ራሷን በመከላከል ሰበብ ለአንድ ሺህ ዓመታት ያህል አንቀላፋች፡፡›› ብሎ የፃፈው፡፡ አሁን ነቅታለች ብለን ብናስብ እንኳን ሌሎቹ ጥለውን ከሄዱ በኋላ ነው የነቃነውና ዋጋው ‹አነስተኛ› ነው፡፡ ዋጋ የለውም ለማለት ግን ፈፅሞ አልደፍርም፡፡
4 - ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ የኖረች ነፃ አገር ናት
ቅኝ መገዛት ብዙ የአፍሪካ አገራትን እንዳነቃቃቸው ይነገራል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ጥቂት ብትቆይ ኖሮ እንዲህ በድህነት አረንቋ አትማቅቅም ነበር›› ብለው የሚከራከሩ አሉ፡፡ እኔ ከነርሱ ጋር አልስማማም ሆኖም ስለኢትዮጵያ ነፃነትም ቢሆን ጥያቄ አለኝ፡፡
እውን ኢትዮጵያ ነፃ አገር ነበረች?
የኢትዮጵያ መሪዎች በየጊዜው ለመንበራቸው ቀናተኛ ነበሩ፡፡ ‹እኔ እያለሁ ማን ይገዛታል› በሚል ጦር ይማዘዛሉ፣ ሕዝብ ያስተባብራሉ፣ ድል ይቀናቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከጥንት እስከዛሬ ከግል ፍላጎታቸው የዘለለ ሕዝባዊ ጥቅምን ያስከበሩ ሀገረ ገዢዎች ከጥንት እስከዛሬ የታል ያፈራችው? ኢትዮጵያ ሀገረ ገዢ እንጂ መሪ መቼ ኖሯት ያውቃል?
እንዲህ በማለቴ የምወዳቸውንና የማከብራቸውን ዳግማዊ ምኒልክን ጨምሮ ሌሎች እውነተኛ ኢትዮጵያውያንንም አብሬ መጨፍለቄ ያሳዝናል፡፡ ሆኖም አንዳንድ ምናባዊ የሚመስሉ መሪዎችንም አፍርተን ነበር፡፡ ለዚህ ነው በአገሬና በሕዝቦቿ ተስፋ የማልቆርጠው፡፡ ተሸፍነው እንጂ ሁሌም ታላላቅ ልጆችን እንደምታፈራ የማምነው፡፡ ሌሎቹ እና የአሁኖቹ ግን ለርስትና ሚስታቸው ‹ዘራፍ› ባዮች እንጂ የሃገር ነገር ያልገባቸው ናቸው፡፡ ለዚህ ነው ኢትዮጵያ በገዛ ዜጎቿም ቢሆን ነፃነቷን የተቀማችና ስትቀማ የኖረች ሃገር ነች የምለው፡፡
5 - ኢትዮጵያውያን ሃገራቸውን ይወዳሉ
የሃገር ወዳድነት መለኪያ በኖረና ይህን በማስረጃ ማስደገፍ በተቻለኝ ኑሮ ደስተኛ እሆን ነበር፡፡ ይህ ግን ከባድ ነገር ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ታክስ በማጭበርበርና በስደት ተወዳዳሪ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ታክስ ባግባቡ ካልተከፈለ በእርዳታ አገር ይበለፅጋል እንዴ? አገር የማሳደጉን ስራ ለመንግስት ቁንጮ ኃላፊዎች ብቻ መተው በራሱ አሳፋሪ ነው፡፡ ታክስ ማለት በእኔ እምነት ለአገር ግንባታ ሁሉም ሰው የሚሳተፍበት የመጀመሪያው ርምጃ ነው፡፡ አባቴ በታክስ ላይ ላወረሰኝ አቋሙ ለዘላለም አመሰግነዋለሁ፡፡ መንግስታችንን ወደድነውም ጠላነው፣ ሙሉ ለሙሉ ቢሰራበት ወይም ግማሹን ቢያባክነው ከእኛ የሚጠበቀው ታክስን በአግባቡ መክፈል ነው፡፡ በሌላ በኩል እዚህ አገር ምን የመሰለ የንግድ ቤታቸውን እየሸጡ በፊልም ያዩትን ኑሮ ለመኖር ራሷን ባልቻለች ጀልባ ተሳፍረው ‹ለመሻገር ሲሞክሩ› በሜድትራኒያን ‹ሰምጠው የቀሩትን› ሜድትራኒያን ራሱ ይቁጠረው፡፡ በየአመቱ 100 ሺህ ኢትዮጵያን ወደ የመን በሕገወጥ መንገድ ይሻገራሉ፡፡ በየወሩ 10 ሺህ ሴቶች ወደ ቤሩት ለቤት ሰራተኝነት ያመራሉ - ብዙዎቹ ግን መጨረሻቸው ‹ሴተኛ አዳሪነት› ነው፡፡ እስከዛሬ ድረስ ከአረብ አገራት ተመልሰው ሕይወታቸውን መቀየር የቻሉት 1000 የሚሞሉ አይመስለኝም፡፡
ታፍራና ተከብራ የሚሏትን ኢትዮጵያን ክብሯን ለመጠበቅ የሚራሩ አይገኙም፡፡ ሽርሙጥና፣ ሌብነት፣ ረሃብተኝነት መጠሪያችን ሁኗል፡፡ ብዙዎቻችን በሃገራችን ቁጭ ብለን በአመለካከት ቅኝ እየተገዛን ነው፡፡ ‹ነጭ አምልኮ› ይሉታል አባቶቻችን፡፡
ስለሃገራችን የምንሰማቸው ግነቶች ሁሉ የተሳሳቱ ናቸው፤ ሆኖም እውነት ማድረግ ግን እንችላለን፡፡ እውን እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ነን ብለን የምናምን ከሆነ ታሪክ ሰርተን ለማለፍ በግልም በጋራም እንነሳ፡፡ የዚህ ፅኁፍ አለማ ማጠልሸት ሳይሆን በተጨባጭ ትችት ላይ የተመሰረተ መነቃቃትን መፍጠር ነው፡፡ ኢትዮጵያ የባሕል አብዮት ያስፈልጋታል፡፡ ማሕበራዊ አኗኗራችን፣ አሰራራችን መለወጥ አለበት፡፡ የማሕበራዊ ጉዳዮች ለውጥ የሚጀምረው በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እርምጃ ነውና እርሶስ ምን ይጠብቃሉ?!
No comments:
Post a Comment