Pages

Tuesday, April 12, 2011

አማርኛ፣ ኣማርኛ፣ ዐማርኛ ወይስ ዓማርኛ?

በበፍቃዱ ኃይሉ -
“እዚህ ግቢ የሚሸጥ ዕንጀራ አለ” የሚል ፅሁፍ አንድ ግቢ በር ላይ ተፅፎ ባላይ ኖሮ ይህንን ፅሁፍ ለመፃፍ አልነሳሳም ነበር፡፡ ማስታወቂያውን አንብቤ ስጨርስ የሆነ ነገር እንደጎደለው ተሰምቶኝ ደግሜ አስተዋልኩት፡፡ እርግጥ ነው ዕንጀራ የሚለው ቃል ውስጥ ያለችው ዕ” ለቃሉ ተስማሚ ትክክለኛዋ ሆሄ አልነበረችም፡፡ ለቃሉ ሌላ ትርጉም ባትሰጠውም ቅሉ እኔን ለማደናገር ያክል ግን በቅታለች፡፡

አማርኛ ቋንቋ የ“ግዕዝ” ፊደላትን መጠቀሙ ያጎናፀፈው ፀጋ ለእያንዳንዱ ድምፅ አንድ ሆሄ ማስቀመጡ ብቻ አይደለም፡፡ አንዳንድ ድምፆች እንዲያውም ትርፍ ሆሄያት አሉዋቸው፡፡ እነዚህ ሆሄያት ከልምድ ብዛት ከቃላቱ ጋር ይዋሃዱ እና በአእምሮአችን ይታተማሉ፡፡ ከላይ እንደገለፅኩት፤ ምናልባት መንትያቸው ተተክቶባቸው ያነበብናቸው ግዜ ልክ የቃላቱ ትርጉም የተለወጠ ያህል ግር ይለናል፡፡ ይሄ ግን ዛሬ፣ ዛሬ በብዙ ወጣቶች ላይ የሚስተዋል ነገር አይደለም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ወጣቶቹ በአማርኛ አፃፃፍ ክህሎታቸው ስለበፀለጉ አይደለም፡፡ ብዙዎቹ እንኳንስ ለሆሄያት ግድፈት ሊጨነቁ ይቅርና ዓረፍተ ነገሮቹን ለዛ ባላቸው መንገድ ገጣጥመው ለመፃፍም እየተቸገሩ ይገኛሉ፡፡ ለምን?

እንዳለመታደል ሁኖ ከላይ ላነሳሁት ጥያቄ ፈጣን ምላሽ የሚሰጠኝ የምርምር ፅሁፍ አጠገቤ አላገኘሁም፡፡ ይሁን እንጂ እኔ በጥያቄው ላይ የራሴን መደዴ መላምት ማስቀመጤ አልቀረም፡፡ ከነዚህም ውስጥ፡-
  • ለአማርኛ ትምህርት የተሰጠው ትኩረት አናሳነት፣
  • የግዕዝ ሆሄያት መብዛት እና
  • የፊደሎች ድግግሞሽና የድግግሞሹ ፋይዳ ማጣትን እንደዓቢይ ምክንያቶች ወስጃቸዋለሁ፡፡

፩ኛ - አማርኛ ለምኔ?
በአገራችን አማርኛ ቋንቋ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሥራ ቋንቋ እንደሆነ በአዋጅ ቢቀመጥም በአፍቃሬ እንግሊዘኛ ትውልድ ቅኝ ግዛት ስር መውደቁን ለመረዳት ብዙ ማሰብ አያስፈልግም፡፡ በጉራማይሌ ከሚደጎመው ንግግር እስከተደበላለቀው የታናሽ እህት ወንድሞቻችን የአማርኛ ፅሁፍ ዋቢ መጥቀስ እንችላለን፡፡ ትምህርት ቤቶች ቢያንስ “በእንግሊዘኛ ተነጋገሩ” ማለት ሲቻል “በአማርኛ አትነጋገሩ” ብለው የግቢያቸው ማስታወቂያ ሠሌዳዎች ላይ እስከመለጠፍ ደርሰዋል፣ እንግሊዘኛ ተናጋሪዎች እንደሁሉን ቻይ እየተቆጠሩ ነው፣ በጥቅሉ ትውልዱ ለአማርኛ የሚሰጠው ዋጋ ወርዷል ብዬ አምናለሁ፡፡

ለዚህ እንደዋነኛ መንስኤነት የምኮንነው ለአማርኛ ቋንቋ ትምህርት የተሰጠውን አናሳ ትኩረት ነው፡፡ ምንም እንኳን አማርኛ የብዙዎቻችን አፍ መፍቻ ቋንቋ ቢሆንም በምርምር (በትምህርት) ብቻ የሚስተዋሉ የራሱ የሆኑ ሕግጋት እና አላባውያን ያሉት መሆኑ እየታወቀ የመንግስትም ሆነ የግል ትምህርት ቤቶች ወጣቶች ከቋንቋው ጋር በፍቅር እንዲወድቁ ትኩረት ሰጥተው አለመስራታቸው፣ ተማሪዎችን በቋንቋ አጠቃቀማቸው እና በፊደል አጣጣላቸው ጫን ያለ አስተያየት አለመስጠታቸው አማርኛ ለምኔ ትውልድ ሊያፈራ በቅቷል፡፡

ቋንቋ ሁሉ ሙሉ ነው ከሚለው ኀልዮት በተፃራሪ አማርኛ ቋንቋ የመግለፅ አቅም እንደሚያጥረው የሚከራከሩ ሰዎችም እየተበራከቱ ናቸው፡፡ ለዚህ እንደምክንያት የሚጠቅሱት በከፍተኛ ፍጥነት እየበለፀገች ያለችው ዓለማችን በየጊዜው አዳዲስ ቴክኖሎጂ አፈራሽ ምርቶችን ታስተዋውቀናለች፡፡ ለነዚህ ፈጠራዎች ከስያሜ አንስቶ አሰራራቸውን ለመግለፅ የሚያስችል እድገት ግን በቋንቋው ላይ አለመስተዋሉን ነው፡፡ ቋንቋውን ከኋላ ቀርነት ጋር ተጣብቆ የቀረ አድርገው እንዲያስቡትም የሚያደርጋቸው ይኸው ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሚመለከተው አካል የሚታይ ስራ የሚሰራ የትርጉም ተቋም ሊኖረው ይገባል፡፡

ቋንቋን መውደድ ባሕልን ብሎም አገርን መውደድ ነው፡፡

፪ኛ - ተዘግኖ የማያልቅ የሆሄያት ገበታ
በአማርኛ ቋንቋ ያሉት የሆሄያት ብዛት አጠያያቂ አይደለም - ብዙ ናቸው፡፡ ከአማርኛ ይልቅ ለግዕዝና ትግሪኛ የበለጠ የሚያገለግሉትንም ከቆጠርን የፊደል ገበታው ከሦስት መቶ የሚበልጡ ሆሄያትን ይዟል፡፡ ለዚህም ይመስላል ከ‘ሀ’ እስከ ‘ፐ’ ያሉትን በቅደም ተከተል አስታውሶ መጥራት ለብዙዎቻችን ፈተና የሚሆንብን፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም በየቦታው እየተስተዋሉ ያሉት ተግዳሮቶች ፊደላቱን የመቁጠር አይደለም፡፡ የቋንቋውን ሆሄያት የማምታታት እና የማሳሳት ፈተናዎች ናቸው፡፡ ከሁሉም አሳፋሪ የሚሆነው ደግሞ ግድፈቶቹ እየታዩ ያሉት ወጣቶችን በሚቀርፁ የሕትመት ስራዎች እና ሚዲያዎች ላይ ሳይቀር መሆኑ ነው፡፡

‘ፓ’ን በ‘ፖ’ ማቀያየር የተለመደ ከመሆኑ የተነሳ በተለያዩ ጋዜጦችና በኢትዮጵያ ቴሌቭዥንም ጭምር “ስፖርት” ተብሎ ሊፃፍ የሚገባው “ስፓርት” እየተባለ ሲፃፍ በተደጋጋሚ ታዝበናል፡፡ ይህ እንግዲህ የቋንቋው ሆሄያት በራሳቸው የፈጠሩት ተግዳሮት ነው፡፡ እነዚህ ፊደላት በማሽን በተለቀመ ፅሁፍ ውስጥ በቀላሉ የሚለዩ ቢሆኑም በእጅ ጽህፈት ላይ ረቂቅ የስዕል ችሎታ እንዲኖረን አስገዳጅ ዓይነት ነው፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ በተለይ በነዚህ ሁለት ፊደላት (‘ፓ’ እና ‘ፖ’) እና መሰሎቹ (‘ጸ’ እና ‘ደ’፣ ‘ኘ’ እና ‘ፕ’) መካከል ያለውን ልዩነት ከሰው ሰው በሚለያይ የእጅ ፅሁፍ ውስጥ በአግባቡ እንዲታይ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ እስከዛሬም ቢሆን ፊደላቶቹን የምንረዳቸው በአገባባቸው ነው፡፡ ይህ ግን በሕትመት ስራዎች ላይ የሚጠበቅ አይሆንም - በስነፅሁፍ ስራዎች ላይ ሲከሰት ደግሞ አሳፋሪ ይሆናል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ግን የማይምታቱትን የማምታታት አባዜም የሚደጋገሙባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ አንዳንዶች በሻ እና ሾ፣ በባ እና ቦ፣ በካ እና ኮ እና በሌሎችም መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት የእድሜ ልክ ዳገት ይሆንባቸዋል፡፡ የእነዚህን ፊደላት ቅርፅ ለመለየት ምንም ጥበብ አያስፈልገውም፡፡ መሰረት የሚጥል የአስተምሕሮ አካሔድ በመዋዕለ ሕፃናት ደረጃ ማስቀመጥ በቂ ይመስለኛል፡፡
፫ኛ - ድምጾች፣ ፊደላቸውና ድግግሞሹ
የአማርኛ የፊደል ሆሄያትን ድግግሞሽ የተመለከቱ ጉዳዮችን ሳነሳ አንዳንድ የእንግሊዘኛ ተናጋሪዎች የአናባቢ ፊደላት አላግባብ መብዛትን በመቃወም የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ አስታውሳለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች አላግባብ የተደነቀሩ አናባቢዎች አስፈላጊ አይደሉም ጊዜም ይፈጃሉ ስለዚህ ተወግደው ቃላቱ ነፃ መውጣት አለባቸው ባይ ናቸው፡፡ ለእንቅስቃሴያቸውም እንደ መሪ ቃል የሚጠቀሙበት “Enough is enuf!” የሚል መፈክር ነው - ችግሩን ከነመፍትሄው በአጭሩ የሚያሳይ መፈክር፡፡

የአማርኛ ቋንቋ ፅሁፍ ምንም እንኳን ከአናባቢዎች ተለጣፊነት የተላቀቀ ቢሆንም የራሱ የሆኑ ድክመቶች አብረውት ይኖራሉ፡፡ ቋንቋ ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ይሞታልም ከተባለ ሆሄያቱም የቋንቋው አካላት እንደመሆናቸው አብረው መወለድ፣ ማደግና መሞት ይገባቸዋል፡፡ ይህ ግን በፊደሎቻችን ላይ አይስተዋልም፡፡ ለዚህ እንደምሳሌ የተደረጉ ጥናቶችን ባላገላብጥም ከራሴ ጋር ስጠያየቅ ያስተዋልኩትን የአማርኛ ፊደል ገበታ አንድ ችግር ልጥቀስ፡፡ እንደምናውቀው ሆሄያቱ በድምጽ ላይ (ከግዕዝ እስከ ሳብዕ ባሉ ድምጾች) ተመስርተው ነው የተደረደሩት፤ ይሁን እንጂ አንዳንድ አፈንጋጮችም ይገኙበታል፡፡ እነዚህ አፈንጋጭ ሆሄያት የ‘ሀ’ እና ‘አ’ ቤተሰቦች ናቸው፡፡ በ‘ሀ’ እና ‘ሃ’ ወይም በ‘አ’ እና ‘ኣ’ መካከል ያለውን የድምጽ ልዩነት መናገር የሚችል ማንም የለም፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም የራብዕ ድምጽ አላቸው፡፡ ታዲያ የነዚህ ድምጾች ቤተሰብ የሆኑት የግዕዝ ድምጾች የት ገቡ?

መልሱ ቀላል ነው፡፡ ይህንን ክፍተት ለመጣፍ ሲባል ብቻ የተፈጠሩ በሚመስሉ ሌሎች የድምጽ ቤተሰቦች ውስጥ ተሰድረው እናገኛቸዋለን፡፡ እነዚህ ምትኮች ‘ኸ’ እና ‘ኧ’ ናቸው፡፡ አባቶቻችን የፊደላቱ መብዛት ናላቸውን አዙሮዋቸው ሳያስተውሉ ያለፏቸው ግድፈቶች የሆኑ እንደሆን እኛ ‹በቃን!› እንዳንልና እንዳናርማቸው የሚያስገድደን ምንድን ነው፡፡ እስኪ ከዚህ በታች ‘አ’ን ‘ኧ’ ብለን ለማንበብ እንዲመቸን ከታች እናስቀምጠውና የድምጽ ጉርብጣቱ እንዴት እንደሚጠፋ እናስተውል፡፡
ኘ  ኙ  ኚ  ኛ  ኜ  ኝ  ኞ
 ኡ  ኢ  ኣ  ኤ  እ  ኦ
ከ  ኩ  ኪ  ካ  ኬ  ክ   ኮ
 ሁ  ሂ  ሃ  ሄ  ህ  ሆ
አባባሌ በ‘አ’ ቦታ ‘ኧ’ ወይም በ‘ሀ’ ቦታ ‘ኸ’ ይቀመጥ ሳይሆን ‘ሀ’ እና ‘አ’ በትክክለኛው የግዕዝ ድምጻቸው እንደ ‘ኸ’ እና ‘ኧ’ ነው መነበብ ያለባቸው ነው፡፡

ሌላው ጉዳይ ምንም እንኳን የአማርኛ ሆሄያት የቱንም ያህል የበዙ ቢሆንም ቅሉ ፊደል ያልተፈጠረላቸው ድምጾች በርካታ መሆናቸው እሙን ነው፡፡ እዚህ ሳልጠቅሰው ማለፍ የማልፈልገው ነገር ግን ላልተውና ጠብቀው ሲነበቡ የተለያየ ትርጉም የሚሰጡ ቃላትን ነው፡፡

የፊደል ገበታችን ብዙ ድምጾችን የተደጋገሙ ሆሄያት ባለቤት አድርጓቸዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ‹ሀ፣ሐ፣ኀ›፣ ‹ሠ፣ሰ›፣ ‹አ፣ዐ› እና ‹ጸ፣ፀ› ሳይጠቀሱ አይታለፉም፡፡ ይሁን እንጂ ከነዚህ ተመሳሳይ ድምጽ የሚሰጡ ሆሄያት መካከል አንዳቸውም ጠብቀውና ላልተው ሲነበቡ የተለያዩ ትርጉም የሚሰጡ ቃላት መፃፍ የሚቻልበት ሁናቴ አስቤ ሊመጣልኝ አልቻለም፡፡ ወይም አቀያይረን ብንጠቀምባቸው የተለያዩ ትርጉም የሚሰጡበትን አጋጣሚ ሕግጋቱ የፈጠሩልን መስሎ አልተሰማኝም፡፡ ለምሳሌ “መሳሳት” የሚለው ቃል ሲጠብቅና ሲላላ ሁለት ትርጉም ይሰጣል፡፡ ነገር ግን ይህንኑ ቃል “መሣሣት” ብዬ ብፅፈው ከሁለት አንዱን ትርጉም አይዝልኝም፡፡ ይህ ካልሆነ ድግግሞሻቸው በልምድ ውስጣችን ከታተሙ ቅርፆች የጎላ ትርጉም የላቸውም፡፡ እንዲያ ከሆነ ደግሞ የመደጋገማቸው ፋይዳም ለመከራከር የሚያበቃ አይደለም፡፡ (ከአማርኛ ይልቅ በግዕዝ ቋንቋ ውስጥ አንድ ድምጽን የሚወክሉ ሆሄያት ድግግሞሽ ይበልጥ ትርጉም እንዳላቸው ሊቃውንቱ አበክረው ይናገራሉ፡፡)

በተመሳሳይ ርዕስ በከፍተኛ ሁኔታ የሚመሰርቷቸው ቃላት በመጥበቅና በመላላት ሁለት ትርጉም የሚሰጡባቸው ‘ለ’ እና ‘ነ’ን የመሳሰሉት የድምጽ ቤተሰቦች ግን አማራጭ መተኪያ የላቸውም፡፡ እንደምሳሌ ‹አለ› እና ‹ዋና› የሚሉት ቃላት እንኳን ብንወስድ በቃላቱ ውስጥ ‘ለ’ እና ‘ና’ አቻ ሆሄ ቢኖራቸው ኖሮ ምናልባት የድምጹን መጥበቅ ወይም መላላት እናመላክትባቸው ነበር፡፡ ስለሆነም የአማርኛ የሆሄ ገበታ በራሱ የቋንቋውን ሕልውና በማይጎዳ መልኩ ቢሆንም ማነቆ ነው ማለት ይቻላል - መደገማቸው ፋይዳ የሌለው ድምጾች በተለያየ ቅርፆች ተደጋግመዋል፤ ቢደጋገሙ እንዲህ እናደርግባቸው ነበር የምንላቸው ደግሞ አቻ የላቸውም፡፡ እንደኔ፣ እንደኔ አባቶቻችን የተዉልንን የፊደል ገበታ ብንከልሰው ተፅዕኖው እስከምን ድረስ እንደሆነ ብጠይቅ ድፍረት አይመስለኝም፡፡ ይህንን ስል ግን ጉዳዩ ትውልድ የማሰልጠን ያህል ከባድ እንደሆነ ተስቶኝ አይደለም፡፡

እንደማጠቃለያ
ይህንን ፅሁፍ የፃፍኩት በጥንቃቄ እና በብዙ የሐሳብ ውጣ ውረድ ነው፡፡ ነገር ግን በቀላሉ አይገኝምና፣ ቀድሞ በተሰራ ጥናት ላይ ተመስርቼ፣ መረጃ አገላብጬ እንዳለመሆኑ ድክመቶች ሊገኙበት ይችላል፡፡ እንደአማርኛ ቋንቋ አፍቃሪነቴ ግን ለአማርኛ አጠቃቀምና ዕድገት ይበጃል ያልኳቸውን ሁሉ መጠቆሜ ባለሞያዎችን ለጥናት ያነሳሳ ይሆናል ብዬ ገምቼ ነው፡፡ ማንም በፅሁፌ ላይ አስተያየት መስጠት የሚፈልግ ሰው በምርምር የተደገፈም ሆነ የግል አተያዩን አደባባይ ቢያወጣው ለማድመጥ በጣም እጓጓለሁ፡፡

አማርኛ ቋንቋችን ነው፡፡ ብቸኛው የራሱ ፊደል ያለው የአፍሪካ ቋንቋም ነው፡፡ እኛ ካልተጠቀምንበት፣ ካላጌጥንበት እንኳንስ መለያችን ሊሆን ቀስ በቀስ እንቆቅልሽ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ አማርኛን በወጉ መማር፣ በአማርኛ መቀኘት ይለምልም፡፡ አሜን!

5 comments:

  1. The Ethiopic Alphabet

    By Dr. Aberra Molla (በዶ/ር ኣበራ ሞላ)

    http://www.ethiopic.com/ethiopic_alphabet.htm


    Some Ethiopic users have drifted from these basic dimensions and problems have crept in to the usage of two groups of first order characters. Characters involved in this error are "ሀ", "ሐ", "ኀ", "አ" and "ዐ" as these glyphs erroneously share the sound with their respective fourth order form varieties. Ethiopic characters do not share sound across orders and thus "ሀ" and "ሃ" as well as "አ" and "ኣ" do not share the same sound. First order phenomes are expressed by opening the mouth only slightly while fourth order phemones are relatively more explosive requiring more opening of the mouth. The true sound of the Geez "አ" is "EA" as in "earth". "ኧ" is "EWA" It is most likely confusion with the wrong usage of "ሀ" as "HA" (instead of "HE" or "ኸ") that forced Unicode to refer to "ሃ" as "HAA" to differentiate it from "ሃ" or "HA". It is because "ሀ" and "ኸ" share the same "HE" sound that "ሃ" and "ኻ" share the "HA" sound or "ሆ" and "ኾ" share the "HO" sound.
    ጥሩ ጽሑፍ ነው። ግን ስለዚሁ ጉዳይ ቀደም ብሎ የተጻፉት መጠቀስ ነበረባቸው። ምክንያቱም http://freetyping.geezedit.com/ ድርገጽ "ኸ" ለ"E" ቁልፍ የተመደበውም በእዚህ ምክንያት ነው።

    ReplyDelete
  2. እና ታዲያ የርእሱ መልስ የት አለ፧

    ReplyDelete
  3. አማርኛ፣ ኣማርኛ፣ ዐማርኛ ወይስ ዓማርኛ?

    ReplyDelete
  4. በአሁኑ ግዜ ኅብረመረብ ላይ ብዙ የአማርኛ ቃላት መድብል አሉ፣ መዝገበ ቃላቱን ሁሉ ጨምሮ። አማርኛ ሃሳብን መግለጽ አያስችልም የሚሉ ሁሉ ስንኩል አይምሮ ያላቸው፣ በተለይ ተማርን ያሉቱ ናቸው። ይህን እንደ ቀመር ማስቀመጥ ይቻላል።

    ReplyDelete
  5. እኔ ግዕዝን ከራብዕ
    ሣልስን ከሳድስ
    ለይቼ መፃፍ ያስቸግረኛል...

    ReplyDelete